Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየካቲት አብዮት - ጥያቄዎችሽ ዛሬም እየወዘወዙን ነው!

የካቲት አብዮት – ጥያቄዎችሽ ዛሬም እየወዘወዙን ነው!

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

አጭር መግቢያ

የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከ1960ዎች ወጣቶች ርዝራዦች አንዱ ነኝ፡፡ ኖረው ጎልምሶው፣ ያለፉባችውን ትግልና ለውጥ ነክ ልምዶች ገምግመው ስህተቶችንና ጥፋቶችን አስተውለው ለበለጠ ለውጥ ውስን አስተዋጽኦ (በጽሑፍ) ካዋጡት ውስጥ ራሴን እመድባለሁ፡፡ ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ አደባባይ ብቅ ያሉት ጽሑፎቼ በሙሉ የጥገና ለውጥ ማዕዘንን አጥበቀው የያዙ ነበሩ፡፡ የዚህ አቋም ዋና መነሻዬም ከደርግ በኋላ የኢትዮጵያ አገረ መንግሥታዊ ዓምዶች አከርካሪ በቡድን መጠለፉ ነበር፡፡ ቡድኑ ፖለቲካውንና አባላቱን ዓምዳዊ አውታሮች አድርጎ ባደራጀበት እውነታ ውስጥ፣ ቡድኑን ለመገርሰስ መሞከር የአገርን መፈራረስ እስከ ማስከተል ውጤት ሊኖረው የሚችል ነው፡፡ በጊዜው የመንግሥት አውታር እስከመሆን ጠልቆ የነበረው ቡድን ባሳየው ባህርይም የዚያ ዓይነት ሥጋትን የሚያሳስብ ነበር፡፡ ይህንን የአገረ መንግሥት ዓምዶች ድረስ የዘለቀ ብልሽት የሚቀይር ነገር በመጣ ጊዜ ይምጣ ብሎ ሁሉን ነገር ለግብታዊ ዕጣ መተውም፣ የሎተሪ ጨዋታ ይሆን ነበር፡፡ እነዚህን ሁኔታዎች ለውጥን በጥገና መንገድ መፈለግና መጣርን እጅግ ልኩና የሚበጀው አማራጭ አድርገውት ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የእኔም ጽሑፎች ምሁራዊነትን በማርካት ዓላማ ቢመርም ቢጣፍጥፍም፣ ሀቅን በመተንተን የተገደቡ አልነበሩም፡፡ በገዥው ቡድንና ተቃዋሚዎቹን ያቀራረበ የለውጥ እንቅስቃሴና ጥረት እንዲመጣ አልመው ያቀዱ ነበሩ፡፡ ተቃዋሚዎች ኢሕአዴግን ሳያካትቱ ለውጥ ማምጣት እንደማይችሉ፣ ኢሕአዴግም ተቃዋሚዎቹን በጠንቅነት ሰርዞ ለውጥ ማሳካት እንደማይችል በግልጽ የሚናገሩም ነበሩ፡፡ የደርግ ጊዜና የሌላ አገር ልምዶችን በተቻለ መጠን ሳያድበሰብሱ ለመማሪያነት ሲያቀርቡ፣ የጊዜውን አገዛዝ እውነታዎችና ልምዶች ደግሞ ሲበረብሩ የቆዩት ተጠንቅቀው ነው፡፡ መስተካከልና መቀየር ያለባቸውን ብልሽቶችና ችግሮች የሚያሳዩት በአጠቃላይ ሥርዓቱን በከፊል ጥሩነት እያሽሞነሞኑ ነው፡፡ ያንንም ሲያደርጉ፣ በገዥው ቡድን ሰዎች ዘንድ ለውጥን የመቀጠል ፍላጎትና ድፍረት እንዲያድግ፣ የመንዘርና የመማረክ ጥረትን አይረሱም፡፡ የገዥውን ቡድንና የተቃዋሚዎቹን የተጠማመደ ፖለቲካ ጎጂነት በማሳየት ረገድም፣ ወደ አንዱ ወገን ያደሉ (የአንዱን ገመና አግንነው የሌላው ለማድበስበስ የሚሞክሩ) ተደርጎ ከመፈረጅ የሚጠነቀቁ ነበሩ፡፡

የኢትዮጵያ የለውጥ አመጣጥ የሕወሓት/ኢሕአዴጎችንና የተቃዋሚዎቻቸውንም ሚና የሚሻ የመሆኑ ግንዛቤ፣ በለውጥ ፈላጊዎች አካባቢ አነሰም በዛ ነበርና የጥገና ለውጥ ሐሳቦች ከተለያዩ አቅጣጫ ይሰሙ ነበር፡፡ ከዚህ አኳያ መጋቢት 2010 ዓ.ም. ለመጣው ለውጥ የእኔም ጽሑፎች የበኩላቸውን አዋጥተዋል፡፡ በተለይ በአገር ቤት ውስጥ ለውጥ ጠሪ ጽሑፎችን ሳያዶለዱሙ በማውጣት ረገድ የሪፖርተር ጋዜጣ የተጫወተው ሚና ቀላል አይደለም፡፡

ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. ወደ እዚህ ባሉ የለውጥ ጊዜያት ውስጥ የጻፍኳቸው ጽሑፎች፣ ለውጡ መቀልበስ ሳያገኘው ወደፊት እንዲራመድ የሚታገሉ እንደ መሆናቸውም ብዙ ጥንቃቄና የአገም ጠቀም ብልኃት የተንፀባረቀባቸው ናቸው፡፡ ትችትና ሙገሳ፣ ሬትና ስኳር የተዋደዱባቸው ናቸው፡፡ ስህተቶችንና ጥፋቶችን ከማሳየት ጋር ድጋፍ እንዳይጎዳ እየሳሱ ማቃኛ ሐሳቦችን ወርውረዋል፡፡ የለውጥ ተቀናቃኞች እንዲቀንሱ በመላና በቅስቀሳ ለማገዝ ጥረዋል፡፡ ከበድ ያለ የለውጥ ተግባር የሚጠይቀውን ዝግጁነት ከማሳየት ጋር ብርታት ሰጪ የመልካም ውሸት ቅመም ነስነስ ማድረግንም አልረሱም፡፡ እንደዚያም ሆኖ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ልሂቃን ከሠራናቸው ስህተቶች ጽሑፎቹ የፀዱ ነበሩ ብሎ አፍ ሞልቶ መናገር አይቻልም፡፡ ይህ የአሁኑ ዘለግ ያለ ጽሑፍም ለውጡ እየተፈተነባቸው ያሉ ችግሮች ከደርግና ከኢሕአዴግ ዘመን ጋር ተያይዞ የመጣ ሥር እንዳላቸው እያሳየ፣ ማካካሻ መላ እያፈላለገና ላለማሳሳት እየጣረ ለለውጡ ስኬት የሚታገል ጽሑፍ እንጂ የታሪክ ጽሑፍ አይደለም፡፡

ዛሬ ‹‹አብዮት›› እየተሰጠው ያለው ትርጉም፣ የመንግሥት አመራር ድረስ፣ ‹‹አፍርሶ ከዜሮ መጀመር›› በሚል አገላለጥ ተንሻፎና ተቃሎ አሉታዊ ድምፀት ይዟል፡፡ የስሙ መነሳት በራሱ የብዙ ሰዎችን ስሜት ይጎረብጣል፡፡ በዚህ በኩል ትልቁን አሉታዊ ሚና የተጫወተው ደግሞ ደርግ ነው፣ ግፉን ሁሉ በ‹‹አብዮት›› እና ‹‹በአብዮታዊ ዕርምጃነት›› ያሽሞነሙን ነበርና፡፡ የአሮጌነትና የአዲስነት መስተጋብሮች በተፈጥሯዊ ክንዋኔዎችም ውስጥ አሉ፣ በኅብረተሰብም ውስጥ አሉ፡፡ ቀስ በቀስ የተጠራቀሙ የአዲስነት አላቦችን/ዝንባሌዎችን ሙሉ (ሁለመናዊ) እንዲሆኑ የሚያደርግ ፈጣን ለውጥ አብዮት ይባላል፡፡ በተፈጥሮ ውስጥም ሆነ በኅብረተሰብ ሕይወት ውስጥ አዝግሞትና አብዮት አለ፡፡ በሥነ ሰብዕ ጥናት ረገድ የሰው ልጅ ቁመናዊ (አካላዊ) ልውጠትም ሆነ ማኅበራዊ ልውጠት የአዝግሞትና የአብዮት ቅንብር ያለበት ነው፡፡ ይህች ነጥብ በድፍኗ አብዮት የሚባልን ነገር ማርክስና ሌኒን የሚባሉ ሰዎችና የ1966 ዓ.ም. ተራማጅ ወጣቶች እንዳላመጡብን ለመገንዘብ ትበቃለች፡፡

የኅብረተሰብ አብዮትን በሁለት መልክ መረዳት የተምታታ የግንዛቤ ችግርን ለማቃለል የሚጠቅም ይመስለኛል፡፡ የኅብረተሰብ አብዮት በአንድ ገጹ ካፈጀ አሮጌ የኑሮ ሥልት ወጥቶ ወደ አዲስ ሥልት ለመግባት ኅብረተሰብ በሰፊው የሚነቃነቅበት ነው፡፡ በፍጥነት ለውጥ ነክ መነቃቃት ከእነ ሙቀቱ ወደ ሰፊ ቦታ ይዛመታል፡፡ በዚህ መልክ የተጋጋመ የለውጥ እንቅስቃሴ የፈለገውን ውጤት የማሳካቱ ነገር ሊሰምርለትም ላይሰምርለትም ይችላል፡፡ ለውጡን በማይፈልጉ ኃይሎች ሊመታና ሊሸነፍ ይችላል፡፡ ወይም ውጤቱ ከፊል ሽንፈትና ከፊል ድል ያለበት ሊሆን ይችላል፡፡ የአብዮቱ የቅርብ ውጤት ምንም ሆነ ምን ግን፣ አሮጌውን የሚተካው የአዲስ ኑሮ ዘይቤ፣ ውሎ አድሮ እያዘገመም ቢሆን መሟላቱ አይቀርም፡፡ ተጠራቅሞ የተሟላው የኑሮ ሥልት (መሠረታዊ ለውጥ) የአብዮት መሟላት ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ ከዱሮው ጋር እየተነፃፀረም የአኗኗር አብዮት ስለመደረጉ ይወራል፡፡

የሰው ልጅ በድንጋይ መሣሪያ ይጠቀም በነበረበት ጥንታዊ ዘመን ውስጥ የብረት ነክ መሣሪያ መፈልሰፍ ከጥበብ (ከቴክኖሎጂ) አኳያ አብዮታዊ ክስተት ነበር፡፡ የሰው ልጅ ከድንጋይ መሣሪያ ተላቆ በብረት ነክ መሣሪያዎች መጠቀም የኑሮው ዘይቤ ለመሆን የበቃበት የለውጥ ዘመን ግን ጊዜ የወሰደ ነበር፡፡ የእንፋሎት ሞተርና የኤሌክትሪክ ሞተር ጥበቦች በየተፈለሰፉበት ዘመን ከጥበብ ዕርምጃ አኳያ ዕመርታዊ (አብዮታዊ) ነበሩ፡፡ የኅብረተሰብ ማኅበራዊ ኢኮኖሚ ውስጥ ዘልቀው አኗኗርን የቀየሩበት (የአብዮት ወቅት) ግን ጊዜ የወሰደ ነበር፡፡ በእኔ ዕድሜ በባለ በከራ ጥብጣብ (Reel Tape) ድምፅና ምሥል ይቀረፅና ይጫወት ነበር፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ሸክላ (ግራማፎን)፣ የካሴትና የ‹ቪኤችኤስ› ቴፕ መጣ፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ ‹ሲዲ› ከች አለ፡፡ ሁሉም በየዘመናቸው የሕዝብ ኑሮ ውስጥ እየተዛመቱ ነባር ጥበብን (ቴክኖሎጂን) ከሥራ ውጪ አድርገዋል፡፡ የዲጂታል ጥበብ ደግሞ ይኼው ብዙ ምርጥና ትኩስ የጥበብ ውጤት ብለን የገዛናቸውን ነገሮች አሮጌ ነገር እያደረገ ነው፡፡ ዛሬም አዳዲስ ነገሮች እየተፈለሰፉ ነው፡፡ ተፈልስው በአውሮፓና በአሜሪካ ሕዝብ ኑሮ ውስጥ ያልገቡ፣ እዚያ መስረፅ ጀምረው እኛ ዘንድ ግን ያልደረሱ ጥበቦችም አሉ፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ የጥበብ ውጤቶች የኑሯችን አካል እየሆኑ አኗኗራችንን ከመለወጣቸው አኳያ፣ የዛሬ ዘመን ኑሯችን በተከታታይ አብዮት ውስጥ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ካሴቶች ከእነ ማጫወቻቸው፣ ሲዲዎች ከእነ ማጫወቻቸው፣ የደረቅና የተንቀሳቃሽ ምሥል ካሜራዎቻችን፣ ወዘተ. ሁሉ እጃችን ላይ አሮጌ ዕቃ የሆኑት፣ ልብ ባላልነው የለውጥ መዛመት ሒደት ነው፡፡ የሰው ልጅ፣ በቴክኖሎጂ ከአብዮት ወደ አብዮት እየተራመደ ቢሆንም፣ በማኅበረ ኢኮኖሚ ሥርዓት ረገድ ግን አዲስ ለውጥ አላሳየም፡፡ ዛሬም ዓለማችን በአንድ በኩል ሀብት ኃይልና ቅንጦት በጥቂቶች እጅ የተሰባሰበባትና በሌላ አንፃር ሰፊ ዕጦተኝነትና ጉስቁልና የተንሰራፋባት ናት፡፡

የ1966 አብዮት ብዙ ፍላጎቶችና ጥያቄዎች የተገማሸሩበት ልዩ ጊዜ ነበር፡፡ የመንግሥት አስተዳደርን ሳይፈሩ አደባባይ መውጣት የተደፈረበት፣ መናገር መተቸት የተቻለበት፣ ምዝበራዎችና በደሎች እየተጋለጡ የወጡበት፣ የሥርዓት ለውጥን፣ መብቶችንና እኩልነትን የሚጠይቁ ትዕይንቶችና በራሪ ወረቀቶች አደባባይ የወጡበት ጊዜ ነበር፡፡ ‹‹ይህም ነበር እንዴ!›› የሚያሰኙ ነገሮች የተሰሙበት፣ የአፄው ሥርዓት ውዳሴዎች ከጊዜ ጊዜ እየተቦደሱ ሲወደቁ የታየበት ጊዜ ነበር፡፡ ሞቅ በረድ የሚል የሥርዓት ውግዘት፣ የዴሞክራሲ መብቶች ጥያቄ እንደተመላለሰ ሁሉ እንዴት እንሆን ይሆን የሚል ግራ መጋባትም ነበር፡፡ ከልዩ ልዩ ሐሳቦች ጋር መገጣጠም፣ መወያየት/መከራከር፣ በለውጥ አስተሳሰብ አዕምሮን የማበልፀግ ጥማት፣ ወቅታዊ ክንዋኔዎችን ነቅቶ መከታተል፣ ወዘተ. ሁሉ የነበረበት የሙቀት ጊዜ ነበር፡፡

ያም ሆኖ፣ የተበታተነውን የሕዝብ እንቅስቃሴ አቅጣጫ አሲይዞ የሚያተምና የሚያራምድ የተደራጀ የፖለቲካ አስኳል ብቅ አልል ሲል፣ ከወታደራዊ ክፍሉ የወጣ ስብስብ ግራና ቀኝ ተገላምጦ የፖለቲካ መድረኩን ተቆጣጠረ፡፡ ሕዝብና ብዙ ለውጥ ፈላጊውም የወታደራዊ ስብስቡን ትንፋሽና ዕርምጃዎች ጠባቂ ሆነ፡፡ ይህ፣ ያ ይደረግ የሚሉ ጥያቄዎችም ለዚሁ ስብስብ የሚቀርቡ ሆኑ፡፡ የሕዝቡን ቀልብ ከሕዝብ/ከዴሞክራሲ አስተዳደር ጥያቄ ጋር የሚያገናኝ፣ በሕዝብ ንቃተ ህሊናና በድርጅታዊ ዝግጅት ላይ የሚተጋ፣ ለዚሁም ከወታደራዊ ስብስቡ ጋር አብሮ ለመሥራት የሚጥር ልሂቃዊ ማዕከል ከሕዝባዊው አብዮት በኩል አልነበረም፡፡ እናም ያለ ተቀናቃኝ ወታደራዊ ስብስቡ ራሱን በጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥትነት ሾመ፡፡ ያ ጊዜ፣ ጉድ ተሠራሁ የማይባልበት ‹‹ከፊል›› ሽንፈት ነበር ለአብዮቱ፡፡ ከአብራኩ የተገኘ ማዕከል ነገር ፈጥሮና ግቡን አውቆ እየተራመደ አልነበረምና፡፡

ከ1967 ዓ.ም. ወዲህ የሕዝብ እንቅስቃሴዎች በአያሌው ጨምተው መግለጫ ጠባቂነት ውስጥ ቢወድቁም፣ የወጣቶች እንቅስቃሴዎች በየፈርጁ (ቅዋሜዎች በማሰማት፣ ጥያቄዎች በማንሳትና በግልጽና በህቡዕ በመደራጀት ረገድ) ነበሩ፡፡ ደርግ ተራማጅ ልሂቃንን ይዞ ያከታተላቸው የገጠር መሬትና የከተማ ቦታና ቤቶች አዋጆች ዕንከን ባያጣቸውም፣ ባፈጀው ሥርዓት ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ያመጡ ነበሩ፡፡ ከእነዚህ አዋጆች ጋር ተያይዞ የተደራጁት የገበሬና የከተማ ነዋሪዎች ማኅበራትም ለሕዝቡና ለወጣቶች የነቃ እንቅስቃሴ ጥሩ መድረክ ነበሩ፣ የመንግሥታዊው ቢሮክራሲ አሻንጉሊት ከመሆናቸው በፊት፡፡ ተራማጅ ቡድኖች በሲቪሉም በወታደሩም አካባቢ ያስፋፉት የነበረው የኅቡዕ አደረጃጀትም ከወታደራዊ አገዛዝ ለመላቀቅ አቅም ሊሆን የሚችል ነበር፡፡ ከዚህ ዕድል አኳያ፣ ተራማጆቹ ቡድኖች ተጣሞዶ መገዳደል ውስጥ የገቡበት ጊዜ፣ ወደ ሲቪል አስተዳደር የመግባት ዕድልም ከዓይን የራቀበት ጊዜ ነበር፣ ሌላ ሽንፈት፡፡

የ1966 ዓ.ም. አብዮት አሮጌ የመሬት ሥሪት ላይ መሠረታዊ ለውጥ ከማምጣቱና በሒደት የንቃተ ህሊና ዕድገት ከማስገኘቱ በቀር፣ ብዙ መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮች ዛሬ ድረስ አሉ፡፡ ከተፈጥሯዊ ኢኮኖሚና ከድህነት የመላቀቅ ጥያቄ፣ የቡድንና የግል መብቶችም ሆኑ የፍትሕና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች የመጠን ለውጥ በደፋ ቀና ጉዞ ከማጠራቀማቸው በቀር፣ ዛሬም ድረስ በአግባቡ አልተመለሱም፡፡

እያጠፉ አለመማር ዛሬ አልተጀመረም

የ1960ዎቹ ተራማጅ ትውልድ ተቀዳሚ፣ መካከለኛና አፍላ ወጣትነት የነበረን መሆኑ ሳይዘነጋ፣ በደፈናው የፖለቲካ አያያዛችን ከስህተት እየተማረና ይበልጥ ለእውነታ ለመታመን እየጣረ ለመብሰል ባለመቻሉ፣ በኤርትራ ውስጥ የነበረውን ትግል የኢትዮጵያንና የኤርትራ ሕዝቦችን በሚበጅ አቅጣጫ ውስጥ እንዲገባም ሆነ እንዲጠናቀቅ የረባ ሚና መጫወት ይቅርና ትውልዳችንን ከእርስ በርስ መፋጀትና በናቅነው ደርግ ከመበላት ለማዳን አላስቻለንም፡፡

በተከፋፈለና ተጠማምዶ እስከ መቀናደብ ጥፋት ይሠራ በነበረ የውስጥ ፖለቲካችን ምክንያት ኢትዮጵያ አገራችንን ለሶማሊያ ወረራ አጋለጥን (ይህ ጥፋት ደርግንም ይጨምራል)፡፡ የአገር ህልውና ጉዳይ ተቀዳሚ፣ ሌሎች የውስጥ ጉዳዮች መለስተኛ መሆናቸውን ባስተዋለ አቋም አንድ ላይ ለመሠለፍ ባለመቻላችን በአንድ ጊዜ አገራችን በውስጥ የፖለቲካ ትንቅንቅና በውጭ ደግሞ ወረራን የመመከት ድርብ ተግባር እንድትጠመድ አደረግን፡፡ በዚህም ጥፋት ሙሉ ልሂቃዊ አቅሟን ለአገር መከላከል እንድታውል ባለማስቻል፣ እንዲያውም የተወሰነ ክፍላችን የውስጥ እሾህ ከመሆን ባልራቀ ግብግብ በመቀጠሉና የተወሰነ ክፍላችን የተጠማመደ ፖለቲካ ባደረሰው አለመተማመን የአገር ተቆርቋሪነቱ ፍዝ ተመልካች ከመሆን ባለማለፉ አገራችንን ጎዳን፡፡

እናም የአገራችን የወረራ ጥቃት ወደ መሀል እስከ መግፋት በረታ፡፡ ይህንን የከፋ ወረራ የመቀልበስና ድል የመምታት ተግባር ከመደበኛ ሠራዊት ባሻገር ኢመደበኛ ፈጣን ሠራዊት በክተት አዋጅ እስከ ማዘጋጃትና የውጭ ወታደራዊ ዕገዛን (የሩሲያን፣ የኩባንና የየመንን) እስከ ማሳተፍ ጠየቀ፡፡ ያም ሆኖ የተከፈለው መስዋዕትነት ቀላል አልነበረም፡፡

 የሶማሊያ ወረራን የመመከት መሰናዶ በሚደረግበት ጊዜና በትንቅንቁ ሒደት ደርግን በመቃወም ተሠልፈው የነበሩ ብዙ ወጣቶች ጥቃታቸው ከፍቶና ፖለቲካቸው ከስሮ ብዙ ረገፉ፡፡ የእርስ በርስ መበላላቱ በረሃ ድረስ የዘለቀም ነበር፡፡ ሕወሓት የቆሰለውን ኢሕአፓ ለማወራረድ እንዳላቅማማ ሁሉ ኢሕአፓም ራሱን በራሱ በረሃ ውስጥ ከመቀርጠፍ አልተመለሰም፡፡

ከዚህ አሳዛኝ ገጽታ ጋር የሶማሊያን ወረራ በድል ከተገላገልን በኋላም ቢሆን ከደርግ ጋር ተጋግዘው የሶማሊያን ወረራ በመመከት ተግባር ውስጥ ዋናውን የቅሳቀሳና የማነቃነቅ ፖለቲካዊ ሠራ የሠሩት ልሂቃን፣ በድህረ ወረራ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ አያያዙን ስላላወቁበት በየተራ ከመቀርጠፍ አላመላጡም ነበር፡፡ እናም ኢትዮጵያ ከወረራ ብትተርፍም ከ1967-1971 ዓ.ም. የደረሳባት የልሂቃን መርገፍ በወደፊቷ ላይ ረዥም ጉዳት ያደረሰ ነበር፡፡ የረገፈው ረግፎ በደርግ ውስጥ የቀረው ልሂቅ ለመንግሥቱ ኃይለ ማሪያም አጎነበሰ፡፡ ከደርግ ጉያ ውጪ የነበረው በእስርና በፕሮፓጋንዳ ተቀጥቅጦ በፍዝነት አቀረቀረ፡፡ ከቅጥቅጣ በፊትና በኋላም ወደ በረሃና ወደ ውጭ የተሰደደውም ተሰድዶ፣ የከተማው ትግል ባዶ ቀረ፡፡

የሶማሊያን ወረራ በድል መወጣትን የሥልጣን መጠናከሪያው ያደረገው የመንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ደርግ፣ በሶማሊያ ላይ የተቀዳጀውን ድል እያራገበና ‹‹የምሥራቁ ድል በሰሜኑም ይደገማል!›› እያለ ፊቱን ወደ ሰሜን አዞረ፡፡ በኤርትራ ሃርነትነትም ሆነ በሕወሓትነት የነበሩት የትጥቅ ታጋዮች የመጣባቸውን ጦርነት በሽምቅ ሥልት ከመጋፈጥ በቀር በፖለቲካዊ መፍትሔ ለመፈታተን የሚያስችል አተያይ አልነበራቸውም፡፡

የኤርትራ ታጋዮች የኤርትራን ጥያቄ ‹‹የቅኝ ግዛት ጥያቄ›› ሲሉ፣ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል መሆኗንም የቅኝነት መቀጠል አድርገው የሚመለከቱ ነበሩ፡፡ ከእነሱ ጋር በትግል መወዳጀትን የሚለኩትም ‹‹የኤርትራን ጥያቄ የቅኝ ግዛት ነው›› ብሎ በመቀበል መሥፈሪያ ነበር፡፡ ኦነግና ሕወሓት ከእነሱ ጋር የተዛመዱትም ይህንኑ አቋም በመቀበላቸው ነበር፡፡ ኦነግ ከናካቴው በቅኝነት የመቀንበር ድርሰትን ለኦሮሞ ጥያቄም ያዋለ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹ዋናው ቅራኔ የብሔሮች ቅራኔ ነው›› በሚል ኩታ ውስጥ የተደበቀው ሕወሓትም ቢሆን ‹‹የብሔሮች መብት እስከ መገንጠል›› የሚል መፈክር ያለው ነበርና አንደኛቸውም ዘንድ ‹‹ገንጣይ አስገንጣይ›› የሚል መንግሥታዊ ውንጀላን አልፎ የሚሄድና ውንጀላውን የሚያከሽፍ የፖለቲካ መፍትሔ አልነበረም፡፡ በሁለቱም አመራር ውስጥ ዋናውን ሥፍራ ይዘው የነበሩት የ1960ዎች ትውልድ ሰዎች እንደ መሆናቸውም ድክመቱ በጊዜው ‹‹ተራማጅነት›› ግቢ ውስጥ  የሚታይ ነው፡፡

ተገትሮ የቀረው አቋማቸውና የትጥቅ ትግል ሥልታቸው የኃይል ሚዛን ለውጥ በማምጣትና የሕዝብን ሥቃይና መስዋዕትነት በማሳጠር ረገድ ጉልህ ሚና የተጫወተ አልነበረም፡፡ በዚያ ዘመን የነበረውም የሃርነት ትግል ወግ፣ በድርድር ፖለቲካዊ መፍትሔ ለመፈለግ እጅግም የሚመች አልነበረም፡፡ ጠመንጃ አንስቶ በረሃ ለገባ ነፃ አውጪነት፣ ገዥውን መንግሥት በኃይል ትግል አዝረክርኮ በድል አድራጊነት ከተማ መግባት በራሱ እንደ ዓላማ የሚናፈቅ ነበር፡፡ ‹ነፃ አውጪዎቹ› የኃይል ሚዛን ለውጥ እንዲያገኙ የጠቀማቸውም ከእነሱ ፖለቲካና ወታደራዊ ጥበበኝነት ይልቅ ደርግ ነበር፣ በብዙ ጥፋቶቹ፡፡ ‹‹ገንጣይ አስገንጣዮችን›› የመታገል አገራዊ አቅም እንዲታደስ በአገር አንድነት መንግሥትነት አሳትፈን ያሉ ኃይሎችን ከማቀፍ ይልቅ የብቻ ሥልጣኑ ስለበለጠበት፡፡ ወታደራዊ ሠራዊቱን በወታደራዊ ስለላና በፖሊሳዊ ፖለቲካ በመተብተቡ፡፡ በሠራዊቱ ዘንድ የተከበሩ ወታደራዊ መሪዎችን በማሰርና በመረሽን ሠራዊቱን በማስከፋቱ፡፡ ሲቪሉና ወታደሩ የለውጥ ተስፋውን አሳርፎበት የነበረው የ1981 ዓ.ም. የመንግሥት ግልበጣ ከከሸፈ ወዲያ፣ የግልበጣውን ተሳታፊዎች በመረሸን የሕዝብና የወታደራዊ ሠራዊቱን አንጀት በማሳረሩ፡፡ ከዚያም በኋላ ለውጊያ ወኔ ማጣት፣ ከጦርነት መሸሽና በጦር ሜዳ ላይ በገፍ እጅ መስጠት የተቃውሞ ትግል ግብታዊ ሥልት ሊሆን በመቻሉ፣ የኃይል ሚዛን ለውጥ አስከትለው ደርግን ለሙሉ ሽንፈትና ለአሜሪካ ‹‹ሲአይኤ›› መጫወቻነት ያበቁት ዋናዎቹ ሰበዞች እነዚህ ነበሩ፡፡

በ1983 ዓ.ም. ኦነግ ተጋባዥ የድል ተቋዳሽ፣ ሻዕቢያና ሕወሓት ዋና ባለ ድል ሆነው በአሜሪካ ሰርራጊነት ለንደን ላይ ተሞሽረው አዲስ አበባና አስመራ ሁለት መንግሥት ከፈጠሩ በኋላ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የተሠራው ነገር የኢትዮጵያንም የኤርትራንም ዘላቂ ጥቅሞች የጎዳ ነበር፡፡ ኤርትራ ሉዓላዊ አገር ብትሆን እንኳ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ዕጣ ፋንታ የተያያዘ ነበርና ኢትዮጵያን በቅኝ ገዥ ዓይን ዓይቶ ለመበቀል መሞከር መልሶ የኤርትራን ሕዝብ መጉዳት ነበር፡፡ የሕወሓትም የኢትዮጵያን ጥቅም መጉዳት የትግራይን ሕዝብ ጥቅም መጉዳት ነበር፡፡ ይህንን እውነት ለማየት ግን የሁለቱም ቡድኖች የዕይታ አጭሬነት አልፈቀደላቸውም፡፡ እናም ድል አድራጊነታቸውን ተከትሎ የመጣው ሒሳብ የማወራረድ ሥራ፣ (ኢትዮጵያን ምርኮ እንደ ወደቀች አገር የቡጥቦጣ ሜዳ ማድረግ) የትግራይንም የኤርትራንም ሕዝብ ዘላቂ ጥቅም ማጥቃት ነበር፡፡

ሕወሓት በቡድናዊ የሥልጣን ጥቅሙ ታውሮ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ታሪክ ማንም አድርጎት የማያውቅ ነውር ሲፈጽም (የኢትዮጵያን የጦር ኃይል አፍርሶና በትኖ የአገሪቱን የፀጥታና የወታደር አውታር ከሞላ ጎደል በራሱ ተጋዳላይ ሲያዋቅርና አየር ኃይልን ወደ ዜሮነት የመቀየር ያህል ሲያኮላሽ) ኢትዮጵያን ጎድቶ ትግራይን እየጠቀመ አልነበረም፡፡ በፖለቲካዊ ድንቁርና የትግራይንም ሕዝብ ህልውና መጉዳቱ ነበር፡፡ በዚያ ዓይነት አኳኋን ሁለቱም አሸናፊ ቡድኖች ህልውናቸውን ሲያቋቁሙ፣ ፍትሕ፣ እኩልነትና የሕዝቦች የተባበረ  ግስጋሴ ትርታቸው እንዳልነበር ገና ከመጀመሪያው የተረጋገጠ ነበር፡፡ ዋል አደር ብሎ የመጣው ‹‹ኢትዮጵያ ብሔራዊ መንግሥት የላትም… አዲስ አበባም አስመራም ያለው መንግሥት አንድ ነው…›› የሚል ሮሮና የትግራይ ሕዝብ ብዙ ነገር ወደ ኤርትራ የሚያጓጉዙትን ከባድ መኪናዎች ለማገት እስከ ማመፅ መድረሱ፣ ይህንኑ ተከትሎም የመጣው የ1990 – 1991 ዓ.ም. ጦርነት፣ ሁለቱ ቡድኖች ተያይዘውት የነበረው ተግባር ምን ያህል የኢትዮጵያ-ኤርትራ ሕዝቦችን ዘላቂ ጥቅም ሲያጠቃ እንደነበር ያሳየ ነበር፡፡

የጦርነት ትንኮሳና ‹‹በል ሞክረኛ!›› የሚል ድንፋታ ሲመጣ፣ የታየው መዝረጥረጥና ያኮላሹትን የአየር ኃይል ለማደራጀት መሯሯጥ በገዛ አገር ላይ የተሠራውን ጥፋት ያጋለጠ ነበር፡፡ የሁለቱ ቡድኖች ብልግና ባመጣው ጦርነት የተደገሰው ጠላትነት፣ ከወዲህና ከወዲያ ሕዝብ እንደ ድንጋይ  መወራወሪያ መደረጉና የሁለቱም አካባቢዎች ኑሮና ኢኮኖሚ በአጥፊ ጦርነት መደቆሱ የሁለቱም ሕዝቦች ጉዳት ነበር፡፡

ከጦርነቱስ በኋላ? ዘመዳሞቹን አገሮች ይመሩ የነበሩት ‹‹የተራማጅነት›› ዘመን ርዝራዦች (ያውም አውራ መሪዎቻቸው ከሁለቱም አካባቢ ከበቀሉ ወላጆች የተወለዱ ሆነው) ከጥፋቻቸው ተማሩ? አልተማሩም፡፡ ቀጥተኛ ጦርነት ቢቆምም፣ መጠቃቃታቸው በእጅ አዙር የጎረቤት አገርን ቀውስ መዋጊያ እስከ ማድረግና ከጦርነት የተረፈ ጥሪትን በዚህ ዓይነት ተግባር እስከ ማባከን ሄዶ ነበር፡፡ እየተጠቃቁ መኳረፉና አንዱ ሌላውን አስገልሎ በማዕቀብ የማቆራመድ ተንኮላዊ ውድድሩ ደርቶ ነበር፡፡ በዚሁም ምክንያት የኤርትራ ወደቦች አፋቸውን ከፍተው የኤርትራ ሕዝብም ኑሮ ባለበት ከመዳህ እጅግም ባልራቀ ሁኔታ ወድቆ ቆየ፡፡

የኢትዮጵያም የውጭ ንግድ ሕይወት በአንድ የጂቡቲ ወደብ ላይ ጥገኛ ከመሆን የሰፋ ነገር አላገኘም፡፡ ተላወሰ/አደገ ሲባል የነበረው የኢትዮጵያ ልማትም በስተኋላ ተጠራቅሞ የመጣው ሒሳብ እንዳሳየው በልማት ሽፋን ውስጥ ሕወሓቶች በመሩት የቡድና ቡድኖች መረባዊ ቡጥቦጣ አገሪቱ ስትጠቃ መቆየቷን ያጋለጠ ነው፡፡ ታየ ከሚባለው ልማት ጋር ያልተግባባው፣ በጊዜው የነበረውን ምዕራባዊ የመንግሥት ድጎማ ከመቀርጠፍ አልፎ የተከማቸው ፋታ ነሺ ብድር፣ አንድ ‹ሜቴክ› ላይ ተቆልሎ የቆየው ዕዳና ጉድለት፣ እንዲሁም ልማት ባንክ ላይ ደርሶ የነበረው ግዙፍ ኪሳራ ስለልማቱ ግልብነት በቂ ምስክር ነው፡፡

በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያ ላይ በኢትዮጵያ የጠቅላይ ሚኒስትር መንበር ላይ ከአዲስ ትውልድ የተገኘ ሰው ወጥቶ ኤርትራና ኢትዮጵያ ዕርቅ ውስጥ የገቡበት ሁኔታ ሲከሰትስ፣ ታላላቆቻችንና የእኛ እኩዮች የሆኑት በሁለቱ አገሮች የነበሩት የትናንትና ‹‹ተራማጅ›› ትውልድ የፖለቲካና የመንግሥት ሰዎች ካለፈ ጥፋት ለመማርና ለመታረም ቻሉ? ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካ ተዋናይነት ውጪ ተደርጋና ወደብ የለሽ ሆና ኤርትራም በጭርታ ተቆራምዳ የቆየችበት የድቀት ልምድ፣ የሁለቱን አገሮች መናቆርና መጠቃቃት ራስን የማጥቃት ወፈፌያዊ ጥፋት እንደነበር ያሳየ ነበር፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ተከስተ ነጋሽ ያሉ ሰዎች አስቀድመው እንዳስተዋሉት፣ ከመጠቃቃት በመለስ ለየብቻ መቆም አለመቻላቸው ያስገነዘበው ነገር ሙሉ መለያየት በራሱ ጉዳታቸው እንደነበር ነው፡፡  ዓብይ አህመድ በዕርቅ አስመራ ሲገባ፣ በየትም ሥፍራ በነበሩ የኤርትራና የኢትዮጵያ ሰዎች ዘንድ በስሜት የተገለጸው መነፋፈቅም ይህንኑ እውነታ ያስተጋባ ነበር፡፡ የሁለቱ አገሮች መሪዎች መጀመሪያ ላይ የነበራቸው የእፍ እፍ ግንኙነት ይህንኑ የተገነዘበ መስሎ ነበር፡፡ ጉጉትና ተስፋ የተንዠረገገበት አጭር ጊዜ የነበረ ቢሆንም፣ ውሎ አድሮ የኢትዮጵያና የኤርትራ ቀጣናዊ ጥቅሞች ከመጎዳት አላመለጡም፡፡ በዚህም ሚና ውስጥ ነገር ሠሪነቱና ተጠያቂነቱ ከ1960ዎች ትውልድ ርዝራዥ ፖለቲከኞች ውጪ አልነበረም፡፡

ከሕወሓት ቡድን ጋር ለመሳሳቅ (ምናልባትም ለመመሳጠር) ዕድል ያገኘው፣ የድሮ አቋሙን እንደያዘ ተገትሮ የቀረው በዳውድ ኢብሳ ይመራ የነበረ የኦነግ ርዝራዥ ቡድን፣ ሰላምን እያወራ በኦሮሚያና መሬት አለኝ ባለባቸው ሥፍራዎች የሰላም ጊዜ (የለውጥ ጊዜ) ተኳሽ ሆኖ አረፈ፡፡ ፀጉራቸው ቢሸብትም ከአፍንጫ አይርቄ ፖለቲካና ሸር አልፈው መብሰል ያልቻሉት ሕወሓትን የሚመሩ አሮጌ ምንቸቶችም ጥፋታቸው ናረ፡፡ በቀድሞ ሎሌያቸው አብዲ ኢሌ በኩል ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያን አምሰው የአገሪቱን መቦዳዳስ ሊያስጀምሩ ሞከሩ፡፡ ያ ቢከሽፍባቸውም በተለያዩ ሥፍራዎች ግጭቶችና ቅራኔዎች በመቆስቆስ ኢትዮጵያን በእርስ በርስ መባላት ውስጥ ለመዝፈቅ ከመልፋት አላረፉም፡፡ ‹‹ከኢትዮጵያ ጋር ያለን ግንኙነት ሕገ መንግሥቱ እስከ ተጠበቀ ድረስ ብቻ ነው፣ ከኤርትራ ጋር ያለን ግንኙነት ግን ስትራቴጂያዊ ነው›› ብሎ በይፋ እስከ መናገር (ከኢትዮጵያዊ ይልቅ ኤርትራዊ ነን የማለት ያህል) ህሊና ሲታጣም ታዘብን፡፡ በኢትዮጵያ የፌዴራል መንበር ላይ በነበሩ ጊዜ የኤርትራን ሉዓላዊነት አክባሪ ይመስሉ እንዳልነበር፣ ህሊና ማጣቱ በለየላቸው ጊዜ ከኢትዮጵያ የሚችሉትን ያህል ለም መሬት ቦድሰውና ኤርትራን ሰልቅጠው ትልቅ ባለወደብ አገር እስከ መፍጠር ቃዡ፡፡ ከዕርቅ በኋላ በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ተከፍቶ የነበርን የየብስ እንቅስቃሴ የኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት መልሶ ለማገድ የፈጠነው ሕወሓቶች በአመፅ/በሴራ ሊያስከትሉ የሚችሉትን የመንግሥት ግልበጣ በማሽተት ነበር፡፡

አዛውንቶቹ ጎረምሶች ግን ቅዠታቸውን አልጣሉም፡፡ የአገር መከላከያና የደኅንነት አውታርን በአንድ ቡድን ከመቆጣጠር ታሪከኛና ተቀዳሚ ነውራቸው ቀጥሎ ያንኑ ምርኩዝ ያደረገ ሌላ ወደር የለሽ ነውር ወደ መፈጸም ዞሩ፡፡ በትግራይ አስተዳደር በጀት በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የሚሊሺያና የልዩ ኃይል ጦር ካደራጁ በኋላ፣ በሰበብ አስባብ አግተው ያቆዩትንና ትግራይን በጥበቃም በልማትም ሲጠቅም የኖረውን ዋናውን የኢትዮጵያ መከለካያ አቅም (ሰሜን ዕዝን) ሌሊት መሣሪያ የለሽ አድርጎ የማጨድና ምርኮኛ የማድረግ ጥቃት አደረሱና ያንን ‹‹የታላቅ አገር›› ግንባታቸውን ዕቅድ ለማሳካት በኤርትራም በኢትዮጵያም ላይ ተኩሳቸውን ከፈቱ፡፡ ኤርትራንም መሰልቀጥ ኢትዮጵያንም መከላካያ የለሽ አድርጎ ማፍረስ ቀላል አልሆን ብሎ፣ በክፉ ቀን በተጋገዙት ዘመዳም ጎረቤቶች ቅዠት እንቦጭ ካለ በኋላም፣ ምንቸቶቹ አዛውንቶች ከጥፋት ለመራቅ አልፈቀዱም፡፡

ብዙ ኃይል አስመትተው ወደ በረሃ ከሸሹ ወዲያ በትግራይ ሕዝብ ደም መጫወት ይብቃን ሳይሉ እጅግ የዘቀጠ (ሰቅጣጭ ነውሮችን በታዳጊና በአዛውንት ላይ ለመፈጸም ያላፈረ) ዘራፊና አውዳሚ ወረራ ከአንዴም ሁለቴ አካሂደዋል፡፡ ወረራ በቃን ብለው ለድርድር የተንበረከኩትም የትግራይ ሕዝብ ደምና ሲዖል አንበርከኳቸው ሳይሆን የራሳቸው ደም ሸትቷቸው ነበር፡፡ አፍ ሞልቶ ለትግራይ ሕዝብ መብትና ህልውና ተዋደቅን ብሎ ሐሰትን ማናፋት፣ እነሱ በወረሩ (ሰብዕናን ያዋረደ ጥቃትና ግድያ በንፁኃን ላይ በፈጸሙ፣ ሙዳየ ምፅዋት፣ የጆሮ ጌጥና መቀነት ሳይቀር በብቀላ ባስሞለጩ) ‹‹የዘር ማጥፋት ወረራ ተፈጸመብን›› ብሎ ማለት፣ እሳት ውስጥ እየማገዱ ያስፈጇቸውን የትግራይን ወጣቶች በ‹‹አርበኝነት›› መሸንገል፣ ይህንን በመሳሰሉ መልኮች የሚያካሂዱት ሽምጠጣ ሁሉ ከፍርድ ማምለጫ የብረት ልብስ መሆኑ ነው፡፡ ክፋቱ ግን ታሪክና ፈጣሪ አይሸወዱም!! ዓይናችን ሥር የተፈተጸመው ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ወገን የተፈጸሙ ግፎች የማይደበቁበት ጊዜ ይመጣል፡፡

እስካሁን ባለን ግንዛቤ ግን፣ የመከላካያ ኃይልን አዘንግቶ፣ አርዶ አገር ላይ ወረራ የመክፈት ታላቁን ወንጀል በመሥራት፣ ወደር የሌላቸው እነሱ ናቸው፡፡ ይህንን የትም ታይቶ የማያውቅ ተራራ የሚያህል ወንጀል ፈጽመውም፣ ደብረ ብርሃን ድረስ የዘመቱት ጠበል ለመርጨትና ታቦት ለማንገስ የነበረ ይመስል  በኡኡታም የሚስተካከላቸው አልተገኘም፣ ወልቃይትና ራያ የተመለሰውን ሰው ‹‹ወራሪ!›› ሲሉም ምላሳቸው ደንቀፍ አይልም፡፡ እነሱ የፈጸሙትን በሌላው ላይ በመላከክ አንደኛነቱ የእነሱ ይሁን እንጂ፣ በምንቸትነት ላይ ተገትረው የቀሩ እነሱ ብቻ አይደሉም፡፡ አጥፍቶ የመማርና የፀፀት ነፍሳቸውን ዝቅጠት የሰለበባቸውም እነሱ ብቻ አይደሉም፡፡ ሌሎቹን ጥሎ ማለፍና የሕወሓትን ገታሮች ጥሎ ማለፍ የሚጠይቀው ሥራ ግን አንድ አይደለም፡፡ እነሱ በመንግሥት ሥልጣን ላይ የአንድ ትውልድ ያህል ጊዜ የቆዩ፣ በሸረኛ ከፋፋይ ፖለቲካ የተራቀቁና የኢትዮጵያን አገረ መንግሥት ለውድቀት የዳረጉ ናቸው፡፡ ዛሬም በትግራይ ውስጥ ጊዜያዊ አስተዳደርና የፀጥታ ኃይል ሆኖ የሚሠራው ቡድን ከእነሱ የተገኘ ነውና ከእነሱ ጋር ያለው ፈተና ገና ነው፡፡ እነሱ ከጠመንጃ እስካልተላቀቀቁና የትግራይ ክልላዊ አስተዳደር የፖሊስ ኃይል ከእነሱ የፕሮፓጋንዳ እስረኝነት እስካልተገላገለ ድረስ የትግራይ ሕዝብ እውነተኛ አስተዳደርና ሰላም ዕውን አይሆንም፡፡ ከድህነት የመገላገል ትግሉም ከእንዘጭ እምቦጭ አልፎ መሄድ ይቸግረዋል፡፡ ይህ እስከቀጠለ ድረስም ሰሜናዊው የኢትዮጵያ ችግር ሽሮ አይሽርም፡፡ የኢትዮ-ትግራይ-ኤርትራ የተማመነ የልማት ግስጋሴ ዕድልም ተጓጉሎ የሚቆይ ይመስላል፡፡ ይህ ሁኔታ የሚቀየረው ከሕወሓትና ከሕወሓታዊዋን ውጪ የሆኑ የለውጥ ቡድኖችና ለሕወሓት የሽምጠጣ ፖለቲካ አሽከር መሆን በቃን ያሉ የትግራይ ወጣቶችና ልሂቃን አንድ ላይ ገጥመው ለአዲስ ሕይወት መንቀሳቀስ ከቻሉ ነው፡፡ ይህንን ሒደት በማፋጠንና በማብሰል ረገድ የኢትዮጵያና የኤርትራ ዝምድና ወጪ በማይጠይቅ መልካም ትንፋሽ ጉልህ ሚና መጫወት ይችላል፡፡

ዛሬ ወደብ በጋራ ጥቅም የማልማት ጉዳይና በቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካ መካተት የኢትዮጵያ የተናጠል ድምፅ ሆኖ ብቅ ማለቱ የሚያስገርም ነው፡፡ የተወሰኑ የኤርትራ ጥቅም ደጋፊ ነን ባዮች፣ ነገርዮውን የኤርትራን ሉዓላዊነት የመጋፋት ዳር ዳርታ አድርገው መተርጎማቸው ደግሞ ይበልጥ አስገራሚ ነው፡፡ የሁለቱ አገሮች መሪዎች ከእፍ እፍ ፍቅር ወደ ዝም ዝም መዞራቸውም ሌላ እንቆቅልሽ ነው፡፡

በዚህ ደረጃ ላይ ሁለቱ አገሮች፣ ሁለት አገርነታቸው እንደተጠበቀ፣ የሕዝባቸውን ሕይወት የሚያነሳ የስትራቴጂያዊ ጉድኝት ውጥን ይዘው መቅረብ በተገባቸው ነበር፡፡ ከዚህ ዋና ተግባር አኳያም ወደብ በጋራ ማልማት ለሁለቱ አገሮች ቁራሽ ጉዳይ መሆን ነበረበት፡፡ ወደ ስትራቴጂካዊ ጥምረት ከማለፍ ያወካቸውና መራራቂያ የሆናቸው የሕወሓት መትረፍ ሆኖ ከሆነ የሚደንቅ ነው! ራሳቸውን በሕወሓት ደረጃ አውርደው ተግባራቸውን ያወኩት ራሳቸው እንጂ ሕወሓት አይደለም፡፡ ሁለቱ አገሮች ቸለልታ ውስጥ ከመግባታቸው በስተጀርባ፣ ሥውር (የእጅ አዙር) መጎነታተል ጀምረው ከሆነም፣ ድርጊታቸው ለአዲስ ዘመንና ተግባር ከማነስ የሚቆጠር ነው፡፡ የሁለቱ አገሮች ዝም ዝም ከአማራ ቀውስ ጋር የተነካካ ነገር ያለው ከሆነም ከታሪክ ልምድ የመማሩ ነገርና የጋራ ጥቅም ግንዛቤው ቅጥ አምባሩን አጥቷል ያሰኛል፡፡ የአማራን ጉዳይ ከኤርትራ ጋር ለማገናኘት በመሞከር አማራ አይጠቀምም፡፡ ኤርትራም አማራ ቀውስ ውስጥ የሩቅ እጇን ብታጠቅስ ከሕወሓት ጋር ያላት ቁርሾ የተወገደበት አዲስ የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት ላይ አትደርስም፡፡ የውስጥ ጉዳይንና ጉርብትናን እንዲህ አድርጎ ማቧካት ለኢትዮጵያም ለኤርትራም መቃወሻ ጠንቅ ነው የሚሆነው፡፡ እንዲህ ያለ እንቆቅልሽ ውስጥ ገብተው ከሆነ፣ የሁለቱን አገሮች የተጣመረ መጠናከር ለሚፈሩና ለሚጠሉ አገሮችም ራሳቸውን ሰንክለው በምሥራችነት እንዳቀረቡ ይወቁት፡፡

የሁለቱ አገሮች ዕርቅ ምን ንፋስ ገብቶት ይሆን የሚል መባዘን ውስጥ ዛሬ መግባታችን አሳዛኝ ነው፡፡ ምክንያቱም የኤርትራና  የኢትዮጵያ ሕዝቦችን በልማት መመንደግ የወደዱ የኢትዮ ኤርትራ ምሁራንና ፖለቲከኞች አንድ ላይ የመከሩበትን ዕቅድ ለሁለቱ አገሮች አቅርበው ማስማማት ችለው ቢሆን ኖሮ፣ እኔ ነኝ ያለ የትኛውም ሸረኛ ቡድን (ከኢትዮጵያም ሆነ ከኤርትራ በኩል) በሁለቱ አገሮች የተጣመረ ጉዞ ውስጥ ሽብልቅ መሆን እንደማይቻለው ባወቀ ነበር፡፡ እንዲህ ደፍሮ ለመናገር የሚያበቃን የሁለቱ አገሮች እውነታ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ሕዝቡም ልሂቁም የኢትዮጵያና የኤርትራ የመጠቃቀም አስፈላጊነት ለሁለቱም የመገስገስ ጉዳይ መሆኑን ከተገነዘበ ከርሟል፡፡ በኤርትራ መንግሥትና ልሂቃን አካባቢ በይፋ የተነገረ ነገር አልሰማንም፡፡ አንስማ እንጂ፣ ከነፃነት ጀምሮ የተሠሩት የሁለቱን አገሮች አስፈላጊ ትስስር የጎዱ ጥፋቶች ነጥረው እንዲጤኑ ለማድረግ ግን፣ የሊቅ ትንታኔና የማሳመን ልፋት ኤርትራውያን የሚፈልጉበት ደረጃ ላይ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም የፈዘዘ የደነዘዘ የሕይወት እውነታቸው ከአፍ በልጦ እየተናገረ ነው፡፡ እናም ጉዳዩ የሚያሳምን የማጣት ነገር ሳይሆን፣ ግብዝነትን ተሻግሮ እውነተኛ ጥቅምን የመቀበል ነው፡፡ ከዛሬ የቀጣናችንና የአገሮቻችንን እውነታዎች አኳያ፣ የኢትዮ ኤርትራ ምሁራን ለሁለቱ አገሮች የሚበጁ ንድፍ የማዘጋጀት ሥራ ቢሠሩ ሥራቸው ፈጥኖም ሆነ መግደርደርን ሞካክሮ ሰሚ ማግኘቱ አይቀርም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...