Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየታዳጊዋ ‹‹እማ ዋሽተሽኛል››

የታዳጊዋ ‹‹እማ ዋሽተሽኛል››

ቀን:

የግጥም ስብስቦቿን ለንባብ አብቅታለች፡፡ ገና በአሥር ዓመቷ የግጥም ስብስቦቿን ለንባብ ያበቃችው በእምነት ወልደ ሩፋኤል፣ ለስኬቷ የቤተሰቧን ድጋፍ ታመሰግናለች፡፡ ለቤተሰቦቿ ልዩ ፍቅር እንዳላት የተናገረችው በእምነት፣ የበኩር ሥራዋ የሆነውን “እማ ዋሽተሽኛል” የግጥም መድበል ለንባብ አብቅታለች።

 “ዕድሜ ለእናትና ለአባቴ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁንልኝ” የምትለው በእምነት፣ ወላጆቿ በተለያዩ ፌስቲቫሎችና ፕሮግራሞች እንድትሳተፍ እንዲሁም መጻሕፍት እንድታነብ እንደሚረዷት ትናገራለች።

የተለያዩ የግጥም መጻሕፍትን ማንበብ ስትጀምር ግጥም የመጻፍ ፍላጎት ያደረባት ሲሆን፣ ‹‹እማ ዋሽተሽኛል›› የግጥም ሥራዋ፣ ለእኩዩቿ መነቃቃትን እንደሚፈጥር ታምናለች።

- Advertisement -

እማ ዋሽተሽኛል አንችን እየራበሽ እኔን አብልተሽኛል፣

እማ ዋሽተሽኛል አንችን እየጠማሽ አጠጥተሽኛል፣

እማ ዋሽተሽኛል አንች እንቅልፍ አጥተሽ አስተኝተሽኛል፣

ከዚህ በኋላማ የዕለት ቀኔን ደስታ ላንች ሰጥቻለሁ፣

እኔ እየተከፋሁ አስደስትሻለሁ፣

እኔ እየተራብኩኝ አንችን አበላለሁ፣

እኔ እየተጠማሁ አንችን አጠጣለሁ፣

ባለ ውለታየ አመሰግናለሁ፣

ደስታሽም ደስታዬ ሳቅሽም ሳቄ ነው ኩራትሽ ኩራቴ፣

ለቅሶሽ ለቅሶዬ ነው ጉዳትሽ ጉዳቴ፣

 ዘላለም ኑሪልኝ ክብርዓለም እናቴ።

በማለት ከመድበሏ ያካተተቸው ግጥም፣ እናት ልጆቿን ተቸግራ ብታሳድግም፣  ለልጆቿ ስትል መከራና ችግሯን ደብቃ እንደምታሳድግ መረዳቷን የገለጸችበት እንደሆነ ታስረዳለች።

የክረምት መግባትን ተከትሎ ትምህርት በሚዘጋበት ወራት ብዙ ተማሪዎች  ጊዜአቸውን ቁም ነገር ሳይሠሩበት ያልፋል። እንደ በእምነት ያሉ ታዳጊዎች ደግሞ  መጻሕፍትን በማንበብ፣ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን በመከታተል ያሳልፋሉ።

ታዳጊዋ ግጥም መጻፍ የጀመረችው በክረምት ነው፡፡ የግጥም አጻጻፏን የተመለከተው አባቷ ‹በርትተሽ ከጻፍሽ አሳትምልሻለሁ› ብሎ ቃል ከገባላት በኋላ ፍላጎቷ የበለጠ እንደተነሳሳ ታስረዳለች።

የአምስተኛ ክፍል ተማሪዋ በእምነት፣ ዋናው ስራዋ ትምህርት ስለሆነ በአሁኑ ወቅት ‹‹ትልቁ ስኬቴና ትኩረቴ ትምህርቴ ነው›› ትላለች።

ግጥሞቿን የምትጽፈውም በትርፍ ጊዜዋ ነው፡፡ በሥነ ጥበብና ሥነ ጽሑፍ  ዘርፍ ያላትን ዝንባሌ በትምህርት በማዳበር የተሻለ ደረጃ ላይ ለመገኘት ከወዲሁ በጥንካሬ እየተጓዘች መሆኑን ተናግራለች።

‹‹ልጆች በትምህርታቸውም ሆነ በሚኖራቸው ዝንባሌ ውጤታማ  እንዲሆኑ ወላጆች እንደ እኔ ወላጆች ልጆቻቸውን መንከባከብና መምከር ይኖርባቸዋል፤›› የምትለው በእምነት፣  ልጆችም ቢሆኑ የወላጆቻቸውን ምክርና ትዕዛዝ ሊያከብሩ እንደሚገባ ትመክራለች።

ብዙ ጊዜ ልጆች አርዓያ አድርገው የሚከተሉት ወላጆቻቸውን በመሆኑ ወላጆች አንባቢ ሊሆኑ ይገባል ያሉት ደግሞ፣ የበእምነት ወላጅ አባት አቶ ወልደሩፋኤል ናቸው።

ልጃቸው በእምነት ወደ ሥነ ጽሑፍ እንድታዘነብል ያደረጋት ቤት ውስጥ ያሉ መጻሕፍትን በፈቃዷ እያገላበጠች በማንበቧ እንደሆነም ተናግረዋል።

ችሎታዋን የተረዱ ወላጆቿም ቤት እንግዳ ሲመጣ፣ ንግግር እንድታደርግና ግጥም እንድታነብ በማድረግ በሰዎች ፊት የመናገርና የማንበብ ችሎታዋ ከፍ እንዲል አድርገዋል።

‹‹በትምህርትሽ ጥሩ ዉጤት ካስመዘገብሽና ጎበዝ ተማሪ ከሆንሽ የአሥር ዓመት የልደት ስጦታሽ ግጥሞችሽን አሰባስበን ማሳተም ይሆናል፤›› ብለዋት እንደነበር የሚናገሩት አቶ ወልደ ሩፋኤል፣ ልጅም ወላጅም በቃላቸው ተገኝተው ‹‹እማ ዋሽተሸኛል›› የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ንባብ ለሕይወት በሚል ተዘጋጅቶ በነበረው ፌስቲቫል  ላይ በርካታ ሕፃናትና ወላጆች በተገኙበት ተመርቃ ለንባብ በቅታለች።

‹‹ልጆቻችን የእኛ ብቻ ሳይሆኑ የሀገርም ጭምር ናቸው፤›› የሚሉት አቶ ወልደ ሩፋኤል፣ ነገ ተምረው ሐኪም፣ መምህር፣ ደራሲና ሌላም ሊሆኑ የሚችሉት  ከወዲሁ ጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርገው ሲሠሩ ነው ባይ ናቸው።

ነገ አገርን ለሚረከቡ  ልጆች ወላጆች ከፊት እየቀደሙ መንገዱን ማቃናትና መልካሙን ሁሉ ማስተማር ተገቢ ነው ሲሉም ተናግረዋል። በእምነት የራሷ የሆነ ፍላጎት እንዳላት ተረድተናል ያሉት ደግሞ የበእምነት እናት ወ/ሮ ትዕግስት ሙሉጌታ ናቸው።

ልጃቸው ያላትን ፍላጎት በመረዳት ከወዲሁ መሠረት ይዛ እንድታድግና ነገ ከጥሩ ደረጃ  እንድትደርስ  የበኩላቸውን ድጋፍና ክትትል እያደረጉላት እንደሆነ የተናገሩት ወ/ሮ ትዕግስት፣ ልጆች በሥነ ምግባር እንዲኮተኮቱና ፈሪኃ እግዚአብሔር  እንዲያድርባቸው ማገዝ የወላጆች ግደታ ነው ሲሉ ያክላሉ።

‹‹ልጆቼን የማሳድገው ሙሉ ጊዜዬን ሰጥቼ ነው፣›› ያሉት ወ/ሮ ትዕግስት፣ አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው ለረጅም ሰዓት ማኅበራዊ ሚዲያ ሲጠቀሙ የጠቀሟቸው መስሏቸው ሲጎዷቸው እንደሚመለከቱ ያስረዳሉ።

ልጆችን በጥሩ ሥነ ምግባር ለማሳደግ ብዙ ፈተናዎችና ልጆችን በቀላሉ ሊያታልሉ የሚችሉ  አሉታዊ ተፅዕኖዎች  እንዳሉ የሚናገሩት ወ/ሮ ትዕግስት፣ ለልጆች የሚደረጉ ነገሮች ከመስመራቸው እንዳይወጡና ዓላማቸውን የማያስቱ ስለመሆናቸው ወላጆች የየዕለት ክትትል ማድረግ አለባቸው በማለት ያስረዳሉ።

ልጆች ስለሚፈልጉት ነገር ጥቅምና ጉዳት በማስረዳት ጥቅሙንና ጉዳቱን ራሳቸው እንዲያውቁና አመዛዝነው እንዲፈርዱ በማድረግ በቀላሉ ከችግሩ እንዲርቁ ማስተማርና መምከር የወላጆች የመጀመሪያ ሥራ ሊሆን ይገባልም ይላሉ።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ