Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለትግራይ ክልል ድርቅ ተፈናቃዮች አፋጣኝና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ

ለትግራይ ክልል ድርቅ ተፈናቃዮች አፋጣኝና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ

ቀን:

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በትግራይ ክልል ውስጥ የተከሰተው ድርቅ በሕዝቡ ላይ እያደረሰ ያለውን አስከፊ ተፅዕኖ ለመግታት የፌዴራል መንግሥት፣ በአጠቃላይ የአገሪቱ ሕዝብና ዓለም አቀፍ አጋር አካላት አፋጣኝና ቀጣይነት ያለው የተቀናጀ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረቡ። 

ቋሚ ኮሚቴው ባለፈው ሳምንት የመጀመሪያ ሦስት ቀናት በትግራይ ባደረገው የመስክ ምልከታ፣ ጦርነቱን ተከትሎ በተፈጠረው ሰው ሠራሽ ችግር ምክንያት የደረሰውን ሰብዓዊ ቀውስና ድርቅ በክልሉ ያስከተለውን ተፅዕኖ ከተመለከተ በኋላ፣ የካቲት 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ለአገር ውስጥ ሚዲያዎች ስለትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ በሰጠው መግለጫ ነው ጥሪውን ያቀረበው። 

የምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) ስለፓርላማ አባላቱ የትግራይ ጉብኝት በሰጡት ማብራሪያ፣ የልዑካን ቡድኑ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች፣ በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች እየኖሩ ካሉ ዜጎች፣ በአሁኑ ወቅት ለተፈናቃዮች ሰብዓዊ ዕርዳታ እያቀረቡ ካሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል። 

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሊቀመንበሩ ቋሚ ኮሚቴው የክልሉ የአደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ባለሙያዎች ስለወቅታዊ የክልሉ ሁኔታ የቀረበለትን ጥናት መገምገሙን፣ እንዲሁም ከአፍሪካ ኅብረት የፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸም ተቆጣጣሪና ገምጋሚ ቡድን (African Union Monitoring and Evaluation Team) ስለክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ ማብራሪያ እንደቀረበላቸውና ውይይትም እንዳካሄዱ ተናግረዋል። 

የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ ሞጋ አባቡልጉ የልዑካን ቡድኑ ከሁሉም ወገኖች የቀረበለት መረጃ ትክክለኛ መሆኑን እርስ በርስ እያመሳከረ ማረጋገጡን፣ ከየትኛውም አካል የተዛባ መረጃ አለመቅረቡን የሚያረጋግጥበት አሠራር መከተሉን አስረድተዋል። 

የፓርላማ አባላቱ በትግራይ ቆይታቸው መቀሌ ውስጥ የሚገኙ የተፈናቃዮችን ማዕከሎችና በከተማዋ ዙሪያ የሠፈሩ ሌሎች ተፈናቃዮችንም አግኝተው ማነጋገራቸው ተገልጿል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በትግራይ ክልል ከደቡባዊ ምሥራቅ ዞን፣ ከምዕራብ ትግራይ ቀበሌዎች፣ ኢትዮጵያን ከኤርትራ ከሚያዋስኗት አካባቢዎች፣ ከአፋር፣ ከአማራ፣ ከኦሮሚያና ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተፈናቀሉና በመቀሌና ዙሪያው የእንደርታ ወረዳዎች የተፈናቀሉበት ከዘርፈ ብዙ ምክንያቶች በተጨማሪ፣ በክልሉ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮችና ስደተኞች ያሉበትን ሁኔታ በአካል ተገኝቶ መመልከቱን ገልጿል። 

በክልሉ የአደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን የቀረበው ጥናት በእንደርታ ከሚገኙ 12 ወረዳዎች ስምንት ቀበሌዎች በድርቁ እንደተጎዱ፣ 522 ሔክታር መሬት ከጥቅም ውጪ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው መመልከቱን ጠቅሷል። 

ከዚህ በተጨማሪም በሪፖርተር የእሑድ የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም አስቀድሞ እንደተገለጸው፣ በክልሉ መዘራት ከነበረበት 1.3 ሚሊዮን ሔክታር መሬት 49 በመቶ ብቻ እንደታረሰ ቋሚ ኮሚቴው ማየቱን በመግለጫው አስረድቷል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ (ዶ/ር)፣ ‹‹በትግራይ ክልል የተከሰተው ውስብስብ ችግር ነው። አንድ ችግር ሲከሰት ሌላ ችግር ይመዛል። በትግራይ መጀመሪያ የተከሰተው በመላ አገሪቱ እንደተፈጠረው የመጀመሪያው የኮቪድ-19  ወረርሽኝ ነበር፣ እሱን ተከትሎ የአንበጣ ወረርሽኝ ተከሰተ፣ ከዚያ በኋላ ሁለት ዓመታት የፈጀ የእርስ በርስ ጦርነት ነበር፣ ከዚህ ጎን ለጎንና ጦርነቱ ካበቃ በኋላም የቀጠለ ድርቅ ተከስቷል፤›› ብለዋል። 

ዲማ (ዶ/ር) አክለውም፣ ‹‹በድርቁ የተጠቁ አካባቢዎችን ጎብኝተናል፣ ድርቅና የውኃ ዕጦት፣ የምግብ እጥረት ሰዎች ላይ አስከፊ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው፣ እንስሳት እየሞቱ ነው፣ የውኃ ዕጦቱ በዕፅዋት ላይ ራሱ አስከፊ የሆነ ጥፋት እያስከተለ ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል። 

እንደ ሰብሳቢው ገለጻ፣ በአሁን ወቅት በትግራይ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚገኙ ሲሆን፣ የሰብዓዊ ዕርዳታና የመልሶ ማቋቋሚያ ድጋፍም እየተጠባበቁ ነው። 

የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ ሞጋ በበኩላቸው፣ ‹‹እውነት እየኖሩ ነው ለማለት አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታ የሚገኙ ሰዎችን ዓይተናል፤›› ብለዋል። አቶ ሞጋ በተፈናቃይ ካምፖች ውስጥ ዞር ዞር ብሎ ለመንቀሳቀስ በማያስችል ጠባብ ቦታ ውስጥ እናቶች፣ ሕፃናትና አዛውንት ተቸግረው ማየታቸውን ተናግረዋል።

እንደ የፓርላማ አባሉ ገለጻ፣ በእነዚህ ካምፖች ውስጥ ያሉት ዜጎች ሁኔታ አሳዛኝ ቢሆንም፣ ቢያንስ የዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች ትኩረትና ድጋፍ አልተለያቸውም፡፡ በእንደርታ ወረዳዎች ትንንሽ ጎጆዎች ሠርተው እየኖሩ ያሉት ተፈናቃዮች ግን የከፋ ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት ብለዋል። 

የቋሚ ኮሚቴ አባሉ፣ ‹‹በመጠለያ ካምፖች ውስጥ ያሉት የመንግሥትና የዓለም አቀፍ ተቋማት ትኩረትና ድጋፍ አላቸው፡፡ በእንደርታ ወረዳዎች ያሉት ተፈናቃዮች ግን ቋሚ የሆነ ሰብዓዊ ዕርዳታ እያገኙ እንዳልሆነ ተረድተናል። በፊት ዙሪያቸው ያለው ነዋሪ በቻለው መጠን ይደግፋቸው ነበር። አሁን ግን ድርቁ በነዋሪዎች ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ ያንን ድጋፍ ይሰጧቸው የነበረውን ዕርዳታ እንዲያቆሙ አድርጓቸዋል። በእንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ልብ የሚሰብር ሁኔታ እናቶች፣ ሕፃናትና አዛውንት እየኖሩ እንዳሉ ዓይተናል፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል።

ቋሚ ኮሚቴው በጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ በፌዴራል መንግሥትና አጋር አካላት ችግሩን ለመፍታት ጥረቶች ማድረጋቸውን አስረድቷል።

አቶ ሞጋ በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ለተፈናቃዮችና ለጦርነቱ ተጠቂዎች አስፈላጊ የምግብ ዕርዳታ በማድረስ፣ የፌዴራል መንግሥት በጦርነቱ የተጎዱ መሠረተ ልማቶችን በመጠገንና የክልሉ አስተዳደርን በመደገፍ፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ተቋማትም ድጋፍ ለሚያስፈልገው ማኅበረሰብ በቻሉት መጠን ለመድረስ መሥራታቸውን ዓይተናል፤›› ብለዋል።

ከእነዚህ ጥረቶች ባሻገር ግን ድጋፉ መሬት ላይ ካለው ጥያቄ አንፃር በቂ እንዳልሆነ መመልከታቸውን ገልጸዋል። የፓርላማ አባሉ አቶ ሞጋ፣ ‹‹ሕዝቡን ማቋቋም በተደራጀ መንገድ ሊኬድበት ያስፈልጋል፤›› ብለዋል። 

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ከሁለት ወራት በፊት በሰጡት መግለጫ፣ በትግራይ የተከሰተው ድርቅ የፈጠረው ረሃብ የ1977 ዓ.ም. አስከፊ ድርቅ የሚስተካከል ነው ማለታቸው ይታወሳል። 

ሪፖርተር ትግራይን ለጎበኘው የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ አባል በትግራይ ያለው ረሃብ በእርግጥ እዚህ ደረጃ ደርሷል ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ነው ወይ? የሚል ጥያቄ አቅርቧል።

ሰብሳቢው ዲማ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹አሁን ያለው ሁኔታ ከ1977 አስከፊ ኩነት ጋር ይወዳደራል አይወዳደርም የሚለውን ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። ቆይታችን አጭር ነበር፣ መላ ትግራይ ክልልን አላዳረስንም፡፡ ስለዚህ እዚህ ላይ ልክ ነው አይደለም የሚል ድምዳሜ መስጠት አንችልም፤›› ብለዋል። 

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹ድርቅ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች ውስጥ የተወሰኑት በጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥር ስላልሆነ ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረስ እንዳልተቻለ ተረድተናል፤›› ሲሉም ገልጸዋል። 

ቋሚ ኮሚቴው የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሰብዓዊ ቀውስና ድርቅ ያስከተለውን ተፅዕኖ፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ብቻውን ሊወጣው የሚችለው ችግር አይደለም ብሎታል።

ዲማ (ዶ/ር)፣ ‹‹ይህንን ክልሉ ብቻውን ሊወጣው የሚችለው ችግር አይደለም አገራዊ ችግር ነው። እንደ አገር ነው ልንወጣው የምንችለው። ዓለም አቀፍ ተቋማት ሕዝቡን ለማቋቋምና አስቸኳይ ድጋፍ እንዲያደርግ የፌዴራል ተቋማትም ተገቢውን ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፤›› ብለዋል። 

የካቲት 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተሳታፊ የነበሩት ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር)፣ ‹‹ያየነው በቂ አይደለም፣ የቆየነው ለአጭር ጊዜ ነው፡፡ ያገኘናቸው ተጎጂዎች ትንሽ ናቸው፡፡ ያገኘናቸው ትንሽ ተፈናቃዮች ግን ወደ ቤታቸው መመለስ የሚችሉበትን መንገድ እንድናመቻች ጠይቀውናል፣ መልሱን ብለዋል። እኛ ያለው ችግር አስከፊና ከባድ መሆኑን ዓይተናል፤›› ብለዋል። 

ቋሚ ኮሚቴው በመስክ ምልከታው በትግራይ ክልል 335 የጤና ተቋማት ሙሉ ለሙሉ እንደወደሙና ማኅበረሰቡም በወባና በሌሎች በሽታዎች ከምግብ እጥረት ጋር እየተሰቃየ መሆኑን ዓይተናል ሲል በመግለጫው አካቷል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ (ዶ/ር)፣ ‹‹አስቀድሜ እንደተናገርኩት በትግራይ የተፈጠሩት ተደራራቢ ችግሮች ሰው በቂ ምግብ በማያገኝበት ጊዜ በሽታ የመቋቋም አቅሙ (Immunity) እየተመናመነ እንደሚሄድ፣ በፊት ለሞት የሚያበቃ ሕመም (Chronic Disease) ያለባቸውንም እንደ ሚያባብስባቸው የታወቀ ነው፤›› ብለዋል። 

መጋዘን ውስጥ እህል ተቀምጦ ለተረጂዎች እየተዳረሰ አይደለም የሚሉ ሪፖርቶች ይሰማሉ እውነት ነው ወይ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ሰብሳቢው፣ ‹‹መጋዘን ውስጥ ያለውን እህል ሄደን አልጎበኘንም። መጋዘን እያለ ይከለከላል ብለን አንገምትም። ካናገርነው ሕዝብ የሰማነው ስሞታም የለም፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ቋሚ ኮሚቴው በመግለጫው 105 ትምህርት ቤቶች ተፈናቃዮች እንደ ተጠለሉባቸውና 522 የሚሆኑት ደግሞ በተለያዩ ኃይሎች ሥር በመሆናቸው፣ ልጆች ትምህርት እንዳይማሩ ተፅዕኖ ማሳደሩንና ማኅበራዊ ሰላም እንዳይረጋገጥ ማድረጉንም ገልጿል። በአጠቃላይ በትግራይ ክልል 1.5 ሚሊዮን ሕዝብ መጎዳቱን ማወቅ ችለናልም ብሏል። 

ሪፖርተር ባገኘው መረጃ መሠረት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ ከፌዴራል የአደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን አባላት ጋር ስለትግራይ ለመወያየት የአሥር ቀናት ቀጠሮ ይዟል። 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...