Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል የመብት ተቆርቋሪዎች እንዲፈቱ ጥያቄ አቀረበ

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል የመብት ተቆርቋሪዎች እንዲፈቱ ጥያቄ አቀረበ

ቀን:

  • የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለአስፈጻሚው አካል ያልተገደበ ሥልጣን መስጠቱን ገልጿል

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ያላግባቡ የታሰሩ የመብት ተቆርቋሪዎች ከእስር እንዲፈቱ፣ በእስር ላይ በሚቆዩበትም ወቅት መሠረታዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩ ጠየቀ፡፡

ማዕከሉ ዓርብ የካቲት 15 ቀን አመሻሽ ባወጣው መግለጫ፣ መንግሥት በሕገ መንግሥቱና አገሪቱ ፈርማ ባጸደቀችው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በሕግ ጥላ ሥር ለዋሉ ሰዎች ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡ መንግሥት ታሳሪዎቹ የሚገኙበትን ሁኔታ በአፋጣኝ እንዲያጤንና በእስር ላይ የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ጨምሮ ሌሎች ታሳሪዎች የተሻለ ሕክምና፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ የመቆያ ሥፍራ እንዲያገኙ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች ከቤተሰቦቻቸውና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር የሚገናኙበትና በአስቸኳይም ፍርድ ቤት ቀርበው የተፋጠነ ፍትሕ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው አሳስብ፣ ጋዜጠኞችን ጨምሮ ለመብት ተሟጋቾች አስፈላጊው የሕግ ከለላ ይሰጥ ብሏል፡፡

- Advertisement -

በአማራ ክልል ግጭት ከተፈጠረ ወዲህ ጋዜጠኞችን ጨምሮ በርካታ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ለእስር መዳረጋቸውን የገለጸው ማዕከሉ፣ ጉዳያቸውን ሲከታተልና ፍትሕ እንዲያገኙ ድምፁን ሲያሰማ የቆየ ቢሆንም ያደረጋቸው ውትወታዎችና ምክረ ሐሳቦች ምላሽ አለማግኘታቸውን አስታውቋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ መንግሥት በወሰደው ዕርምጃ ጋዜጠኞችን ጨምሮ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ እንዲሁም በርካታ ቁጥር ያላቸው ግለሰቦች ለጅምላ እስር መዳረጋቸውን አስታውሷል፡፡

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ለእስር መዳረግ የለባቸውም ብሎ ቢያምንም፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የስድስት ወራት ጊዜ ገደብ ሲያልቅ ግን በነፃ ይፈታሉ የሚል ተስፋ እንደነበረው በመግለጫው አስታውቋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንደገና ለአራት ወራት መራዘሙ እስረኞቹ እጅግ አስቸጋሪ በሆነው የእስር ሁኔታ ውስጥ እንዲቆዩ፣ ፍትሕ የሚያገኙበት ዕድልም የጠበበ እንዲሆን ስለማድረጉ በመግለጫው አትቷል፡፡

በእስር ላይ የሚገኙ ግለሰቦች በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ በተደነገገው መሠረት በሚኖሩበት አካባቢ የመታሰር፣ በቤተሰቦችና በሕግ አማካሪዎቻቸው የመጎብኘት መብቶቻቸው ባለመከበራቸው ለከፋ እንግልትና ለተለያዩ የመብት ጥሰቶች መዳረጋቸውን በክትትሉ ማረጋገጡን ማዕከሉ ገልጿል፡፡

በተጨማሪም ፍርድ ቤት የመቅረብ መብታቸው በመጣሱ፣ በፍርድ ሒደት የማለፍና በነፃ ችሎት ተዳኝቶ ፍትሕ የማግኘት መብቶቻቸውንም እንዲያጡ ተደርገዋል ብሏል። አክሎም ታሳሪዎቹ በእስር የሚገኙበት እጅግ አስቸጋሪ ሥፍራ በጤናቸው ላይ እያደረሰባቸው ካለው ከፍተኛ ጉዳት ባሻገር፣ እጅግ ከፍተኛ ለሆነ የሥነ ልቦና ጫና እንዳጋለጣቸው ከቤተሰቦቻቸው ባገኘው መረጃ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች አገሮች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚያወጡበት ጊዜ አዋጁ ተመጣጣኝነት፣ ሕጋዊነት፣ ቅቡልነትና አስፈላጊነት መርሆችን የተከተለ መሆን እንዳለበት መደንገጉን የገለጸው ማዕከሉ በልዩ ሁኔታ የተጋረጠውን ችግር ብቻ የሚፈታ፣ የሕግ መሠረት ያለው፣ ግልጽነት የሚታይበት፣ ተጠያቂነትን ያረጋገጠና ገደቦች በጥንቃቄና በጠባቡ የተተረጎሙ መሆን እንዳለባቸው አስታወሷል፡፡

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከእነዚህ ዓለም አቀፍ የሥነ ሥርዓት መርሆች አንፃር ሲገመገም ብዙ ጉድለቶች የሚታዩበትና ለሕግ አስፈጻሚው አካል ያልተገደበ ሥልጣን በመስጠት፣ ተመጣጣኝ ባልሆነ መንገድ ጋዜጠኞችን ጨምሮ በሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ላይ ያልተገባና የጅምላ እስር እንዲደረግ ከለላ እየሰጠ ስለመሆኑ አብራርቷል፡፡

የካቲት 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዋሽ እስር ቤት በደረሰው የአውሎ ንፋስ አደጋ የመመገቢያ አዳራሹ ላይ ጉዳት መድረሱን     የጠቀሰው የማዕከሉ መግለጫ፣ ይህ አስከፊ አደጋ በተጎጂዎች ላይ ሊደርስ የቻለው በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በሕግ ጥላ ሥር ለዋሉ ሰዎች መደረግ የሚገባቸው መሠረታዊ ጥበቃዎችና ጥንቃቄዎች ስላልተሟሉ ነው ብሏል፡፡ አክሎም በመደበኛ እስር ቤትነት የማይታወቅ ሥፍራ በመሆኑ ምክንያት ነው ሲል ማዕከሉ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...