Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሴቶች ሥጋት የሆነው የማኅፀን በር ካንሰር

የሴቶች ሥጋት የሆነው የማኅፀን በር ካንሰር

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ ‹‹የማኅፀን በርና የጡት ካንሰር ምርመራ በማድረግ ጤናማና ምርታማ ሴቶችን እንፈጥራለን!›› በሚል መሪ ቃል፣ የካቲት 12 ቀን 2016 ዓ.ም. የማኅፀን በርና የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ የማድረግና ግንዛቤ የማጨበጫ መርሐ ግብር አካሂዷል፡፡

የሴቶች ሥጋት የሆነው የማኅፀን በር ካንሰር | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ወ/ሮ ሥፍራሽ አልማው

በአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሴቶች ዘርፍ ተሳትፎ ማብቃትና ተጠቃሚነት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሥፍራሽ አልማው እንደተናገሩት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ113ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ48ኛ ጊዜ የሚከበረውን ‹‹ማርች 8›› የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ፣ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ አሥራ አንዱም ክፍላተ ከተሞች ለሚገኙ ሴቶች የማኅፀን በርና የጡት ካንሰር በሽታ የግንዛቤ መፍጠርና የምርመራ መርሐ ግብር በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ጋር በቅንጅት በሚሠራው በዚህ የምርመራና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ፣ ሴቶች ራሳቸውን ከበሽታው እንዲከላከሉ ከማስቻል ባሻገር ቤተሰባቸውን፣ ጎረቤታቸውንና በአጠቃላይ ማኅበረሰቡን የመድረስ አቅም ስለሚኖራቸው፣ ይህንን ገዳይ በሽታ ለመከላከል ታሳቢ ተደርጎ መርሐ ግብሩ መዘጋጀቱንም ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የማኅፀን በርና የጡት ካንሰር በሽታን ለመከላከል ከግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ባሻገር፣ በአሥራ አንዱም ክፍላተ ከተሞች በሚገኙ 98 ለሚሆኑ ጤና ጣቢያዎች ምርመራ እየተሰጠ እንደሚገኝና እስካሁንም ከ2000 በላይ የሚሆኑ ሴቶች ምርመራ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡

በልደታ ክፍለ ከተማ ጤና ጽሕፈት ቤት የበሽታ መከላከል ቡድን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ኦፊሰር ወ/ሮ ሔለን መኮንን እንደተናገሩት፣ የማኅፀን በር ካንሰር ሒውማን ፓፒሎማ ቫይረስ በተሰኘ ረቂቅ ተህዋስያን አማካይነት የሚከሰት ነው፡፡

ተህዋስያኑ የማኅፀን በር ህዋሳትን በመውረር ጤናማ ያልሆነ ዕድገትና ብዜትን እያስከተለ ወደ ሌሎች አካላት ክፍሎች በመሠራጨት የሰውነትን ተለምዷዊ ተግባር በማወክ የበርካታ ሴቶችን ሕይወት በመንጠቅ ላይ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ በሽታው ሥር ሳይሰድ በምርመራ ከተደረሰበት ታክሞ መዳን ይቻላል፡፡

ማንኛውም ግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈጽማ የምታውቅ ሴት ለማኅፀን በር ካንሰር ዋነኛ መንስዔ ለሆነው ፓፒሎማ ቫይረስ የመጋለጥ አጋጣሚ እንደሚኖራት የጠቆሙት የጤና ኦፊሰሯ፣ በለጋነት ዕድሜ (ከ20 ዓመት ዕድሜ በታች) የግብረ ሥጋ ግንኙነት የጀመሩ ሴቶች፣ ከተለያዩ ወንዶች ጋር ግብረ ሥጋ የሚፈጽሙ፣ ከተለያዩ ሴቶች ጋር ግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚፈጽሙ የወንድ ጓደኛ ያላቸው ሴቶች፣ በተለያዩ ምክንያቶች የሰውነት በሽታ የመቋቋም ኃይል መቀነስ ያጋጠማቸው ሴቶች (ለምሳሌ ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ)፣ በአባላዘር በሽታ መያዝና ሲጋራ የሚያጨሱ ሴቶች ይበልጥ ለበሽታው ተጋላጭ ናቸው፡፡

የማኅፀን በር ካንሰር ሥር እስኪሰድ ድረስ ምንም ዓይነት የሕመም ስሜትና ምልክት ሳያሳይ ከ15 እስከ 20 ዓመታት ሊቆይ ይችላል፡፡ በሽታው ከተስፋፋ በኋላ ግን ከግብረ ሥጋ ግንኙነት በኋላ የደም መፍሰስ (ይህ ክስተት በዕድሜ ምክንያት ወር አበባ ባቋረጡ ሴቶች ላይም ይከሰታል)፣ የማኅፀን ፈሳሽ በብዛት መፍሰስና በማኅፀን አካባቢ የሕመም ስሜት የበሽታው ዋነኛ ምልክቶች መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የጤና ኦፊሰሯ እንደተናገሩት፣ የማኅፀን በር ካንሰር እስኪስፋፋ አዝጋሚ በመሆኑ፣ በሽታው ተባብሶ ለሕይወት አሥጊ ከመሆኑ በፊት ቅድመ ካንሰር ምርመራ በማድረግ ከበሽታው ታክሞ መዳን ይቻላል፡፡

በምርመራ ወቅት የቅድመ ካንሰር ምልክት ከታየ ‹‹ክራዮቴራፒ›› የተባለውን የሕክምና ዓይነት በመጠቀም የማኅፀን በር ካንሰርን 90 በመቶ መከላከል እንደሚቻልና ከ30 እስከ 49 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ወቅታዊና ተከታታይ ምርመራ ማድረግ እንደሚኖርባቸውም ገልጸዋል፡፡

የጡት ካንሰር መነሻው ይህ ነው ተብሎ የሚታወቅ ባይሆንም፣ በቤተሰብ የሚተላለፍና እጅግ የበዛ ውፍረት ለበሽታው አጋላጭ ምክንያቶች መሆናቸውን የሚናገሩት የጤና ኦፊሰሯ፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የጡት ካንሰር 14 በመቶ፣ የማኅፀን በር ካንሰር ደግሞ 31.9 በመቶ ሴቶችን እያጠቃ የሚገኝ በሽታ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ባዘጋጀው የማኅፀን በርና የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራና የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብር መድረክ፣ ከከተማዋ 11 ክፍላተ ከተሞች የሚገኙ ሴት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሴት አደረጃጀት ተወካዮች፣ ሴት የጄኔራል ካውንስል አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው ሴቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...