Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየመጀመሪያው የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት ነገ በቢሾፍቱ ከተማ ይፋ ይደረጋል

የመጀመሪያው የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት ነገ በቢሾፍቱ ከተማ ይፋ ይደረጋል

ቀን:

  • የኢትዮጵያን ሁለተኛ ሳተላይት ለማምጠቅ ዓለም አቀፍ ጨረታ ሊወጣ ነው

የኢትዮጵያ የህዋ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ያለማውን የአገሪቱ የመጀመሪያ የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት፣ ነገ ሐሙስ የካቲት 14 ቀን 2016 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ ፒራሚድ ሪዞርት ይፋ ሊደረግ መሆኑ ታወቀ።

በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደርና በኢንስቲትዩቱ የፋይናንስ ትብብር በቢሾፍቱ ከተማ ተግባራዊ የተደረገው የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት የ33,000 ቤቶችን መረጃ ያዘለ፣ ለእያንዳንዱ ቤት ባለ አሥር ቁጥር መለያ አድራሻ (10 Digit Address) ያስቀመጠ ሥርዓት ሲሆን፣ የአድራሻ አገልግሎቱን መጠቀም የሚያስችሉ ድረ ገጽ (Website) እና መተግበሪያ (Application) ተሠርተውለታል። 

በኢንስቲትዩቱ የኢትዮጵያ ዲጂታል አድራሻ ሥርዓት ፕሮጀክት ዋና ኃላፊ አቶ አግማሰ ገበየሁ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት የሚታየውን መንገዶችን በትክክል የሚጠቁም፣ እንዲሁም  ትክክለኛ ወቅታዊ ካርታዎችን የሚያሳይና የዲጂታል አቅጣጫ መምርያ ውጤታማ ሥርዓት አለመኖር የሚፈጥራቸውን ችግሮች የሚፈታ ነው፤›› ብለዋል።

- Advertisement -

ዋና ኃላፊው አክለውም ከነገ ጀምሮ ለተጠቃሚዎች ክፍት የሚሆነው ድረ ገጽና መተግበሪያ፣ የከተማዋን መንገዶች በትክክል አቅጣጫ መምራት የሚችል፣ አማራጭ መንገዶችን የሚጠቁም፣ ለእያንዳንዱ ቤት የተሰጠውን ባለአሥር ቁጥሮች መለያ በመጠቀም ትክክለኛ መገኛቸውን ማሳወቅና መርቶ ማድረስ እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

የአድራሻ ሥርዓቱ ከዚህ በተጨማሪም የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎችን፣ ሆቴሎችን፣ የእንግዳ መቀበያ ቤቶችን (Guest Houses)፣ እንዲሁም የሌሎችንም የንግድ ተቋማት ትክክለኛ መገኛ እንደሚያሳይና መንገድ መርቶ ማድረስ እንደሚያስችልም ተገልጿል። 

አቶ አግማሰ በአድራሻ ሥርዓቱ የተካተቱ ቤቶችን በተመለከተ፣ ‹‹በከተማው መዋቅር ሥር ያሉ ሁሉም ቤቶች ተካተዋል። ከከተማው ራቅ ብለው በሚገኙ አካባቢዎች (Remote Areas) ላይ ያሉትን ቤቶችን ግን በአድራሻ ሥርዓቱ ውስጥ አላስገባንም፤›› ብለዋል። 

የቢሾፍቱ የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት ትግበራ የማሳያ ፕሮጀክት መሆኑን፣ ወደፊት ሥርዓቱን በመላ አገሪቱ ላይ ለመዘርጋት ኢንስቲትዩቱ እየሠራ ነው ብለዋል። 

ጥር 16 ቀን 2016 ዓ.ም. የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ ከአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ይዞታ ምዝገባና ኤጀንሲዎች ዋና ዳይሬክተር አቶ ግፋ ወሰን ደሲሳ ጋር፣ የመዲናዋን የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል። 

ይህ በዚህ እንዳለ የኢትዮጵያን ሁለተኛ ሳተላይት ለማምጠቅ ዓለም አቀፍ ጨረታ ሊወጣ መሆኑን፣ የህዋ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ግርማ ደጀኔ ለሪፖርተር ገልጸዋል።

‹‹ሳተላይቱን እኛ እንደምንፈልገው የሚሠራልንና የሚያመጥቅልን ዓለም አቀፍ ሕጋዊ ተቋም ለማግኘት የሚያስችለን ዓለም አቀፍ ጨረታ በሒደት ላይ ነው፤›› ብለዋል።

ለማምጠቅ የታሰበው ሁለተኛ ሳተላይት ከመጀመሪያው ጋር አገልግሎቱ ተመሳሳይ እንደሚሆን ማለትም፣ የመሬት ምልከታ ሳተላይት እንደሚሆን ገልጸው፣ ነገር ግን የመጀመሪያው ከነበረው 13.5 የጎላ የምሥል ጥራት (Resolution) ይኼኛው ከፍ ብሎ 0.5 ከፍተኛ የጥራት ደረጃ እንዲኖረው እንደሚፈለግ አስረድተዋል። 

ኢንስቲትዩቱ ሁለተኛውን ሳተላይት የማምጠቅ ሥራ ዓለም አቀፍ ጨረታና አፈጻጸም ሒደት፣ በተያዘው እ.ኤ.አ. 2024 እንዲካሄድ በበጀት ዓመት ዕቅዱ ላይ ማስቀመጡም ተገልጿል። 

ተጫራች ዓለም አቀፍ ተቋማት የገንዘብ ሚኒስቴር ተግባር ላይ ባዋለው የመንግሥት የኤሌክትሮኒክስ ጨረታ ሥርዓት (Electronic Government Procurement System) ወይም ኢፒጂ ላይ ለኢንስቲትዩቱ በተሰጠው መለያ (Code) በኩል ጨረታው እንደሚወጣላቸው፣ በዚያ ላይ ተመዝግበው የመወዳደሪያ ሰነዶቻቸውን እንዲያስገቡ እንደሚደረግ፣ ግዥዎቹም በመንግሥት ግዥ ኤጀንሲ በኩል እንደሚፈጸሙም አቶ ግርማ ተናግረዋል።

ሁለተኛዋን ሳተላይት ለመሥራትና ለማምጠቅ ከዋጋና ከጥራት አንፃር፣ ተጫራቾች ማሟላት የሚገባቸውን የተለዩ ደረጃዎች (Specifications) ዝርዝር የሚያወጣ የቴክኒክ ቡድን መዋቀሩንም አስረድተዋል። 

የቴክኒክ ቡድኑ በሚያወጣቸው መሥፈርቶች መሠረት አገሮችና የሳተላይት አምራችና አምጣቂ ድርጅቶች እንዲሳተፉ የሚጋብዝ ጨረታ መሆኑን ጠቁመዋል። 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...