Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበአማራ ክልል በመንግሥት አስተባባሪነት ከተካሄደው የሰላም ውይይት ባልተናነሰ ግጭቱ ቀጥሏል

በአማራ ክልል በመንግሥት አስተባባሪነት ከተካሄደው የሰላም ውይይት ባልተናነሰ ግጭቱ ቀጥሏል

ቀን:

  • ሕዝብ ትራንስፖርት መቆም ዜጎችን ለእንግልት መዳረጉ ተገልጿል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) ጨምሮ የመንግሥት ከፍተኛ ሥራ ኃላፊዎች በአማራ ክልል የተፈጠረውን ቀውስ ለመፍታት ሕዝባዊ የሰላም ውይይት ሲያካሂዱ ቢሰነብቱም ከውይይቱ ጎን ለጎን በጎጃም፣ በወሎ፣ በሸዋና በጎንደር በመንግሥት ኃይሎችና በታጣቂዎች መካከል ጦርነቱ አገርሽቶ መቀጠሉን ከክልሉ የሚወጡ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

ሰባት ወራት ባስቆጠረውና በአማራ ክልል በመከላከያ ሠራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በቀጠለው ጦርነት ወደ ክልሉ የሚገቡና የሚወጡ የሕዝብ አገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች ሥራ ማቆም ዜጎችን ለእንግልት፣ ለከፋ አደጋና ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸው ተገልጿል፡፡ 

ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃምና ጎንደር መስመር የሚጓዙና ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ፣ በተመሳሳይ ወደ ደቡብና ሰሜን ወሎ፣ እንዲሁም ወደ ትግራይ የሚያመሩና የሚመለሱ አገር አቋራጭ የሕዝብ ተሽከርካሪዎች በአማራ ክልል ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ሥራ ላይ ናቸው ብሎ መናገር እንደማይቻል፣ አንድ የአገር አቋራጭ ትራንስፖርት አገልገሎት ሰጪ የማርኬቲንግ ኃላፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በጦርነት እየታመሰ ባለው የአማራ ክልል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ልኮ በተመረጡ የክልሉ የዞን ከተሞች መፍትሔ ያሻቸዋል ባላቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ሲያደርግ ቢቆይም፣ በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች መካከል የጀመረው ጦርነት ሊቆም አልቻለም፡፡ በሰላም ዙሪያ የሚከናወነው ሕዝባዊ ውይይት ከዞን ወደ ወረዳ፣ ከወረዳ ወደ ቀበሌ ድረስ አሁንም መቀጠሉን ከተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡

ከዚሁ የሰላም ውይይት ጎን ለጎን ጦርነቱ ከሰሞኑ በምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም በርትቶ ሲቀጥል እንደገና ባገረሸው የሰሜን ሸዋ፣ ሰሜን ወሎና ኦሮሚያ ልዩ ዞን አካባቢዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስቱ አማካይነት የትራንስፖርት ገደብ ተጥሏል፡፡

የአማራ ክልል መንግሥት የካቲት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹በጽንፈኞች መሪ ተዋናይነት በክልላችን በቅርብ ባጋጠመ የሰላም መደፍረስ ምክንያት የዜጎች እንቅስቃሴ የተገታበት፣ የመንግሥት ተቋማት ሥራ የተስተጓጎለበትና የተዘረፉበት፣ ከሁሉ በላይ አውቀውም ይሁን ሳያወቁ የክልላችን ወጣቶች የጽንፈኞች ሐሳብ ተሸካሚ ሆነው የሕይወት ዋጋ የከፈሉበትን ሁኔታ አስተናግደናል፤›› ብሏል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ ባለው አማራ ክልል ከሰሞኑ የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ባወጣው አስቸኳይ ውሳኔ ከየካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ማለርም ከደሴ-ሸዋሮቢት-ደብረ ብርሃን፣ እንዲሁም ከደብረ ብርሃን-ሸዋሮቢት-ደሴ የሚደረግ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ለጊዜው እንዲቆም መወሰኑን አስታውቋል፡፡

ኮማንድ ፖስቱ፣ ‹‹በቀጣናው ፅንፈኛ ኃይሎች ላይ ዕርምጃ እየወሰደ በመሆኑ ሰላማዊ ዜጎች ጉዳት እንዳይደርስባቸውና አካባቢውን በአጭር ቀናት ከፅንፈኛ ኃይሉ ነፃ ለማድረግ ኦፕሬሽን ሥራ የተጀመረ ስለሆነ፣ ከተጠቀሰው ቀን ጀምሮ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዲቆም የተወሰነ በመሆኑ ነው፤›› ብሏል፡፡

የአገር መከላከያ ሠራዊት ማክሰኞ የካቲት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ከየካቲት 16 እስከ 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ በጎጃም የተለያዩ አካባቢዎች 168 ታጣቂዎችን መደምሰሱን አስታውቋል፡፡

ከክልሉ ሰላም ዕጦት ጋር በተገናኘ ሪፖርተር ያነጋገራቸውና ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ በጨፋ ሮቢት ከተማ ሕክምና ሙያ ላይ የተሰማሩ አንድ ባለሙያ በየጊዜው በሚነሳው ግጭትና ከሰሞኑ በኮማንድ ፖስት መንገድ መዘጋት ምክንያት፣ እሳቸው በሚያገለግሉበት የሕክምና ተቋም ታማሚዎች ተጨማሪ ሕክምና ሲጠይቁ ለሪፈራል መላክ አለባቸው ተብሎ ከታመነ፣ ባጃጆች አቆራርጠው አንዱ ለሌላው እያሸጋገሩ አቋራጭ መንገዶችን በመፈለግ በጫካ ለመሄድ ተገደዋል ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል አንፃራዊ ሰላም መገኘቱን የፌዴራልና የክልሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ እንዲሁም የመከላከያ ኃላፊዎች ሲናገሩ ቢደመጡም ዜጎች አሁንም በሥጋት ላይ መሆናቸውን ሪፖርተር ያነጋገራቸው የባህር ዳር ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ በተመሳሳይ በባህር ዳር ከተማ የሚገኝ አንድ ዩኒቨርሲቲ ምሩቅ፣ ‹‹ቤቴ ያለ ሥራ ከተቀመጥኩ ዓመት አለፈኝ፡፡ አዲስ አበባ የሚገኙ ተቋማት ካወጧቸውና በድረ ገጽ ከተመዘገብኳቸው በርካታ የሥራ ማስታወቂዎች ለሁለቱ ለቃለ መጠይቅ ተጠርቼ መንገድ በማጣቴ ቀረሁ፤›› ብሏል፡፡ ‹‹በአውሮፕላን አልሄድ የሚከፈል የለም፣ በመኪናው መመላለሱም አይደጋገምም፣ ሥራ አጥነቱን እያማረርኩ መንቀሳቀስም አልቻልኩም፤›› ሲል ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ ከተማ መቀመጫቸውን አድርገው ዕርዳታ ከሚያከፋፍሉ የወርልድ ቪዥንና የዓለም ምግብ ድርጅት ሠራተኞች መካከል ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡ ግለሰቦች ከሰሞኑ የተፈጠረውን ሁኔታ ሲያብራሩ፣ ድርጅቶቹ በኮማንድ ፖስት ሥር የሚገኙ አካባቢዎች ለመሄድ አለመቻላቸውንና ዕርዳታ ለማቅረብ መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡

አንድ አስተያየት ሰጪ፣ ‹‹አሁን ከደብረ ብርሃን ወደ ደሴ የሚሄድ ትራንስፖርት የለም፡፡ ትራንስፖርቱ ሲኖር ደግሞ በድርጅት ልሂድ ብትል ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር ስትገናኝ በተቀናቃኞች ትገደላለህ፡፡ እንደ ግለሰብ ልሂድ ብትል ደግሞ በተለይ ከሰሜን ሸዋ ወጥተህ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ስትገባ የያዝከው መታወቂያ የአማራ ከሆነ አደጋ አለው፣ በተመሳሳይ እሱን አልፈህ ወደ ደቡብ ወሎ ዞን ስትገባ የኦሮሞ መታወቂያ ካለህ አሁንም ሌላ ፈተና ነው፡፡ በአጠቃላይ ወስነህ የምታደርገው አስፈሪ እንቅስቃሴ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ነዋሪ የነበረው ባንታምላክ እያየሁ ከዚህ በፊት ከአዲስ አበባና ከሌሎች ትልልቅ ከተሞች በሚመጡ ተሽከርካሪዎች የሚያገኛቸውን ሸቀጦች ባለችው ትንሽ መደብር እየሸጠ ይተዳደር እንደነበር፣ ነገር ግን አሁን ጦርነቱ በፈጠረው ቀውስ ምክንያት ለቀናት አቆራርጦ አዲስ አበባ በመግባት በሎተሪ ሽያጭ እንደሚተዳዳር ገልጿል፡፡ ሪፖርተር በክልሉ ያነጋገራቸውና ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምሁራን መፍትሔው መንግሥት የችግሩን ምንጭ በመረዳት፣ ሕዝባዊ ቅቡልነት ካላቸው የፖለቲካ ቡድኖች ጋር በመነጋገር መፍትሔ የሚያሻቸው ነጥቦች ላይ በመወያየት ስምምነት እንዲደረስ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...