Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ቱግ ቱግ!

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ለመታደም የመጡ እንግዶችን ሸኝተን ከፒያሳ ወደ ቦሌ ልንጓዝ ነው። ተዘጋግቶ የሰነበተው ጎዳና በእንጀራ ፈላጊዎች ተጨናንቋል። አንዳንዱ በመንገድ መዘጋጋት አቁሞት የነበረውን ሥራ እንደ አዲስ ለመጀመር ይጣደፋል። አፍሪካውያን ወገኖቻችን በዓመት አንዴ በሚያጨናንቋት አዲስ አበባ ተገቶ የነበረው እንቅስቃሴ ከቆመበት ሊቀጥል እየተውተረተረ ነው። ለአገር ክብር፣ ፍቅርና ዕድገት ሲባል የተጠየቀውን ለማድረግ የማያመነታው የከተማችን ነዋሪ፣ እንግዶቹን ሸኝቶ ላቡን ጠብ አድርጎ የሚጎርሰውን እንጀራ ፍለጋ ሲሰማራ ወጉም በዚያው ልክ መቀጠል ይጀምራል፡፡ በሰው ላብና ዕንባ የሚነግዱም ትወናቸውን ካቆሙበት ለመቀጠል ጥድፊያ ውስጥ እንዳሉ ይታመናል፡፡ ጎዳናችን ይህንን ሁሉ እየታዘበ እንደ እምነታችንና ፍላጎታችን ያለ ገደብ ያስተናግደናል። እርግጥ ነው ገደብ የበዛባቸው በርካታ ነገሮች ቢኖሩም, ጎዳናው ግን ሁላችንንም ያለ አድልኦ ማስተናገድ መቻሉ ተስፋ ያጭራል፡፡ ያለ ተስፋ ደግሞ ሕይወት ይጎመዝዛል፡፡ እንዲያ ነው!

ከረጅም ጥበቃ በኋላ የተገኘው ታክሲ ላይ  በተራ ገብተን ተሰይመናል፡፡ ገብተን ከመቀመጣችን አንዱ ወጣት፣ ‹‹የመረጃ እጥረት የሚሉት ነገር ታክሲ ተራ ገባ እንዴ?›› ቢል፣ ‹‹ከላይ ከተጀመረ ወደ ታች  መውረዱ መቼ ሊከብድ?›› ሲል አዋዝቶ መሀል መቀመጫ ላይ የተቀመጠ ጎልማሳ መለሰ። ‹‹ሰው ምን እንደሚታየው እንጃለት ታክሲ ሲሳፈር የአሜሪካን አፈር የረገጠ ይመስለዋል እኮ…›› ይለዋል ሌላ ጎልማሳ አብሮት ላለው ጓደኛው። ‹‹የዘንድሮዋን አሜሪካ እንዲህ እንደ ዋዛ መርገጥ አለ ብለህ ነው? ትራምፕ ሊመረጥ ነው እየተባለ ነው እኮ…›› ሲለው፣ ‹‹ትራምፕን ለአሜሪካውያን ተወውና የአገርህን ሰው አትታዘብም? ታክሲ ውስጥ በነፃነት እንዴት እንደሚነጋገር?›› በአግራሞት እያየ ጠየቀው። ‹‹መብቱ ወረቀት ላይ ብቻ ነው ቢባልም የትም ይሠራል። ይልቅ የሚገርመኝ ሰው ታክሲ ሲሳፈር የሚያመጣው የንግግር ድፍረት ነው…›› እያለው ወሬያቸውን ቀጠሉ። አዳማጩ ጆሮውን አንቅቷል። የሚጥለውን እየጣለ የመረጠውን የሚለቅመውን ልቦና ይቁጠረው። አላምጦ መብላትና መስማት ሕመሙ ሲከብደን አላውቀው ብለናል። አዳሜ ሳያላምጥ ሲውጥ ከነገር እስከ እንጀራ እያነቀው አላሳዝን ማለት ጀምሮላችኋል። አለመተዛዘን ለካ እንዲህ ቅርብ ነው እንበል ይሆን!

‹‹በዚህ ኑሮ በስንት መከራ የሚገኝ እንጀራ ብቻ ሳይሆን ነገር እያነቀን ስንባክን ጉድም አይደል? ብክነትና ብክለት ምነው ጎዳናውን ሞላው?›› ሲል እንሰማለን ከኋላ ጥጉን ይዞ የተቀመጠ ጎልማሳ። ‹‹መባከን የጎዳናው አንዱ ምልክት ነው ሲባል ስትሰሙ፣ በሰላምና በዴሞክራሲ ዕጦት ደግሞ የብዙ ሰው አቅምና ዕድሜ ሲባክን አይታያችሁም?›› ትላለች ከጎኔ የተቀመጠች ባለ ጉዳይ ወይዘሮ። ‹‹እኛ ልክ እንደ  ፖለቲከኞች መስሚያ የለንም…›› ይላል ወያላው እያሾፈ። ‹‹አንተን ማን ጠየቀህ?›› ትላለች ወይዘሮዋ። ‹‹እንዲህ እኔን በነገር እንደምትወጊው በቀደም እዚህ አዲስ አበባ በስማችን ጉባዔ ተሰይመው ሲወስኑልን የነበሩትን የአፍሪካ መሪዎች ተንኮስ ብታደርጊ ኖሮ መልካም ነበረ፣ ምን ያደርጋል በነበር ቀረ እንጂ…›› እያለ ሲያሾፍ ሰማነው፡፡ ወይዘሮዋም ፈገግ እያለች፣ ‹‹አንተ አነካኪ እዚያ ምን አደረሰህ እዚሁ ወረዳና ክፍለ ከተማ ያሉትን የመተንኮስ መብት ቢኖረን እኮ ጉዳያችን በአጭሩ ያልቅ ነበር፡፡ አሁንማ በዋትስአፕ ነው የጉቦ ፕሮፖዛል የሚያቀርቡት አሉ…›› ብላ ከት ብላ ስትስቅ የታክሲዋ ተሳፋሪዎች አንድ ላይ በሚባል ሁኔታ ሳቅ በሳቅ ሆኑ፡፡ አንጀታችን እያረረ እንሳቀው እንጂ!

አንድ አዛውንት ከሾፌሩ ጎን ተቀምጠው እስከ ኋለኛው መቀመጫ ድረስ በሚሰማ ሳቃቸውና ድምፃቸው ጋቢና ከተቀመጡት ተሳፈሪዎች ጋር ጨዋታ ጀምረዋል። ‹‹አቤት ዘንድሮ ሁሉንም ነገር እኮ እንደ አዲስ ስታደርጉት ታስቃላችሁ። እዚህ አገር ጉቦ ማለት ልክ እንደ ጥሬ ሥጋና ጠጅ ከትውልድ ወደ ትውልድ ስንቀባበለው የኖርነው ቅርሳችን ነው፡፡ ይህንን ቅርሳችንን ይፍረስ እንዳትሉ ብቻ…›› እያሉ ስቀው ድንገት ደግሞ ኮስተር ብለው ጉዳዩን ያነሳውን ጎልማሳ አስተዋሉት። ፊታቸውን እንዴት እንዴት እንደሚያደርጉት እያየን በቀልዳቸው መገረም ከመጀመራችን፣ ‹‹አንተ ግን ለአገሩ አዲስ ነህ እንዴ?›› አሉት ልክ እንደሚያውቁት ሁሉ። ‹‹ፋዘር እኔ ለአገሩ ቤተኛ ነኝ…›› ሲላቸው፣ ‹‹ወይ ጉድ ይህች ይህች መቼ ትጠፋናለች? ለማንኛውም እዚህ አገር ድሮ ጉቦ ሙክት፣ ቅቤ፣ ማር፣ እህልና መሰል ነገሮች ይሰጡ ነበር። ቀጥሎ ደግሞ ብር ሸጎጥ ማድረግ ተጀመረ፡፡ ከዚያም ቼክ መጻፍ ቀጠለ፡፡ አሁን ደግሞ ዋትስምንትስ ባልከው ተነጋግረህ አካውንቱ ውስጥ ትዶልለታለህ፡፡ ልብ በል እንግዲህ፣ ጉቦ መስጠትም ሆነ መቀበል በሕግ የተከለከለ ወንጀል ነው፡፡ ሕጉን የሚያወጣው፣ የሚተረጉመውም ሆነ የሚያስፈጽመው ከላይ እስከ ታች በዚህ መንገድ የሚጓዝ ቢሆን ኖሮ ጉቦ አልቆለት ነበር፡፡ ነገር ግን ሊሆን አልቻለም…›› ብለው አሁንም ለብቻቸው ሳቁ። ቆዩና ድምፃቸውን ቀነስ አድርገው በሹክሹክታ አንድ ወሬ አውርተው ሳቅ በሳቅ አደረጓቸው። እኛም ሳቅ አምሮን ባልሰማነው ጉዳይ ፈገግ አልን። ወይ የስበት ሕግ!

ሁለት ተሳታፊዎች ወርደው አራት ሰዎች በምትካቸው ተጫኑ። ሾፌሩ በመስኮቱ አሻግሮ በተቃራኒ አቅጣጫ የሚመጣ ባለታክሲ ወዳጁን በመጣበት መንገድ ትራፊክ ፖሊስ መኖር አለመኖሩን ይጠይቀዋል። ‹‹የለም!›› ብሎ ይመልሳል ያኛው። ‹‹ጫን በደንብ…›› ይለዋል ሾፌሩ ወያላውን። ‹‹ለማን አቤት ይባላል? ቢባልስ እስካሁን ያልነው አይበቃም ነበር?›› ይላል ጎልማሳው። አንዲት ጠይም ቆንጆ በበኩሏ፣ ‹‹ሹማምንቱ እንኳን ተነግሯቸው ላያቸው ላይ አስተዳደር ቢገነባባቸውም አይነቁ…›› ትላለች፣ የሚስቅ ይስቃል። ‹‹ኧረ አሁንም ግምገማ ላይ ነን እህት…›› ይላታል ሌላው። ‹‹ተስፋ መቁረጥ የለም…›› ብሎ አንድ ድምፅ ሲጮህ ሁላችንም ዞረን አየነው። ሙሉ ልብስ ነው የለበሰው። በእጁ የላፕቶፕ ቦርሳ ይዟል። ‹‹በሚቀጥለው ምርጫ እኔን ከመረጣችሁኝ ችግራችሁን ሁሉ ገደል ነው የምሰደው…›› ብሎ ቅስቀሳውን ጀመረ። ‹‹እሺ ትራምፕ ለመሆኑ ለሚቀጥለው ምርጫ ተዘጋጅተሃል ወይስ እንደ ስመ ዴሞክራቶች ወይ በምርጫ ካልሆነም በዱላ እያልክ ይሆን…›› አንዱ አላጋጭ ነገር ወጋ ያደርጋል። ሰውዬው ወዲያው ለመጪው ምርጫ ዕጩ የግል ተወዳዳሪ ለመሆን ማሰቡን ነገረን። ‹‹ለመሆኑ…›› አለው አንድ ተሳፋሪ፣ ‹‹… እንዴት ብለህ ነው የታክሲ ሠልፍን ብሎም ዕጦትን እስከነ አካቴው ልታስረሳን የምትችለው? መቼም እንደ ትራምፕ ሠልፈኛው እንዳይታይ ግንብ እገነባለሁ እንደማትለን ተስፋ አደርጋለሁ…›› ሲለው ሙሉ ፈገግታ ፊቱን ወርሶት፣ ‹‹ይኼማ ቀላል ነው፣ አያችሁ ብዙዎቻችን ከእንቅስቃሴ ጋር ተቆራርጠናል። ጠንካራና ጤናማ ዜጋ ለአንድ አገር ህልውና ወሳኝ ነው። ጠንካራና ጤነኛ ኅብረተሰብ የአገሩን ዳር ድንበር  ከማስከበር አልፎ በጥሩ ሁኔታ ሳይደክመው እየሠራ ጥሩ ግብር ከፋይ ይሆናል። ስለዚህ የታክሲ ችግርን መቅረፍ የሚቻለው በእግር ለመሄድ ስንወስን ነው። ጤናችሁንና ገንዘባችሁን ገና በብዙ ጉዳዮች ዙሪያ ስለማተርፍላችሁ ግድ የለም እኔን ምረጡ፣ አመሠግናለሁ…›› ሲል ታክሲዋ ደም በለበሱ ዓይኖች ንዴት በሚያቁነጠንጣቸው ተሳፋሪዎች ተሞላች። ‹‹አይ ምርጫና አልጫ..›› የሚሉት አዛውንቱ ነበሩ። እውነታቸውን ነው!  

ወደ መዳረሻችን ተጠግተናል። በኅብረቱ የመሪዎች መደበኛ ጉባዔ ማግሥት ቦሌ ሞቅ ሞቅ ብላለች። ይኼን ዓይቶ አንዱ፣ ‹‹ምንድነው እንዲህ ሞቅታው? አሜሪካኖች ቦሌን ወደ ራሳቸው ግዛትነት ጠቀለሏት እንዴ?›› አለ። ‹‹ውይ እንዲያው የአሜሪካን ስም የት አገር ይሆን የማልሰማው፣ ምንአለበት ብንተወው። ከአሜሪካኖቹ ዕብደት እኮ የእናንተ ማዳነቅ ባሰን?›› ትላለች ወይዘሮዋ። ‹‹ኧረ እባክሽ ሴትዮ ቀስ በይ። እዚህ ማን ነው የአሜሪካ ጉዳይ አሳስቦት የነገር ድር ያደራው? እኛ እኮ እያሳሰበን ያለው የአገራችን፣ ባስ ሲልም የአፍሪካ ጉዳይ ነው፡፡ አሁንስ ገባሽ እመቤት?›› ይላል ከኋላ ጥግ የተቀመጠው። ‹‹እባካችሁ የገዛ ድስታችንን እሳት ላይ ጥደን እያረረ የሰው አናማስል…›› ይላሉ አዛውንቱ። ‹‹አይዞን ፋዘር አሜሪካን ሳያዩማ አይሞቱም…›› ቢላቸው ወያላው፣ ‹‹ወይድ አንተ ሟርተኛ፣ ሞቴን እርግጠኛ ሆነህ ለቪዛው የምታፅናናኝ የት አውቀኸኝ ነው?›› ብለው ተቆጡ። ‹‹ወይ ስምንተኛው ሺሕ፣ ልጅ አዋቂው እንዲህ ቱግ ቱግ እያለ ዕውን ከዚህ የተረፈ የሰላም ዘመን ይቀረን ይሆን?›› ወይዘሮዋን ሐዘን ዋጣት። አዛውንቱ ለማረጋጋት፣ ‹‹አይዞሽ ወይዘሮ፣ ምንም ቢሆን እኮ እኛ ለአፍሪካ፣ አፍሪካ ደግሞ ለእኛ ሆነን ስለኖርን የአሜሪካ ነገር ያን ያህል አያሳስበንም፡፡ ቱግ ቱግ የሚያደርገኝ የድሮ ወኔ ነው…›› ብለው ነገሩን አረገቡት፡፡ እኛም ቦሌ ደርሰን በሰላም ተሰነባበትን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት