Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትበስታዲየም ችግር የተሸበበው የኢትዮጵያ ስፖርትና የሚጠበቁ ውድድሮች

በስታዲየም ችግር የተሸበበው የኢትዮጵያ ስፖርትና የሚጠበቁ ውድድሮች

ቀን:

ከሳምንታት በፊት በአይቮሪኮስት ሲከናወን የነበረው የአፍሪካ ዋንጫ ካስመለከታቸው ያልተጠበቁ ውጤቶች ባሻገር፣ በርካታ ጉዳዮች ተስተውለዋል፡፡ ስሟ በእርስ በርስ ጦርነት ሲነሳ የምትታወቀው አይቮሪኮስት ማራኪ ጨዋታ ከማሳየቷም በላይ፣ ለስፖርት መሠረተ ልማት ረብጣ በማውጣት ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞችን መገንባት ችላለች፡፡

ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ የአፍሪካ ዋንጫውን ማሰናዳት የቻለችው አይቮሪኮስት፣ አራት አዳዲስ ስታዲየሞችን ስትገነባ፣ ሁለት ስታዲየሞችን በማደስ ለውድድሩ ምቹ ሁኔታን መፍጠር አስችሏታል፡፡

ስታዲየሞቹ በጥራት ከመገንባታቸው በዘለለ ደረጃቸውን የጠበቁና ሁለገብ አገልግሎቶችን መስጠት የሚችሉ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ አይቮሪኮስት ለእግር ኳስ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች ማሰናዳቷን ተከትሎ፣ የተለያዩ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ዝግጁ እንደሆነችና በተለይ በስታዲየም ዕጦት የሚቸገሩ ብሔራዊ ቡድኖች ስታዲየሞቿን መጠቀም እንዲችሉ ጥሪ አቅርባለች፡፡

- Advertisement -

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ጨምሮ ሌሎች ብሔራዊ ቡድኖች የካፍ ዕውቅና ያገኘ ስታዲየም በማጣታቸው የሞሮኮ ስታዲየሞችን ሲጠቀሙ መክረማቸው ይታወሳል፡፡   

ከዚህ ጋር ተያይዞም አይቮሪኮስትና ሞሮኮ በርካታ የካፍ ዓመታዊ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ቅድሚያ የሚሰጣቸው አገሮች መሆን ችለዋል፡፡

ይህም አገሮቹ ጥራት ያላቸውና ለረዥም ጊዜ ያለ ምንም እንከን ውድድር ማስተናገድ የሚችሉ ስታዲየሞችን በመገንባታቸው ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ከአራት ዓመታት በላይ የአፍሪካ ዋንጫና የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎችን በአገር ውስጥ ማከናወን ሳይችል በመቆየቱ የተለያዩ አገሮችን ደጅ ሲጠና ቆይቷል፡፡

ይህም በኢትዮጵያ የካፍን መሥፈርት የሚያሟላ አንድም ስታዲየም ባለመኖሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ካፍ በኢትዮጵያ የተገነቡት፣ እንዲሁም እየተገነቡ ያሉት ስታዲየሞች የሚጠበቅባቸውን መሥፈርቶች እንዲያሟሉ ማዘዙ ይታወሳል፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ የካፍን መሥፈርት ማሟላት የቻለ አንድም ስታዲየም አለመኖሩ የዘንድሮውን ውድድር መርሐ ግብር አሳሳቢ አድርጎታል፡፡

የካፍ እንዲሁም የፊፋ መርሐ ግብር መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተለያዩ የማጣሪያ ውድድሮችን ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከዚህም ባሻገር ዓርብ የካቲት 15 ቀን 2016 ዓ.ም. በኬንያ በተካሄደው የሴካፋ ጠቅላላ ጉባዔ፣ የሴካፋ ውድድሮች አስተናጋጅ አገሮች የታወቁ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የ2024 የሴካፋ ዞን የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ ውደድር እንድታስታግድ ተመርጣለች፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ውድድሩን ኢትዮጵያ እንደምታስተናግደው ማረጋገጫ መስጠቱን አሳውቋል፡፡

ሆኖም በኢትዮጵያ እየተገነቡ የሚገኙ ስታዲየሞች መጠናቀቅ አለመቻላቸውና የካፍን መሥፈርት ያሟላ ስታዲየም አለመኖሩ ጉዳዩን ጥያቄ ያስነሳበታል፡፡

ግንባታቸው ከተጀመረ ዓመታትን ያስቆጠሩ ስታዲየሞች አሁንም አለመጠናቀቃቸው፣ የዋሊያዎቹ የዘንድሮ ተሳትፎ እንደ ዓምናው በስደት የታጀበ ይሆን ወይ? ብለው የሚጠይቁ በርካቶች ናቸው፡፡   

በግንባታ ላይ የሚገኙ ስታዲየሞች ሒደት

በኢትዮጵያ ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ ከ13 ስታዲየሞች በላይ ግንባታቸው እየተከናወነና እየታደሰ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ የባህር ዳር፣ መቀለ፣ ሐዋሳ፣ ሠመራ፣ ጅግጅጋ፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ ነቀምቴ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ ጋምቤላ፣ አሶሳ፣ አበበ ቢቂላና አዲስ አበባ ስታዲየም፣ እንዲሁም አደይ አበባ ስታዲየም በዕድሳትና በግንባታ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ እየተገነቡ የሚገኙትን የአደይ አበባና የአቃቂ ቃሊቲ ስታዲየም፣ እንዲሁም በዕድሳት ላይ የሚገኘው አዲስ አበባ ስታዲየም በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ፈሶባቸዋል፡፡ ሆኖም በተለያዩ ውስብስብ ችግሮች ተሸብበው ለዘንድሮ ውድድር መድረሳቸው አጠራጣሪ ነው፡፡

ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበትና የአብዛኛውን የስፖርት እንቅስቃሴ ችግር ይፈታል ተብሎ የታመነበት በአዲስ አበባ እየተገነባ የሚገኘው የአደይ አበባ ስታዲየም አንደኛው ነው፡፡

የብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ ተረክቦ ሲያከናውን የነበረው የቻይናው ኮንስትራክሽን ዲዛይን ኮርፖሬሽን፣ የግንባታው የተወሰነውን ክፍል ቢጋመስም በስምምነቱ መሠረት መቀጠል ተስኖት ውሉ እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡

ከስድስት ዓመታት በፊት በ2.47 ቢሊዮን ብር ሊገነባ የታቀደው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም ግንባታ በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይቷል፡፡ የሁለተኛው የግንባታ ምዕራፍ ሲጀመር በነበረበት ወቅት ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመግባቱና ለድርጅቱ የሚከፈል የቅድመ ክፍያ የውጭ ምንዛሪ በወቅቱ ባለመከፈሉ እንዲዘገይ አድርጎት ነበር፡፡

ከዚህም በላይ ተቋራጩ ሁለተኛውን ምዕራፍ ለማጠናቀቅ የዋጋ ማሻሻያ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ በተገባው ውልና በቀረበው የዋጋ ማስተካከያ ጥያቄ መሠረት የሥራ ወጪ ላይ የክፍያ ማስተካከያ በማድረግ 12.5 ቢሊዮን ብር ለመክፈል ስምምነት ላይ ተደርሶ እንደነበር፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል፡፡

በአንፃሩ ተቋራጩ የተከፈለውና በመጀመሪያ የግንባታ ምዕራፍ ውስጥ የሚገኙ ያልተጠናቀቁ ሥራዎችን አንድ ላይ ለማከናወን ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ በመጠየቁ፣ ሁለቱ ተቋማት በስምምነቱ ውል ለማቋረጥ ተገደዋል፡፡ ሚኒስቴሩ የተለያዩ ተቋራጮችን በጨረታ እየለየ እንደሆነም ተጠቅሶ ነበር፡፡  

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የ2016 ዓ.ም. በጀት ዓመት የአምስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት በቀረበበት ወቅት ከዓረብ ኤምሬትስ በተገኘ የ50 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ቀጣይ ምዕራፍን ለማጠናቀቅ ውል መታሰሩን ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳ አስረድተዋል፡፡

ሆኖም ግንባታው መቼ እንደሚጀመርና መቼ እንደሚጠናቀቅ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ ሪፖርተርም ዝርዝር ጉዳዮችን ማወቅ ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

ሌላው ለዘንድሮ የስፖርት ውድድር መርሐ ግብር ዝግጁ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው፣ ላለፉት ሦስት ዓመታት ዕድሳት ላይ የነበረው አዲስ አበባ ስታዲየም ነው፡፡

ስታዲየሙ ሙሉ በሙሉ ግንባታው እንደተጠናቀቀ በሪፖርት የቀረበ ቢሆንም፣ የካፍ መሥፈርትን ያሟሉ የ‹‹ቪአይፒ›› እና ‹‹ቪቪአይፒ›› መቀመጫዎች ባለመሟላታቸው መዘግየቱ ተጠቅሷል፡፡ በአንፃሩ ስታዲየሙ ሙሉ ለሙሉ ዝግጁ ሲሆን ካፍ የሚሰጠው ምላሽ የሚጠበቅ ይሆናል፡፡

ቀሩ የተባሉት ቁሳቁሶች ከተሟሉ በዘንድሮ የውድድር ዘመን የካፍና የፊፋ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ዕድል ያለው የአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

ሌላው የተወሰኑ የማጣሪያ ጨዋታዎችን አስተናግዶ በካፍ የታገደው የባህር ዳር ስታዲየም ነው፡፡ 60 ሺሕ ተመልካቾች የመያዝ አቅም ያለው ስታዲየሙ ግንባታው ሳይጠናቀቅ ዘጠኝ ዓመታት ሞልቶታል፡፡

ስታዲየሙ በካፍ ከታገደ በኋላ ዕድሳቱ ሲጓተት በመቆየቱ፣ ዋሊያዎቹ ጨዋታቸውን በአገራቸው እንዳያደርጉ ዳርጓቸዋል፡፡ ሆኖም በቅርቡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስታዲየሙ እያከናወነ ስለሚገኘው ዕድሳት ማብራሪያ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

ስታዲየሙ ማሻሻያ እንዲደረግበት ካፍ የዘረዘራቸው፣ መታደስ የሚገባቸው የስታዲየሙ ዋና ዋና ክፍሎች፣ እነሱም የመጫወቻ ሜዳ፣ የልምምድ ሥፍራ፣ የስታዲየሙ ዙሪያ፣ የመልበሻ ክፍል፣ እንዲሁም ተያያዥ ክፍሎች ዕድሳት እንደተደረገባቸው ተጠቅሷል፡፡ በቅርቡም የስታዲየሙ ጣራና መቀመጫዎች ይገጠማሉ ቢባልም ለዘንድሮ ውድድር ዝግጁ መሆን? አለመሆኑ? የተገለጸ ነገር የለም፡፡

በሌላ በኩል ከስታዲየም ዕድሳት ጋር በተያያዘ ሰሞኑን ስሙ እየተነሳ የሚገኘው የድሬዳዋ ስታዲየም ሲሆን፣ በቅርቡ የፊፋን ደረጃ ማሟላት የቻለ የሰው ሠራሽ ሳር ተከላ ማከናወኑን ይታወቃል፡፡

ምንም እንኳን ስታዲየሙ ሰው ሠራሽ ሳር ማስተከል መቻሉ ብቻውን የብሔራዊ ቡድኑን የማጣሪያ ጨዋታ ያስተናግዳል ማለት አይደለም፡፡ ካፍ የሚጠይቃቸው መሥፈርቶች ማሟላት የሚችል ከሆነ ለብሔራዊ ቡድኑ ሌላ አማራጭ የሚሰጥ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ በስታዲየም ዕጦት ችግር መመታት ከእግር ኳሱም ባልተናነሰ መልኩ አትሌቲክሱንም እየጎዳው ይገኛል፡፡ አትሌቶች መደበኛ ልምምዳቸውን ለማድረግ እየተቸገሩ እንደሚገኙ ባገኙት አጋጣሚ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ በኢትዮጵያ አንድም ትራክ ያለመኖሩ ችግሩን ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡

አትሌቶች አገርን ወክለው ለሚያደርጉ ዝግጅት በተላላጠ ትራክ (መም) ላይ ለመሥራት ተገደዋል፡፡ የዚህ ሁሉ ችግር መፍትሔ ዘንድሮ ምላሽ ያገኝ ይሆን? የሚለው የአብዛኛው ሰው ጥያቄ ነው፡፡.      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...