Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበደብረ ብርሃን ከተማ በመጠለያ ያሉ ተፈናቃዮች ‹‹ወደ መጣንበት እንድንመለስ ግፊት እየተደረገብን ነው››...

በደብረ ብርሃን ከተማ በመጠለያ ያሉ ተፈናቃዮች ‹‹ወደ መጣንበት እንድንመለስ ግፊት እየተደረገብን ነው›› አሉ

ቀን:

‹‹ማንም ሰው በግዳጅ እንዲመለስ አልተደረገም››

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳዳር

ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች፣  አስተማማኝ የፀጥታ ሁኔታ ባልተፈጠረበት ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ግፊት እየተደረገባቸው መሆኑን ተናገሩ።

- Advertisement -

ስለተፈናቃዮቹ ቅሬታ ጥያቄ የቀረበለት የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር በበኩሉ፣ ማንም ሰው በግዳጅ እንዲመለስ አልተደረገም ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ነገር ግን ከሁለቱ ክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት በጉዳዩ ላይ ከተፈናቃዮች ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ የፀጥታ ሥጋት የሌለባቸው አካባቢዎች ተለይተው እንዲመለሱ  የማድረግ ሥራ መጀመሩን፣ የደብረ ብርሃን ከተማ ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች ከ30 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች መኖራቸውን የተናገሩት ከንቲባው፣ ካለው የተፈናቃይ ቁጥር አንፃር የመመለስ ሥራው ገና ጅምር ነው  ብለዋል።

በግዳጅ ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ እየተደረገ ነው የሚባለው ከእውነት የራቀ ነው ያሉት አቶ በድሉ፣ ወደ ቀዬአቸው መመለስ የሚፈልጉት ተፈናቃዮች ተመዝግበው አንፃራዊ ሰላም ወዳለባቸው አካባቢዎች እንደሚመለሱ ገልጸዋል።

ከየካቲት 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በግዳጅ ወደ መጡበት አካባቢ እንዲመለሱ በሚደረግባቸው ግፊት፣ ብዙዎቹ መጠለያቸውን ለቀው እየወጡ መሆኑን ተፈናቃዮች ተናግረዋል። 

ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በነበረው ተፈናቃዮችን የመመለስ እንቅስቃሴ በ13 ተሽከርካሪዎች አቅመ ደካሞች፣ ሥራ መሥራት የማይችሉና ረዳት የሌላቸው ሰዎች በረሃብ ከምንሞት ብለው ወደ ምዕራብ ወለጋ መመለሳቸውን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ተፈናቃዮች ገልጸዋል።

የእርሻ መሬታቸውና ንብረታቸው አልጠፋም የተባሉ ሰዎች ስም ዝርዝራችው   ከወለጋ ተመዝግቦ የመጣ በመሆኑ፣ መመለስ ይኖርባችኋል ተብለው በፀጥታ ኃይል ተገደው እንዲመለሱ እየተደረጉ መሆናቸውን አክለዋል።

መጀመሪያ ለደረሰባቸው ግድያና ጭፍጨፋ ኃላፊነቱን የወሰደ አካል አለመኖሩን የሚናገሩት ተፈናቃዮቹ፣ በአሁኑ ወቅት ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ ለሚደርስባቸው ግድያ   ኃላፊነቱን የሚወስድ አካል እንደማይኖር ሥጋታቸውን ተናግረዋል።

 በተመላሾች ላይ ለሚደርሰው ችግር ሁለቱ ክልሎችና የፌዴራል መንግሥት ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ ቃል መግባታቸውን  አቶ በድሉ ጠቁመዋል፡፡

‹‹በግዳጅ የሚባል ነገር የለም፤›› ያሉት አቶ በድሉ፣ አንፃራዊ ሰላም ያሉባቸው አካባቢዎች ተለይተው ቤትና መሬታቸው ያልተወሰዱባቸው ሰዎች ብቻ እንዲመለሱ የማድረግ ጅማሬ መኖሩን አክለዋል፡፡

ተፈናቃዮቹን ወደ ነበሩበት ለመመለስ የኦሮሚያ ክልል ተሽከርካሪዎችን በማቅረብ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ከንቲባው አስታውቀዋል።

‹‹ሙሉ መረጃ ለመስጠት ኮማንድ ፖስቱ ይገድበኛል›› ያሉና በጉዳዩ ላይ በቅርበት እንደሚሠሩ የተናገሩ ኃላፊ ስሜ አይጠቀስ ብለው እንደተናገሩት፣ ከ30 ሺሕ ተፈናቃዮች ስድስት ሺሕ ያህሉ ብቻ ከኦሮሚያ ክልል ስማቸው ተመዝግቦ መምጣቱን፣ ከተመዘገቡት ውስጥ 750 ያህሉ በፈቃደኝነት ወደ ቀዬአቸው ተመልሰዋል ብለዋል።

 ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ጉጉት ያደረባቸው ሰዎች ቢኖሩም፣ ያለው የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑ መመለስ አለመቻላቸውን ገልጸዋል።

የተመላሾችን ስም ዝርዝር የሚያቀርበው የኦሮሚያ ክልል ብቻ መሆኑን የተናገሩት አስተያየት ሰጪው ስም ዝርዝራቸው የመጣው ተፈናቃዮችም ቢሆኑ ተገደው ሲሄዱ አለማየታቸውን ተናግረዋል።

‹‹መንግሥት አሁንም ቢሆን አስገድዶ የመውሰድ ዝንባሌ የለውም፤›› ያሉት ኃላፊው፣ ነገር ግን  ዕርዳታ እንዳይቀርብ በማድረግ ሊያስገድድ እንደሚችል ጠቁመዋል።

በየትኛውም መንገድ ወደ ቀዬአቸው የሚመለሱ ሰዎች ድጋሚ ሞትና መፈናቀል እንዳይገጥማቸው፣ የፌዴራል መንግሥት ጥበቃ እንደሚያደርግ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...