Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትበዓለም አትሌቲክስ የሚካፈሉ አትሌቶች ዝግጅት ጀምረዋል

በዓለም አትሌቲክስ የሚካፈሉ አትሌቶች ዝግጅት ጀምረዋል

ቀን:

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አትሌቲክስ ቡድን የዓለም አትሌቲክስ ለዘንድሮ ይፋ ያደረገውን መርሐ ግብር ተከትሎ ለሚካፈልባቸው ሁለት ውድድሮች ዝግጅቱን ጀምሯል፡፡ መጀመሩን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡

በስኮትላንድ በግላስኮ ከተማ የሚከናወነው 19ኛው የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና፣ እንዲሁም በቱኒዝያ ቱኒስ በሚከናወኑት 6ኛው የአፍሪካ አገር አቋራጭ ውድድር የሚካፈሉ አትሌቶች መደበኛ ዝግጅታቸውን መጀመራቸውንም ፌዴሬሽኑ ገልጿል፡፡

በግላስኮ ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች ከየካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. መደበኛ ልምምዳቸውን በኢትዮጵያ ስፖርት አካዴሚ መጀመራቸውን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡ 

- Advertisement -

ኢትዮጵያ በቤት ውስጥ ሻምፒዮና በ1500 ሜትር፣ በ3000 ሜትር በሴቶችና በወንዶች፣ እንዲሁም በ800 ሴቶች በአጠቃላይ ስምንት ሴቶችና አምስት ወንዶች በድምሩ በ13 አትሌቶች ትወክላለች፡፡

በቤት ውስጥ ሻምፒዮናው ለመካፈል በተለያዩ ከተሞች የወርቅ ደረጃ የተሰጣቸው የዙር የቤት ውስጥ ውድድሮች ሲከናወኑ የሰነበቱ ሲሆን፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን ተካፍለውበታል፡፡ የዙር ውድድሩ በሻምፒዮናው ለመካፈል የሚያስችላቸውን ውጤት ለማምጣት የሚያግዝ በመሆኑ አትሌቶቹ ሲሳተፉ ቆይተዋል፡፡ 

በዙር የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ከሴቶች ጉዳፍ ፀጋይ፣ ድርቤ ወልተጂ፣ ሀብታም ዓለሙና ፍሬወይኒ ኃይሉ ሲወዳደደሩ የሰነበቱ ሲሆን፣ በወንዶች ለሜቻ ግርማ፣ ሰለሞን ባረጋ፣ ጌትነት ዋለ፣ እንዲሁም ወጣቱ ቢንያም መሐሪ ተሳትፈዋል፡፡

የሁለት ጊዜ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮኗ ጉዳፍ ፀጋይ በቤት ውስጥ ውድድር ከደመቁ አትሌቶች መካከል ቀዳሚዋ  ነች፡፡ ጉዳፍ በቅርቡ በፈረንሣይ ሊቨን በተከናወነውና የወርቅ ደረጃ በተሰጠው የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የ3000 ሜትርን 8፡17፡11 ማጠናቀቅ ችላለች፡፡

ጉዳፍ የርቀቱ ሦስተኛውን ፈጣን ሰዓት ሆኖ ማስመዝገቧ ይታወሳል፡፡ በዳይመንድ ሊግ፣ እንዲሁም በዓለም ሻምፒዮና በትራክ ውድድሮች የደመቀችው ጉዳፍ፣ በግላስኮ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ከፍተኛ ግምት ካገኙ አትሌቶች መካከል ብቸኛዋ ነች፡፡

ሌላዋ በቤት ውስጥ ውድድር የደመቀችው ሀብታም ዓለሙ ነች፡፡ ሀብታም ለረዥም ጊዜ በ800 ሜትር ርቀት ስትሳተፍ የቆየች ሲሆን፣ የወርቅ ደረጃ በተሰጠው የፖላንድ ቱራን ከተማ በተከናወነው ውድድር በ800 ሜትር በ1፡57፡86 የርቀቱን ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ ችላለች፡፡ ሀብታም በግላስኮው የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን በ800 ሜትር ትወክላለች፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያን በወንዶች ከሚወክሉ አትሌቶች መካከል የቶኪዮ ኦሊምፒክ 10 ሺሕ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤቱ ሰለሞን ባረጋ ይገኝበታል፡፡ በረዥም ርቀቱ ውድድሮች ሲሳተፍ የሚታወቀው ሰለሞን በ3000 ሜትር ይወዳደራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሰለሞን በቱራን የወርቅ ደረጃ በተሰጠው የዙር የቤት ውስጥ ውድድር በ3000 ሜትር 7፡25፡82 በመግባት የራሱን ሰዓት ሲያሻሽል አምስተኛውን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብም ነው፡፡

በሌላ በኩል በወንዶች 1500 ሜትር ተስፋ የተጣለበት ቢንያም መሐሪ ይጠበቃል፡፡ ቢንያም በቅርቡ ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ የገባ ሲሆን አመርቂ ውጤት ያመጣል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ በቱራን በተደረገ የቤት ውስጥ ውድድር 1500 ሜትር 3፡34፡83 በመግባት ዕድሜያቸው ከ20 በታች ክብረ ወሰን መጨበጥ ችሏል፡፡

ሌላው በቤት ውስጥ ሻምፒዮናው የሚጠበቀው ለሜቻ ግርማ ነው፡፡ በ3000 ሜትር መሰናክል የሚታወቀው ለሜቻ፣ የወርቅ ደረጃ በተሰጠው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ውድድር በ2000 ሜትር ተወዳድሯል፡፡ በውጤቱም 4፡51፡23 በማጠናቀቅ ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ ችሏል፡፡ ለሜቻ ወደ ውድድሩ ከመግባቱ አስቀድሞ በቀነኒሳ በቀለ ተይዞ የነበረው የርቀቱን 4፡49፡99 ክብረ ወሰን ለመስበር ቢያቅድም ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት ግን ማስፈጸም ችሏል፡፡  

በ1997 በፈረንሣይ በተከናወነው ሻምፒዮና በወንዶች 3000 ሜትር ኃይሌ ገብረ ሥላሴ 7፡34፡71 በመግባት ክብረ ወሰን በመጨበጥ ሳያስደፍር ቆይቷል፡፡ በ2022 በሰርቢያ ቤልግሬድ በተካሄደው ሻምፒዮና ሳሙኤል ተፈራ በ1500 ሜትር 3፡32፡77 በማጠናቀቅ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት መሆን ችሏል፡፡

በሴቶች ጉዳፍ ፀጋይ በቤልግሬዱ ሻምፒዮና በ1500 ሜትር 3፡57፡19 በመግባት የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት መሆን ችላለች፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በሻምፒዮናው መሳተፍ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በ2022 በሰርቢያ ቤልግሬድ የተከናወነ የቤት ውስጥ አትሌክስ ሻምፒዮና አራት ወርቅ፣ ሦስት ብር፣ እንዲሁም ሁለት ነሐስ፣ በድምሩ ዘጠኝ ሜዳሊያዎችን በመሰብበሰ ከዓለም አንደኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀበት ስኬታማው ሻምፒዮና ነበር፡፡

በሌላ በኩል የካቲት 20 ቀን በቱኒዝያ ለሚደረገው 6ኛው የአፍሪካ አገር አቋራጭ ውድድር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ዝግጅቱን ቀጥሏል፡፡ 

ለአራት ዓመታት ተቋርጦ የነበረውና በአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን የሚዘጋጀው የአፍሪካ አገር አቋራጭ ውድድር፣ ከማክሰኞ የካቲት 8 ቀን ጀምሮ ዝግጅቱን መጀመሩ ተገልጿል፡፡ 

በውድድሩ ከ20 ዓመት በታች ስድስት ኪሎ ሜትር፣ በወንዶች ስምንት ኪሎ ሜትር፣ በአዋቂዎች አሥር ኪሎ ሜትር ወንዶችና ሴቶች እንዲሁም ድብልቅ ሪሌ ይሳተፋሉ፡፡ ኢትዮጵያ በሁለቱም ፆታ በ28 አትሌቶች ትወክላለች፡፡. 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...