Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአንድነት ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ችግሮች መፍትሔ አላገኙም ተባለ

የአንድነት ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ችግሮች መፍትሔ አላገኙም ተባለ

ቀን:

‹‹የወላጆች ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከትምህርት ቤቱ ጋር በመነጋገር ችግሮቹን መፍታት ይገባቸዋል››

ወ/ሮ ሳባ አንሳሮ፣ የአንድነት የትምህርትና ሥልጠና ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ

የአንድነት ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ወላጆች የትምህርት ቤቱ ችግሮች መፍትሔ ማግኘት ሲገባቸው፣ ምንም ዓይነት መፍትሔ አለመገኘቱንና የትምህርት አሰጣጡም አለመሻሻሉን ተናገሩ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የትምህርት ቤቱ የወላጆችና የመምህራን ኅብረት የካቲት 9 ቀን 2016 ዓ.ም. በኢኮኖሚክስ አሶሴሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ ባደረገው ስብሰባ፣ ወላጆች በርካታ ቅሬታዎችን አንስተዋል።

ወላጆች ካነሷቸው ቅሬታዎች መካከል በተደጋጋሚ የተነሳው ትምህርት ቤቱ ኢንተርናሽናል ካሪኩለም የሚከተል እንደ መሆኑ መጠን፣ የትምህርት አሰጣጡ መሻሻል እንዳለበት፣ በቂ መምህራንን በየክፍሎቹ መመደብ እንደሚገባ፣ እንዲሁም የተማሪዎች መጻሕፍት ለሁለት ዓመታት አቅርቦቱ መስተጓጎል መቅረፍ አለበት የሚሉት ይጠቀሳሉ።

ትምህርት ቤቱ ሥነ ምግባር በጎደላቸው አንዳንድ  ተማሪዎች ላይ የሚወሰዱ ዕርምጃዎችን በማጠናከር፣ ሌሎች ተማሪዎች እንዳይበላሹ የማድረግ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በወላጆች ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል የትምህርት ጥራት መሻሻል ዋናው ጉዳይ ሲሆን፣ ትምህርት ቤቱ በዓለም አቀፍ ካሪኩለም መሠረት ይሠራ የነበረ ቢሆንም፣ ቀድሞ ይከተለው የነበረውን ካሪኩለም በዚህ ዓመት ሲቀይር በበቂ ዝግጅት ባለመሆኑ ተገቢውን ዝግጅት እንዲያደርግ፣ በተጨማሪም ለመምህራንና ለተማሪዎች የሽግግር ጊዜ እንዲሰጥ የሚሉ ይገኙበታል፡፡ ተማሪዎች ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ መምህራን በበቂ ቁጥር መመደብ ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለያየ ምክንያት ሥራ የሚለቁ መምህራን ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ወላጆች ጠቅሰው፣ ትምህርት ቤቱ ይህንን ችግር ለመፍታት በዓመቱ መጀመሪያ ከወላጆች ከሰበሰበው 75 በመቶ ጭማሪ ለመምህራን ቃል በገባው መሠረት የደመወዝ ጭማሪ ባለማድረጉ፣ በለቀቁ መምህራን ምትክ በፍጥነት ቦታውን ከመሸፈን ይልቅ ክፍለ ጊዜዎቹ ያለ ትምህርት የሚያልፉ በመሆናቸው ትምህርት ቤቱን ወቅሰዋል።

የትምህርት ቤቱ ትምህርት አሰጣጥ ቀውስ ውስጥ በመግባቱ፣ እንዲሁም ከ2,000 በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እያገኙ ስላልሆነ የትምህርት ሚኒስቴር ጣልቃ በመግባት የትምህርት አሰጣጡ እንዲሻሻል ማድረግ እንደሚገባው ጠይቀዋል።

በተጨማሪም የመጻሕፍት አቅርቦት ችግር እንዲቀረፍ ወላጆች በጋራ ባደረጉት ጥረት ከውጭ የሚገቡ መጻሕፍት ቀረጥ እንዲቀንስ የትምህርት ሚኒስቴርንና የጉምሩክ ኮሚሽንን ድጋፍ በመጠየቅ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ጥረት ቢደረግም፣ ትምህርት ቤቱ አስፈላጊውን እንቅስቃሴ አላደረገም ሲሉ ወቀሳ አቅርበዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ የትምህርት ቤቱ ባለአክሲዮንና የአንድነት የትምህርትና ሥልጠና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ ለወ/ሮ ሳባ አንሳሮ ሪፖርተር ጥያቄ አቅርቦላቸው በሰጡት ምላሽ፣ በወላጆች በኩል የተነሳው ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም፣ ወላጆች ከትምህርት ቤቱ ጋር በመነጋገር ችግሮችን መፍታት ይገባቸዋል ብለዋል።

የትምህርት አሰጣጥ ላይ የሚያጋጥመው ችግር መምህራን ሥራ ሲለቁ የአንድ ወር ጊዜ መስጠት ሲኖርባቸው ሳያደርጉ በድንገት ስለሚለቁ የሚፈጠር ክፍተት ነው ብለዋል።

የመጻሕፍት አቅርቦት ችግርን በተመለከተም በትምህርት ቤቱ ብቻ የሚፈታ ሳይሆን ወላጆች በሚስማሙበት የክፍያ መንገድ ከውጭ እንዲገባ በማድረግ መሆኑን  ወ/ሮ ሳባ ተናግረዋል።

የተማሪዎችን የሥነ ምግባር ችግር በሚመለከት የቀረበው ጥያቄ እውነት መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ በተለያዩ ምክንያቶች የሥነ ምግባር ችግር ካለባቸው ተማሪዎች ውስጥ ዕርምጃ በመውሰድ የተባረሩ መኖራቸውን ገልጸዋል።

የአንድነት ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት የወላጆችና የመምህራን ኅብረት ኃላፊዎች ከወላጆች የተነሳውን ጥያቄ በመያዝ፣ በትምህርት ሚኒስቴር የሚፈታውን ችግር ወደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በመውሰድ፣ እንዲሁም በሕግ የሚያስጠይቁ ጉዳዮችን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ የትምህርት ቤቱን የትምህርት አሰጣጥ ማሻሻል ማስቀጠል እንደሚገባ አስረድተዋል።

የአንድነት ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት የወላጆችና የመምህራን ኅብረት፣ ከትምህርት ቤቱ አስተዳደር ጋር ላለፉት ስድስት ወራት ውዝግብ ውስጥ መቆየቱ ይታወሳል። 

በተፈጠረው አለመግባባት ሳቢያ ለአንድ ሳምንት የዘለቀ የትምህርት ማቆም አድማ ከተደረገ በኋላ፣ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ  (ፕሮፌሰር)፣ ሁለቱ አካላት መግባባት ላይ እንዲደርሱ አቅጣጫ መስጠታቸው አይዘነጋም፡፡

በትምህርት ላይ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች መልካም ትውልድን ለማፍራት እንጂ እንደ ሌሎች መስኮች ትርፍን ብቻ ማዕከል ያደረጉ አለመሆናቸውን አፅንኦት ሰጥተውት ተናግረው ነበር፡፡ ስለዚህም ትምህርት ቤቶች ይህን መነሻ አድረገው እንዲሠሩ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ሒደቱን የሚከታተል አንድ ሰው በመወከል ውዝግቡን ለመፍታት ጣልቃ እንደሚገባ መገለጹ የሚታወስ ነው፡፡ የወላጆች ተወካዮች ግን የትምህርት ቤቱ አመራሮች የትምህርት ሚኒስቴር የሰጠውን የመፍትሔ አቅጣጫ ባለመቀበላቸው፣ ጉዳዩን በሕግ ለመጠየቅ በሒደት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...