Friday, May 24, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ታሪካዊ ቅርሶችን፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ከቤተሰቦቻቸው በስጦታ ተረከበ፡፡

ከሰባት ዓመታት በፊት ያረፉት ጄኔራል ለገሠ፣ ሶማሊያ ኢትዮጵያ በምሥራቅና በደቡባዊ ምሥራቅ ግንባሮች በወረረችበት ወቅት (1969 – 1970) በተዋጊ ጄት አብራሪነት ወደር የሌለው ጀግንነት የፈጸሙ ናቸው፡፡ በወቅቱ በነበረው ውጊያ አውሮፕላናቸው ተመትቶ በመውደቁና በመያዛቸው ለ11 ዓመታት በሶማሊያ በእስር ከቆዩ በኋላ የተለቀቁ ናቸው፡፡

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ቅርሶቹን ያስረከቡት ወ/ሮ ሙሉ ብርሃን ተፈራ የጄነራል ለገሠ ተፈራ ፋውንዴሽን መሥራች

በራስ መኰንን አዳራሽ የካቲት 12 ቀን 2016 ዓ.ም. በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ላይ ቤተሰቦቻቸው የለገሷቸው ታሪካዊ ቅርሶች የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ፣ የየካቲት 1966 ዓ.ም. 1ኛ ደረጃ ኒሻን፣ የጄኔራልነት ማዕረግ ያላቸው ወታደራዊ አልባሳት፣ ጠላትን ለመደምሰስ ጄት ሲያበሩ የተጠቀሙባቸው አልባሳት፣ በሶማሊያ እስር ቤት ለ11 ዓመት በቆዩበት ወቅት ይገለገሉበት የነበረው ቱታና ነጠላ ጫማ ናቸው፡፡

‹‹ብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ማለት ወታደራዊ ሥነ ምግባርን ጠንቅቆ ያወቀ፣ እንደ ሻማ ተቃጥሎ እያጓራ ለአገሩ ኩራት የተሰዋና የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ነው፤›› ያሉት ቅርሶቹን ያበረከቱት የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ታናሽ እህትና ነዋሪነታቸው በአሜሪካ የሆነው ወ/ሮ ሙሉ ብርሃን ተፈራ ናቸው፡፡

እንደ ወ/ሮ ሙሉ ብርሃን አነጋገር፣ ታላቅ ወንድማቸው ጀግናው ብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ወደር የሌለው ሁለት የኢትዮጵያ የጀግና ሜዳይና ኒሻን መሸለማቸውን፣ ይህም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ተሸላሚ አድርጓቸዋል፡፡ በእኚሁ ጀግና ጄኔራል ሕይወት ዙሪያ ያተኮሩ መጻሕፍት በማዘጋጀት ላይ መሆናቸውንና ከዚህም ሌላ በአሜሪካ የለገሠ ተፈራ ፋውንዴሽን ማቋቋማቸውን አስረድተዋል፡፡

የፋውንዴሽኑ ዋና ዓላማ ያልተዘመረላቸውና ያልተነገረላቸውን ወገኖች መዘከር፣ ምን ጎደላችሁ? እንዴት ናችሁ? ብሎ መጠየቅና የሚረዱባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በወጣትነት ዕድሜያቸው በጦር ሜዳ ከጠላት ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ሲተናነቁ ጉዳት ለደረሰባቸውም ጀግኖች አስፈላጊውን እንክብካቤ የሚያደርግ መሆኑን ከማብራሪያቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡

በሚኖሩባት አገር ውስጥ ‹‹አፍሪካን አሜሪካን ሒስትሪ ሙዚየም›› እንዳለ፣ ስጦታዎቹን ሁሉ በዚሁም ሙዚየም ማስቀመጥ ይችሉ እንደነበር፣ ነገር ግን ይህንን ያላደረጉበት ምክንያት የአሁኑም ሆነ ቀጣዩ ትውልድ እንዲማርበት በማሰብ ለኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ለማስረከብ እንደወሰኑ ነው የተናገሩት፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም በተለያዩ ጊዜ የኢትዮጵያን ስም ከፍ ላደረጉ ባለሙያዎች በየኮርነሩ (በየጥጉ) እያደራጀ ትውልድ እንዲማርባቸው እያደረገ ነው፡፡ ‹‹ይህ ዛሬ የምናከብረው ዕውቁ ጄኔራል ለገሠ ተፈራ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ያሳረፉ፣ ኢትዮጵያ ታላቅ ሆና እንድትቀጥል ካደረጉት ዕንቁ ልጆች መካከል አንዱ ስለሆኑ፣ በሚመጥናቸው ቦታ ላይ በክብር በማኖር ትውልድ እንዲማርበት ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንጉሡ መኖሪያ ቤት ከነበረበት ‹ከፓላስ ወደ ካምፓስ› ተቀይሮ ብዙ የሠራና እስዛሬዋም ዕለት ድረስ ከ280 ሺሕ በላይ ትውልድ ለኢትዮጵያ ያፈራ ከ70 ዓመት በላይ ያስቆጠረ አባወራ ዩኒቨርሲቲ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

በቀጣይም ለኢትዮጵያ ታላቅነት የበኩሉን እንደሚሠራ፣ ከሚሠራቸውም ጉዳዮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ትውልድ የትናንቱን እንዲገነዘብ፣ የዛሬውን እንዳይረሳና ለነገውም እንዲዘጋጅ ማድረግ መሆኑንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዋና ዳይሬክተር ታከለ መርዕድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ተቋሙ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ ቅርሶችን መሰብሰቡን ገልጸው፣ የአሁኑ ስጦታ ጀግኖች አባቶች የሚታሰቡበት ብቻ ሳይሆን፣ ትውልድ የሚማርበት፣ ምርምር የሚሠራበት፣ ጽሑፍም የሚዘጋጅበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳነት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያውያንን በግፍ የጨፈጨፈበት የካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ በተከበረበት ቀን የጀግናው ብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ የአገሩን ዳር ድንበር ለማስከበር ያበረከተው ተጋድሎና ሥራ መዘከሩን ተናግረዋል፡፡

የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ አብሮ አደግና የትምህርት ቤት ጓደኛ የሆኑት አቶ ግርማ ዋቄና የሥራ ባልደረባቸው የነበሩ ብርጋዴር ጄኔራል ካሳዬ ጨመዳ ያላቸውን አስተያየት በየተራ አንፀባርቀዋል፡፡

ካንፀባረቋቸውም አስተያየቶቻቸው ለመረዳት እንደተቻለው ጄኔራል ለገሠ ንፁህ፣ ትሁትና ጠንካራ የሆኑ፣ ወታደራዊ ዲሲፕሊን የተላበሱ፣ ከሁሉም በላይ አገራቸውን የሚወዱና መጻሕፍትን ማንበብ የሚያዘወትሩ ነበሩ፡፡

በቀለም ትምህርት 12ኛ ክፍል ከደረሱ በኋላ ሐረር ጦር አካዴሚ ገብተው የሚፈለገውን ወታደራዊ ትምህርት ካጠናቀቁ በኋላ አየር ኃይል መመደባቸውን አስረድተዋል፡፡

ታላላቅ የጦር መኮንኖች የጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ማኅበር አባላት፣ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን፣ የጄኔራሉ ቤተሰቦችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...

ያልነቃ ህሊና!

ከሽሮሜዳ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። ነቀፋ አንሶላው፣ ትችት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...