Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምኃያላኑ የመከሩበት የሙኒክ የደኅንነት ጉባዔ

ኃያላኑ የመከሩበት የሙኒክ የደኅንነት ጉባዔ

ቀን:

የአፍሪካ መሪዎች 37ኛውን የመሪዎች ጉባዔ በአዲስ አበባ ሲያካሂዱ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስን ጨምሮ ምዕራባውያኑ ደግሞ በደኅንነታቸው ዙሪያ ለመምከር ሙኒክ ነበር የከተሙት፡፡

ከዓርብ የካቲት 8 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት የተካሄደውን 60ኛውን የሙኒክ ደኅንነት ጉባዔ የከፈቱት የተመድ ዋና ፀሐፊ ጉተሬስ፣ ዓለም የምትከተለው አካሄድ ለሁሉም የዓለም ሕዝብ የሚሆን አይደለም ሲሉ ዓለም ያለበትን ሁኔታ ገልጸውታል፡፡

 ችግሮችን በጋራ እየፈቱ ሁሉም ሰው በሰላም መኖር የሚችልበት አማራጭ ቢኖርም፣ አገሮች ከዚህ አፈንግጠው፣ ለሁሉም በሚጠቅም ዓለም አቀፍ ሥርዓት ሳይሆን፣ ግላዊነት ላይ በተመሠረተ ዓለም ውስጥ ገብተዋል ብለዋል፡፡

- Advertisement -

ይህ ሁሉንም ዋጋ እያስከፈለ ነው የሚሉት ጉተሬስ፣ ‹‹ዛሬ አገሮች ያለምንም ተጠያቂነት የፈለጉትን ሲያደርጉ እያየን ነው፡፡ አገሮች ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርጉ አሠላለፎችን ትተው ራሳቸውን በማስቀደም ውድድር ውስጥ ገብተዋል፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

ዓለም ዛሬ ላይ ከተፈጥሮ እስከ ሰው ሠራሽ አደጋ መናኸሪያ ሆናለች፡፡ የአየር ንብረት ለውጡ ካመጣቸው ችግሮች በተጨማሪ፣ ኃያላኑ የገቡበት ቀጥታና የውክልና ጦርነት የዓለምን በሰላም የመኖር ሥርዓት አመሰቃቅሎታል፡፡

በመካከለኛው ምሥራቅ ወራትን ያስቆጠረው የእስራኤል ፍልስጤም ጋዛ ጦርነት፣ ዓመት የዘለለው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት፣ ከአሥር ዓመታት በፊት የዓረብ አብዮትን ተከትሎ ወደ ጦርነት ከገቡበት መውጣት ያልቻሉት ሶርያ፣ ሊቢያና የመን፣ በአፍሪካ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካና በምዕራብ አፍሪካ የሚታዩ ጦርነቶችና ግጭቶች እንዲሁም ከማይናማር በገፍ ወደ ባንግላዴሽ የሚሰደዱ ሮሃኒንጋዎች የዓለም ሰላም መደፍረስና ችግሩን ከመፍታት ይልቅ የማባባስ እንቅስቃሴዎች መገለጫዎች ናቸው፡፡ ኃያላኑን አገሮች የጦር መሣሪያ ውድድር የገቡበት፣ በአንድ ላይ ሠርቶ ችግር ከመፍታት ይልቅ ጎራ ለይተው የተቧደኑበት ጊዜም ነው፡፡ ይህ ደግሞ የዓለም ሕዝባችን ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል፡፡

ጉተሬስ እንደሚሉት ደግሞ፣ ይህ ለሁሉም ፅንፍ ይዘው ለተሠለፉ አገሮች የሚበጅ አይደለም፡፡ የጋዛ ጉዳይም የዓለም አገሮች አዎንታዊ ግንኙነት ምን ያህል እንደተዘጋ የሚያሳይ ነው፡፡

ሃማስ በእሥራኤል ላይ የወሰደው ድንገተኛ ጥቃትም ሆነ፣ እሥራኤል በምላሹ በፍልስጤም ንፁኃን ላይ ካለፉት ሦስት ወራት ወዲህ የምታካሂደው ወታደራዊ ዕርምጃ ተቀባይነት የለውም፡፡ ሃማስ ከእሥራኤል ወገን ያገታቸውን ዜጎች መልቀቅ፣ እሥራኤልም ተኩስ አቋም ስምምነትን መቀበል አለባቸው ሲሉም ጉተሬስ ተናግረዋል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳዮችና የደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፍ ቦሬል እንደ ጉተሬስ ሁሉ፣ ‹‹እኛ የአገሮች ከፍተኛ ፍጥጫና ዝቅተኛ ትብብር ባለበት ዓለም ውስጥ እየኖርን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ዓለም የበለጠ አደገኛ ቦታ ሆናለች ያሉት ቦሬል፣ የዘንድሮውን የሙኒክ ደኅንነት ጉባዔ ‹‹ዓለም ጥልቅ በሆነ ጂኦፖለቲካዊ ውጥረትና በኢኮኖሚ አለመረጋጋት ውስጥ ባለችበት ያደረግነው ነው›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡

በሙኒኩ የደኅንነት ጉባዔ ትኩረት ያገኙት የእስራኤልና ፍልስጤም ጋዛ እንዲሁም የሩሲያ ዩክሬን ጦርነቶች መሆናቸውን የጠቀሱት የዓለም አቀፍ ሪስኪዩ ኮሚቴ ዋና ሥራ አስፈጻሚና ፕሬዚዳንት ዴቪድ ሚሊባንድ በበኩላቸው፣ በዓለም እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ የሱዳን የሰብዓዊ ቀውስን ጨምሮ ትኩረት ያልተሰጣቸው በርካታ ቀውሶች እንደሚታዩ ተናግረዋል፡፡

‹‹ዓለም ተጠያቂነትን በማይፈሩ እየተዋጠች ነው፡፡ በርካታ መዘበራረቆችም ይታያሉ፤›› ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

50 የአገር መሪዎችን ጨምሮ ከመላው ዓለም ከ900 በላይ ተሳታፊዎችና ከ100 በላይ ሚኒስትሮች በተካፈሉበት ጉባዔ፣ በአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ የተመራው ልዑካን ቡድን ተሳታፊ ነበር፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንቷ እንዳሉት፣ እሳቸውም ሆኑ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በዩክሬንንም ሆነ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ አሜሪካ ችላ ያለችው ነገር የለም፡፡

የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች እየገጠማቸው ባለው የደኅንነት ሥጋት በመከሩበት በዚሁ ጉባዔ፣ ጂኦፖለቲካዊ ጉዳይ ተነስቷል፡፡ በተለይ በዩክሬን በጋዛና በደቡባዊ አገሮች የሚታዩ ችግሮች እነሱንም እየጎዱ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በጉባዔው በተለይ የእስራኤል ጋዛ ጉዳይ ትኩረት ያገኘ ሲሆን፣ እስራኤል በወረራ በያዘችው የፍልስጤም ግዛት ውስጥ እየፈጸመች ያለው ሰፈራ ችግር እያባባሰ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የአይሁድ ሰፋሪዎች በተለይ ሃማስ ድንገተኛ ጥቃት በእስራኤል ላይ ከፈጸመ ከጥቅምት 2016 ዓ.ም. ወዲህ፣ በፍልስጤማውያን ላይ የሚፈጽሙት ጥቃት እየጨመረ መምጣቱንም ቦሬል ተናግረዋል፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ሕገወጥ ሰፈራ መበራከቱን መናገራቸውን ጠቁመዋል፡፡

‹‹ለፍስጤማውያን መልካም አመለካከት ከሌለ በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም አይሰፍንም፣ የእስራኤል ደኅንነትም በመሳሪያ ኃይል ብቻ የሚመጣ አይሆንም›› ሲሉም ለሁለቱም ወገን የሚሆን መፍትሔ እንዲተገበር ጠይቀዋል፡፡

እንደ ጉተሬስ፣ ተጠያቂ ካለመሆንና ከውድድር ጋር ተያይዞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀውሶች እየተባዙ ነው፡፡ በመሆኑም ለሁሉም የሚሠራ፣ ክፍተቶችን የሚሞላና ለተከሰቱ ችግሮች ሁሉ መፍትሔ የሚሆን ዓለም አቀፍ ሥርዓት መተግበር አለበት፡፡ ለዚህም አገሮች በተመድ ቻርተር የተቀመጡትን ግዴታዎች ቢወጡ፣ የዓለም ሕዝብ በሙሉ በሰላምና ክብሩ ተጠብቆ መኖር ይችላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...