Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየኢትዮጵያ የሙዚቃ አብዮት

የኢትዮጵያ የሙዚቃ አብዮት

ቀን:

አቶ ሠርፀፍሬ ስብሐት በአዲስ አበባ ኪነ ጥበብ፣ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የኪነ ጥበብ ዘርፍ ኃላፊ ናቸው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በተከናወኑ የኢትዮጵያውያን የሙዚቃ ውድድሮች ‹‹ኢትዮጵያ አይዶል›› በዳኝነት በማገልገል ይታወቃሉ፡፡ በሙዚቃ ሥራዎች ዙሪያ ሂስና አስተያየት በመስጠትም በዘርፉ አሻራቸውን ካሳረፉ ባለሙያዎች አንዱ ናቸው፡፡ አሁን የሙዚቃ ላይ ቃናቸው ለየት ያሉ ዘፈኖች በወጣት ድምፃውያን እየተለቀቁ ነው፡፡ በወጣት ድምፃውያን እየወጡ ባሉ አዲስ የሙዚቃ አልበሞችና በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ዙሪያ የማነ ብርሃኑ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ዘንድሮ በተለይም የጥር ወር በርከት ያሉ የሙዚቃ አልበሞች ተሠርተው ለአድማጭ ጆሮ ደርሰዋል፡፡ እነዚህ የሙዚቃ አልበሞች ይዘው የተነሱት የሙዚቃ ፍልስፍና፣ የሙዚቃ መሣሪያዎች አሰኛኘትና የቅማሬ (ኮምፖዚሸን) አስተሳሰብ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ሠርፀፍሬ፡- የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን በአልበም ደረጃ ይዘው የመጡ ድምፃውያን አንድ ዓይነት ሥልት ይዘው የመጡ ሳይሆን፣ የተለያየ ዘይቤ (ስታይል) ተከትለው የመጡ ናቸው፡፡ በሕዝብ ዘንድም እንዲወደዱ ያደረጋቸው የዘይቤ ልዩነታቸው ነው፡፡ አልበሞቹ የተጻፉበት፣ የተቀረፁበትና የታተሙበት መንገድ ይለያያል፡፡ ለምሳሌ የአስቻለው ፕሮዳክሽን ከየማ ፕሮዳክሽን በጣም ይለያል፡፡ አንዳንዶቹ ለዓለም አቀፍ የሙዚቃ አድማጭ እንዲሆኑ ታስበው ሲሠሩ፣ የተቀሩት ደግሞ የአገር ውስጥ የሙዚቃ አፍቃሪን ለማስደሰት ታልመው የተዘጋጁ ናቸው፡፡ አንዳንድ አልበሞች ድምፃውያኑን ከማጉላት ባሻገር፣ ሙያዊ ግብዓታቸው ከፍ ያለና የሙዚቃ ባለሙያዎች እጃቸውን በደንብ የከተቱበት አልበሞችንም ተመልክቻለሁ፡፡ የሮፍናን፣ የየማ፣ የዳዊት ቸርነትንና የሌሎችንም ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በተለያዩ ድምፃውያንም እየቀረቡ የሚገኙ እነዚህ አልበሞች በአንድ ሠልፍ የሚመደቡ ሆነው አላገኘኋቸውም፡፡ የወጡበት ወቅት ተመሳሳይ ቢሆንም፣ ይዘው በተነሱት ሙዚቃዊ ፍልስፍናና በዳራቸው ይለያያሉ፡፡ 2016 ዓ.ም. በተለይም የጥር ወር የሙዚቃ ወር ይመስል ነበር፡፡ ጆሮ ገብ የሆኑ ምርጥና ደስ የሚሉ ሙዚቃዎችን ሰምተናል፡፡ በሙዚቃችን አብዮት የሚመስል ነገርም ዓይቻለሁ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሪፖርተር፡- በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኢትዮጵያን የሙዚቃ ባህል ከሌሎች አገሮች የሙዚቃ ባህል ጋር አዋህዶ የመሥራት ነገር ይታያል፡፡ ይህ መሆኑ ሙዚቃችን ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ ይኖር ይሆን?

አቶ ሠርፀፍሬ፡- የትኛውም ባህል ብቻውን ራሱን መግለጽ የሚችል በቂ አቅም አለው፡፡ የትኛውም የሙዚቃ ባህል በራሱ ምሉዕ ነው፡፡ ሙዚቃው በአንድ የሙዚቃ መሣሪያ ብቻ ይሠራ፣ በድምፃዊው ብቻ ይሠራ፣ በከበሮ ብቻ ይሠራ በራሱ ምሉዕ ነው፡፡ ከበቂ በላይ ማኅበረሰቡን ይገልጻል፡፡ ይህ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ነገር ግን ወሰን ተሻግረን ለመደመጥና ዓለም አቀፍ ጣዕሞችን ለማምጣት ከፈለግን፣ ሙዚቃችንን ከሌሎች አገሮች ሙዚቃ ጋር በማዋሃድ፣ የአድማጫችንንና የተደራሽነታችንን ስፋት መጨመር ይገባናል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ቅኝታችንንና ሥልት ምታችንን ሙላቱ አስታጥቄ ‹‹ኢትዮ ጃዝ›› በማለት፣ ከጃዝ ጣዕም ጋር አዋህዶ የሙዚቃ ባህላችንን ዓለም አቀፋዊ ይዘት አላብሶታል፡፡ የራሱ ቅርፅ ያለውና ዓለም አቀፋዊ የሆነውን ጃዝ ኢትዮጵዊ ጣዕም በመስጠት ሙላቱ የአድማጩ ቁጥር እንዲጨምርና የተደማጭነት ወሰኑም ከፍ እንዲል አደረገው ማለት ነው፡፡ የህንድ ሙዚቃዎች በእኛ ዘንድ ተወዳጅና የሚደመጡ ናቸው፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ የእነሱ የሙዚቃ ኤለመንት ባህሪ ወይም መገለጫ ከእኛ አገር ሙዚቃ ጋር ስለሚቀራረብ ነው፡፡ ስለሆነም የእኛን አገር ሙዚቃ ብቻውን ወደ አውሮፓ ወስደን እናስደምጥ ብንል ከእነሱ የሙዚቃ ባህል በጣም የራቀ በመሆኑ የማዳመጫ ሚስጥሩን (‹ኮዱ›ን) አያገኙትም፡፡ ስለዚህ ጥረት ታክሎበት ሙዚቃዎቻችንን ከሌሎች አገሮች ጋር እያዋሃድንና እየቀየጥን ብንሠራ፣ ሙዚቃችንን ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ ከፍ ለማድረግና ለማሳደግ አንዱ መንገድ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ ከእነ ሙላቱ አስታጥቄ ሥራዎች ጀምሮ በደንብ የታየና የተመሰከረበት በመሆኑ ውጤታማ ነው ብሎ መናገርም ይቻላል፡፡   

ሪፖርተር፡- በዚህ ዘመን እየተሠሩ ያሉ የሙዚቃ ሥራዎች በዜማ ድርሰታቸው በ1960 እና 1970ዎቹ ከተሠሩ ሥራዎች ሲነፃፀሩ ያሉበት ደረጃ ምን ይመስላል?

አቶ ሠርፀፍሬ፡- በተለያዩ ድምፃውያን አሁን እየተሠሩ ያሉ ዘፈኖችን የዜማ ቀረፃቸው እንዲህ ነው እንዲያ ነው ብሎ በጥቅል ማስቀመጥ ይቸግራል፡፡ እያንዳንዳቸውን በተናጠል መተንተን የሚጠይቅ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ያየሁት በጎ ነገር ምንድነው፣ እስካሁን ድረስ ወደ ዘይቤ ማድላት እንጂ ዜማን በግልጽ የማውጣት (አርቲኩሌት) ነገር እየቀረ የመጣ ይመስል ነበር፡፡ ድምፃዊነት ትንሽ ፈተና የገጠመውም ይመስል ነበር፡፡ አንድ ሰው የተወሰነ ዘይቤ/ሥልት ከቻለ እንደ ዘፋኝ ሲቆጠር ቆይቷል፡፡ አሁን የመጡትና እያደመጥናቸው ያሉ ድምፃውያን ጥሩ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡ ለምሳሌ ዳዊት ጽጌ በ1950 እና 1960ዎቹ የነበሩ ቆየት ያሉ ሙዚቃዎችን የሠራበትና ያስደመጠን መንገድ ግሩም ነው፡፡ የድምፃዊነቱንም ብቃት ያስመሰከረበት ነው፡፡ የማስተዋል እያዩም የማዜም ብቃት እንዲሁ ከፍተኛ ነው፡፡ የዜማ ደራሲዎችም፣ የድምፃዊውን የድምፅ ባህሪ ግምት ውስጥ ያስገባና የሚመጥን ሥራዎች እንደሰጡት አምናለሁ፡፡ በተለይ አበበ ብርሃኔ የሠራቸው ሥራዎች ከድምፃዊው የሙዚቃ ተፈጥሮ ጋር የተስማማ ጥሩ የዜማ ድርሰት እንደሰጠው ይሰማኛል፡፡ የእንግሊዝኛ ዘፋኝ የነበረችው የማርያም ቸርነት (የማ) የተለያዩ የኢትዮጵያ ቅኝቶችን በደንብ እንድትሠራ ዕድል ተፈጥሮላታል፡፡ በዚህም ውጤታማ ሆናለች፡፡ ከልዑል ሲሳይ በጣም የወደድኩት የአዘፋፈንና የዜማ ተለያይነት መኖሩን ነው፡፡ በአጠቃላይ ድምፃውያኑ የዜማን ፈተና በደንብ መቋቋም የሚችሉ ዓይነት እንደሆኑ ይሰማኛል፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንድ ድምፃውያን በዘፈኖቻቸው ውስጥ የተለያዩ ቋንቋዎችን ሲጠቀሙ ይስተዋላል፡፡ ይህ የተለያዩ ቋንቋዎችን መጠቀም በሙዚቃው ዘርፍ ምን አንድምታ ይኖረዋል?

አቶ ሠርፀፍሬ፡- የተለያዩ ቋንቋዎችን በዘፈኖች ውስጥ መጠቀም በአንዳንድ አልበሞች ተመልክቻለሁ፡፡ እነዚህም ጥሩ ሙከራዎች ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት ታደሰ ዓለሙና ጋሻው አዳል ባህላዊ በሆነ መንገድ ብዙ ቋንቋዎችን እንደአፋርኛ፣ ሱዳንኛ፣ ሶማሌኛ፣ ትግርኛና የመሳሰሉትን ከዘፈኖቻቸው በማዋሃድ ለመጫወት ሙከራ አድርገዋል፡፡ ታደሰ መከተም እንዲህ ዓይነት ሙከራ ማድረጉን ዓይቻለሁ፡፡ ይህ ራሳቸው በተቀኙበት መንገድ ሄደው ያቀረቡት ጥሩ ልምምድ ነበር፡፡ ግን መካተት የነበረባቸው የቀሩ ነገሮች እንደነበሩም ይሰማኛል፡፡ ወደ እዚህ ዘመን ስንመጣ ድምፃውያኑ ሌሎች ቋንቋዎችን የማጥናትና የማኅበረሰቡን ባህል በጥልቀት የመመልከት ነገር ዓይቻለሁ፡፡ ለምሳሌ የየማ ራሱን የቻለ የማስተርስ ጥናት ነው፡፡ የሥነሰውና የሙዚቃ ጥናት (የኢትኖግራፊክስና የሙዚካል ኦንትሮፖሎጂ) ምርምር ውጤት ነው፡፡ በድርሰት፣ በሙዚቃ መሣሪያ (በኢንስትሩመንት)፣ በዳራ (በባክግራውንድ) በየማ አልበም ውስጥ የማኅበረሰቡ አባላት የተሳተፉበት ነው፡፡ ይህ ለሙዚቃችን ትልቅ ዕድገት የሚያመጣ ነው፡፡ እስከዛሬ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ብቻ ተገድቦ የነበረ የሙዚቃ አስተሳሰባችንን ሰፋ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በፊት ዓብዩ ሰለሞን የተባለ ታላቅ ሙዚቀኛ (ኢትዮ ስታር የነበረ) የተለያዩ ባህሎችን በአርት ፕሮዳክሸን ላይ ‹‹In search my roots›› በሚል አልበሙ በሰፊው መሞከሩን አስታውሳለሁ፡፡ ሌሎች ታዋቂ ድምፃውያንም እንደ እነዚህ ዓይነት ባህሎችንና ቋንቋዎችን እያጠኑ ቢጫወቱ በሙዚቃችን ላይ አዲስ ተጨማሪ ቀለም እንደሚፈጥር አምናለሁ፡፡ ሰሜኑ ላይ የምንሰማው በነጠላ የድምፅ ወይም የሙዚቃ መሣሪያ ቅላፄ ‹‹Monophonic›› የሙዚቃ አካሄድ ነው፡፡ ወደ ደቡብ ስንሄድ ደግሞ ከአንድ በላይ ድምፅና የሙዚቃ መሣሪያ ቅላፄ ‹‹Polyphonic›› እንደገና እየሰፋ፣ ሥሪቱም እየወፈረ ይሄዳል፡፡ ስለሆነም አሁን ላይ በአስቻለውና በየማ ሙዚቃዎች የታየው ሙከራ መስፋትና ማደግ ይኖርበታል እላለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ሙዚቃ ሲነሳ በተለይ በ1950፣ 1960 እና 1970ዎቹ ወርቃማ የሙዚቃ ዘመናት ናቸው የሚሉ አሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ ምልከታ ምንድነው?

አቶ ሠርፀፍሬ፡- አንድ ሙዚቃን ሂስ ለሚያደርግ፣ በደንብ ለሚያይና ለሚያስተውል ሰው ወርቃማ፣ ብርማና መዳብማ የሚባሉ ነገሮች የገበያ ቃሎች ናቸው፡፡ አካዴሚ ቃሎች አይደሉም፡፡ በአንድ አካዴሚ ተርም ውስጥ ወርቃማ የሚባል ቃል መጠቀም መለኪያው ዋጋ የሚያስከፍል ይሆናል፡፡ ምንድነው ‹‹ወርቃማ›› ያስባላቸው የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ እነዚያ የቀደሙ ዘመናትም ሆኑ የአሁነኞቹ ያሟሏቸው የሙዚቃ ባህሪያት እንዳሉ ሁሉ፣ የሚጎድሏቸውም ነበሩ፡፡ የአሁኑ ዘመን ከዚያኛው ዘመን ተሻግሮ ያመጣቸውና ያሳደጋቸው ነገሮች እንዳሉ መታወቅ አለበት፡፡ የሙዚቃ መሣሪያዎችን ብቻ ብንመለከት በሙዚያ መሣሪያዎችና በአደራደር በኩል የአሁኑ ዘመን የተሻለ ነው፡፡ የድምፃውያኑንን ብቃት እንመልከት ካልን የቀድሞዎቹ ድምፃውያን ከፍ ያለ ብቃት ነበራቸው፡፡ ዛሬ ማንኛውም ሰው ድምፃዊ ነኝ ብሎ ካመነና የማሳተም አቅም ካለው፣ ወደ ሙዚቃ በጅምላ የመግባት ነገር ይታያል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ አንድ የሙዚቃ ዘመን ከሌላኛው ዘመን በዚህ ይሻላል፣ በዚያኛው ደግሞ ያንሳል ብሎ መፈረጅ እጅግ ከባድ ይሆናል፡፡ ተቃርኖም የሚፈጥር ነው፡፡ በሙዚቃ ደረጃ ላይ ቆመን የምንነጋገር ከሆነ አሁን እየተደመጡና የምርምር አስተሳሰቦችን በአልበማቸው ይዘው የመጡ ድምፃውያንን በሚዲያ ብናስተዋውቃቸው፣ ገበያው ቢቀበላቸው፣ ብናበረታታቸውና ብናግዛቸው የኢትዮጵያ ሙዚቃ አንድ ደረጃ ከፍ እንደሚል አምናለሁ፡፡     

ሪፖርተር፡- በቅርቡ የወጡ የድምፃውያን ሥራዎች እየተደመጡ ያሉት በተለያዩ ፕላት ፎርሞች ሳይሆን፣ በራሳቸው በድምፃውያኑ ዩቲዩብ ነው፡፡ ይህ ከምን የተነሳ ነው ብለው ይገምታሉ?

አቶ ሠርፀፍሬ፡- አርቲስቱ በራሱ ገጽ ላይ የሙዚቃ ሥራዎቹን ይዞ መምጣቱና በሌሎች ፕላት ፎርሞች ላይ አለመጠቀሙ በመቶኛ ብቻ ያገኝ የነበረውን ገቢ ሙሉ በሙሉ ራሱ እንዲያገኝ ያደርገዋል፡፡ ቀደም ሲል በተለያዩ ፕላት ፎርሞች ሥራዎችን ለመሸጥ በሚደረገው ጥረት፣ የኮንትራት ስምምነት ላይ ችግር መኖሩን እሰማለሁ፡፡ ከአርቲስቱ ይልቅ ፕላት ፎርሙን የፈጠሩ ግለሰቦች የበለጠ ተጠቃሚ ናቸው የሚባልም ነገር ነበር፡፡ አሁን ግን ድምፃውያኑ በስማቸው፣ በራሳቸው ዩቲዩብ ከፍተው ሰብስክራይብ በሚያደርገው ሰው ልክ በሥራዎቻቸው የተሻለ ገቢ የማግኘት ዕድላቸው ይሰፋል የሚል ሐሳብ አለ፡፡ እኔም ይህንን እጋራለሁ፡፡ ችግሩ ግን ቴክኖሎጂው ከኢትዮጵያ የሙዚቃ አድማጭ ጋር እኩል በእኩል እየሄደ ነው የሚለው ነው፡፡ ሙዚቃን በዩቲዩብ ሰብስክራይብ አድርጎ የሚጠቀም ማኅበረሰብ ፈጥረናል የሚለው ጥያቄም ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ ቴክኖሎጂው እኛ አገር ካለው ሁኔታና አሠራር ጋር ሲነፃፀር ትንሽ የፈጠነ ይመስለኛል፡፡ አንዳንዴ ይህ ነገር ድምፃውያኑንና ሙዚቃዎቻቸውን ፈተና ውስጥ እንዳይከተው የሚል ሥጋት ያድርብኛል፡፡ ትንሽ የልምምድ ጊዜ የሚጠይቅ ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡ በቴክኖሎጂ የሚደገፉ እንደ ኔትዎርክና ኮኔክሽን የመሳሰሉ ነገሮች ለማኅበረሰባችን እምብዛም ቅርብ አይደሉም፡፡ በቴፕ ሪከርደር ሙዚቃ ስንሰማና መኪና ውስጥ ሙዚቃ ስናዳምጥ ለኖርን ሰዎች፣ ምቾቱ ትንሽ ራቅ ያለና ፈተና ያለው ይመስለኛል፡፡ ዞሮ ዞሮ እስኪለመድ ለትንሽ ጊዜ መስዋዕትነት መከፈሉ አይቀርም ብዬ እገምታለሁ፡፡ ወጣት ድምፃውያኑን ነገ በተሻለ ቦታና ከፍታ ላይ እናያቸው ዘንድ በዩቲዩብ ያለው ግብይትም ብቻውን በቂ አይሆንም፡፡ የጥበብ ሥራ ውጤታማነቱ በገንዘብ የሚለካ ባይሆንም፣ እሱም በገንዘብ ካልተደገፈ አርቲስቶቹ ጥልቅ ነገር መሥራታቸውን ያቆሙና ርካሽና ለገበያ ብቻ የሚሆን ሥራ እንዲያቀርቡ ሊገደዱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህም በሚዲያ፣ በማስተዋወቅና፣ በቀጥታ ሥራቸውን በማቅረብ መደገፍ ይገባቸዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡    

ሪፖርተር፡- በአንጋፋ ድምፃውያን የተሠሩ የቀደሙ የሙዚቃ ሥራዎች በወጣት ድምፃውያን እንደገና ተሠርተው እየሰማናቸው ነው፡፡ በድጋሚ መሠራታቸው በሙዚቃ ዕድገት ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ ይኖር ይሆን? ከመብትስ አንፃር?

አቶ ሠርፀፍሬ፡- የሮያሊቲ መብት መከበር እንዳለበት የሚደነግግ ሕግ አለ፡፡ የቅጂና የተዛማጅ መብቶችን የሚያስጠብቁ ሕጎችም ወጥተዋል፡፡ በአፈጻጸም ደረጃ ግን ዛሬም ሊታዩ የሚችሉ ችግሮች ይኖራሉ፡፡ የቀደሙ ሙዚቃዎችን በድጋሚ መሥራት በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎች አገሮችም የተለመደና የሚሠራበት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም የቀደሙ ሥራዎችን አሻሽሎ መጫወት ለትውልድ መልካም ነገሮችን ለማቅረብ አንዱ መንገድ እንደሆነ ይታሰባል፡፡፡ ይህ በራሱ ችግር የለውም፡፡ ለምሳሌ በውጭው ዓለም እነ ማይክል ቦልተን የሌሎች የቆዩ ድምፃውያንን ሥራ እንደ አዲስ ግሩም አድርገው ሲጫወቷቸው ሰምተናል፡፡ የእነ ፍራንክ ሲናትራን ዘፈን ውብ አድርገው ሲያዜሟቸው ተመልክተናል፡፡ እኛ አገር በቅርቡ ዳዊት ጽጌ የእሳቱ ተሰማን ቤተሰቦች መብታቸውን አክብሮና የሚጠበቅበትን ክፍያ ከፍሎ የድምፃዊውን ቆየት ያሉ ሥራዎች ውብ አድርጎ በድጋሚ ሠርቷቸዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ባህል በሌሎችም ድምፃውያን መለመድ አለበት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ አንጋፋ ድምፃውያን ‹ሥራችን ያላግባብ ተወሰደብን› ብለው ጥያቄ ሲያነሱም እሰማለሁ፡፡ አያሌው መስፍን ለጋሻው አዳል የሰጠውን ዘፈን፣ አንድ ድምፃዊ ያለ ፈቃድ ተጫውቶት ቅሬታውን ሲያቀርብ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ይህ አግባብ አይደለም፡፡ አርቲስቶቹ በሕይወት ባይኖሩ እንኳን፣ ቤተሰቦቻቸው የመብቱ ባለቤቶች በመሆናቸው እነሱን አክብሮና የሚገባውን ዕውቅና ሰጥቶ፣ የገንዘብ ውል ካለም ተዋውሎ ሥራዎቹ ቢሠሩ መልካም ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያን ሙዚቃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ወጣት ድምፃውያን ምን ማድረግ አለባቸው ይላሉ?

አቶ ሠርፀፍሬ፡- አንድ ድምፃዊ የተሻለ ሥራ ይዞ እንዲቀርብና ሙዚቃውም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደማጭ እንዲሆን፣ ይህን አድርግ ተብሎ በአንድ መንገድ የሚገለጽ አይሆንም፡፡ ነገር ግን ሥር የሰደደ ልምምድ ሙዚቃን ከፍ እንደሚያደርግ እረዳለሁ፡፡ በጣም ትኩረት ያለው ልምምድ፣ ጣዕም የመፈለግና ብዙ ጣዕሞችን የማጣጣም ጉዳይ ፈጠራን እጅግ የሚያሳድግ ይሆናል፡፡ በጣዕም ያለ መገደብና አዕምሮን የማስፋት ጉዳይ ቢኖር ጥሩ ሥራ የመሥራት አቅም ይጨምራል ብዬ አምናለሁ፡፡ አንድ ተማሪ ዕውቀቱን ለማሳደግ የንባብ ልማዱን ማዳበር እንደሚኖርበት እንደሚመከር ሁሉ፣ ድምፃውያንም የተሻለ ሥራ ይዘው ለመቅረብ የተለያዩ የሙዚቃ ጣዕሞችን በልምምድ ማዳበር ይገባቸዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ይህ ነው ተብሎ የሚነገር የተለየ መላ አለ ብዬ አላስብም፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...