Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትለአምባሳደርነት ውል ያሰረችው እንስቷ አሠልጣኝ

ለአምባሳደርነት ውል ያሰረችው እንስቷ አሠልጣኝ

ቀን:

እጅግ አስቸጋሪ በሆነውና የተለየ ጥረት በሚጠይቀው በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ውስጥ ጎልታ መውጣት ችላለች፡፡ ከአዲስ አበባ ሠፈር ለስሜት ከሚደረግ የእግር ኳስ ጨዋታ እስከ ሞኖሮቪያ የብሔራዊ ቡድን የዘለቀ የእግር ኳስ ሕይወትን አሳልፋለች፡፡

ተወልዳ ባደገችበት ሃያ አራት ሠፈር ጨፌ ሜዳ የእግር ኳስ ተጫዋችነቷን ጀመረች፡፡ ከሠፈር በዘለለ የካ የሚገኘው የእግር ኳስ ፕሮጀክት ሰላም ዘርዓይን የሥልጠና ዕድል ሰጣት፡፡ በዚህ ፕሮጀክት የነበራት እንቅስቃሴም ሰላምን ዓይን ውስጥ አስገብቷት ለሀይኮፍ የሴቶች እግር ኳስ ክለብ የመጀመሪያ ፊርማዋን አሳረፈች፡፡

ሰላም በሀይኮፍ እግር ኳስ ክለብ ጥሩ ጊዜ ማሳለፏን ታስታውሳለች፡፡ ሁሌም ፈተና የበዛበት የሴቶች እግር ኳስን በሀይኮፍ ፈትኗታል፡፡ በዚህ ፈተና ውስጥ ታዲያ ሰላምና ጓደኞቿ ችግር ውስጥ ገቡ፡፡ የእግር ኳስ ቀጣይ ሕይወታቸው አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት ሰዓት፣ ሰላም በሌላ ክለብ ውስጥ የመታቀፍ ዕድልን አገኘች፡፡ የሰላም ቀጣይ ማረፊያዋ አዲስ አበባ ኤግልስ ክለብ ሆነ፡፡ ከዚያም ወደ ‹‹ኤስዋይጂ›› ስፖርት ክለብ በማምራት ተጫውታለች፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የተጫዋችነት ዘመኗ ‹‹በፈተና የተሞላ ነበር›› የምትለው ሰላም፣ ከቤተሰብ አልፎ ጎረቤት ሳይቀር ሴት ልጅ እግር ኳስን መጫወቷ እንደ ነውር  በሚቆጠርበት ጊዜ ነው የተጫዋችነት ሕይወቷን ያሳለፈችው፡፡ ይህ ጫና ግን ሰላምን አላስቀራትም፡፡ ይልቁንም የተሻለ ነገር እንድታልም እንዳደረጋት ታስረዳለች፡፡

በኢትዮጵያ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሴቶች እግር ኳስ ክለብን ጨምሮ የተለያዩ ክለቦችን፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሴቶች ቡድንን ማሠልጠን የቻለቸው ሰላም፣ በካፍ ውስጥ ብቸኛ ሴት ኢንስትራክተር ነች፡፡ በቅርቡ የላይቤሪያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድንን ለማሠልጠን ውል አስራ እያሠለጠነች ትገኛለች፡፡

አሠልጣኝ ሰላም በቅርቡ የስፖርት ትጥቅ ማምረት የጀመረው ‹‹ዋናው የስፖርት ትጥቅ አምራች›› ለሦስት ዓመታት አምባሳደር አድርጎ ሾሟታል፡፡ በውሉም መሠረት አሠልጣኟ ትጥቁን በተለያዩ ሥፍራዎችን የምታስተዋውቅ ሲሆን፣ በተለይ በላይቤሪያ ከሚገኙ ክለቦች ጋር መሥራት የሚቻልበትን ድልድይ ትፈጥራለች ተብሏል፡፡  

በሀብቴ ጋርመንትና ኅትመት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የስፖርት አልባሳት ብራንድ የሆነው ‹‹ዋናው የስፖርት ትጥቅ››፣ በኢትዮጵያ የስፖርት ኢንዱስትሪ ውስጥ በተቀላቀለ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ተቀባይነት እያገኙ ከመጡ ካምፓኒዎች መካከል አንዱ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

 ዋናው ስፖርት በኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን የስፖርት አልባሳት የጥራት፣ የተደራሽነትና በዋጋ ዙሪያ ያሉ ክፍተቶችን በመፍታት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያውያን ለስፖርት ያላቸው ፍቅርና ተሳትፎ ከፍተኛ መሆንና እያደገ የመጣው የተጠቃሚው የጥራት ፍላጎት፣ ዋናው ስፖርት በተሻለ የሰው ኃይልና ቴክኖሎጂ በመታገዝ ምርቱን በጥራትና በብዛት እንዲያሳድግ ማድረጉም ተነግሯል፡፡

በሌላ በኩል በተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ለሚደረጉ የታዳጊዎች ሥልጠና የስፖርት ትጥቅ እያበረከተ እንደሚገኝ፣ ዘንድሮ ብቻ ለ45 የታዳጊ ማሠልጠኛዎች ስፖርት ትጥቅ ድጋፍ ማድረጉ ተጠቅሷል፡፡

ለአትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ መረብ ኳስ፣ እጅ ኳስና ለሌሎችም ተወዳዳሪዎች የሚውሉ ቀላል፣ የማይሞቁና ምቹ አልባሳትን እያመረተ እንደሚገኝ፣ ከአገር ቤት ውጪ በሩዋንዳና ዑጋንዳ ለሚገኙ ክለቦችም ትጥቅ እያቀረበ መሆኑን ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...