Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሕክምና የሚሻው ቤተ ሕክምና

ሕክምና የሚሻው ቤተ ሕክምና

ቀን:

ከአንድ መቶ ሃያ ስምንት ዓመታት በፊት ወራሪውን የጣሊያን ሠራዊት ከአገር ለማባረር ወሳኝ ጦርነት የተካሄደበት ቦታ ዓድዋ ነበር፡፡ በተራራማው አካባቢ በተደረገው ጦርነት ድሉን የጨበጡት ኢትዮጵያውያኑ ከሕይወት መስዋዕትነት እስከ አካል ጉዳት በመክፈል ነበር፡፡

በየካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ፍልሚያ ጉዳት የደረሰባቸው ቁስለኞች ሕክምናን ያገኙበት፣ እንዲያገግሙ የተደረገበት ቦታ ከዘጠኝ አሠርታት በፊት ሆስፒታል ተገንብቶበት ለአካባቢው ኅብረተሰብም ሆነ ከትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ሕሙማንን ሲያክም ኖሯል፡፡

የሆስፒታሉ መጠሪያም ለዓድዋው ጦርነት ድል መገኘት ወሳኝ አመራር ይሰጡ ከነበሩት ግንባር ቀደም አዝማቾች መካከል አንዱ በነበሩት በራስ መንገሻ ዮሐንስ ስም እስከ የደርግ መንግሥት መምጣት ድረስ ይጠራ ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በታሪካዊው ቦታ በታሪካዊው የጦር ጀግና ስም ይጠራ የነበረው ሆስፒታል በአሁኑ ጊዜ በዓድዋ ስም ነው የሚታወቀው፡፡

የሆስፒታሉ የማስፋፊያ ግንባታ ፕሮጀክት ከስድስት ዓመታት በፊት ተጀምሮ እየተሠራ ሳለ ተግባሩ እንዲቋረጥ ያደረገው ዐብይ ክስተት በክልሉ ከሦስት ዓመታት በፊት የተፈጠረው ጦርነት ነው፡፡

በሆስፒታሉ ላይ ጦርነቱ የከፋ ሁኔታ ፈጥሮበታል፡፡ ሕንፃው ከመቆሙ በቀር በውስጡ የነበሩት የሕክምና መሣሪያዎችና የአገልግሎት መስጫ ቁሳቁሶች ተዘርፈዋል፣ ተወስደዋል፡፡

ሆስፒታሉን ዳግም ወደ ነበረበት ለመመለስ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር የተውጣጡ የአካባቢው ተወላጆች ኮሚቴ አቋቁመው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

ለዓድዋ አጠቃላይ ሆስፒታል ዓለም አቀፍ የድጋፍ ቡድንን ካደራጁት አንዱ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ፀጋዬ በርሔ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

እሳቸው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጦርነቱ እንደመጣ ሁሉም ንብረት ተወስዷል፣ ሕንፃው ብቻ ነው የቀረው፡፡

ሰላሙ ከመጣ በኋላ ሆስፒታሉን መመልከታቸውን የተናገሩት ፀጋዬ (ዶ/ር)፣ ‹‹አልጋም፣ ፍራሽም የለም፡፡ መጠለያ ነው የሚመስለው፤›› ብለዋል፡፡

ዓድዋ ከኤርትራ ድንበር 40 ኪሎ ሜትር ርቀት መገኘቱ በተደጋጋሚ ለዘረፋ ተጋልጧል፡፡

‹‹የኤርትራ ወታደሮች ሁለትና ሦስት ጊዜ እየተመላለሱ ዘርፈውታል፤›› ያሉት የአስተባባሪ ኮሚቴው አባል ትምህርት ቤቶችና ጤና ጣቢያዎችም ከመዘረፍ አለመዳናቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህንን ጉዳት የደረሰበት ሆስፒታል ደግሞ ነፍስ ለመዝራት ከለንደን ወ/ሮ ሊሊ ፀጋዬ፣ ከአትላንታ አቶ ቴዎድሮስ ሐጎስና እሳቸው በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚገኙ የአካባቢውን ተወላጆች በበይነ መረብ በማገናኘት ‹ዓለም አቀፍ የድጋፍ ቡድን ለዓድዋ አጠቃላይ ሆስፒታል› የሚል ተቋም መፍጠራቸውን ገልጸዋል፡፡

ተልዕኮውን በተመለከተ ቡድኑ በድረ ገጹ እንዳሠፈረው፣ በአሁኑ ወቅት በዓድዋ ያለውን አስከፊ የጤና ሥርዓት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ይሠራል፡፡

‹‹የእኛ ተልዕኮ ሕይወት አድን የሕክምና አገልግሎቶችን መስጠት፣ የሕክምና ቁሳቁዎችን ማቅረብና የጤና ሥርዓቱን ማሻሻል ነው፡፡››

የዓድዋን ሆስፒታል ለማዳን በተጀመረው እንቅስቃሴ የመጀመሪያ ዕቅዳቸው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ማዘጋጀት እንደሆነ የገለጹት ፀጋዬ (ዶ/ር)፣ 180 ሺሕ ዶላር ለማሰባሰብ ታልሞ፣ የተሳካው 178 ሺሕ ዶላር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የተሰባሰበው ገንዘብ ካለው ፍላጎት አንፃር ብዙም የሚያስገዛ ባይሆንም፣ በዕርዳታ ለምናገኛቸው ለማጓጓዣና በመጠኑም ለማደስ ለማዋል አስበናል ብለዋል፡፡

የካቲት 23 ቀን በሚከበረው የዓድዋ ድል በዓል አጋጣሚ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር መዘጋጀቱን፣ ለዚህም ኮሚቴ መቋቋሙን፣ መሪ ቃሉም ‹‹የዓድዋ ድል ለዓድዋ ልማት›› የሚል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ኅብረተሰቡም ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከነባሩና ታሪካዊው ሆስፒታል በተጨማሪ በቀጣይ የታቀደው በክልሉና በፌዴራል መንግሥት አማካይነት የተገነባውና ቀሪ ሥራዎች የሚቀሩት እንዲጠናቀቅ ማድረግ እንደሆነም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በጦርነቱ በከፋ ሁኔታ ዝፊያ የተፈጸመበት የዓድዋ ሆስፒታልና አካባቢው በመሆኑ፣ የፌዴራል መንግሥትም ሆነ ክልሉ ተገቢ ትኩረት እንዲሰጡትም ጠይቀዋል፡፡.

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...