Monday, May 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምርጥ ዘር ለሚያቀርቡ ኩባንዎች ምቹ መወዳደሪያና የውጭ ምንዛሪ ሊቀርብ ይገባል ተባለ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ምርጥ ዘር ለሚያቀርቡ ኩባንያዎች ምቹ የመወዳደሪያ ሜዳና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እንዲኖር ጥያቄ ቀረበ፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በአትክልትና ፍራፍሬና ምርት ከ1,200 በላይ ዓይነት ምርጥ ዘሮችን በማቅረብ ታዋቂ የሆነው ቢኤኤስኤፍ የተሰኘው ድርጅት፣ የኔዘርላንድ የልማት ድርጅት ኤስኤንቪ ለሚደግፋቸው አርሶ አደሮች 30 ሚሊዮን ብር የሚገመት ዋጋ ያላቸው አራት የምርጥ ዘር ዓይነቶችን በድርቅና ግጭት ለተጎዱ የትግራይና የአማራ ክልሎች ለግሷል፡፡

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ቤን ዲፕራቴር የምርጥ ዘር አቅርቦትን በተመለከተ ለሪፖርተር ሲያስረዱ፣ በአርሶ አደሩ ያለው ከፍተኛ የሆነ የተሻሻለ ምርጥ ዘር አቅርቦት እያደገ ቢመጣም የአቅርቦት ችግር አሁንም ችግር ነው ብለዋል፡፡ ይህ እጥረት ሊከሰት የቻለው በውጭ ምንዛሪ እጥረት መሆኑን፣ የምርጥ ዘር አከፋፋዮች የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ወረፋ እየጠበቁ መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡

ችግሩ እንዲፈታ የውጭ ምንዛሪ ለገበያ ምቹ በሆነ መንገድ መቅረብ አለበት ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የአርሶ አደሮች የምርት ችግር ተቀርፎ በፈለጉበት ጊዜና ቦታ ምርጥ ዘር እንደ አካባቢው ሁኔታ ሊቀርብላቸው ይገባል ብለዋል፡፡

የምርጥ ዘር አቅርቦቱ ጤነኛ መሆን አለበት ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በምርጥ ዘር አቅራቢ ኩባንያዎች መካከል ያለው ውድድር ጤነኛ ከመሆንም በላይ ወደ አገር የሚያስገቡት ምርጥ ዘር የተሻሻለ መሆን እንዳለበት፣ ለአርሶ አደሮች አማራጭ ምርጥ ዘሮች ምርታማነትን ለማስገኘት መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የግብርናው ዘርፍ ያለውን ገበበበዥበበደአቅም በተገቢው መንገድ ለመጠቀም ምርጥ ዘር በተገቢው ሰዓትና ቦታ ለአርሶ አደሩ መቅረብ እንዳለበት፣ ለዚህ መሳካት የውጭ ምንዛሪ በተፈለገው ጊዜ በማቅረብ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ምርጥ ዘር በሌለበት ግብርና አለ ብሎ ማውራት አይቻልም፣ ይህ ደግሞ ተገቢው ግብዓት ካልቀረበ ገበያው ላይ ምርት በተከታታይ ሊቀርብ አይችልም፤›› ብለዋል፡፡

ሁለቱ ድርጅቶች በጋራ ያደረጉት ድጋፍ ለአራት ሺሕ አርሶ አደሮች የሚሰጥ ሲሆን፣ በግጭትና በድርቅ የተጎዱ አርሶ አደሮችን መልሶ ለማቋቋም የተደረገ ድጋፍ መሆኑን የድርጅቱ ኃላፊዎች ድጋፉን ለግብርና ሚኒስቴር ባስረከቡበት ወቅት ተናግረዋል፡፡

የአትክልት ዘሮችን በማቅረብ በሚታወቀው በቢኤኤስኤፍ አማካይነት የቀረበው ድጋፍ 800 ኪሎ ግራም የቀይ ሽንኩርት፣ 666,000 ኪሎ ግራም የቃሪያና 1.5 ሚሊዮን ኪሎ ግራም የቲማቲም ምርጥ ዘሮችን በኤስኤንቪ ለሚደገፉ የአርሶ አደሮች የመስክ ማሳያ ትምህርት ቤቶች የቀረበ ነው፡፡

ትምህርት ቤቶቹ 4,000 ለሚሆኑ አርሶ አደሮች አስፈላጊውን ሥልጠና በመስጠት የምርጥ ዘር የማከፋፈል ሥራን እንደሚያከናወኑ፣ በጥምረት የተደረገው ድጋፍ በግጭትና ድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋምና በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደር ማኅበረሰቦች ኑሯቸውን መልሰው የሚቋቋሙበትን ዕድል ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

 የምርጥ ዘር ርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ማክሰኞ የካቲት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. በግብርና ሚኒስቴር ቅጥር ግቢ ውስጥ ሲካሄድ፣ ቢኤኤስኤፍ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ የአርሶ አደር ቤተሰቦችን ምርጥ ዘር ከማቅረብ ባለፈ በዘላቂነት ለመደገፍ ቁርጠኝነት አለኝ ብሏል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹በኢትዮጵያ የሚገኙ አርሶ አደር ማኅበረሰቦችን መደገፍና የኑሮ ሁኔታቸውን መልሰን መገንባት የምንቀጥል በመሆናችን ኩራት ይሰማናል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ትብብራችን በተለያዩ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች አርሶ አደሮችንና የአካባቢውን ማኅበረሰቦች ለማብቃት ያለንን ያላሰለሰ ጥረት ያሳያል፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ለአርሶ አደሮች ምርጥ ዘሮችን መስጠትና የሚዘሩበትን መንገድ ለማሳየት ሥልጠና መስጠት የሚገኘውን ምርት ከመጨመሩ ባሻገር፣ ቤተሰቦች የተመጣጠነ ምግብ እንዲመገቡ አስተዋጽኦ በማድረግ በሕይወታቸው ላይ ጉልህ የሆነ አዎንታዊ ተፅዕኖ መፍጠር መቻላችንን መመልከት የላቀ ስሜት አለው ብለዋል፡፡

የኤስኤንቪ ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ጁሊ ግርሃም፣ ‹‹ከቢኤኤስኤፍ ጋር ያለን አጋርነት አዎንታዊ ውጤቶችን አስመዝግቧል፡፡ የመጀመርያውን ዙር ምርጥ ዘሮች ያገኙት የመስክ ማሳያ ትምህርት ቤቶች አባላት የሆኑት አርሶ አደሮች ምርታማነታቸው በመሻሻሉ፣ የምርቱ በሽታ መከላከል አቅም በመጨመሩ፣ የተሻለ የአትክልት ዕድሜ በመኖሩና ከፍተኛ ዋጋ ከምርቶቹ በማግኘታቸው ተጠቃሚ ሆነዋል፤›› ብለዋል፡፡

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ቤን ዲፕራቴር ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ምርጥ ዘሩን እንዴት ማደረስ ይቻላል ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄ ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ‹‹ትራንስፖርት መጠቀሙም ሆነ ማሠራጨቱ ቀላል አይሆንም፡፡ ነገር ግን አማራጭ መንገዶች አይጠፉም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ሁሉም ሰው ሰላም ይፈልጋል፣ ሁሉም ዜጋ ሰላምና ፀጥታን ይናፍቃል፤›› ብለው፣ ይህ ድጋፍ የአነስተኛ እርሻ አርሶ አደሮች ከዚህ ቀደም በደረሰባቸው ድርቅና የፀጥታ ችግር ምክንያት የተጎዳባቸውን ሕይወት ለመደገፍ ነው፡፡ ነገር ግን ሁሉም አካላት ለሰላምና ለፀጥታ ማድረግ ያለባቸውን ነገር ያውቃሉ፣ እሱን መፈጸም ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች