Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉየመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

ቀን:

በኑረዲን አብራር

በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት ጊዜ ቢቆጠር በጣም ትንሽ ነው፡፡ በዚህ ሒደት የፍላጎት ግጭቶችና የፖለቲካ ውዝግቦች በማጋጠማቸው ዜጎች ለሰላም ዕጦት ተጋልጠዋል፡፡ የፖለቲከኞች ግጭት የሕዝብ ዕልቂት መፈናቀል፣ የንብረት ውድመትና የልማት መስተጓጎል እያስከተለ ሒደቱ እንደቀጠለ ነው፡፡

የፖለቲካ ምኅዳሩና የዴሞክራሲው መስተጋብር ለውጥ ማሳየት ተስኖት አሁንም የጥላቻ ንግግር፣ ውዝግብና አሉባልታ የአብሮነታችን እንቅፋት መሆናቸው ክፉ ልማድ ከሆነ ሰነባበተ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አገራችን ከነበረችበት ጥልቅ የጭቆናና የበደል ታሪኳ ተላቃ በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ለመራመድ ብትፍጨረጨርም፣ ስለበደልና ጭቆና ከመጠን በላይ ያወሩ ሥልጣኑን ሲይዙ ተመልሰው ችግር ፈጣሪ መሆናቸው የታሪካችን አካል ከሆነ ቆየ፡፡ ሌላው ቀርቶ የዛሬ ሃምሳ ዓመት በኢትዮጵያ ምድር ድንገት የተከሰተው አብዮት ይዞት የመጣው ጦስ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ ዕድሜዋ ሦስት ሺሕም ተባለ፣ የአሁኑን ቅርጿን ከያዘች ወዲህ ያለው ብቻ ተቆጥሮ 150 ዓመት ቢባል በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ልዩ ልዩ ሃይማኖቶችና ታሪኮችን ሰብስባ የያዘች ምድር ነች፡፡ በጂኦግራፊ አቀማመጧም ሆነ በተፈጥሮ ፀጋዋ ጠላት የበዛባት፣ በዚያው ልክም ሕዝቧ ለዘመናት ሉዓላዊነቷን በደምና በአጥንቱ ያስከበረላት የጀግንነት ምድር ናት፡፡

በዚያው ልክ ከማንም የላቀ ሀብት ኖሯት፣ ከማንም በታች ሆና በድህነትና በኋላቀርነት የኖረች፣ ከማንም ያላነሰ ታታሪና አገር ወዳድ ሕዝብ እያላት በድህነት ስትማቅቅ የዘለቀች አገርም ነች፡፡ መደማመጥና ሥልጡን የፖለቲካ ባህል ባለመገንባቱም፣ እርስ በርስ ሲፋጁ የነበሩ ትውልዶችም ያለፉባት ናት፡፡ የዚያ መዘዝ በዚያው የታሪክ ምዕራፍ ባለመቋጨቱም እስካሁኑ ትውልድ ውዝግቡና ተቃርኖው ዘልቆ ከትርምስ ለመላቀቅ አልተቻለም፡፡ ምንም ቢሆን ግን፣ ‹‹ከመጣነው አብረን የምንጓዘው ይበልጣል›› የሚለውን የብልህ አባቶች ጥልቅ ምክር ማሰብና መገንዘብ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡          

ኢትዮጵያ ሀብቷ ዕልፍ ነው፡፡ በከርሰ ምድር ውስጥ ያለውን ሀብት ትተን እንኳን በሕዝቧ መሀል ያለውንና ዓለምን የሚያስደምመውን ቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርስ ወይም  የብዙኃነት ሀብት ብንመለከት፣ እንደ ኢትዮጵያ የታደለ አገር ማግኘት ሲበዛ ብርቅ ነው፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ግን ይህ ሀብቷ ለዘመናት ውበቷና ጌጧ ሳይሆን ቆይቷል፡፡ የጭቆናና የተዛባ ታሪክ ሰለባ በመሆናችንም እርስ በርስ ስንባላባት መቆየታችንም አይዘነጋም፡፡

አሁን እየገጠመን ያለው አስከፊው እውነት ደግሞ የጋራ ሀብቶቻችንን የጋራ ዕድላችንን ለመወሰን ተሳስበን ሥራ ላይ ማዋል ሲገባን፣ በክልልና በመንደር ታጥረን ወደ ቀውስ የምናመራ በመሆናችን ነው፡፡ ኧረ ጎበዝ? ቆም ብለን እናስብ የሚያስብለውም ለዚህ ነው፡፡

በእርግጥ ይህ የብሔር ውዝግብም ሆነ የጥላቻ ፖለቲካ ዛሬ ብቻ የመጣብን አይደለም፡፡ ይልቁንም ከጥንት በተለይም ከቅኝ ገዥዎች ሴራ በኋላ በላያችን ላይ እንደተነዛብን የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ፡፡ ይህ የተዛባ የእርስ በርስ ግንኙነት መታረም በነበረበት ጊዜ ባለመታረሙ፣ መስተካከል በነበረበት አጋጣሚም ሳይስተካከል በመቅረቱ፣ የአገራችን ዕድገት እንደ ግመል ሽንት የኋልዮሽ ሲፈስ እንደኖረ ሊዘነጋ አይችልም፡፡ ቢያንስ አሁን በዕርቅና አብሮነት ጉዞ ተደማምጦ ማስተካከል የሚገባው ይህን እውነት በሆነ ነበር፡፡

እንደ አንድ አገር ሕዝቦች ከተማ/ገጠር፣ ቆላ/ደጋ፣ ዳር/መሀል ሳይባል አንዳችን ለሌላችን እኩል ማስፈለጋችን ሳይገለጥልን፣ ወይም እንዲገለጥልን ሳንፈልግ ለዘመናት በመኖራችን መድረስ በነበርንበት ሥፍራ ላይ ሳንደርስ ኖረናል፡፡ ይኼ እንደ አገር ሊያንገበግበንና ሊያስቆጨን ሲገባ፣ አሁንም ስለመለያየትና ውዝግብ ብሎም ስለግጭትና ትርምስ መስበክ እጅግ አሳፋሪና ኋላቀር አስተሳሰብ ነው፡፡

በተለይ ዓለም አሁን  ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ አኳያ ራሳችንን አዘምነን ያለንን የጋራ ሀብት አስተባብረን ፍትሐዊነቱ የተረጋገጠ ሥርዓት ከማደላደል ይልቅ፣ ወደኋላ እንደመመለስ ያለ ጭቃ ውስጥ መግባት ሊኮነን ይገባዋል፡፡  

በመሠረቱ ሁላችንም የዚህች አገር ዜጎች በተለይም የአዲሱ ትውልድ አባላት ‹‹ከመጣነው አብረን የምንጓዘው ይበልጣል›› ማለት ይገባናል ስንል፣ በቅንነትና በመተሳሰብ ጎዶሏችንን ለመሙላት ነው፡፡ እውነት ለመናገር የደርግ ሥርዓት ወድቆ በዚች አገር ላይ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ሲጀምር፣ በሕዝብ ልጆች ደምና ላብ በተመሠረተ ተጋድሎ ነበር፡፡

በ1987 ዓ.ም. ሁሉንም የአገራችን የፖለቲካ ኃይሎች ያሳተፈ ሕገ መንግሥት መቅረፅ ባይቻልም፣ ለበርካታ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዕውቅና የሰጠ ሰነድ እንደነበርም ሊካድ አይችልም፡፡ ያም ሆኖ የተገነባው ሥርዓትና የተቀረፀው ሕገ መንግሥት በአፈጻጸም ጭምር ተዳክሞ፣ ለዛሬዋ ኢትዮጵያ መሠረት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ዛሬም ድረስ ለሚታዩ ትልልቅ ክፍተቶች በር ከፍቷል፡፡

ይህ ሥርዓትና ሕገ መንግሥት ለአሁኗም ብቻ ሳይሆን ለወደፊቷ ኢትዮጵያ ዋስትና ሊሰጥ የሚችለው ግን፣ እንዳለፉት ጊዜያት ጭራሹን ጠፍቶ አዲስ በመጻፍ ሳይሆን በሕገ መንግሥቱ መሠረት ዳግም ማሻሻል ሲቻል ነው፡፡

አፍሪካ የቅርብ ዓመታት የዴሞክራሲ ልምድ አላት ስንል በተደጋጋሚ ሕገ መንግሥት ሊያሻሽሉ ይችላሉ እንጂ፣ እያፈረሱ ሲገነቡ እንዳልነበሩ የሚታወቅ ነው፡፡ ስለሆነም እኛም ከበረታንና ከተደማመጥን ሕገ መንግሥቱን ሥርዓት ባለው መንገድ በጋራ አሻሽለን 29 ዓመታት አብረን መጓዝ ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊትም እያሻሻልንና ጎዶሎዎችን እየሞላን ዕልፍ ዘመን ተያይዘን እንጓዝበታለን፡፡ ለዚህም ነው አብረን ከመጣነው ገና የምንጓዘው ይበልጣል የሚባለው፡፡

ምንም እንኳ የዛሬ ስድስት ዓመት ገደማ የጀመርነው ለውጥ የተደነቃቀፈ ቢሆንም፣ ገና ወደፊት አብረን የምንጓዘው ዘመን ይልቃል ሲባል ግን የምንጓዝበት መንገድ አልጋ በአልጋ ነው ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አሁንም ድረስ ለሕገ መንግሥታዊነትም ሆነ ለአገሪቱ ጉዞ አደጋ የሆኑ ችግሮች ገና መልክ መልክ አልያዙምና ነው፡፡

እነዚህ እንከኖች ከፅንፈኛ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ መስፋፋት፣ የእኔ የእኔ ከማለትና የዕርቅ መንገድን ከመሳት ጋር ያላቸው ዝምድናን ለይቶ ለማረም መረባረብ ያስፈልገናል፡፡ እንደ መንግሥትም እንደ ሕዝብም ማለት ነው፡፡ ጊዜያዊና አላፊ በሆነ ጠብ አገር ማውደምና የሕዝብን ሕይወት አደጋ ውስጥ መክተት ለማንም እንደማይጠቅም በግልጽ እየታየ ነው፡፡

ሃያ ዘጠኝ ዓመታት የሞሉት ሕገ መንግሥት የጋራ ሰነድ ነው ቢባልም ብዙ ችግሮችን በውስጡ መያዙ ይታወቃል፡፡ የጋራ ቤት ለመገንባት ውል የሚታሰርበትና የጋራ ፍኖተ ካርታ ነው ቢባልም፣ ውስጡ ባሉ ድንጋጌዎችም ሆነ በአፈጻጸሙ በርካታ ችግሮች አሉት፡፡ ከሕገ መንግሥቱ የሚመነጩ ችግሮችን በጥናት ላይ ተመሥርቶ መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡

በቀዳሚነት የአስተዳደር ወሰንና የክልል አስተዳደርን ከብሔር ጋር ብቻ ማቆራኘቱ የውድቀቱ መጀመርያ ነው፡፡ የአገሪቱን ዋና ከተማና የኦሮሚያ ክልልን ጉዳይ የያዘበት መንገድ፣ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ አጠቃቀም፣ የአንቀጽ 39 ጉዳይና መሰል ድንጋጌዎችም ዳግም መታየት ያለባቸው ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ በቅርቡ የሚጀመረው አገራዊ ምክክር አጋዥ ስለሚሆን፣ መላው የፖለቲካ ኃይሎችና ሕዝቡ በሆደ ሰፊነት በመጪው ዘመን በጋራ የምንኖርበትን ዘላቂ መንገድ አገናዝበው በስክነት መነጋገር ይጠበቅባቸዋል፡፡

አንዳንድ ምሁራን አሁን ያለው ሕገ መንግሥት አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመፍጠር ግብ ያለው ነው ይላሉ፡፡ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ቀኖና ላይ የተመሠረተ ሕገ መንግሥት በመሆኑ፣ አሳታፊና አቃፊ አይደለም በማለት የሚተቹት ቁጥራቸው ብዙ ነው፡፡ ምንም ተባለ ምን እንደታሰበው ወደ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ መሄድ ያለበት ጉዞ በሚፈለገው ፍጥነት እየተተገበረ ካለመሆኑም ባሻገር፣ እንደ ሕዝብ ረዥም ርቀት አስተሳስሮን እንዲቀጥል መደረግ አለበት፡፡

ያሉ ችግሮችን ማመን ወይም መለየት የመፍትሔ ግማሽ አካል ነውና በስሜት ሳይሆን፣ በተጨባጩ መነጋገርና ቁርጠኝነት ለዘለቄታው የሚጠቅም ሕገ መንግሥት አሻሽሎ ለትውልድ ማስተላለፍ የሁሉም ወገን ቁልፍ ኃላፊነት ነው፡፡ ስለሆነም ከዚህ በኋላ አብረን የምንሄደው ጉዞና ዘመን ይልቃልና ከወዲሁ መሠራት ያለበት ሁሉ በሁሉም ወገኖች ሊሠራ ይገባል፡፡

የማይካደው እውነት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በልዩነት ውስጥ አንድነት የነበራቸው በኢፍትሐዊ አገዛዞችም ዘመን ጭምር ነበር፡፡ ድርብ ጭቆና የነበረባቸው ወገኖች ቢኖሩም ያልተጨቆነ ሕዝብ ነበረ ማለት ግን አጉል ቀልድ ነው፡፡ ይሁንና ፖለቲከኞቻችን እርስ በርስ በመገፋፋት፣ ባለመከባበርና በቅጡ ለመነጋገር ባለመፈለጋቸው የተነሳ በአጉል ድርቅና ዘመናትን ገፍተዋል። ግጭት ውስጥ ገብተው ጥቃትም ተሰናዝረው ሕዝብ አስፈጅተዋል።

ቢያንስ ያን ምዕራፍ ከሞላ ጎደል ለአምስት አሠርት ዓመታት ተሻግረነው ሊያገረሽ አይገባም ነበር፡፡ እንዲያውም በመነጋገርና በዴሞክራሲያዊነት እያራቅነው መሄድ ይጠበቅብናል፡፡ ያሉት ሃምሳ ዓመታት ያተረፉልን ጦርነት፣ ዕልቂት፣ መፈናቀል፣ ረሃብ፣ ስደትና ጥልቅ የሆነ ድህነት ብቻ ነው፡፡

በተለያዩ ጽንፈኛ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው የተዛባ ትርክት ወደ ግጭት አዙሪት ለመግባት መንደርደር ፍፁም ሊወገዝ የሚገባው ነው፡፡  አሁን በተለያዩ አካባቢዎች የሚታየው የዜጎች ከኖሩበት አካባቢ መሰደድ፣ በማንነት መገደል፣ መገለልና መሸማቀቅ ሊያሳዝነን የሚገባው ሁላችንንም ሊሆን ይገባል፡፡

ይህ አደገኛ ክስተት እየተባባሰ ከሄደ አገር ለማሳደግ ሊኖር የሚገባውን ተነሳሽነት ማወኩ አይቀሬ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው ድርቅና ረሃብም ይባባሳል፡፡ የአገር ገጽታ ከመበላሸቱ ባሻገር ወደ ልማትና ዕድገት ምዕራፍ የሚደረገው ጉዞም ይስተጓጎላል።

በመሠረቱ አሁን ያለው ብሔር ተኮር የፌዴራሊዝም ሥርዓቱም ቢሆን ከሕገ መንግሥት ማሻሻያው ጋር ወደፊት መልክ መያዙ አይቀርም። ብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ፣ እርስ በርሳቸው ከመተዋወቅም አልፈው ለጋራ አገራቸው ልማት በኅብረት ለመሥራትና በፍትሐዊነት ተጠቃሚ ለመሆን እንዲነሳሱ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ አሁን የያዘውን አሳዛኝ ገጽታ መለወጥ የግድ ነው፡፡

አሁን በተደረሰበት የታሪክ ምዕራፍ ግን የሁሉም ሕዝብ ዓላማ በአንድ አገር ተባብሮና በእኩልነትና በፍትሐዊነት መኖር እንዲሆን መሥራት ሊሆን ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከጠባብ ብሔርተኝነትና ለእኔ ብቻ ከማለት በመውጣት በመተሳሰብና በጋራ መኖር ይጠበቅብናል።

ፖለቲከኞች ወደ ራሳቸው ፍላጎት እየጠመዘዙት እንጂ ከዚህ በኋላ አሀዳዊነትም ሆነ ጨፍላቂነት አብቅቶላቸዋል፡፡ ማንም ያለ ፍላጎቱ ተገዶ አንድ ቀን መቀጠል አይፈልግም፡፡ የኃይል ሚዛን ልዩነት ካልሆነ በስተቀር ይህ አስተሳሰብ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሆኗል፡፡ ይህንን ሀቅ በመካድ አጉል መወራጨት ለማንም አይጠቅምም፡፡

ዛሬም ሆነ ወደፊት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፍላጎት ሥርዓቱ ለአንዱ ሰጥቶ ሌላውን የሚከለክል ሳይሆን፣ ሁሉንም በእኩልነት የሚያስተናግድ እንዲሆን ነው የሚባለውም ከዚሁ እውነታ አንፃር ነው። ነገር ግን እኩልነት ሲጠየቁ ‹አሀዳውያን መጡላችሁ› እያሉ ጽንፈኞች የሚያስፈራሩበት ተራ ፖለቲካ ዋጋ አልባ እንደሚሆን ይታወቅ፡፡

እናም ይህን ፍላጎታቸውንና እምነታቸውን ማክበርና ማስከበር ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና ተከታዮቻቸው ተግባር ሊሆን ይገባል። በተለይ የፖለቲካ መሪዎችና ድርጅቶች በዚህ ላይ ተመሥርተው አብሮነትን፣ ዕድገትንና ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሚረዱ መንገዶችን መጥረግ ነው የሚበጃቸው፡፡

በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች አሁን ያለውን ፌዴራላዊ ሥርዓትና ውጤቶቹን ማጣጣል ብቻ ሳይሆን ተጋግዞ ለመሥራት፣ የተዛነፈ ካለም ለማረም ተቀራርቦ መነጋገር ያስፈልጋቸዋል። መንግሥትም ለዚህ አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ዝግጁ መሆኑን በተግባር ማረጋገጥ አለበት። ስለዚህ እንደ ፖለቲከኛ፣ እንደ ሕዝብም ሆነ እንደ መንግሥት የቆምንበትን መሠረት ፈትሾ ለዘላቂ ጥቅምና ነገ ትውልድ ስለሚኖርባት የጋራ አገር አስቦ መሥራት ያስፈልገናል፡፡

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ልጆቿን በጉያዋ አቅፋ እንደያዘች የጋራ የዕድገት ጉዞዋን ትቀጥላለች እንጂ፣ ወደ ቀድሞዋ አስከፊ ሁኔታ መመለስ ፈፅሞ አትፈልግም፡፡ ከዚያ ለመውጣትም በተለያዩ ጊዜያትና ሥፍራዎች ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሏል፡፡ ለአገርና ለሕዝብ የማያስቡ ኃይሎች ውዥንብር ከመንዛት ባይወጡም፣ ልጆቿ ተቻችለውና ተከባብረው ለመኖርም በቃል ኪዳን መተሳሰር አለባቸው፡፡ አንዳቸው ከሌላኛቸው ጋር በጋራ በሚገነቧት አገር በጋራ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተማምነውና ተሳስበው እንዲዘልቁ ማድረግ ግን፣ የመንግሥትና የዚህ ትውልድ ቀዳሚ ኃላፊነት መሆን ይኖርበታል፡፡

በኢትዮጵያ የተስፋ ብርሃን ፈንጥቆ ልጆቿ ከድቅድቅ ጭለማ ወጥተው የልማትና የዕድገት ጎዳናውን በጋራ ይገንቡ። የአገር ተስፋን ማጨለም የሚያልሙ ኃይሎች ልቦና ይስጣቸው። አሁንም በመንደር አስተሳሰብና በጥቃቅን የሠፈር አጀንዳዎች ጦር ሊያማዝዙን የሚሹ ይብቃቸው፡፡ እነዚህን ማሳፈርና ማስቆም ብሎም ትልቁን አገራዊ ኅብረትና አብሮነት ማማተር ያለብን እኛውና እኛው ብቻ ነን፡፡ በዚህ ላይ መንግሥትም ውስጡን አፅድቶ ቆፍጣና አቋም ይዞ ሕግ አክብሮ ማስከበር ይጠበቅበታል፡፡

ኢትዮጵያውያን እስኪሻሻልም ሆነ እስኪቀየር ድረስ አሁን ያለው ሕገ መንግሥት ገዥ መመርያ መሆኑን በመገንዘብ ለሰላም መስፈን ቁርጠኝነት ያሳዩ፡፡ ስለሆነም ዋነኛ መመርያቸውን ማክበርና ማስከበርን መዘንጋት የለባቸውም፡፡ በብዙ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ውዝግቦችንና የተወላከፉ አስተሳሰቦችን  እንደማይቀበሉ፣ ለአገራቸውና ለጋራ ደኅንነታቸው ታማኝና ዘብ በመሆን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ሁሉም የአገራችን ሕዝቦች በግልም ሆነ እንደ ቡድን  እኩልነታቸውን፣ አንድነታቸውንና በጋራ ለልማትና ለዕድገት መቆማቸውን ማረጋገጥ የሚችሉት በዚሁ መንገድ ብቻ ነውና፡፡ ‹‹ከመጣነው አብረን የምንጓዘው ይበልጣል››  የሚለውን የአባቶችን ምጡቅ ሐሳብ አክብረን ልንፈጽም የምንችለውም በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡-  ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...