Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜና‹‹በአፍሪካ ኅብረት ግቢ ውስጥ ለተፈጠሩ ክስተቶች ኢትዮጵያ ልትወቀስ አይገባም›› የውጭ ጉዳይ...

‹‹በአፍሪካ ኅብረት ግቢ ውስጥ ለተፈጠሩ ክስተቶች ኢትዮጵያ ልትወቀስ አይገባም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ቀን:

ከ37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ጋር በተያያዘ ከሚነሱ ቅሬታዎች ጋር በተገናኘ በኅብረቱ ቅጥር ግቢና አዳራሽ ውስጥ በተፈጠሩ ማናቸውም ክስተቶች መወቀስ ያለበት የአፍሪካ ኅብረት እንጂ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት አይደለም ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ከየካቲት 9 እስከ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. በኅብረቱ ጉባዔ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ከገቡ ተሳታፊዎች፣ በዴሞክራቲክ ኮንጎ ልዑካንና በሌላ ተሳታፊ አገር ልዑክ ልዑካን መካከል በኅብረቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ አለመግባባት ተፈጥሮ እንደነበር ሲዘገብ ነበር፡፡ በተመሳሳይ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ፣ ‹‹ወደ ስብሰባው እንዳልገባ የመከልከል ሙከራ ተደርጎብኛል፣ ኢትዮጵያ አላከበረችኝም›› የሚል ወቀሳ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ ፕሬዚዳንቱ የኅብረቱ ጽሕፈት ቤት ከአዲስ አበባ እንዲነሳ ቅሰቀሳ ማደረጋቸው አይዘነጋም፡፡

ይሁን አንጂ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በሰጠው መግለጫ፣ እንደ አስተናጋጅ የሁሉንም አገሮችና መንግሥታት መሪዎችን ደኅንነታቸውን የመጠበቅ ኃላፊነት ኢትዮጵያ እንዳለበት ጠቅሶ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ልዑካን በመንግሥት የተመደቡላቸውን የፀጥታ አካላት አንቀበልም ማለታቸውን መግለጹ አይዘነጋም፡፡ የሶማሊያ የደኅንነት አባላት የጦር መሣሪያ ታጥቀው ወደ አፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ለመግባት ሲሞክሩ፣ በኅብረቱ የፀጥታ አካላት መከልከላቸውንም አክሎ ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ እ.ኤ.አ. ጥር 1 ቀን 2024 የተፈራረሙትን የመግባቢያ ስምምነት የኢትዮጵያ መንግሥት ውድቅ እንዲያደርገው፣ የሶማሊያ መንግሥት በተደጋጋሚ ጥሪ እያቀረበ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም (ዶ/ር) ከሰሞኑ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከሶማሊያና ከአንዳንድ አገሮች በጉባዔው ላይ ቅሬታዎች መቅረባቸውን አስመልክቶ በጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡

ቃል አቀባዩ በሰጡት ምላሽ የኅብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ከጅምሩ እስከ መጨረሻው እንከን የለሽ ነበር ካሉ በኋላ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሚና እንግዶችን ተቀብሎ የአፍሪካ ኅብረት በር ማድረስ ነው፣ ነገር ግን እንግዶች ወደ ኅብረቱ በርና ቅጥር ግቢ ከደረሱ በኋላ ቀሪው ጉዳይ የኅብረቱ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የአፍሪካ ኅብረት ግቢ ውስጥ ያለ መስተንግዶ የአፍሪካ ኅብረት ነው፣ የእኛ ኃላፊነት እስከ በር ማድረስ ነው፡፡ በሩ ላይ ካደረስን በኋላ ያለው የአፍሪካ ኅብረት ነው፣ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያያዝ አይደለም፡፡ የኅብረቱ መቀመጫ ኢትዮጵያ ስለሆነች ብቻ ጉዳዩ የኢትዮጵያ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹በመሆኑም ከግቢው ጀምሮ ያለው አሠራር የአፍሪካ ኅብረት ጉዳይ እንጂ የኢትዮጵያ ባለመሆኑ፣ በኅብረቱ ጉባዔ ላይ ለነበሩ ክፍተቶች ምላሽ መስጠት ያለበት ኅብረቱ ነው፡፡ ነገር ግን በአጠቃላይ የነበረው ሒደት ይገመገማል፤›› ሲሉ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡

‹‹ለኅብረቱ የመሪዎች ጉባዔ የመጡ እንግዶች ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ የሚገባቸውንና የተመቸ አቀባበል አድርገናል፤›› ያሉት መለስ (ዶ/ር)፣ በብዙ ዓለም አቀፍ መድረኮች በሚኒስትር ደረጃ አቀባበል የተለመደ ባይሆንም ኢትዮጵያ ለዲፕሎማሲ ስትል እንዳደረገችው አስረድተዋል፡፡

‹‹እኛም ተጋብዘን በምንሄድባቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች ለምሳሌ ኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባዔ ጭምር የኤምባሲ ሰውና አንድ የፕሮቶኮል ኦፊሰር አቀባበል እንደሚያደርጉ ይታወቃል፤›› ብለው፣ በተመሳሳይ በቅርቡ በኡጋንዳ በተካሄደው የገለልተኛ አገሮች ንቅናቄ፣ እንዲሁም ከዚያ ቀድሞም በቡድን 77 ጉባዔ የነበሩት አቀባበሎች በእንግሊዝኛ (low key) ይባላሉ ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በወታደራዊ የሙዚቃ ባንድ የታጀበ በቂ መስተንግዶ ማድረጓን የተናገሩት ቃል አቀባዩ፣ ይህ የዲፕሎማሲ ወግ በመሆኑ ለሁሉም አገር እኩልና ተመሳሳይ መስተንግዶ ተደርጓል በማለት አብራርተዋል፡፡

‹‹የውጭ ግንኙነት እንቅስቃሴያችን ዳገቱን ወጥቶ ከፍ ብሎ መታየት ጀምሯል፤›› ያሉት ቃል አቀባዩ፣ ለኅብረቱ ስብሰባ የመጡት ከብራዚል ፕሬዚዳንት ሉላ ዳሲልቫና ከፖርቹጋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር የነበሩ የጎንዮሽ ስብሰባዎች የዚህ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያና በኬንያ መካከል ያለው ግንኙነት ውድድር ሳይሆን ትብብር ነው ያሉት መለስ (ዶ/ር)፣ ከሰሞኑ በበርካታ ጉዳዮች ማለትም በቱሪዝም፣ በባህልና ስፖርት፣ በዓሳ ልማት፣ በፔትሮሊየም በተለይም ሊዘረጋ በታሰበው የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመርና በኃይል ማመንጫ ሁለቱ አገሮች ስምምነት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡

በተያዘው ሳምንት በኬንያ በሚደረገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ስብስባ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከኬንያ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...