Saturday, April 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ሁለቱ ወጎች፡ ከሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! እስከ በዓሉ ቤርሙዳ

በተክለ ጻድቅ በላቸው

ሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ!

ከሁለት ሦስት ዓመት በፊት ነው፣ የእንግሊዝኛ መምህራን ማኅበር ቅዳሜ ጧት በየወሩ ይሁን በየሁለት ሳምንቱ የሚሰባሰቡበት በወመዘክር አንድ ኮርነር ነበራቸው። እኔም በተቋማችን ስለቅኔ ትምህርት የጥናት ፕሮጀክት እያካሄድን ስለነበር፣ አንዳንድ በትምህርት አሰጣጥ ዙሪያ ምልከታዎቼን እንዳጋራቸው በአንድ ባልንጀራዬ በኩል ጋብዘውኝ ሄድኩ። ያው በመካከሉ የዘመናዊ ትምህርት ብቻ ሳይሆን በውጭ ቋንቋ ብቻ የማለሉ ባለሃብቶች ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያዊ መካከለኛ ኑሮ ነዋሪዎች እንዲሁም ዳያስፖራው ባህሉንና እሴቱን ቀርቶ ግለታሪኩን እንኳን ለገዛ ልጆቹ ለማጋራት እንዴት እንደተቸገረ ተነሳ።

በፈረንሳይኛ ወይም በእንግሊዘኛ መናገር የዕውቀት ጥግ ተደርጎ በአንዳንድ ያገራችን የግል ትምህርት ቤቶች “አማርኛ መናገር ያስቀጣል” እስከመባል እንደምን ተደረሰ? በዩኒቨርሲቲዎችም በአጠቃላይ በሂዩማኒቲስ በተለይ በአማርኛና በግዕዝ ቋንቋዎች የሚሰጠው ትምህርት ጥራት መቀነስ፤ በሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ የግዕዝ ፈተና መዘንጋት፤ በከፍተኛ ደረጃ ዩኒቨርሲቲዎች (ለምሳሌ አአዩ) ግዕዝን ትተው ቻይንኛ ላይ ማተኮራቸውን እያነሳን ተብሰለሰልን ውይይታችንን ቀጠልን።

“ነፃ አውጪዎች ነን ባዮች” ቋንቋን ከመግባቢያነቱ አስወጥተው ፖለቲከኞች ጨቋኝ ተጨቋኝ የሚል የውሸት ትርክት ፈጥረው የባዕድ ፊደልና ቋንቋ ወሰዱ። አንዱ ወዳጄ እንዳለው አማርኛ የኛ አይደለም ቢሉ እንኳን እንደቅርብ ጎረቤት መዋስ ሲችሉ ሺ ማይልስ ርቀት ከላቲን መዋሳቸው ምን ይሉታል ያለው ትዝብቱ አስታወሰኝ። በዚህ መካከል ብዙ ቤተሰቦች ለተለያዩ ጉዳቶች እንዴት እንደተጋለጡ ማየት ይቻላል። ወላጅ ከልጅ፣ ማኅበረሰብ ከማኅበረሰብ ባይተዋር ወደመሆን ተደርሶአል። አንድ ገጠመኜን ላውጋችሁ። ባለቤቴና እኔ ችካጎ ድኅረ ምረቃ ተማሪዎች ሳለን በበጋው ዕረፍት የጁላይ አራት አሜሪካኖቹ የነፃነት በዓል በሚሉት፣ በችካጎ አካባቢ አፍሪካውያን ሀብታሞች ይደግሱና ሌላውም ያለውን እየያዘ በሚሰባሰብበት አንድ ፓርክ ውስጥ አንዲት እናትና ልጆች አጋጠሙን። (ክርስቶስ ለሥጋው አደላ እንዲባል) እኛም ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ገምተን ተጠግተን ስንጨዋወት በአሥራዎቹ መጀመሪያ ያለችው ታዳጊና እናት መግባባት አቅቶአቸው ሲቸገሩ አየናቸው። ጨዋታችንን በአማርኛ አድርገን ከልጇ ጋር ያላት ግንኙነት ግን በመገረም አየን፣ መቼም እናት እንዴት ብላ ታሪኳን ለልጇ ታወጋታለች? ሌላም ሌላው ተአዝቦቴን ተናግሬ ስጨርስ ቀጥሎ አንዱ የእንግሊዝኛ መምህር ለድኅረ ምረቃ እንግሊዝ አገር በነበረበት የገጠመውን አጫወተን።

በወቅቱ ይጓዝበት በነበረው ባቡር ላይ ያጋጠመችው ሴት ልጇ ባስነጠሰው ቁጥር ብለስዩ (bless you! bless you!) ስትለው በቅርብ ርቀት ስታዘብ ስለነበር፣ እና ኢትዮጵያዊ መሆኗን ስለጠረጠርኩ “ሰላም!” ብያት “ለምን ይማርህ!” ብለሽ አትገላገይም ወይ አሥሬ ብለስ ዩ ከምትዪው አልኳት። እሷም ለልጇ አማርኛ እንዳላስተማረች ነገረችው። ለምን ቢላት። “ምን ያደርጋል? ወንዝ የማያሻግር ቋንቋ!” በማለቷ ብልጭ ብሎበት ቆይ በሰላምታ እንጀምርና እንግሊዞች እንዴት ነው ሰላም የሚባባሉት? ሲላት፤ ጉድ ሞርኒንግ፣ ጉድሞርንኒግ። ያው ውው የጦጣ ቋንቋ ይመስላል። እሽ በአማርኛስ እንዴት ነው? ጤና ይስጥልኝ ወይም እንዴት አደርሽ/ክ? ምላሹስ? እግዚአብሔር ይመስገን።

አዬሽ ወንዝ አያሻግርም ያልሽው ቋንቋ ሰማየ ሰማያት አድርሶ ሲመለስ ያላትን አጋራን። አየሽ ሰማየ ሰማያት አድርሶ ሲመልስ ያለው ዘይገርም ነው!!!።

የበዓሉ ቤርሙዳ ~ ‹‹እምባ እምባ ይለኛል››

ኦሮማይን አባቴ ነበር ያነበበልን። ያኔ ድብቅ በነበረበት ጊዜ በጋዜጣ ተሸፍኖ ማታ ማታ፡፡ በዓሉ ምንም እዚህ ያደርሰኛል ብሎ አንዳላሰበ ነው የሚያሳዬው ቲያትሩ። ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር “አንዱ ብቻ የደርግ አባል ከጠላህ ያልቅልሃል!” ብሎኝ ነበር ይላል። ጓድ መንግሥቱን በተወሰነ መልኩ ንጹህ ያደርገዋል። መንግሥቱ ገና ፎቶው ሲታይ ከዛም ብቅ ሲል አዳራሹ ውስጥ የነበረው ጭብጨባ ይገርማል። መልኩም ትወናውም ቁጭ ነው።

የፊያሜታ ሚና ተወዳጅ መደረግ አግባብ ይሆን? ከጸጋዬ (እሱም ጎበዝ ነው በትወና) ጋር የነበራት እና ፈጣሪዋን በዓሉን የምትገልጽበት ጸጋዬም የሚገልጽበት ግሩም ነው። ግን ሌላኛው በሻዕብያ የተገረፈ ኤርትራዊ ገጸባህርይ የበዓሉ አምሳያ እንዲያውም ለበዓሉ ሞዴል (vicariously suffered and gives hope) ሆኖ የቀረበበት ግን ግነት የሞላበትና ከበዓሉ አልፎ ተውኔቱን የኤርትራ ጉዳይ አስመስሎታል።

የበዓሉን የተጫወተው ልጅ ግሩም ነው ትወናው። መልኩም ከሜካፓ ጋር መስሎታል። ድንጋጤው ከመጀመሪያውም ባይሆን። በድምፅ ትንሽ ቸኮል ቸኮል ባይልማ። በቴሌቪዥን የተቀረጸውን የበዓሉ ድምፁን ትንሽ ዘግዬት ይላል ሲናገር። መሪ ተዋናዩ ሲሸልሙት እምባ በምባ ሆኖ ነበር። መጨረሻ ላይ ከወዳጄ ጋር ሆነን በአድናቆት እጁን ወዝውዘናል።

መርማሪ ሆኖ የሠራውም ጎበዝ ነው። አንድ ሁለት “ቀሽሞች” አይጠፉም። እና በመጨረሻ ላይ መርማሪው ጸጸት ይሰማዋል። ሌላ ደኅንነት መጥቶ ሲተኩስበት ይጨልማል። ምስጢሩ መርማሪው ጋ ነው ያለው። በቲያትሩም በገሃዱም። እሱን የወከለው አሰቃይተው ገድለውትም ሆነ እንዲሁ የሚያውቀው መርማሪው ወይም መርማሪዎቹ ናቸው። ታዲያ በገሃዱ ላይ በቂ ማስረጃ ሳይኖር •••?

ቲያትሩ በእንዳለጌታ መጽሐፍ ላይ የተመረኮዘ እንደሆነ በመክፈቻው ላይ ተነስቶአል። ግን የበዓሉ መሰወር ተገድሎአል ብለን ብንደመድም እንኳን አማሟቱ በስቃይ (በግርፋት /ቶርቸር) ነው ለማለት አያስደፍርም። መረጃ እስካልተገኘ።

ደግሞም የተሻለ መረጃ ያላቸው። በጽሑፋቸውም ከበዓሉ በፊትም ሆነ በኋላ የመጡ ደራስያን ሥልጣን ላይ የነበሩትን ተጋፍጠዋል። ከዛም ተሰቃይተዋል። ተግዘዋል። ተገድለዋል። ለአብነት ያክል አቤ ጉበኛ። ለምን እነሱ ተረሱ? የቲፎዞ ነገር ይሆን? የበዓሉ ሚስትዬው እንኳን አልኖሩ አልኩ። ግን ልጆቹስ ቢሆን የአባት ማጣት የፈጠረባቸው ሕመም አልበቃ ብሎ ተሳቃይቶ ነው የተገደለው የሚል የመርዶ ቲያትር መምጣቱ ድርብ ስቃይ ይፈጥርባቸው ይሆን የሚል ስጋት በእዝነ ልቦናዬ ውልብ አለብኝ።

ቅር ያለኝ ተመልካቹ (ከተመልካቹ መካከል ቀላል ቁጥር አለው የማይባል ቲፎዞ) በአሳዛኝ ድርጊቶች ውስጥም ቢሆን ትወናው ሞቅ ደመቅ ካለ (ለምሳሌ የስቃይ ግርፊያው በዳንስ ወይም በኮሪዮግራፊ ትእይንት ታጅቦ) ስታይ ያጨበጭባሉ፤ ያፉጫሉ፤ ይፈነጥዛሉ፤ ያውካካሉ። መቼስ መንጌን ስለማያውቁት ወይም ከሱ በኋላ ከመጡት የተሻለ ነው እንበል። ለስቃይ ግርፋቱስ? እናም በአሳዛኝ ትዕይንት ደራሲውም ሆነ አዘጋጁ ሊያስፈነጥዙ የፈለጉ አይመስለኝም። በአጠቃላይ ፊልም ላይ ትምህርት literacy ያስፈልጋል እል ነበር። ቲያትርና ሌሎች ኪነጥበቦች ላይም ሳያሰፈልግ አይቀርም። ለተመልካችም (ከደራሲ ከያንኒያን ሐያሲያን በተጨማሪ) ማለቴ ነው።

እምባ እምባ ይለኛል።

ይተናነቀኛል

ግን እምባ የት አባቱ

ደርቋል ከረጢቱ፡፡

እያለ ይገጥማል በዓሉ በመጽሐፉም በቲያትሩም። በቲያትሩ አጋልጥ የሰርጎ ገቦችንን ስም ዝርዝር ጻፍ ሲሉት እንደአዝማች ይደግመዋል። እኔም የአድማጭ ተመልካቹን ሁናቴ እምባ እምባ አስብሎኛል።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles