Friday, May 24, 2024

የሶማሊያ ሰሞናዊ እንቅስቃሴ የፈጠረው ትኩሳት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

እ.ኤ.አ. በዲሴምበር 2023 ሶማሊያ 4.5 ቢሊዮን ዶላር የዕዳ ማቃለያ ከዓለም አቀፍ አበዳሪዎች ተደርጎለት ነበር፡፡ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ለሶማሊያ ዕድገት እንቅፋት እየሆነ ነው ያሉትን ዕዳ ማቃለላቸውን በወቅቱ አስታውቀው ነበር፡፡ የአሜሪካ መንግሥት የገንዘብ መሥሪያ ቤት በበኩሉ ሌሎች የሶማሊያ አበዳሪዎችም ተመሳሳይ የዕዳ ማቃለያ ዕርምጃ እንዲወስዱ ነበር የጠየቀው፡፡

በዚያው በዲሴምበር ወር መግቢያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት፣ በሶማሊያ ላይ ተጥሎ የቆየውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ በሙሉ ድምፅ እንዲነሳ መወሰኑን አስታውቆ ነበር፡፡ ለ31 ዓመታት ፀንቶ የቆየው የተመድ ውሳኔ ቁጥር 2713 ሶማሊያ ከውጭ መሣሪያ እንዳትገዛም ሆነ እንዳታስገባ የከለከለ ነበር፡፡ አገሪቱ በፀጥታው ረገድ ብዙ መሻሻል ስላሳየችና በአልሸባብ ሽብር ቡድን ላይ ጠንካራ ዘመቻ እያካሄደች በመሆኑ፣ ማዕቀቡ ሊነሳላት ይገባል በሚል ነበር ውሳኔው በወቅቱ የተወሰነው፡፡

የተመድ ፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት እ.ኤ.አ. በ2023 ሶማሊያን በተመለከተ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል እ.ኤ.አ. በ2024 መገባደጃ ተጠቃሎ ይውጣ የሚለው ይገኝበታል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ በሶማሊያ ወይም (ATMIS) የተባለው የኬንያ፣ የኢትዮጵያ፣ የብሩንዲ፣ የጂቡቲና የዩጋንዳ ሠራዊቶችን ያቀፈው ወታደራዊ ኃይል ሥራውን ጨርሶ በ2024 መገባደጃ እንዲወጣ ጊዜ ገደብ ተቀምጧል፡፡

ሶማሊያ የራሷን ሰላም ማስከበር ትችላለች፣ የውጭ ሰላም አስከባሪ ኃይል አያስፈልግም የሚለው ውሳኔ ላይ የደረሰው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሶማሊያ የተሠማራው ጦር የሚወጣበትን ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰኞ የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. የሶማሊያን ጉዳይ ሲመለከት የዋለው የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ሶማሊያ አልሸባብን በመዋጋት ስኬታማ ስለመሆኗ ጎልቶ ተነስቶበታል፡፡ ሶማሊያ በምክር ቤቱ አልሸባብን ለማሸነፍ ተቃርባለች በሚል ስትወደስ ውላለች፡፡ ሆኖም የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ሶማሊያ በአልሸባብ ላይ እያደረገች ያለችውን ውጊያ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች እያደናቀፉት ነው የሚል ክስ የተደመጠበት ነበር፡፡

በዚህ ጉባዔ ላይ ስለሶማሊያ ዝርዝር ሪፖርት ያቀረቡት የተመድ ዋና ጸሐፊ የሶማሊያ ልዩ ልዑክ ካትሪና ላይንግ ኢትዮጵያ አልሸባብ እንዲጠናከር ምክንያት እየሆነች ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ባደረገችው የባህር በር ስምምነት፣ በተቃራኒው አልሸባብ አዳዲስ አሸባሪዎችን ለመመልመልና ራሱን ለማጠናከር እየተጠቀመበት ነው ሲሉ ሪፖርት አድርገዋል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች በከፈሉት ከባድ መስዋዕትነትና ለዓመታት ሳይሰለቹ በሶማሊያ ሰላም ለማስከበር ባደረጉት ጥረት ሶማሊያ አሁን ያገኘችውን አንፃራዊ ሰላም ለማግኘት መብቃቷን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ አለመረጋጋት ምንጭ ሆናለች የሚለው ክስና ወቀሳ ጎልቶ እየተደመጠ ነው፡፡

ይህ በኢትዮጵያ ላይ የሚሰማ ክስና ወቀሳ ደግሞ በሶማሊያ ፕሬዚዳንት በሼክ ሀሰን መሐመድ ብቻ የሚስተጋባ ሳይሆን፣ እንደ ተመድ የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ባሉ መድረኮች ላይም የሚደመጥ ሆኗል፡፡

ረቡዕ የካቲት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ጸሐፊ ሞሊ ፊ፣ እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመርና በሱዳን የአሜሪካ አምባሳደር ጆን ጎድፍሬ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም፣ የኢትዮጵያና የሶማሊያ ጉዳይ ተነስቶ ነበር፡፡ በዚሁ መግለጫ ላይ የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ የወደብ ስምምነት በአልሸባብ ላይ የሚደረገውን ውጊያ ያስተጓጉላል ብላችሁ ታምናላችሁ ወይ የሚል ጥያቄ ተጠይቀው ነበር፡፡

ሞሊ ፊ ለዚህ ጉዳይ በሰጡት ምላሽ በይፋ አይናገሩት እንጂ፣ የሶማሊያዎችን ውንጀላ ደጋፊ የሆነ አስተያየት ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹አልሸባብን የመዋጋቱ ግብ የሶማሊያ ብቻ ሳይሆን ለሶማሊያ መረጋጋት ፍላጎት ያላቸው ወገኖች ሰላም አስከባሪ ኃይል ያዋጡትን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮችን ጨምሮ የእኛም ፍላጎት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ያላትን ፍላጎት እንረዳለን፡፡ ይህ ፍላጎት ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተፈጻሚ የሚሆንበትን አግባብ እንደግፋለን፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ የጋራ ግባችን የሆነውን አልሸባብን የመደምሰሱ ጥረት እንዲደናቀፍ አንፈልግም፤›› በማለት ነበር የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያ በሶማሊያ ሰላም ለማስከበር ገንቢ ሚና ከሚጫወቱ አገሮች አንዷ ናት ስትባል ቆይታለች፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመች ወዲህ ይህ በተቃራኒው የተቀየረ ይመስላል፡፡ አሁን የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ ስምምነት አልሸባብን እያጠናከረ ነው የሚለው ወቀሳ በሶማሊያ ባለሥልጣናት በከፍተኛ ደረጃ ጎልቶ እየተደመጠ ነው፡፡ ይህን ወቀሳ ደግሞ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ተቀብሎ እያስተጋባው ነው፡፡

በተመድ የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት አቋማቸውን ያስተጋቡ ሌሎች አገሮችም ቢሆኑ አንዳንዶቹ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችውን ስምምነት በሶማሊያ መረጋጋት ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት  አደናቃፊ ነው የሚል ድምዳሜ ሲያንፀባርቁ ታይተዋል፡፡ በሌላ በኩል ይህ ስምምነት የሶማሊያን አጠቃላይ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት የሚጋፋ ነው በማለት የሚደመድሙ አሉ፡፡

ይህ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ አለመረጋጋት ምንጭ እየሆነች ነው የሚለው ውንጀላ በተለያዩ መድረኮች እየተስተጋባ ባለበት በዚህ ወቅት ደግሞ፣ ከሶማሊያ ጎን ለመቆምና የሶማሊያ አጋር ሆኖ ለመታየት የሚደረገው ሽሚያም መቀጠሉ ይታያል፡፡ ከሶማሊያ ጋር ወታደራዊ ስምምነት የሚፈራረሙ አገሮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርክተዋል፡፡ ቀደም ብሎ ግብፆቹ፣ አሁን ደግሞ ኳታር፣ አሜሪካ፣ ቱርክ፣ ወዘተ እያለ ቁጥራቸው ሲጨምር ታይቷል፡፡

ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ኳታር ዶሃ ተገኝተው የነበሩት የሶማሊያ አየር ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ማህሙድ ሼክ ሀሰንና የሶማሊያ ጦር ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ኢብራሂም ሼክ ሙህዲን፣ ከኳታር የጦር ባለሥልጣናት ጋር ተስማምተው መመለሳቸው ተዘግቧል፡፡ ሶማሊያ የራሷን ሰላም በራሷ የፀጥታ ኃይል ለመጠበቅ የምታደርገውን ጥረት ኳታር በሥልጠናና በወታደራዊ ድጋፍ እንደምታግዝ ቃል የገባች ሲሆን፣ ሁለቱ አገሮች በፀጥታ ዘርፍ በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን ነው የጦር ባለሥልጣናቱ ያሳወቁት፡፡

የካቲት 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ደግሞ የሶማሊያና የአሜሪካ ባለሥልጣናት የጦር ስምምነት መፈራረማቸው ይፋ ተደርጓል፡፡ የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ጸሐፊዋ ሞሊ ፊ እና በሶማሊያ የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳዮች ፈጻሚ ሼን ዲክሰን፣ ከሶማሊያ የመከላከያ ሚኒስትር አብዱልቃድር መሐመድ ኑር ጋር ነበር ስምምነቱን የተፈራረሙት፡፡ በዚህ ስምምነት መሠረትም አሜሪካ ለሶማሊያ ሠራዊት አምስት ወታደራዊ ካምፖች ትገነባለች ተብሏል፡፡ አሜሪካ በዋናነት ከምታሠለጥነው ደናብ ለተባለው ብርጌድ ነው የጦር ካምፖቹን የምትገነባው ተብሏል፡፡

ይህን የአሜሪካና የሶማሊያን የጦር ስምምነት በማስመልከት ‹‹Why is the U.S. building bases for a chinese ally?›› የሚል ትንታኔን በዋሽንግተን ኤግዛማይነር ላይ ያስነበቡት ማይክል ሩቢን፣ አሜሪካ ከሶማሊያ ጀርባ ያላትን ፍላጎት በሰፊው ይዘረዝራሉ፡፡ አሜሪካ በታይዋን ላይ የምትከተለውን ፖሊሲ በይፋ ለተቃወመችው፣ እንዲሁም በብዙ ጉዳዮች የቻይና ጥብቅ አጋር ለሆነችው ለሶማሊያ ለምን የጦር ካምፕ ትገነባለች ሲሉ ጸሐፊው አጥብቀው ይጠይቃሉ፡፡ አሜሪካ ብዙ ሚሊዮን ዶላሮች አፍስሳ በሶማሊያ የምርጫ ድግስ ስፖንሰር የምታደርገውም ሆነ፣ መቶ ሚሊዮን ዶላሮችን አፍስሳ የደናብ ብርጌድ ለተባለው የጦር ኃይል ወታደራዊ ካምፕ የምትገነባው ዲፕሎማቶቿ በሚያስቀርፁት የተዛባ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የተነሳ ነው ሲል ሐተታው ያብራራል፡፡

ደናብ ብርጌድ አልሸባብን በመዋጋት ውጤታማ አይደለም ሲል ዘገባው ይሞግታል፡፡ ይህ ኃይል ከዚያ ይልቅ በቻይና ድጋፍ በተካሄደው የሶማሌላንድ የማጥቃት ዘመቻ የተካፈለ ነው ይላል፡፡ ከኤምባሲ ቅጥር ወጥተው ተጨባጩን የሶማሊያ ወቅታዊ ሁኔታ በቅርቡ የማይገነዘቡ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች አሜሪካ በሶማሊያ ጉዳይ የተሳሳተ ፖሊሲ እንድታራምድ እያደረጉ ነው በማለት ዘገባው ወቀሳ ይሰነዝራል፡፡

ሶማሊያ ከአሜሪካ ጋር ያደረገችው ስምምነት ብዙ እያነጋገረ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ሶማሊያ ከቱርክ ጋር ሌላ የመከላከያ ስምምነት መፈራረሟ ከፍተኛ መነጋገሪያን የፈጠረ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ወዳጅ ስትባል የቆየችው ቱርክ ከዚህ ቀደም ከሊቢያና ከሱዳን ጋር፣ አሁን ደግሞ ከሶማሊያ ጋር ለአሥር ዓመታት የሚዘልቅ የመከላከያ ስምምነት መፈራረሟ ብዙ እያነጋገረ ነው፡፡

የሶማሊያ ምክር ቤት ያፀደቀው የቱርክና የሶማሊያ የመከላከያና የኢኮኖሚ ትብብር ስምምነት በዋናነት ኢትዮጵያና ሶማሌላንድን ጫና ውስጥ ለመክተት የተደረገ ዕርምጃ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዛ አብዲ ባሬ ስምምነቱ ሽብርተኝነትን፣ የባህር ውንብድናን፣ እንዲሁም በሶማሊያ የባህር ክልል የሚፈጸመውን በካይ ቆሻሻ የመድፋትና ሕገወጥ ዓሳ የማጥመድ ድርጊትን በጋራ ለመከላከል የተደረገ ነው ሲሉ አስተባብለዋል፡፡

የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ በዚህ ጉዳይ ማስተባበያ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹እኛ ከቱርክ ጋር የተፈራረምነው ኢትዮጵያንም ሆነ ሌላ አገር ለመውረር አስበን አይደለም፤›› በማለት መናገራቸው ተዘግቧል፡፡ ይሁን እንጂ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ከፍተኛ የሶማሊያ ባለሥልጣን ለቪኦኤ እንግሊዝኛ የዜና ምንጭ የስምምነቱ መንፈስ ከዚህ ፍፁም የተለየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቱርክ የመከላከያ ሚኒስትር ያስር ጉለርና በሶማሊያ አቻቸው አብዱልቃድር መሐመድ ኑር ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም. የተፈረመው ስምምነቱ፣ ‹‹በአጋጣሚና በቶሎ የተካሄደ ስምምነት ነው፤›› በማለት ባለሥልጣኑ ገልጸዋል፡፡

ባለሥልጣኑ እንዳጋለጡት ስምምነቱ የሶማሊያ መሪዎች እንደተናገሩት ቆየት ያለና ታስቦበት የተደረገ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ የወደብ ስምምነትን ይፋ መሆንን ተከትሎ አፀፋ ለመስጠት የተደረገ ጥረት ነው ተብሏል፡፡ ቱርክ በዚህ ስምምነት መሠረት የሶማሊያ የባህር ክልል ውስጥ የባህር ሀብቶችን የማውጣት መብት የምታገኝ ሲሆን፣ እስከ 35 በመቶ የመጠቀም መብትም እንደሚኖራት ታውቋል፡፡ በሶማሊያ የባህር ክልል ብቻ ሳይሆን በሶማሊያ መሬትም ሠራዊቷን ታሠፍራለች ተብሏል፡፡

ቱርክ በስምምነቱ መሠረት ለሶማሊያ ጦር በሥልጠናና በሌላም ወታደራዊ ድጋፍ ታደርጋለች ተብሏል፡፡ ከዚህ ቀደም እ.ኤ.አ. ከ2017 ጀምሮ ቱርክ በሶማሊያ ግዙፍ ወታደራዊ ሠፈር የገነባች ሲሆን፣ በዚህ የጦር ሠፈር ለሶማሊያ ሠራዊት በተለይም ጩሉሌዎቹ (ጎርጎር) ለሚባሉ ወታደሮች ሥልጠናና ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷ ተነግሯል፡፡

ስምምነቱ በብዙ ተቺዎች ዘንድ ሶማሊያ ሉዓላዊነቷን አሳልፋ የመስጠት ዕርምጃ እንደወሰደች ነው የተቆጠረው፡፡ ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃምዛ አብዲ ባሬ፣ ‹‹ከቱርክ ጋር የተደረገው ስምምነት የሶማሊያን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የተደረገ ታሪካዊ ውል፤›› በማለት ነበር ያሞካሹት፡፡ በርካታ ሶማሊያዊያንም ይህን ስምምነት ሲያሞካሹት የታዩ ሲሆን፣ ለሶማሌላንድና ለኢትዮጵያ የወደብ ስምምነት ከሶማሊያ መሪዎች የተሰጠ አፀፋ አድርገው ሲገልጹ ሰንብተዋል፡፡

ከሶማሌላንድ ጋር የወደብ ስምምነት በመፈራረምና የአገርነት ዕውቅና ለመስጠት ፍላጎት በማሳየት ሶማሊያ ላይ በደል ፈጽማለች ለሚሏት ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እንደ አሜሪካና ቱርክ ካሉ በጦር አቅም ከጠነከሩ አገሮች ጋር ስምምነት በመፈራረም ተመጣጣኝ አፀፋ ሰጥታለች የሚሉ ወገኖች ጉዳዩን ለሶማሊያ እንደ ተመዘገበ ትልቅ ድል አድርገው ሲያራግቡት ከርመዋል፡፡

ይሁን እንጂ የአፍሪካ ቀንድ ለወትሮም ከቀውስ ተለይቶ እንደማያውቅ የጠቀሱ አንዳንድ ወገኖች፣ የቱርክ በቀጣናው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ማድረግ የበለጠ ችግር ይዞ እንደሚመጣ እየተናገሩ ነው፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ በተለይም በቀይ ባህር ጠረፎች ኃያላኑ አገሮች ወታደራዊ የጦር ሠፈር በመገንባት ሽሚያ ውስጥ ገብተው መቆየታቸውን እነዚህ ወገኖች ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ይህ ሽሚያ ጂቡቲን ማዕከል ያደረገ እንደነበርም ያወሳሉ፡፡ በጂቡቲ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ፈረንሣይ፣ ጃፓን፣ ጣሊያንን ጨምሮ ከአሥር ያላነሱ አገሮች የጦር ሠፈር መገንባታቸውን ወይም የባህር ኃይል ማሳረፋቸውን ይገልጻሉ፡፡

ይህ የባህር ውንብድናንና ሽብርን በመከላከል፣ እንዲሁም የባብኤል መንደብ የንግድ መተላለፊያን ደኅንነት ለመጠበቅ በሚል ሽፋን የሚደረግ የወታደራዊ መስፋፋት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ አሁን ደግሞ ይህ ወታደራዊ መስፋፋት አቅጣጫውን ለውጦ በሶማሊያ ዙሪያ መሽከርከር መጀመሩን እነዚህ ተቺዎች ያስረዳሉ፡፡

ከሰሞኑ ከግብፅ እስከ ቱርክ፣ ከኳታር እስከ አሜሪካ ወደ ሶማሊያ ማንጃበብ መጀመራቸውን ይጠቀማሉ፡፡ በተለይ የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ ስምምነትን ተከትሎ የሶማሊያ ባለሥልጣናት በደም ፍላትና በጀብደኝነት ለውጭ ጣልቃ ገቦች በራቸውን መክፈታቸው፣ የቀጣናውን የኃይል አሠላለፍ የበለጠ እንዳያወሳስበው እየተሠጋ ነው፡፡

በመካከለኛው ምሥራቅ በእስራኤልና በሐማስ ግጭት የተወጠሩት ግብፆች በጎረቤት ሊቢያ፣ እንዲሁም በሱዳን በሚካሄዱ ጦርነቶች እጃቸውን ነክረው ቆይተዋል፡፡ ግብፆች ይህ ሳይወስናቸው የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ ስምምነት በተፈረመ ማግሥት የሶማሊያ ቀዳሚ አጋርና ዋና አስተዛዛኝ ሆኖ መቅረብን እንደተካኑበት ታዛቢዎች ይገልጻሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ቱርክ ከግብፆች ጋር የገቡበትን ውጥረት ማርገባቸውና ግንኙነታቸውን ማሻሻላቸው ተጨማሪ ድጋፍ እንደሆናቸው ያስረዳሉ፡፡ የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ ስምምነት በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ፍጥጫ መፍጠሩ እንደ ግብፅ ላሉ አገሮች የጂኦ ፖለቲካ ፍላጎት ማስፈጸሚያ ተጨማሪ ዕድል መፍጠሩን ነው የሚያብራሩት፡፡

ግብፆች በሶማሊያ ጉዳይ አስታከው በኢትዮጵያ ላይ ለማሴር ስለመንቀሳቀሳቸው ምንም ያሉት ነገር የለም፡፡ ቱርኮቹ ከሶማሊያ ጋር የተፈራረሙት ወታደራዊ ስምምነት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የተደረገ ነው የሚለውን ውንጀላ ግን ወዲያው ለማስተባበል ሞክረዋል፡፡

የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹ኢትዮጵያ በአፍሪካ አኅጉር በንግድ፣ በኢኮኖሚም ሆነ በወታደራዊ መስክ እጅግ ጠቃሚዋ አጋራችን ነች፤›› በማለት ገልጿል፡፡ መግለጫው ቱርክ ከኢትዮጵያ ጋር ላላት የረጅም ጊዜ ግንኙነት ልዩ ቦታ እንደምትሰጥ አክሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -