Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትለፓሪስ ኦሊምፒክ ማጣሪያ ለወርልድ ቴኳንዶ ሲዘጋጅ የነበረው አትሌት አለመመረጡ ቅሬታ አስነሳ

ለፓሪስ ኦሊምፒክ ማጣሪያ ለወርልድ ቴኳንዶ ሲዘጋጅ የነበረው አትሌት አለመመረጡ ቅሬታ አስነሳ

ቀን:

  • የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች ማጣሪያውን አላለፉም

በፓሪስ ለሚከናወነው የኦሊምፒክ ጨዋታ ኢትዮጵያን በወርልድ ቴኳንዶ ለመወከል ለማጣሪያው ሲዘጋጅ የነበረው ተወዳዳሪ በብሔራዊ ቡድን ውስጥ ሳይካተት መቅረቱ ቅሬታ አስነሳ፡፡

በቶኪዮ ኦሊምፒክ ለመጀመሪያ ጊዜ በወርልድ ቴኳንዶ ኢትዮጵያን በመወከል ዲፕሎማ ማምጣት የቻለው ሰለሞን ቱፋ፣ በሴኔጋል ዳካር በሚደረገው የዘንድሮ የማጣሪያ ውድድር ለመሳተፍ ሲዘጋጅ ቢቆይም፣ ‹‹እንዳልሳተፍ ተደርጌያለሁ›› የሚል ቅሬታ አቅርቧል፡፡

ለፓሪስ ኦሊምፒክ ማጣሪያ ለወርልድ ቴኳንዶ ሲዘጋጅ የነበረው አትሌት አለመመረጡ ቅሬታ አስነሳ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የወርልድ ቴኳንዶ አትሌቱ ሰለሞን ቱፋ

በፓሪስ ኦሊምፒክ ለመካፈል ከሦስት ዓመታት በላይ ሲዘጋጅ እንደነበርና ለዚህ ዝግጅት ከነበረበት አሜሪካ የማጣሪያ ውድድሩ ሲቃረብ ሥልጠና አቋርጦ መምጣቱን ተናግሯል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹በአሜሪካ ዝግጅት እያደረግኩ በነበርኩበት ወቅት ሥልጠና አቋርጬ እንድመጣ በፌዴሬሽኑ በኩል ደብዳቤ ደረሰኝ፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ ከደረስኩኝ በኋላ ምዝገባዬ መሠረዙ ተነገረኝ፤›› በማለት፣ ሰለሞን ቱፋ ለሪፖርተር ስለሁኔታው አስረድቷል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም ደብዳቤው የደረሰው በወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የፋይናንስና የግዥ ክፍል ውስጥ በምትሠራ ግለሰብ አማካይነት እንደሆነ ገልጾ፣ በቀን 9/4/2016 ዓ.ም. የጥሪ ደብዳቤው እንደደረሰው፣ በቀን 10/4/2016 የልምምድ ቦታና ሆቴል እንዲገኝ ጥሪ እንደቀረበለት አብራርቷል፡፡

በዚህም መሠረት ላለፉት ስድስት ወራት በአሜሪካ ዝግጅቴን እያከናወንኩ መሆኑ እየታወቀ፣ በአንድ ቀን ኢትዮጵያ መጥቶ ብሔራዊ ቡድኑን እንዲቀላቀል ጥሪ እንደረሰው ያስረዳል፡፡

‹‹አሜሪካ እያለሁ ስለጉዳዩ ለመወያየት በተደጋጋሚ ለፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ስልክ ብደውልም ሊያነሳልኝ አልቻለም፤›› ሲል ሰለሞን ስለሁኔታው ያብራራል፡፡

አትሌቱ በሴኔጋሉ የወርልድ ቴኳንዶ የማጣሪያ ውድድር ለመካፈል እንደተመረጠ የጽሕፈት ቤት ኃላፊው እስከመጨረሻው ሰዓት ድረስ ሲናገር እንደቆየና የክብደት መጠኑን (ኪሎውን) ሲያስተካክል መቆየቱን ለሪፖርተር አስረድቷል፡፡

ሆኖም እስከመጨረሻው ሰዓት ድረስ ዝግጅት ሲያደርግ ቢቆይም፣ ከብሔራዊ ቡድን ዝርዝር ውጪ መሆኑን፣ ከዓለም አቀፉ ተቋም ወርልድ ቴኳንዶ ኢሜይል እንደደረሰው ገልጿል፡፡ በአንፃሩ ፌዴሬሽኑ ስህተት ነው የሚል ምላሽ ሲሰጠው እንደቆየ ተናግሯል፡፡

አትሌቱ ለ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ለመካፈል በሚደረገው የቅድመ ማጣሪያ ውድድር ለመሳተፍ በቤልጂየም፣ በፈረንሣይ፣ በአሜሪካ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ በቂ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን አስረድቷል፡፡ ‹‹በተለያዩ አገሮች እየተዘዋወርኩ ዝግጅት ሳደርግ ሙሉ በሙሉ ወጪዬን በራሴ ሸፍኜ ነው፡፡ ሆኖም ፌዴሬሽኑ ይህንን ልፋቴንና ጥረቴን ሊረዳው አልቻለም፤›› በማለት አትሌቱ አስተያየቱን ይሰነዝራል፡፡  

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ መካፈል የሚገባትን ሁለት የሲኒየር አፍሪካ ሻምፒዮናና የዓለም ሻምፒዮና ሳትካፈል መቅረቷን ገልጿል፡፡ 

በአንፃሩ የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ለአትሌቱ ከሌሎች የብሔራዊ ቡድን አትሌቶች ጋር ተቀላቅሎ ልምምድ እንዲያደርግ ጥሪ እንዳቀረበለት፣ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት አስፋው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም አትሌቱ በኦሊምፒክ፣ በዓለም አቀፍና በአኅጉር ውድድሮች በመሳተፍ ልምድ ያካበተ በመሆኑ፣ በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ ለተካተቱ አዳዲስ ወጣቶች ልምድ እንዲያካፍልም ዕቅድ ነበረን ብለዋል፡፡

ሆኖም አትሌቱ በተባለው የልምምድ ሥፍራ ተገኝቶ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ተቀላቅሎ ባለመሥራቱ በማጣሪያ ውድድሩ ከሚካፈለው ቡድን ውጪ መደረጉ ተጠቅሷል፡፡

በአንፃሩ ከቀናት በፊት በሴኔጋል ዳካር በተከናወነው የወርልድ ቴኳንዶ የማጣሪያ ውድድር፣ በወንዶች ጌትነት አጥናፉ በ68 ኪሎ ግራም፣ ዘመድኩን ዘለቀ በ58 ኪሎ ግራም፣ በሴቶች ጽዮን ባለው በ57 ኪሎ ግራም፣  አሚና ጀበል በ49 ኪሎ ግራም ኢትዮጵያን ወክለው ተወዳድረዋል፡፡

በሒደቱም ከጽዮን ባለው በቀር ሦስቱ ተወዳዳሪዎች በመጀመሪያ ጨዋታ ተረተዋል፡፡ ጽዮን በመጀመሪያ ጨዋታዋ የሶማሊያ አቻዋን ብታሸንፍም በቀጣዩ ጨዋታዋ የሞሮኮ ተቀናቃኟን  መርታት አልቻለችም፡፡

የሽንፈት ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ በዘንድሮ የፓሪስ ኦሊምፒክ በወርልድ ቴኳንዶ አለመካፈሏ ታውቋል፡፡

በ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን በመወከል የተወዳደረውና ዲፐሎማ ያገኘው ሰለሞን ቱፋ ለዚህ ክብር የበቃው፣ አስቀድሞ በሞሮኮ ራባት በተሰናዳው የወርልድ ቴኳንዶ የማጣሪያ ውድድር የቻድ፣ የሱዳንና የሴኔጋል አቻዎቹን በመርታቱ እንደነበር ይታወሳል፡፡.  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...