Tuesday, April 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቆዳና የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች በትምህርት የታገዙ እንዲሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የቆዳና የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ፣ ዩኒቨርሲቲዎች በተግባር የተደገፈ ትምህርት እንዲሰጡና ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥያቄ ቀረበ፡፡

ጥያቄው የቀረበው የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኤግዚቢሽን፣ የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ሐሰን መሐመድ፣ የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች ለመፍታት የምርምር ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎችን በሳይንስ፣ እንዲሁም በቴክኖሎጂ በማስፋፋት ጠንካራ ትስስር መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣውን የኢንዱስትሪ ፖሊሲን ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ዕቅዶች ተዘርግተው እየተሠሩ እንደሆነ ገልጸው፣ አምራች ኢንዱስትሪውን በምርምርና ልማት አቅም በማሳደግ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማፍጠን እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲዎች የተከናወኑ የምርምር ሥራዎች ወደ ትግበራ እንዲሸጋገሩ ለማድረግ ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር መሥራት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ሚኒስትር ደኤታው፣ በቀጣይ ሁሉም የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የቆዳና የጨርቃ ጨርቅ ምርት ውጤቶችን በተግባር የታገዙ እንዲሆኑ የበኩላቸውን መወጣት እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል፡፡

የጨርቃ ጨርቅና የቆዳ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጥራት ባለውና በሚፈለገው መጠን ማምረት ባለመቻላቸው ዘርፉ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኝ፣ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይል አምራች ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ታምራት ተስፋዬ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቆዳ ምርት የምትታወቅ አገር እንደ መሆኗ መጠን ምንም ዓይነት ውጤታማ ሥራ አለመሥራቱን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ ይኼም የሚያሳየው ዘርፉ በትምህርት የታገዘ አለመሆኑን ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡ 

በተለይ ሃይላንድ የሚባለው የቆዳ ምርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ ቢሆንም፣ በተሻለ ጥራትና ብዛት አምርቶ ለገበያ ማቅረብ አለመቻሉ የችግሩን ስፋት እንደሚያሳይ አክለው ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ብቻ ሦስት ሚሊዮን ሔክታር ቦታ ያላት ቢሆንም፣ ይህንን ማልማት ባለመቻሏ ምክንያት ከአሥር በመቶ ብቻ ያነሰ ቦታ መጠቀሟን አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሠረት ምርትና ምርታማነት ሊቀንስ መቻሉን ገልጸው ዩኒቨርሲቲዎች፣  መንግሥት፣ የዘርፉ ተዋናዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት አንድ ላይ በመቀናጀት መሥራት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች