Monday, April 15, 2024

በርካቶችን ሰለባ ያደረገው የመርአዊ ግድያና የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ማሳሰቢያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች መፈጸማቸው ሪፖርት ቢደረግም እነዚህን ወንጀሎች ለፍርድ ለማቅረብ ሲሠራ እንደማይታይ፣ በጄኔቫ የሚገኘው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ዓምና ባካሄደው ጉባዔ ላይ በጉልህ ገልጾ ነበር፡፡ የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ሪፖርት ያደመጠው በስተኋላም ምክር ቤቱ የመደበውን የሰብዓዊ መብቶች አጣሪ ገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን ግኝት የተከታተለው ምክር ቤቱ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች ተጣርተው ለሕግ የሚቀርቡበት ዕድል ደካማ ነው በማለት ከባድ ወቀሳ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

ዓምና በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ከትግራይ ሸማቂዎች ጋር ሲደረግ የቆየው ግጭት በመቆሙ፣ የሰብዓዊ መብት ወንጀሎችና ሰብዓዊ ቀውሱ ስለመቀነሱ ብዙ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ መስከረም ላይ ሪፖርት ያቀረበው የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ያቋቋመው በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ወንጀሎችን እንዲያጣራ የተመደበው ገለልተኛ የባለሙያዎች አጣሪ ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ቀውስ በፕሪቶሪያ ስምምነት ብቻ የሚቆም አለመሆኑን አስታውቆ ነበር፡፡

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በተወሰኑ አካባቢዎች የጥይት ጩኸትን ቢያስቆምም፣ የኢትዮጵያን ችግር ግን ሙሉ ለሙሉ አልተፈወሰም ነበር ያለው፡፡ በትግራይ ክልል ሰላም የሰፈነና ሁኔታዎች የተሻሻሉ ቢሆንም፣ በአማራና በሌሎች ክፍሎች ግን ከፍተኛ ግጭቶች ይስተዋላሉ፡፡ እነዚህ ግጭቶች ደግሞ የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳይቀረፉ እያደረጉ ነው በማለት ነበር ኮሚሽኑ የገለጸው፡፡

‹‹የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት በኢትዮጵያ ያሉ ግጭቶችን ሙሉ ለሙሉ አላስቆመም፣ በአገሪቱ ሁለንተናዊ ሰላምም አልፈጠረም፤›› በማለት ሪፖርቱ ሁኔታውን ገልጾታል፡፡ በኢትዮጵያ የጅምላ ግድያ፣ የአስገድዶ መድፈር፣ ማስራብ፣ ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማትን ማውደም፣ ከቤት ንብረት ማፈናቀል፣ አሻሚ የሆኑ የጅምላ እስራቶች በከፍተኛ ሁኔታ መፈጸማቸው ቀጥሏል በማለት ነበር ኮሚሽኑ በዓለም አደባባይ ፊት ኢትዮጵያን የወነጀለው፡፡

በአማራ ክልል ጦርነቱ ከተጀመረ ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህም ቢሆን፣ በተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች ስለመፈጸማቸው ሪፖርት እየተደረገ ነው፡፡ ከጎጃም ደብረ ኤልያስ ጀምሮ፣ በደብረ ማርቆስ፣ በፍኖተ ሰላም፣ በአማራ ሳይንት፣ በሰሜን ሸዋ፣ በጎንደር እስቴ አካባቢ በአማራ ክልል ግጭቱ ከጀመረ ወዲህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመውባቸዋል ተብለው ይጠቀሳሉ፡፡

አሁን ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ዞን መርአዊ ከተማ በርካቶችን ሰለባ ያደረገ ግድያ መፈጸሙን ሪፖርቶች አረጋግጠዋል፡፡ ይህ አጋጣሚ ባለፉት አምስት ዓመታት ከደረሱ ማንነትን ዒላማ ካደረጉ ጥቃቶች ጋር ተደማምሮ እየቀረበ ይገኛል፡፡ በምዕራብ ጎጃም መርአዊ ከተማ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ስለተፈጸመው ጭፍጨፋ ቀድሞ ሪፖርት ያደረገው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)፣ ጥቃቱ የተፈጸመው በአካባቢው በፋኖና በመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች መካከል ግጭት መካሄዱን ተከትሎ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡

በግጭቱ አንዳችም ተሳትፎ የሌላቸው ከ80 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ያለው ኢሰመጉ፣ ክስተቱ በሁለት መንገዶች መፈጠሩን ገልጾ ነበር፡፡ በግጭቱ ወቅት የነበረው ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ የተወሰኑ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉን፣ በሌላ በኩል ቤት ለቤት በመሄድ በንፁኃን ላይ ግድያ መፈጸሙን ማረጋገጡን አስታውቆ ነበር፡፡

ከተገደሉት በተጨማሪም የአካል ጉዳት፣ ድብደባ፣ ማስፈራራትና ሌሎችም የመብት ጥሰቶች በመርአዊ ከተማ መፈጸሙን እንዳረጋገጠ መግለጹ አይዘነጋም፡፡ ከጥር 21 ቀን ጀምሮ የሟቾችን አስክሬን በጅምላ ጭምር ሕዝቡ እንደቀበረ ገልጿል፡፡ ኢሰመጉ እንደሚለው የአካባቢው ሕዝብ በተፈጸመው ጭፍጨፋ ባደረበት ድንጋጤ አካባቢውን ለቆ እስከ መሰደድ የደረሰበት አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡

በአማራ ክልል እንደ አስፈላጊነቱ ደግሞ በመላ አገሪቱ ተፈጻሚ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ኢሰመጉ አውስቷል፡፡ ይህን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተፈጻሚነት የሚከታተል መምርያ ዕዝ መቋቋሙንም ገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ ዕዙ በተገቢው ሁኔታ አስፈላጊ መረጃዎችን ማጋራት ላይ ክፍተት ይታይበታል ሲል ነው የገለጸው፡፡ ይህ ሁኔታ እያለ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም ማድረጉ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሥጋቱን የበለጠ ያጎላዋል በማለት ነው ያብራራው፡፡

ኢሰመጉ ይህን ጉዳይ ሪፖርት ካደረገ ከቀናት በኋላ የራሱን ግኝት ይዞ የመጣው መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በበኩሉ፣ በምዕራብ ጎጃም ዞን በመርአዊ ከተማ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ቢያንስ 45 ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸውን አረጋግጫለሁ ሲል ሪፖርት አውጥቷል፡፡ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በመንግሥት ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከማለዳው 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ውጊያ ሲካሄድ ማርፈዱን ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡ ውጊያውን ተከትሎ ደግሞ የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች የፋኖ አባላት ናቸው በሚል ጥርጣሬ የተያዙና ለፋኖ ድጋፍ አድርገዋል ያሏቸውን ሰዎች ከሕግ ውጪ መግደላቸውን እንዳረጋገጠ ኢሰመኮ በሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡

ኢሰመኮ የዓይን እማኞችን ምስክርነት ዋቢ አደረግኩ ብሎ ባቀረበው ሪፖርት፣ በከተማው ተኩስ ድንገድ ሲከፈት በድንጋጤ በአንድ ቦታ የተጠለሉ 18 ሰዎች ተገድለዋል ይላል፡፡ ቀበሌ 02 በተለምዶ ሚሊኒየም ተብሎ በሚጠራው ሠፈር የጠፋ አባላችንን በደንብ አላፋለጋችሁንም በሚል የፀጥታ ኃይሎች ስምንት ሲቪሎችን መግደላቸውንም በሪፖርቱ ተካቷል፡፡ ኢሰመኮ ከዚህ በተጨማሪም 12 ባጃጆችን የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች አቃጥለዋል ይላል፡፡

የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ውጊያ ካደረጉ በኋላ ቤት ለቤት አሰሳ መደረጉን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡ በፍተሻው እንዲሁም በመንገድ ላይ የተገኙ ቢያንስ 15 ሰዎች ሴቶችን ጨምሮ መገደላቸውን ነው የገለጸው፡፡

የመርአዊ ግድያን ተከትሎ በአማራ ክልል አስከፊ ገጽታን እየተላበሰ የመጣው ጦርነት የሚያበቃው መቼ ነው የሚል ጥያቄ ከየአቅጣጫው እየተስተጋባ ይገኛል፡፡ በግጭቱ ሰለባ ከሚሆኑ ሰዎች በተጨማሪ ንፁኃን ዜጎችና መላው የክልሉ ሕዝብ ለጉዳት መዳረጋቸው አሳሳቢ መሆኑ በተደጋጋሚ እየተነሳ ነው፡፡ ግጭቱ በአስቸኳይ ካልቆመ የክልሉ ሰቆቃ እንደማያባራ ሥጋት እየተነሳ ነው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአማራ ክልል ጦርነቱ እንደጀመረ አካባቢ ሪፖርት ያወጣ ሲሆን፣ በግጭቱ 200 ያህል ሰዎች ሰለባ መሆናቸውን ገልጾ ነበር፡፡ በጊዜው በጦርነቱ ድሮን ጭምር ጥቅም ላይ እየዋለ ነው ብሎ፣ በግጭቱ የሰላማዊ ዜጎች ሕይወት አደጋ ላይ መውደቁ እንዳሳሰበው አስታውቆ ነበር፡፡

ግጭቱ ቆሞ በሰላማዊ መንገድ የአማራ ክልል ቀውስን ለመፍታት እንዲሞከር ከብዙ አቅጣጫ ውትወታ ቢደረግም፣ እስካሁን ሰላማዊ የችግር አፈታት ጥረቶች ሲደረጉ አልታዩም ነው የሚባለው፡፡ ግጭቱ ተባብሶ መቀጠል ደግሞ ለጉዳት የሚጋለጡ ሰዎችን ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉ ነው የተነገረው፡፡

በአማራ ክልል በጦርነቱ ሳቢያ በርካታ የመሠረተ ልማትና መንግሥታዊ አገልግሎቶች ተቋርጠዋል፡፡ ከመብራት፣ ከኢንተርኔትና ከትራንስፖርት አገልግሎት ጀምሮ የሸቀጦች አቅርቦት መስተጓጎል መፈጠሩ ብዙዎችን ችግር ላይ ጥሏል ይባላል፡፡

በአማራ ክልል የተፈጠረውን ግጭት በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት መቆጣጠር ባለመቻሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለፉት ስድስት ወራት ታውጇል፡፡ እንደ አስፈላጊነቱ በመላው የአገሪቱ ክፍል ተፈጻሚነት ይኖረዋል የተባለውን ይህን አዋጅ ደግሞ ለሚቀጥሉት አራት ወራት እንዲራዘም የሚያደርግ ውሳኔ በቅርቡ በተወካዮች ምክር ቤት ተወስኗል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም ደግሞ የዜጎች መሠረታዊ መብቶች የበለጠ እንዲጣስ በር የሚከፍት ነው የሚል ስሞታ ሲያስነሳ ነው የቆየው፡፡ ተመድ እንደሚለው ከመሠረታዊ የመንቀሳቀስ መብት ጀምሮ ሕግ ለማስከበር ብዙ ንፁኃን ዜጎችን በጅምላ መቀጣት (Collective Punishment) የሚዳርግ ነው የሚለውን ሥጋት አጉልቶታል፡፡

በአማራ ክልል መርአዊ የደረሰውን ግድያ ዓለም አቀፉ የአማራ ጥምረት አውግዞታል፡፡ ነፍሰጡር፣ ሴት፣ ሕፃን፣ የሃይማኖት አባትና አረጋዊ ሳይል በግፍ ንፁኃን መጨፍጨፋቸው የመንግሥትን ኃላፊነት የጎደለው አካሄድ እንደሚያሳይ ጥምረቱ አመልክቷል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ በውጭ የሚንቀሳቀሱ የአማራ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ የሲቪክ ማኅበራት ድርጅቶችና መገናኛ ብዙኃን ከየአቅጣጫው በመንግሥት ላይ ውግዘት ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡ ቁጥራቸው ውስን ቢሆንም በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ጉዳዩ ያሳሰባቸው መሆኑን ባወጡት መግለጫዎች ሲገልጹ ሰንብተዋል፡፡

ከአማራ ድርጅቶችና ሚዲያዎች ውጪም እንደ አሜሪካ መሰል አገሮች ጉዳዩ እንዲጣራ በይፋ ሲጠይቁ ታይቷል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት የመርአዊ ጭፍጨፋ እንዲጣራ ከመጠየቅ በተጨማሪ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጊዜ ገደብ ለተጨማሪ አራት ወራት መራዘሙ እንዳሳሰበው ሲገልጽ ታይቷል፡፡

ይሁን እንጂ ከጥቂት ድርጅቶችና አገሮች ውጪ የመርአዊውን ጉዳይ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሲያነሱት አለመታየታቸው አነጋጋሪ ሆኖ ነው የሰነበተው፡፡ ለወትሮው በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ጉዳይ ላይ መግለጫና ሪፖርት በተደጋጋሚ በማውጣት የሚታወቁት ሂዩማን ራይትስዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶችና ሌሎችም በጉዳዩ ላይ ዝምታን መምረጣቸው ያልተለመደ እንደሆነ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ስለመርአዊው ግድያ ለቪኦኤ አማርኛ ማስተባበያ ሰጥተዋል፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱ ሲቪሎችንም ሆነ የሲቪል ተቋማትን ዓላማ አድርጎ እንደማያውቅ ተናግረዋል፡፡ ‹‹መርአዊ በአራት አቅጣጫ ፅንፈኛው ኃይል መከላከያውን ሊያጠቃ ሲሞክር አፀፋ ተወስዷል፡፡ እነዚህ ኃየሎች ዩኒፎርም የላቸውም፡፡ ሲፈልጉ ታጣቂ ሲፈልጉ ሲቪል ይሆናሉ፡፡ መከላከያ ዕርምጃ ሲወስድ በየቤቱ ገብተው ሲቪል ለመሆን ሲሞክሩ እንጂ፣ ሆን ተብሎ በሲቪሎች ላይ የተወሰደ ዕርምጃ የለም፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የመርአዊው ግድያ አስደንጋጭና በአማራ ክልል ያለው የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ አሳሳቢ መሆን፣ በአገር ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች በጉልህ ተነስቷል፡፡ በአማራ ክልል የሚካሄደው ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ዕልባት እንዲያገኝም እነዚህ ወገኖች እየወተወቱ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ከመርአዊ ግድያ በኋላም ቢሆን ይህ ውትወታ ሰሚ ጆሮ ማግኘቱን የሚያጠራጥሩ ዜናዎች መሰማታቸው የቀጠለ ይመስላል፡፡

በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በኩል በፋኖ ኃይሎች ላይ የሚወሰደው ዕርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን የሚገልጹ መረጃዎች እየተሰሙ ነው፡፡ በተቃራኒው በፋኖ ደጋፊ ሚዲያዎች በኩል በየግንባሩ ስለተመዘገቡ ድሎች ተደጋግሞ ሲዘገብ ይደመጣል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት ሚዲያ የካቲት 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መረጃ ሠራዊቱ በአጭር ጊዜ በአማራ ክልል ተደቅኖ የነበረውን አደጋ በመቀልበስ ውጤታማ ሥራ መሠራቱን ይገልጻል፡፡ ፅንፈኛ የሚለውን የፋኖ ኃይል መከላከያው ደምስሶ በአማራ ክልል የዞንና የወረዳ ከተሞችን ነፃ ማውጣቱን መረጃው ይጠቁማል፡፡ የፅንፈኛውን ህልም በማክሸፍም የክልሉን ሕዝበ የማረጋጋት ሥራ መሠራቱንም አስታውቋል፡፡

የመከላከያው ሚዲያ ዘገባውን ሲቀጥልም፣ ‹‹ጎጃምና አካባቢውን ወደ ሰላም የመመለስ ሥራ መሠራቱ ለክልሉ ኢኮኖሚ መነቃቃት ትልቅ ሚና አለው፤›› ሲሉ የጦር አዛዦች መናገራቸውን ጨምሮ ነው፡፡

ከግራም ከቀኝም ደመሰስን እንዲሁም አፀዳን የሚሉ መረጃዎች ሲወጡ ቢደመጥም፣ ከእነዚህ በተለየ ሁኔታ ደግሞ የሰላም ጥሪና ግፊት መቀጠሉ ይሰማል፡፡ ይሁን እንጂ የሰላም ንግግር በምን መንገድ ነው መስተናገድ የሚችለው የሚለው ጥያቄ መነጋገሪያ የፈጠረ ጉዳይ ሆኗል፡፡

በቅርቡ የየክልሉ አመራሮችና የፌዴራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአማራ ክልል በ15 ከተሞች ውስጥ ከሕዝብ ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ በእነዚህ የውይይት መድረኮች በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ጋር ንግግር እንዲደረግ ሕዝቡ ሲጠይቅ ተደምጧል፡፡ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡ አንዳንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ታጣቂዎቹ መጀመሪያ ትጥቅ ካልፈቱ ድርድር እንደማይኖር ነበር አበክረው የተናገሩት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -