Tuesday, April 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቡና ግብይት ሰንሰለት በክፍያ ችግር መዘግየት ምክንያት መስተጓጎሉ ተነገረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከቡና አምራች አርሶ አደሮች ጀምሮ እስከ ኤክስፖርተሮች ድረስ ያለው የቡና የግብይት ሰንሰለት በክፍያ ችግር መዘግየት ምክንያት እየተስተጓጉለ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማኅበር አስታወቀ፡፡

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ሁሴን አምቦ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት የቡና አልሚዎች፣ አርሶ አደሮችና መጠነኛ ኢንዱስትሪ ያላቸው አቅራቢዎች ባንኮች ብድር ስለማይሰጧቸው ችግር ውስጥ ወድቀዋል፡፡

የቡና ግብይት ሰንሰለት በክፍያ ችግር መዘግየት ምክንያት መስተጓጎሉ ተነገረ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማኅበር ፕሬዚዳንት
ሁሴን አምቦ (ዶ/ር)

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሁሉም ባንኮች ብድር የሚሰጡት ታች ላሉ አርሶ አደሮች ሳይሆን፣ ለኤክስፖርተሮችና ለትልልቅ አቅራቢዎች ስለሆነ የግብይት ሰንሰለቱ ሊጎዳ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

አብዛኛውን ጊዜ የቡናን የጥራት ደብዛ የሚያጠፉት አርሶ አደሮች ናቸው ተብሎ እንደሚታሰብ፣ ነገር ግን ዋናው ችግር ያለው አቅራቢዎችና ኤክስፖርተሮች ዘንድ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡

በተለይ የቡና አምራች አርሶ አደሮች የቡና ምርቶቻቸውን ለቅመው ለአቅራቢዎች በብድር መልክ ቢያቀርቡላቸውም፣ አቅራቢዎቹ ክፍያውን በአግባቡ እንደማይፈጽሙና በርካታ አርሶ አደሮችም ችግሩን ታሳቢ በማድረግ ወደ ክስ እያመሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

መንግሥት አልሚዎችና አርሶ አደሮች ቀጥታ ብድር የሚያገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ኤክስፖርተሮችም ከአቅራቢዎች በብድር የቡና ምርት ከወሰዱ በኋላ ከባንኮች ብድር አላገኘንም፣ በዓለም ገበያ ምክንያት የቡና በመውደቁ መሸጥ አልቻልንም በሚል ተቀባይነት የሌለው ምክንያት ለአቅራቢዎች ክፍያ እንደማይከፍሏቸው አብራርተዋል፡፡

አቅራቢዎች ከአርሶ አደሮች ቡና ሲረከቡ በመረጃ በተደገፈ መንገድ ስላልሆነ፣ አርሶ አደሮች ፍርድ ቤት ቢሄዱም ተገቢውን ፍርድ እንደማያገኙ ተናግረዋል፡፡

በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን፣ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞንና በምዕራብ አርሲ የሚገኙ አርሶ አደሮች በዚህ ችግር ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ማጣታቸውን፣ የዘንድሮ የቡና ምርታቸው ለመልቀም ምንም ዓይነት መንቀሳቀሻ ገንዘብ ማጣታቸውን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

በተለይ ኤክስፖርተሮች ከአቅራቢዎች በብድር መልክ ቡና ከወሰዱ በኋላ፣ ክፍያ እንደማይፈጽሙና በዚህ ሳቢያ በርካታ አቅራቢዎች ከንግድ ዘርፉ እየወጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አቅራቢዎችና ኤክስፖርተሮች በቢን ካርድ ግብይት በመፈጸም ስምምነት ላይ እንደሚደርሱ ጠቅሰው፣ የፈጸሙት ግብይት ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ስለሆነ እንዲህ ዓይነት ችግር ሊፈጠር ችሏል ብለዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት ማኅበሩ ከቡናና ሻይ ባለሥልጣን ጋር በመሆን ከኤክስፖርተሮችና ከአቅራቢዎች ጋር ውይይት ማድረጉን ገልጸው፣ ችግሩ የአገር በመሆኑ ዘርፉ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ወድቋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኤክስፖርተሮች ከአቅራቢዎች ቡና ገዝተው ገንዘብ አልከፈሉም የሚል ጥያቄ ከማንም እንዳልቀረበላቸው፣ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛት ወርቁ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ቡና አቅራቢዎች ለኤክስፖርተሮች ቡና ሰጥተው ገንዘብ አልተቀበሉም መባሉን መስማታቸውን የተናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ነገር ግን አርሶ አደሮች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሳይከፈላቸው ቀርቷል የሚለው ከእውነት የራቀ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት ቡና የሚገዛ ኤክስፖርተር ቅድሚያ ገንዘብ ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ ማስገባት እንደሚኖርበት፣ በአሁኑ ወቅት ግን ሁለቱ የዘርፉ ተዋናዮች ‹‹ቨርቲካል ኢንተግሬሽን›› በተባለ ስምምነት ተፈራርመው የሚገበያዩ መሆኑናቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ቨርቲካል ኢንተግሬሽን›› ጥርት ያለ ባለመሆኑና ሕጉን የሚያስፈጽም አካል የላላ በመሆኑ የፈጠረው ችግር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው የብድር መጠን ገደብ በርካታ ኤክስፖርተሮች የሚፈለገውን ያህል ገንዘብ እንዳያገኙ እንዳደረጋቸው ጠቅሰው፣ ይህም የዋጋ መረጋጋት መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡

የቡና አርሶ አደሮች፣ አቅራቢዎች፣ እንዲሁም ኤክስፖርተሮች ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ እንዴት ነው የሚለውን በተመለከተ ባንኮችን በስልክ ለማነጋገር ጥረት ቢደረግም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች