Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየአብዮቱን የሃምሳ ዓመታት ጉዞ በውይይት መድረኮች ለመፈተሽ ዝግጅት መጠናቀቁ ተነገረ

የአብዮቱን የሃምሳ ዓመታት ጉዞ በውይይት መድረኮች ለመፈተሽ ዝግጅት መጠናቀቁ ተነገረ

ቀን:

የኢትዮጵያ አብዮት የሃምሳ ዓመታት ጉዞ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በውይይት መድረኮች ለመፈተሽ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን፣ ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (FSS) አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ አብዮት ‹‹ከየካቲት እስከ የካቲት›› በሚል ርዕስ የፖሊሲ ፋይዳ ባላቸው ስድስት ወሳኝ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር የውይይት መድረክ ከመጋቢት ወር መጀመሪያ ጀምሮ ለማካሄድ ዝግጅት ማጠናቀቁን፣ ተቋሙ ሰኞ የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡

ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ካሉ የተለያዩ ተቋማትና ክፍሎች ጋር በመተባበር ውይይቱን የሚያካሂድ መሆኑን፣ ውይይቱም ለአንድ ዓመት ያህል እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡  

- Advertisement -

በኢትዮጵያ የሽግግር ፖለቲካ አለመረጋጋትና ግጭቶች በመስፋፋታቸው ምክንያት፣ የአገሪቱን የሃምሳ ዓመታት ጉዞ በጥናት ለመፈተሽ መገደዳቸውን የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የራስ ወርቅ አድማሴ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አብዮት ለዘንድሮ በወርኃ የካቲት ሃምሳኛ ዓመት የሞላው መሆኑን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ተማሪዎች፣ ሠራተኞች፣ ወታደሮች፣ እንዲሁም የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከየካቲት ወር 1966 ዓ.ም. ጀምሮ ባደረጉት ሕዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ እንደተጀመረ አስታውሰዋል፡፡

የአብዮቱ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ማዕበል በመፍጠር ሥር ነቀል ለውጥ በኢትዮጵያ መምጣቱን፣ ለውጡም ዛሬ ኢትዮጵያ ላለችበት መልካምም ሆነ አሉታዊ ገጽታ አስተዋጽኦ ማድረጉ አይካድም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን ከአብዮቱ በኋላ የተከተሉ ትውልዶች አብዮቱን የሚረዱበት መንገድ የተለያየ ከመሆኑም በላይ፣ ምናልባትም አብዮቱ ካስከተለው ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ግጭት ጋር ብቻ የተያያዘ መስሎ እንደሚታያቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹በተለይ ከዚህም አልፎ የአብዮቱ ተዋንያን በሚጽፏቸው የሕይወት ታሪኮችና ክርክሮች ግራ መጋባት ላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባትም ስለአብዮቱ ግድ የለሽ ትውልድም ተፈጥሮ ይሆናል፡፡ ዞሮ ዞሮ ሁላችንም በዚህ አብዮት ትሩፋትና ዕዳ ውስጥ እንደምንኖር ግልጽ ነው፤›› በማለት የራስ ወርቅ (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ያለፈውንና ረዥሙን የሃምሳ ዓመታት በተለያየ መንፈስ ጉዞ ያደረገች አገር ናት፤›› ያሉት የራስ ወርቅ (ዶ/ር)፣ በዚህ ግማሽ ምዕተ ዓመት ጉዞ ውስጥም እመርታ ያሳየችበት፣ ወደኋላ የተንሸራተተችበት፣ እንዲሁም ባለችበት የሄደችበት ሁኔታ እንዳለ ይታመናል ብለዋል፡፡

በዚህ መሠረት የሃምሳ ዓመታትን ጉዞ ቆም ብሎ ለመፈተሽ የአብዮቱ የሃምሳኛ ዓመት የወርቅ እዮቤልዩ ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ ገልጸው፣ በተጨማሪም ‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታ ምን ላይ ይገኛል?›› የሚለውን በተጨማሪ ለመዳሰስ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡

በአንድ ዓመት ውስጥ በየሁለት ወራት የሚካሄደው የውይይት መድረክ ዓላማው ወደኋላ ተመልሶ የአብዮቱን ዘመን ክርክሮች ለመድገም ሳይሆን፣ የሰከኑ ምሁራዊ አካዴሚያዊ ውይይቶች ለማድረግ የታለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

የኢዮቤልዩ ዝክር ወደኋላ ሄዶ ከማስታወስ ባሻገር ለዛሬ የፖለቲካ ፖሊሲ ትልም ክርክሮች የሚበጁና ለነገ ስንቅና አሻጋሪ የሚሆኑ ክርክሮችን፣ እንዲሁም ውይይቶችን በማድረግ ትርጉም በሚሰጥ መንገድ ማክበር እንደሚያስፈልግ ተቋሙ እንደሚያምን አስረድተዋል፡፡    

ረዥሙ የሃምሳ ዓመታት ጉዞ ከአብዮቱ ሕልምና ትልም አንፃር እንዴት ይታያል? የአብዮቱ ትውልድ ጥያቄዎች ዛሬ ከሃምሳ ዓመታት በኋላ የት ደረሱ? ዛሬ የሚነሱ ሕዝባዊ ጥያቄዎች ከሃምሳ ዓመታት በፊት ከተነሱት ምን ያህል ይዛመዳሉ? የሚሉትንና ሌሎች መሰል ጥያቄዎች ለውይይቱ መነሻ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡

በእነዚህ ጥያቄዎች ሥር የመሬት ጉዳይ፣ የማንነት በተለይም የብሔር፣ የሃይማኖትና የፆታ ጥያቄዎች፣ የሠራተኛ (ሌበር) ጉዳዮች፣ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ፣ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች የውይይቶቹ ዋነኛ ርዕስ እንደሚሆኑ አክለዋል፡፡

‹‹አብዮቱ በራሱ በታሪክ ሒደት ውስጥ ያለው ቦታ ምንድነው?›› የሚለው ጉዳይ በውይይቶቹ መጠናቀቂያ ላይ የሚቀርብ መሆኑን፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

የአብዮቱ ሃምሳኛ ዓመት ሲዘከር ከዚህ በፊት የነበሩ የአብዮቱ ተዋንያንና አሁን ያሉ ወጣቶች እንዲሳተፉ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...