Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርቢሮአቸውን ዘግተው በተገልጋዮች ላይ የቅርብ ሩቅ የሆኑ ሹማምንት ጉዳይ ያሳስባል

ቢሮአቸውን ዘግተው በተገልጋዮች ላይ የቅርብ ሩቅ የሆኑ ሹማምንት ጉዳይ ያሳስባል

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

 በአሁኑ ወቅት ብቻ ሳይሆን ትናንትም ቢሆን የተመረጡም ሆኑ የተሾሙ ባለሥልጣኖች ወደ ታች እየወረዱ ከሕዝብ ጋር የመገናኘት፣ ሕዝብን የማዳመጥና ዕንባ የማበስ ባህል ማዳበር/ማጠናከር ‹‹አለባቸው›› የሚለውን አቋም የሚያራምዱ ሰዎች በርካታ ናቸው፡፡ ግን እምብዛም ሰሚ ሲያገኙ አይታዩም፡፡

እንዲያውም የተገኘን ሥልጣን ራስንና ቡድንን ለማበልፀግ ብሔራዊ ጥቅምን ሳይሆን፣ የግል ክብርን ለማሳየት፣ ዕድገትና ብልፅግና ሳይሆን በሸፋፋ አስተዳደር ኢፍትሐዊነትን ለማንበር፣ ሕዝብን በታማኝነት ለማገልገል ሳይሆን ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለማስፈን የሚሯሯጡበት ሲሆን እየታየ ነው የሚሉ በርክተዋል፡፡ ይህ ከሆነማ የኢሕአዴግ ሰዎችስ ከዚህ በላይ ምን አደረጉና ይወቀሳሉ ማለት እንዳይጀመር ያሳስባል፡፡

- Advertisement -

እውነት ለመናገር ኢትዮጵያዊያንም ብንሆን፣ የዓለምን ሥልጣኔንና የኑሮ መሻሻል ብቻ ሳሆን የለውጥ ጭላንጭል ዓይተናልና በመካከላችን የሚገኝ አብሮን የሚበላ፣ አብሮን የሚጠጣ፣ በመከራና በደስታችን ጊዜ ከጎናችን የሚገኝ ‹‹ሰው ሰው የሚሸት›› መሪ እንፈልጋለን፡፡ እሱ ሲፈልገን ብቻ ሳይሆን እኛም ስንፈልገው የሚገኝልን አለቃና መሪ ብናገኝ አንጠላም፡፡ በአኗኗሩና በሁኔታው ሠራተኛውን መምሰል ቢቀር መቀራረብ የከበደው ተኮፋሽም፣ ለዘመናት የምናውቀው የእቡይነት መገለጫ ነውና አንሻውም፡፡

አሁን አሁን ሁሉም ሊያስብል በሚያስችል ሁኔታ አብዛኞቹ ሹመኞቻችን ግን ቢሮአቸውን ቆልፈው ስልካቸውን አጥፍተው እንደ ድመት አድፍጠው ‹‹ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጪ ናቸው›› እያሰኙ በመስመር ስልካቸውም እንዳይገኙ ለጸሐፊያቸው አስጠንቅቀው፣ በዙሪያቸው ያለውን ዓለም ረስተውና እነሱም በአካባቢያቸው ካሉ አገልግሎት ፈላጊዎች የቁምነገር ማኅደር ውስጥ ተፍቀውና ተረስተው ቀን እየቆጠሩ ደመወዝ የሚጠብቁ ዓይነቶት ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሰላም ዕጦቱና የደኅንነት ሥጋቱም ያገዛቸው ይመስላል፡፡

አንዳንዶቹ ደግሞ የበለጠ በራቸውን መክፈት ይፈራሉ፣ ከተገልጋዩ ኅብረተሰብና ደንበኞች ጋር ብቻ ሳይሆን ከሠራተኞቻቸው ጋርም ፊት ለፊት ለመገናኘት ልብ የላቸውም፣ የራስ መተማመን አይታይባቸውም፡፡ ቢሮአቸውን ቆልፈውና መሽገው የሚውሉ ሰዎች ከፍተኛ የብቃት ማነስ ያለባቸው ናቸው፡፡ የሚመሩበትን ሥርዓት፣ ዓላማና ግብ ያልተረዱ ወይም ያላመኑ፣ ወይም ከውስጥ ሆነው ሥርዓቱን እንደ ጥንጣን አብሰክስከው ለመጣል የተሠለፉ ነቀዞችም ይገኙበት ይመስለኛል፡፡

እንዲህ ያሉ ሰዎች ሕዝብና መንግሥትን የሚያቃቅሩ አልምጦች ናቸው፡፡ ወይ በቂ የትምህርት ዝግጅት የላቸው፣ ወይ በቂ የሥራ ልምድ የላቸው፣ ወይ በችሎታ አወዳዳሪ በሆነ ሥርዓት (ሜሪት ሲስተም) መሠረት ያልተመዘኑና ቅጥሩንም ሆነ የያዙትን ቦታ በዘመድ አዝማድ አልያም በብሔር ኮታ ያገኙ ሰነፎች መሆን አለባቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች የቢሮአቸው በር ሲከፈት የሚያማቸው (Open Door Syndrome) ያለባቸው፣ የባለጉዳይ አቤቱታ ብርድ እንዳይመታቸው ቢሮአቸውን ጥርቅም አድርገው ዘግተው ድምፃቸውን አጥፍተው መዋልን የሚመርጡ ናቸው፡፡

አሁን በብልፅግናውም ወቅት እንደ ትናንቱ ሁሉ ባለጉዳይ በመጣ ቁጥር ‹‹ስብሰባ ላይ ናቸው›› እያሰኙ፣ በሥራ ዘመናቸው ፍራሽ ላይ የሚተኙ በርክተውና ተበራክተው ይገኛሉ (አንዳንዴ የአገር መሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ፕሬዚዳንቷ፣ ከንቲባዎች፣ የክልል ፕሬዚዳንቶችና አፈ ጉባዔዎች እየመሰሉ የመጡትም ለዚሁ ይሆን)፡፡ አብዛኞቹ የሹም ጸሐፊዎች ደግሞ ‹‹ኧረ ባለ ጉዳይ ቆሟል›› ብለው ለመናገር ወኔ የላቸውም፡፡ ባለጉዳይ በመጣ ቁጥር ፊታቸውን ቀጨሞ አስመስለው ‹‹ስብሰባ ላይ ናቸው›› የሚል ነጠላ ዜማ እያሰሙና እንደተጫረ ሲዲ እሱን ሲመላልሱ የሚውሉ የማይነኩ የሹም ዶሮዎች ይመስል ተኮፍሰው የሚኖሩ ‹‹ቀለብተኞች›› ናቸው፡፡

ለውጡ ሥራ ሲጀምር ስብሰባም ገደብ ተደርጎለት ከመደበኛ ሥራ ውጪ የተመደበለት መሆኑ ቢገርም እምብዛም መተግበር አልቻለም፡፡ እንዲያውም ለአንዳንዶች ዋና ሥራቸው ባለጉዳይን በተሰላቸ መንፈስ እያዩ ስለአለቃቸው በስብሰባና በሥራ ብዛት መወጠር እያጋነኑ፣ ቀሪውን ጊዜ የወሬ ከበሮ እየደለቁ በግል ጉዳያቸው ዙሪያ ብቻ ተወጥረው ማሳለፍ እንዲሆን ነው ያደረገው፡፡

እንኳንስ ስለጸሐፊዋ የሥነ ምግባር ጉድለትና ሥራ ፈትነት የሚያመለክትበት ጊዜና ቦታ ቀርቶ፣ የራሱን ጉዳይ የሚተነፍስበት በር ሁሉ የተቆለፈበት ባለጉዳይም አምላኩንና አገሩን እያማረረ ከመቀጠል በቀር አማራጭ ያገኘ አይመስልም፡፡ እናም ለወደፊቱም ቢሆን ሕዝብ እንዳይማረርና በአገሩ ኮርቶና ሠርቶ እንዲኖር ከተፈለገ፣ የሹመኞችን ቢሮ እንዲከፈት ማድረግ ወይም መክፈት ያስፈልጋል፡፡

የቢሮው በር የሚከፈተው ባለጉዳይ እንዲገባበት ብቻ ሳይሆን፣ ሹመኛው ራሱ እየወጣ ወደ ሕዝብ እንዲሄድበት ጭምር ነው፡፡ ባለጉዳይን ወይም ሠራተኛን ቢሮ መጥራትና ‹‹ቢሮዬ ክፍት ነው›› ማለት ጥሩ ቢሆንም፣ የራሱ የጎንዮሽ ችግሮችም አሉት፡፡ አሁን አሁን የትንንሾቹ ግልገል ሹመኞች ቢሮ ጭምር እጅግ ዘመናዊ በሆኑ የቢሮ ቁሳቁሶች የተደራጀ ነው፡፡ በደሃ አገር የማይጠበቀው ቢሮ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ከቢሮው በር አንስቶ ኃላፊው እስከ ተቀመጠበት ቦታ ድረስ ያለው ርቀት ረጅም ነው፡፡

ወለሉ በቀይ (አሁን አሁን ቢጫም እየሆነ ነው) ምንጣፍ ተንቆጥቁጧል፡፡ መሀሉ ላይ ረጅም የስብሰባ ጠረጴዛና በጥቁር ቆዳ የተለበጡ በርካታ ወንበሮች አሉበት፡፡ ሹመኛው ባለሦስት ማዕዘን ሰፊና ትልቅ ጠረጴዛ ጀርባ ተኮፍሶ መቀመጡ የሚጠበቅ ነው፡፡ ከበስተጀርባው ምን የመሰለ ግዙፍ መደርደሪያ በወረቀት ጥራዞችና ፋይል መያዣዎች ተሞልቶ ተገሽሯል፡፡ ሹሙ ከተቀመጠበት በስተቀኝ ኮምፒዩተር መኖር አለበት (ቢሠራበትም ባይሠራበትም)፡፡

አለፍ ሲልም በስተግራው ደግሞ ከላይ ወደ ታች የተንጠለጠለ የማንበቢያ (የራስጌ) መብራት ይገኛል፡፡ ይኼ ቢጫ የቻይና እርሳስ ተቀርፆ ተቀርፆ በጣሳ ተሞልቶ መቀመጥ የግድ ነው (ቢጻፍበትም ባይጻፍበትም)፡፡ የወጪና ገቢ ደብዳቤዎች ማስቀመጫ የሽቦ ትሪ፣ ፖስታ መክፈቻ ቢለዋ፣ ስቴፕለር፣ ሽቦ መንቀያ፣ አጀንዳ፣ ካላንደር፣ የወረቀት ቅርጫት፣ የፕላስቲክ ውኃ፣ የኮት መስቀያ፣ የፌዴራልና የክልል ባንዲራ መኖራቸው የማያጠራጥር ነው፡፡

ፅዳት ሠራተኛዋ አፀዳድታ ስታበቃ “ኤር ፍሬሽነር” ነፍታበት ትወጣለች፡፡ ጸሐፊዋ ትመጣና ደግሞ በተቀባችው ሽቶ ቢሮውን ታጥነዋለች፡፡ ልብ አድርጉ የቢሮው አጠቃላይ ሞገስ የምስኪኑን ባለጉዳይ የመናገር ወኔ ለመስለብ ከበቂ በላይ የሆነ ኃይል አለው፡፡ ከደሃ ጎጆው በአውቶብስ ተጋፍቶ መጥቶ፣ እንዲህ በመሰለ ቢሮ ውስጥ ባለጉዳይ ሲገባ ግራ ይጋባል፣ ትንሽነት ይሰማዋል፣ ይዞት የመጣውን ሐሳብ በተሟላ ሁኔታ ለመግለጽ ጉልበት ያጥረዋል፣ ሊንተበተብ ሁሉ ይችላል፣ ለመውጣት ይቸኩላል፡፡

ጉዳዩን በተገቢው ሁኔታ ሳያስረዳና ተገቢ ምላሽና መፍትሔ ሳያገኝ ባልመጣበት ሁኔታ ይመለሳል፡፡ ‹‹እገሌን አነጋግረው፣ ጸሐፊቱን ጠይቃት፣ እንዲህ ያለ ቁጥር ቢሮ ሄደህ ንገራቸው…›› ተብሎ ይሸነገላል፡፡ ምስኪኑ ባለጉዳይ እሱ በከፈለው ግብር በተደላደለ ቢሮ ውስጥ ባለው ሁኔታ ተንገዳግዶ እግሩን እየጎተተና በተሰበረ ወኔ አንገቱን ደፍቶ እየቆዘመ ይሄዳል፡፡ ይህ ሁኔታ ለበርካታ ጊዜያት ሲሠራበት ቆይቶ ተባብሶ መታየቱ ሊያስቆጭ ይገባል፡፡

ስለዚህ የሹመኞች ቢሮ ክፍት መሆን ያለበት ሹመኛው ራሱ እየወጣ ወደ አገልግሎት ፈላጊው ሕዝብ እንዲሄድበት መሆን አለበት የሚሉ ታላላቅ ጥናታዊ ድርሳናት አሉ፡፡ ሁሉም ጽሑፎች በተከፈተው የቢሮ በር ባለጉዳይ ከሚገባ ይልቅ፣ ወይም የሚገባውን ያህል ሹመኛው እየወጣ ወደ ሕዝቡ እንዲቀርብ የሚሰብኩ ናቸው፡፡ በተለይ አንፃራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ወጥቶ ማየት አለበት፡፡

አመራር ይሁን ባለሙያ የሚያገለግለውን ሕዝብ ችግር መሀሉ ተገኝቶ ማወቅ አለበት፡፡ በተጨባጭ ባየው ነገር ላይ ተመሥርቶ የማስተካከያና የመፍትሔ ዕርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡ የሕዝቡንም ብሶት ይቀንስ ዘንድ ግዴታ አለበት፡፡ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል እንደ መልካም ድልድይ ሆኖ ቅርርብና ትስስር ይፍጠር፡፡ እጁን ኪሱ ከትቶ ከሚሽከረከር ከሕዝብ ጋር ይነጋገር መባልም ይኖርበታል፡፡

እንደምንታዝበው እንዲያውም የደኅንነት ሥጋት ያለባቸው ትልልቆቹ መሪዎች በመስክ ጉብኝት፣ በምርቃትና በሌሎችም ዘዴዎች ወደ ሕዝብ የመቅረብና እየተሠራ ያለውን ነገር ዓይተው ለመረዳት ይሞክራሉ፣ መፍትሔም ይሰጣሉ፡፡ ከታችኛው ማኅበረሰብ ጋር በቂ ባይባልም፣ ከሕዝብ ተወካዮች ጋርም ይነጋገራሉ፡፡ የእኛ ችግር ግን ይኼ አይደለም፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ሕዝብ የተቸገረው ለችግሩ መፍትሔ የመስጠት ኃላፊነት ያለባቸው ትንንሾቹ ሹመኞች የቢሮአቸውን በር ቀርቅረው የቅርብ ሩቅ ስለሆኑበት ነው፡፡

እባካችሁ ቢሮ ማለት እኮ አልቤርጎ ማለት አይደለም (የግድ መዘጋት የለበትም ለማለት ነው)፡፡ መጀመሪያ ነገር የሹመኞች ቢሮ የሚዘጋው ለምንድነው? የቢሮ መዘጋትን ጉዳይ አብዛኞቹ የዘርፉ ምሁራን አይደግፉትም፡፡ ተነሳሽነትን የማይፈጥር ግልጽነት የጎደለው መጥፎ ተግባር ነው እየተባለም ይኮነናል፡፡ ቢሮ ክፍት መሆን አለበት፡፡ በዙሪያው ያሉ ሠራተኞችንና ባለጉዳዮችን ማየት በሚያስችል ሁኔታ በመስታወት የተከፋፈለና ግልጽነት ያለው (ትራንስፓረንት) መሆን አለበት፡፡

የቢሮው ኃላፊ ከባለጉዳዮች ቅርበት ለመጠበቅ (ፕራይቬሲ) ሲል ድምፅ የማያሰማ ግን የሚታይ ቢሮ ካለው በቂ ነው፡፡ የመንግሥት ቢሮዎች የባንኮችን የቢሮ አቀማመጥ (ኦፊስ ሴትአፕ) ሌላው ቀርቶ የሪፖርተር ጋዜጣ ቢሮን በሞዴልነት ቢጠቀሙ ጥሩ ይሆን ነበር፡፡ አንዳንድ የተሻሻሉ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶችም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

አሁን ማለት የተፈለገው ዋናው ነገር ሹመኞቻችን ከመረጣቸውና ደመወዝ ከሚከፍላቸው ሕዝብ ጋር ለመገናኘት የሚያስችል ወኔ የሚያስፈልጋቸው መሆኑ ነው፡፡ ቢሮአቸውንና ልባቸውን ክፍት የማድረግ ወኔ፣ እየወጡ የሕዝቡን ችግሮች የማየት ወኔ፣ ባለጉዳዩ ፊት ለፊት አግኝቶ የመነጋገር ወኔ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ቅንነትና ምላሽ ሰጪነት የሚመጣው ከዚያ በኋላ ነው፡፡

ግልጽነትና ተጠያቂነትን ለማዳበርም ለይስሙላ ሳይሆን ጠንካራ የግብረ መልስ መሣሪያ ለማድረግ የሐሳብ መስጫ ሳጥን አዘጋጅተው ለተገልጋዩ አመቺ በሆነ ሥፍራ ላይም ማስቀመጥ አለባቸው፡፡ የባለጉዳዩ ሐሳብ ቢያንስ በየአሥራ አምስት ቀኑ እየተሰበሰበ በኮምፒዩተር እየተመዘገበና እየተገናዘበ መታየትና ለሥራ ማሻሻያ መዋል አለበት፡፡

የሚመለከታቸው ኃላፊዎችም የባለጉዳዮችን አስተያየት የሚገመግሙበት ስብሰባ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የሕዝብ አስተያየት እጅግ በጣም ጠቃሚ መሆኑን መረዳት ብልህነት ነው፣ ስብሰባ ያስፈልጋል፣ አይብዛ እንጂ፡፡ የሹመኞች መደበቂያ ምሽግና ሰበብ አይሁን እንጂ በወጉ ከተጠቀሙበት ተሰባስቦ ጉዳዮችን ማየት ቢያንስ ክፋት የለውም፡፡

እውነት ለመናገር አሁንም ድረስ ሥጋና ውስኪ ቤት ለሚያጣብቡ ደላሎችና ጉዳይ አስፈጻሚ ነን ባዮች ትልቁን በር የሚከፍተው የመረጃ እጥረት ብቻ ሳይሆን፣ በየደረጃው ያሉ ሹመኞች በሥራቸው ላይ ያለመገኘትና በትጋት መልስ ያለመስጠት ችግር ነው፡፡ ደላላው ባለጉዳዩን ከሚያቀዣብርበት ሰበቦች ግንባር ቀደሙ ኃላፊዎች አይገኙም፣ ነጋ ጠባ ስብሰባ ላይ ናቸው፣ ነጋ ጠባ ግምገማ ነው፡፡ ስለዚህ ሰው በሰው ካልሆነ ጉዳይን ማስፈጸም አይቻልም በማለት ነው፡፡

እኛ ግን እዚያ ውስጥ ሰው ስላለን ጉዳይህን በአጭር ጊዜ እናስፈጽምልሃለን ይሉታል፡፡ ሰነዶችና ማስረጃዎች ከተሟሉ ማንኛውም ጉዳይ በአጭር ጊዜ የሚያልቅ መሆኑን መረጃ የሌለው ባለጉዳይም ያምናቸዋል፡፡ ‹ገንዘቤን ይጭነቀው› ይልና ሥራውን ለደላሎች ይሰጣል፡፡ በነፃና በአጭር ጊዜ ባለጉዳዩ ራሱ ሊያስፈጽመው የሚችለውን ሥራ ለደላሎች አሳልፎ የሚሰጠው ሹመኞች (ኃላፊዎች) ‹‹አይገኙም››/አያናግሩም በሚለው መረጃ ላይ ተመሥርቶ ነው ሊባል ይችላል፡፡

ስለዚህ በደላሎች አማካይነት የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቅረፍ ኃላፊዎች ለተገልጋዩ በቅርብ የሚገኙ መሆን አለባቸው፡፡ ይህ ሲባል ግን የከተማው ከንቲባ በየቀበሌው እየዞረ የፈነዳ ቧንቧ ሲቆጥሩ ይዋሉ ማለት አይደለም፡፡ የሚመለከታቸው ክፍሎች ሥራቸውን ከሠሩ በቂ ነው፡፡ ላይ ድረስ የሚያስኬድ ነገር የለም፡፡ ግልገሎቹ ከሠሩ አውራዎቹ ዘንድ ለመድረስ መቸገር አያስፈልግም፡፡ ትልልቆቹ ሹሞች አስቀድሞ በተያዘ ቀጠሮ ባለጉዳይ በሌለበትና ንፁህ ሆኖ በተዘጋጀ ስብሰባ ወይም ጉብኝት ላይ መገኘት ፋይዳው ትንሽ ነው፡፡

ያልታቀደና ድንገተኛ ጉብኝት፣ ሕዝብ ማነጋገርና ሠራተኛው በሥራው ላይ መኖሩን መጎብኘት፣ የፊት ለፊቱን ብቻ ሳይሆን የጓሮውን ሁኔታ ጭምር የማየት ድፍረት ያስፈልጋል፡፡ ነገሮችን በሪፖርት መስማትና ታች ወርዶ መሬቱ ላይ በተጨባጭ እየተሠራ ያለውን ነገር በግምባር ተገኝቶ ማየት ቢቻል ‹‹እግዜር መሬት ወረደ›› የማለት ያህል ነው፡፡

እውነት ለመናገር ፖለቲካዊ መፍትሔና መተማመን እያገኙ ከሄዱ፣ በርከት ባሉት አካባቢዎች የሚስተዋሉት የፀጥታና የጥበቃ ችግሮችም ይኼን ያህል አሥጊ አይደሉም፡፡ የክፍለ ከተማ ሹም በሥሩ ያሉትን የሥራ ዘርፎችና ተገልጋዮች (ኗሪዎች) ለማየት ቢሄድ የሚፈራበት አንዳችም ምክንያት የለም፡፡ አንዳንዱን ማን አውቆትስ ይነካዋል? ዝም ብሎ ራሱን አግዝፎ ከማየት የተነሳ ራሱ የፈጠረው መሠረተ ቢስ ፍራቻ (ፎቢያ) ካልሆነ በቀር ‹‹ዝንቡን እሽሽ›› የሚል እንደማይኖር ይታወቃል፡፡

ምን ስለሆነ? ወደ ሕዝቡ ስለወረደ፣ በዓይኔ ዓይቼ እወስናለሁ ስላለ ከቶ ማን ሊነካው ይችላል? ኃላፊነቱ ትልቅ ይሁን እንጂ ሹመቱ እኮ ትንሽ ናት፡፡ የፖለቲካ ፍላጎት ባላቸው ኃይሎች የጥቃት ሰለባ የምታደርገው ዓይነት ሥልጣን እንዳልሆነች ይታመናል፡፡ ‹‹እፈራለሁ›› ካለም ቆመጥ ብቻ የያዘ አንድ፣ ሁለት ፖሊስ ይበቃዋል፡፡ ለሕዝብ ክብርና ፍትሐዊ ምልሽ መስጠት ከተቻለ እኮ ማኅበረሰቡ ራሱ ጠባቂ ይሆናል፡፡

ዋናው ነገር ወደ ሕዝብ ለመውረድ ወኔ ያለው ሹም መሆኑ ነው እንጂ፣ እንዲህ ያለውን ኃላፊ ሕዝቡ ራሱ ይጠብቀዋል የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ማንም ተነስቶ ቢተናኮለው ሕዝቡ ዝም አይልም፣ ለሹሙ ይቆምለታል፡፡ በዚህ መንፈስ ያልተቃኙ ሰዎችን ከሕዝቡ ብሶትና ምት (ሪትም) ጋር እንዲቃኙ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ጥቂት የሽውሽው ትምህርትና የአንድ ሰሞን የሥልጠና ሁካታ ላይበቃቸው ይችላል፡፡ ደጋግሞ መቃኘትና ከወገን ጋር መተማመን  ካልተቻለ ብልፅግናም ቢሆን ለዓመታት የሰፈነውን የቢሮክራሲ ልክፍት ሊሻገረው አይችልም፡፡

እውነት ለመናገር ከፌዴራል እስከ ክልሎች በሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎችን የሚያስለቅሱና ብሶቱን እያባባሱ ለአመፅ የሚገፋፉ ባለሥልጣናትን ማስወገድ ሊያስፈልገውም ይችላል፡፡ ከዚያ በፊት ግን በእነሱ እግር የሚተካውን ሰው አስቀድሞ ማዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ የሚመጣውም ያው ከሆነ የተሻለ መፍትሔ ስለማይመጣ ችግሩ ባለበት ሊቀጥል ይችላልና ታጥቦ ጭቃ እንዳይሆን ማሰብና ማሰላሰልም በምልዓተ ሕዝብ ከመወገዝ ያድናል፡፡ እኔ ግን እንደ ባለጉዳይ ያስመረረኝን የቢሮክራሲውን ስላቅ እንደ ትናንቱ አሁንም ደጋግሜ አየሁትና ተቸሁት፡፡

ሰላም!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው nwodaj@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...