Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበገንዘብ ዕጦት የሚፈተኑ የሴቶች ማኅበራት

በገንዘብ ዕጦት የሚፈተኑ የሴቶች ማኅበራት

ቀን:

በባህልና በተለያዩ ምክንያቶች በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስቀረት የሚደረግ ጥበቃና እንክብካቤ ከጉዳት የሚታደገው ሴቶችን ብቻ ሳይሆን፣ ልጆችን ቤተሰብንና አገርን ነው፡፡

‹‹ሴትን መበደል አገርን መበደል ነው›› እንደሚባለው፣ አገርን ከጥፋትና ከውድቀት ለመታደግ እንዲሁም ኑሮን ምቹና ሰላማዊ ለማድረግ ሴቶችን ከጓዳ በማውጣት ወደ መድረክ ማምጣት አስፈላጊ ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ።

የሥርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ፣ የሴቶችን መብት ለማስጠበቅ እንዲሁም ሴቶችን ከሚደርስባቸው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫናዎች ማላቀቅና ተሳትፏቸውን ከፍ የማድረግ ጉዳይ መንግሥትን ጨምሮ የተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶችን ንቁ ተሳትፎ የሚሻ ነው።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ለዚህም ኢትዮጵያ ሴቶችና ሕፃናትን አስመልክቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ የወጡ የሕግ ማዕቀፎችንና የተደረጉ ስምምነቶችን መቀበሏ እንደ ጥሩ መነሻ የሚያገለግል ነው፡፡

ሆኖም ሴቶችና ሕፃናትን መሠረት አድርገው የሚቋቋሙ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ በጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚቋቋሙበትን ዓላማ ለማሳካት ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች እንደሚያጋጥሟቸው፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት (ኢሴማቅ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሳባ ገብረ መድኅን ተናግረዋል፡፡

የሴቶች ማኅበራት አበረታች ውጤቶችን እያስመዘገቡ ቢሆንም፣ ከፍተኛ የገንዘብ ችግር እንደገጠማቸው ወ/ሮ ሳባ ያስረዳሉ፡፡ ድርጅቶቹ የሴቶችን ችግሮች ከማቃለል አንፃር እየሠሩ ያለው መልካም ሥራ በመንግሥት አካላትና በሌሎች ዘንድ አለመታወቅና ጎልቶ አለመታየት፣ በሴቶች ማኅበራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያደረሰ እንደሆነም ያክላሉ፡፡

እነዚህንና መሰል ችግሮችን ለመፍታትና ማኅበራት የሚሠሩትን ሥራ ለመንግሥት፣ ለረጂ ድርጅቶችና ለሚመለከታቸው አካላት ለማስተዋወቅና በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የውይይት መድረክና ኢግዚቢሽን የካቲት 7 እና 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል ተዘጋጅቶ ነበር።

በውይይት መድረኩ በገንዘብ እጥረት ሥራቸውን ለመሥራት የተቸገሩ የሴት ማኅበራትን ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች ጋር የማስተዋወቅና የማገናኘት ሥራ መሠራቱን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት በሥሩ 37 አባል ድርጅቶች ያሉት ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ሴቶችና ሕፃናት በጎ አድራጎት ማኅበራት የታቀፉ ከ80 በላይ አባል ድርጅቶች እንደሚገኙም አክለዋል፡፡

እነዚህ ማኅበራት በኢኮኖሚ የደከሙ ሴቶችን በማገዝና ድምፅ ላጡ ድምፅ በመሆን ያላቸው ሚና የጎላ ነው የሚሉት ወ/ሮ ሳባ፣ የሴቶችን መብት የሚጋፉ ሕጎች በሚወጡበት ወቅት እንዲቀየሩ፣ የሚወጡ ፖሊሲዎች ሴቶችን ያቀፉ እንዲሆኑ ጥረት እያደረጉ ስለመሆናቸው ያስረዳሉ፡፡

ይሁን እንጂ ከችግሩ ስፋት አንፃር የሴቶች ማኅበራት ብቻቸውን መፍታት ስለማይችሉ መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹ ቢያደርጉ የብዙ ሴቶችን ችግር ከመፍታት አኳያ፣ ተጨባጭ ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ችግሮች ከተከሰቱ በኋላ መፍትሔ ፍለጋ ከመውጣት ቅድመ መከላከል ላይ መሥራት ተገቢ ነው የሚሉት ወ/ሮ ሳባ፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅትም ቅድመ መከላከልን መሠረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን አክለዋል፡፡

ሴቶች ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶችን በተመለከተ ዓለም አቀፋዊ ሕጎችና ስምምነቶች መኖራቸውን የሚናገሩት ደግሞ የ‹‹ሴቶች ይችላሉ›› ድርጅት መሥራችና ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ የምወድሽ በቀለ ናቸው፡፡

ምንም እንኳን ሕጎቹ ቢኖሩም፣ በአሁኑ ወቅት እየተተገበሩ አይደለም የሚሉት ወ/ሮ የምወድሽ፣ ሕጉ ወረቀት ላይ መኖሩ ጥሩ ቢሆንም፣ አፈጻጸሙ ላይ ብዙ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

በሴቶችና በሕፃናት ላይ የሚደርሱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዲሁም ፆታዊ ጥቃቶችን ለመቆጣጠርና ለመከላከል በሴቶች ስም የተቋቋሙ ድርጅቶችና ማኅበራት ብቻ ሊፈቷቸው አይችሉም ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፣ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚገባ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት (ኢሴማቅ) በኢትዮጵያ የሥርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥና የሴቶችን መብት ለማስጠበቅ የተቋቋመ መንግሥታዊ ያልሆነች የሴቶች ማኅበራትና ድርጅቶች ጥምረት ናት፡፡

‹‹ኢሴማቅ›› ከምትሠራቸው ሥራዎች አንዷና ዋነኛዋ ሴቶች የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶችና የሴቶችን ጥያቄዎች ወደሚመለከታቸው መንግሥታዊ ውሳኔ ሰጪ አካላት እንዲሁም ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት በማቅረብ ትኩረት እንዲያገኝና የፖሊሲና የሕግ ምላሽ እንዲሰጥ ማድረግ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...