Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትየድሬ ዋንጫን ያነሱት የዋሊያዎቹ ተተኪ ወይስ ድንገተኛ ስብሰብ?

የድሬ ዋንጫን ያነሱት የዋሊያዎቹ ተተኪ ወይስ ድንገተኛ ስብሰብ?

ቀን:

በእግር ኳስ ታዳጊዎችና ወጣቶች ላይ መሥራት ወደፊቱን መቆጣጠር እንደሆነ ጄሰን ቢትብር ስለተተኪ ቡድን (ሻዶ ቲም) በጻፈው ጽሐፉ ላይ ይጠቅሳል፡፡ ክለቦችና ብሔራዊ ቡድኖች ተተኪ ቡድን ለማቀፍ አካዴሚዎችን ለመገንባት ሙዓለ ንዋይ ያፈሳሉ፡፡

ታዳጊ ተጫዋቾችን ለማግኘት ወደ ቀበሌ፣ ወረዳና ትምህርት ቤቶች ወርደው ይመለምላሉ፡፡ በእግር ኳስ ቀጣዩን ተረካቢ ትውልድ ለመቅርፅ ረብጣዎች ያፈሳሉ፡፡

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እየተጫወተ የሚገኘው የበርንለይ እግር ኳስ፣ ክለብ፣ ከታች ጀምሮ እስከ አካዴሚ ክትትል በማድረግ ለዋናው ክለብ ግብዓት የሚሆኑ ተጫዋቾችን ያበቃሉ፡፡

- Advertisement -

ክለቡ ዕድሜያቸው ከ16 እስከ 18 ዓመት የሆኑትን ተጫዋቾች በአካዴሚ በማቀፍ መሠረታዊ የእግር ኳስ ክህሎት እንዲያሳድጉ ያደርጋል፡፡ ታዳጊዎችን ወደ አካዴሚው ለማስገባት በሚደረገው ሒደት ውስጥ ክለቡ ከአካባቢው ነዋሪ ጋር በቁርኝት ይሠራል፡፡

በእንግሊዝ የተለያዩ ክለቦች ዕድሜያቸው ከሰባት እስከ 16 የሆኑ ታዳጊዎችን በማቀፍ ተተኪ ብሔራዊ ቡድን ይገነባሉ፡፡

ተጫዋቾቹ እንደ ዕድሜያቸው ደረጃ ከአንዱ ቡድን ወደ ተከታዩ ቡድን እያደጉ ክህሎታቸውን በማሳደግ ወደ ዋናው ቡድን ይቀላቀላሉ፡፡

ከክለቦች ባሻገር ብሔራዊ ቡድኖችንም ከ15፣ ከ17፣ እንዲሁም ከ20 በታች ቡድኖችን በመያዝ ተተኪዎችን እያፈሩ ለአገራዊ ውድድሮች ያዘጋጃሉ፡፡

ለብሔራዊ ቡድን ተተኪ ተጫዋቾችን ለማግኘት ተጫዋቾችን ለመኮትኮትና ለማሳደግ አካዴሚዎች የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡

በርካታ ብሔራዊ ቡድኖች በዓለም ዋንጫ ለመካፈል በአራት ዓመታት ውስጥ ለዋናው ብሔራዊ ቡድን የሚሠለፉ ተጫዋቾችን ያዘጋጃሉ፡፡

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን እ.ኤ.አ. 2014 በብራዚል ለተዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ተፎካካሪ ባለድል ለመሆን፣ ከ2010 ጀምሮ ሲዘጋጅ ቆይቷል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ታዳጊዎችን ከአካዴሚና ከክለቦች በመሰብሰብ የተጠና ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህም ብሔራዊ ቡድኑ የብራዚሉን ዋንጫ ማሸነፍ ችሏል፡፡

በአፍሪካም የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ወጥ ቡድን ይዞ በአፍሪካ ዋንጫው የመቅረቡ ምስጢር ከአገሪቱ ይህም ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካዴሚዎች የተውጣጡና በአውሮፓ የተለያዩ አካዴሚዎች ውስጥ ማደግ የቻሉ ወጣት ተጫዋቾች ይዘው መጓዝ መቻላቸው ነው፡፡

በቅርቡ የተለያዩ ብሔራዊ ቡድኖች የስምንት ዓመታት ዕቅድ ነድፈውና ወጣቶችን መልምለው በመደበኛ መርሐ ግብር ለዓለም ዋንጫ እያዘጋጁ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ምን ላይ ናት?

የድሬዳዋ ስታዲየም ሰው ሠራሽ ሳር ትከሉን ተከትሎ በተዘጋጀው የዋንጫ ጨዋታ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዑጋንዳ ተተኪ ብሔራዊ ቡድን ጋር ተጫውቷል፡፡

ዋሊያዎቹ የዑጋንዳ አቻቸውን 1 ለ 0 በሆነ ውጤት በመርታት የድሬ ዋንጫ ማንሳት ችለዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለተጫዋቾች ጥሪ ሲያደርግ ለዋንጫ ጨዋታው ከዚህ ቀደም በብሔራዊ ቡድን ተጠርተው የማያውቁ ተጫዋቾች በአብዛኛው ጥሪ እንደተደረገላቸው አሳውቆ ነበር፡፡  

በአሠልጣኝ ገብረ መድኅን ኃይሌ የሚያሠለጥነው ቡድኑ ለ30 ተጫዋቾች ጥሪ አድርጓል፡፡ ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾቹ በፕሪሚየር ሊግና በብሔራዊ ሊግ የሚጫወቱ ናቸው፡፡

አብዛኛዎቹ የመጀመሪያ ተሳትፏቸውን ያደረጉ ቢሆኑም፣ ድንገተኛ ጥሪ የተደረገላቸው እንጂ ፌዴሬሽኑ እንደገለጸው ተተኪ ቡድን (ሻዶ ቲም) አለመሆናቸው የሚያስረዱ አሉ፡፡

ባለሙያዎቹ፣ ቡድኑ ተተኪ ቡድን ለመባል በትክክል ታስቦበትና ታቅዶበት በዋና አሠልጣኙ አማካይነት ዝግጅት ሲደረግበት ነው ይላሉ፡፡ በአንፃሩ በድሬዳዋ ዋንጫ የተመረጡት ተጫዋቾች የይድረስ ይድረስ ከተለያዩ ክለቦች የተመረጡ መሆናቸው ተነስቷል፡፡

‹‹በትክክለኛ ታምኖበት እንዲሁም በዕቅድ የተሠራ ስሙን የሚጠቀስ ቡድን ነው ብዬ አላምንም፤›› ሲል የሶከር ኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኛ ዳንኤል መስፍን አስተያየቱን ይሰጣል፡፡

ተተኪ ቡድን ለመመሥረት ቢያንስ ዕድሜያቸው ከ15 በታች ተጫዋቾችን በማቀፍ ለረዥም ጊዜ ይዞ መዝለቅ ይገባል ይላል፡፡

በአንፃሩ በኢትዮጵያ በሁለቱም ፆታ ለአኅጉራዊ ውድድሮች ሲዘጋጁ ተጫዋቾችን ከዚህም ከዚያም ጠርቶ ለውድድር የማዘጋጀት አባዜ መጠመዳቸው ይነሳል፡፡  

ቡድኑ በአኅጉራዊ ውድድሮች ከተሳተፈ በኋላ መበተኑ የተለመደ አሠራር ሆኖ ዘልቋል፡፡ በዚህም ምክንያት በዋና ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ይህንኑ ተከትሎ ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ ተጫዋቾችን የሚተኩ ተጫዋቾችን ማፍራት አልተቻለም፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ በዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚያሠልፋቸው አማራጭ ተጫዋቾችን በማጣቱ ውጤት ሲያጣ ይስተዋላል፡፡

ቡድኑ በተደጋጋሚ የግብ ጠባቂና የአጥቂ ዕጦት መቸገሩም እንደ ምሳሌ ይጠቀሳል፡፡

ከዚህም በላይ የዋሊያዎቹ ስብስብ ከ31 ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ሲያልፍ የነበሩ የተወሰኑ ተጫዋቾች ተተኪ ሳይኖራቸው እስከ 2021ዱ የካሜሮን አፍሪካ ዋንጫ ድረስ መዝለቃቸው ይታወሳል፡፡

በድሬዳዋ ዋንጫ የዑጋንዳ ብሔራዊ ቡድንን የገጠሙት የዋሊያዎቹ ስብስብ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም፣ ከጨዋታው በኋላ መበተናቸው አግባብ እንዳልሆነና ስብስቡ የብሔራዊ ቡድን አማራጭ ቡድን መሆን እንደሚገባው የሚያነሱ አሉ፡፡

ለድሬዳዋ ዋንጫ ተጋብዞ የመጣው የዑጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ከ17 ዓመት በታች ውድድር ጀምሮ አብሮ የዘለቀ ተተኪ ቡድኑ እንደሆነ ከጨዋታው በኋላ አሠልጣኙ አስረድተዋል፡፡

በዚህም መሠረት በቡድኑ የተካተቱትን ተጫዋቾች እስከመጪው የአፍሪካ ዋንጫ ድረስ የተለያዩ የወዳጅነት ጨዋታዎች እየተሳተፉ ለዋና ብሔራዊ ቡድን እንዲበቁ እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ቡድን በድሬ ዋንጫ የታዩትን ተጫዋቾች የዋና ብሔራዊ ቡድን ተተኪ የሚሆኑበትን መንገድ ነድፎ ለቀጣይ ውድድሮች ማሰናዳት ይጠበቅበታል፡፡

በመጪው መጋቢት ለሚጀምረው የሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት የሚጀምር ሲሆን፣ በድሬዳዋ ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዋሊያዎች መሠለፍ የቻሉ ተጫዋች በአሠልጣኝ ገብረ መድኅን ኃይሌ ስብስብ ውስጥ ይካተታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...