Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ግዴታን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን ሥርዓት

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍና የማኅበራዊ ጤና መድኅን ሥርዓቶችን መሠረት አድርጎም ይሠራል፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት በኢመደበኛ ኢኮኖሚ የሚሠሩ ወይም መደበኛ ደመወዝና ገቢ የሌላቸው ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡ ሁለተኛው ማኅበራዊ የጤና መድኅን ግን በመደበኛ ክፍለ ኢኮኖሚ የተሠማሩትን ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥርዓት ነው፡፡ አቶ ዘመድኩን አበበ በኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት የኮሙዩኒኬሽንና ሞቢላይዜሽን ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በጤና መድኅን እንቅስቃሴና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረ ማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ግዴታን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን ሥርዓት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ሪፖርተር፡- በየክልሎች ያለው የጤና መድኅን አገልግሎት እንዴት ይገመገማል?

አቶ ዘመድኩን፡- የጤና መድኅን አገልግሎት ከጥቂቶቹ በስተቀር በአብዛኞቹ ክልሎች ተደራሽ ናቸው፡፡ ከእነሱም መካከል በአማራ ክልል እየታየ ያለው የፀጥታ ችግር እንዳለ ሆኖ፣ ኅብረተሰቡ ጥቅሙን ቀደም አድርጎ በመረዳቱ ከሌሎች ክልሎች በግምባር ቀደምነት የሥርዓቱ 100 በመቶ ያህል ተጠቃሚ ሆኗል ለማለት ይቻላል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ባሉት ወረዳዎች ሙሉ ለሙሉ የጤና መድኅን ሥርዓትን ተደራሽ ለማድረግ እየሠሩ ነው፡፡ በትግራይ ክልል ኅብረተሰቡ ለጤና መድኅን ሥርዓት ተጠቃሚነት ያለው ፍላጎት ከፍተኛ ቢሆንም፣ በምግብ ዕጦትና በተለያዩ በሽታዎች ሳቢያ እየተሰቃየ ይገኛል፡፡ በመሆኑም መቼ? የጤና መድኅን አገልግሎት ምዝገባና ዕድሳት የሚያካሂደው የሚለውን ለማሳየት ከኅብረተሰቡ፣ ከመንግሥትና በተለይም ከጤና ሚኒስቴር ጋር በጋራ ታይቶ የሚወሰን ይሆናል፡፡ ከዚህ በተረፈ በሶማሌ ክልል የጤና መድኅን የተዘረጋው በሦስት ወረዳዎች ውስጥ ብቻ ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ 13 ወረዳዎች ውስጥ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ከሦስት ወረዳዎች በስተቀር በቀሩት ወረዳዎች በፀጥታ ችግር ሳቢያ አልተስፋፉም፡፡ በጋምቤላና በአፋር ክልሎችም የጤና መድኅን በቀጣይ ለማስፋፋት ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ እየተካሄደ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችለው ምዝገባና ዕድሳት መቼ መቼ ነው የሚካሄደው?

አቶ ዘመድኩን፡- በመላ ኢትዮጵያ የጤና መድኅን ምዝገባና ዕድሳት የሚከናወነው በየዓመቱ ከመስከረም 1 ቀን እስከ የካቲት 30 ቀን ባሉት ስድስት ወራት ነው፡፡ እያንዳንዱ ወረዳ ኅብረተሰቡ ገቢ ያገኝባቸዋል ብሎ ያመነባቸውን ሁለት ወራት መርጦ ምዝገባና ዕድሳት እንዲያካሂድ ያደርጋል፡፡ በዚህ መልኩ የሚከናወነው ምዝገባና ዕድሳት የካቲት 30 ቀን መጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡ ታካሚውም ጤና ተቋምም ውል ይፈርማል፡፡ ቅድመ ክፍያ ለጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች በምዝገባና የመክፈል፣ ዕድሳት የተገኘው ገቢና ተጓዳኝ ተግባራትን ያካተተ ሪፖርትም ለማዕከል ይቀርባል፡፡

ሪፖርተር፡- በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች ሳቢያ በተያዙት ወራት ውስጥ ምዝገባና ዕድሳት ላላካሄዱ ወረዳዎች ምን ማካካሻ ይደረግላቸዋል?

አቶ ዘመድኩን፡- የተጠቀሱት ችግሮች ላሉባቸው ወረዳዎች ተጨማሪ አንድ ሳምንት ገፋ ሲል ደግሞ የ15 ቀን ጊዜ ይሰጣቸዋል፡፡ ይህም የሚሆነው የክልሉ መንግሥት ሲያምንበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ሲል በተዘረዘሩት ክልሎች ውስጥ የጤና መድኅን አገልግሎት ከሞላ ጎደል ዝቅተኛ የሆነበት ምክንያቶች ምንድናቸው?

አቶ ዘመድኩን፡- ምክንያቶቹ ብዙ ናቸው፡፡ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል የፀጥትና የአለመረጋጋት፣ ቶሎ ያለመድረስና የትራንስፖርት ችግሮች ይገኙበታል፡፡ የግንዛቤ ማስፋፋትና ሕዝቡን የማሳመን ሥራ በአግባቡ ወይም ጭርሱኑ አለመከናወኑ፣ የጤና ጣቢያ አለመኖርና ቢኖርም እንኳን የሰው ኃይል ወይም የባለሙያ ዕጦት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የጤና መድኅን አባል የሆነ ማንም ሰው ድንገት ቢታመም ምን ዓይነት የሕክምና አገልግሎ ማግኘት ይቻላል?

አቶ ዘመድኩን፡- የጤና መድኅን አገልግሎ አባል የሆኑ ሁሉ ሲታመሙ ወይም የጤና መታወክ ሲደርስባቸው የተመላላሽ፣ የተኝቶ፣ የቀዶ ሕክምና፣ የላቦራቶሪና የመድኃኒት አገልግሎቶችን የማግኘት መብት አላቸው፡፡ የእነዚህ አገልግሎቶች ተቋዳሽ ለመሆን ቀደም ሲል አንድ አባወራ ወይም እማወራ በዓመት 250 ብር፣ ቀስ በቀስ ደግሞ 300 ብር ከዛም ከፍ ሲል 500 ብር ይከፍሉ ነበር፡፡ አሁን ግን በየወረዳው ወይም በየገጠሩ 500 ብር +50፣ እና 950 ብር የሚከፍሉ አሉ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ግን ዓመታዊ ክፍያው 1,500 ብር ሆኗል፡፡ ከዚህ ውስጥም አባወራው 1,000 ብር ሲከፍል መንግሥት ደግሞ 500 ብር ይደጉማል፡፡

ሪፖርተር፡- ክፍያው አልበዛም?

አቶ ዘመድኩን፡- በእርግጥ ክፍያው ከፍ ብሏል፡፡ ይህም የሆነው በተፅዕኖ ወይም ጫና በመፍጠር ሳይሆን፣ በህክምና መገልገያ መሣሪያዎችና በተለያዩ መድኃኒቶች ላይ የታየውን የዋጋ ጭማሪ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ አንድ አባወራ በዓመት 1,000 ብር ከፍሎ እሱም ስድስት/ሰባት የሚሆኑ ቤተሰቦቹ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ምንም የሌላቸው ደሃዎች የሥርዓቱ ተጠቃሚ የሚሆኑት በምን መልኩ ነው?

አቶ ዘመድኩን፡- በነፃ ይታከማሉ፡፡ ወጪውን መንግሥት ይሸፍናል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ እየተካሄደ ያለው የ2016 ዓ.ም. የጤና መድኅን ምዝገባና ዕድሳት እንዴት ይታያል?

አቶ ዘመድኩን፡- ባለፈው ዓመት በስድስት ወራት ማለትም ከመስከረም እስከ የካቲት መጨረሻ ድረስ ለተከናወነው የምዝገባና ዕድሳት ሥራ 1,006 ወረዳዎች ተደራሽ ተደርገዋል፡፡ በዚህም 1,200 እናቶች፣ አባወራዎችና እማዎራዎች ተመዝግበዋል፡፡ 56 ሚሊዮን ሕዝብም የጤና መድኅን ሥርዓት ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ የዘንድሮ ምዝገባና ዕድሳት በተያዘለት ወራት ውስጥ በመከናወን ላይ ሲሆን፣ እስከ ጥር 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ 1,022 ወረዳዎችን ተደራሽ ለማድረግ ተችሏል፡፡ ይህ ቁጥር ግን እስከ የካቲት መጨረሻ ድረስ ከፍ ሊል ይችላል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ...

ከጎዳና ከማንሳት ራስን እስከማስቻል የሚዘልቀው ድጋፍ

ጎዳና ተዳዳሪነትን ለማስቀረት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለዓመታት ሠርተዋል፡፡ ከችግሩ ስፋት አንፃር ሙሉ ለሙሉ መፍትሔ ባያገኝለትም፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለመለወጥ በሚሠሩ ሥራዎች ዕድሉን አግኝተው ራሳቸውን...