Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ተፈታኞች በብዛት የሚወድቁበትን ምክንያት አጥንቶ ባለማቅረቡ ተወቀሰ

ትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ተፈታኞች በብዛት የሚወድቁበትን ምክንያት አጥንቶ ባለማቅረቡ ተወቀሰ

ቀን:

  • ‹‹የኢትዮጵያን የትምህርት ችግር ምክንያት በአንድ ወር አጥንቶ ማጠናቀቅ አይቻልም››

ትምህርት ሚኒስቴር

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ‹‹የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የብሔራዊ ፈተናን በብዛት የሚወድቁበትን ምክንያት እንዲጠና ባዘዝኩት መሠረት አጥንተህ አላቀረብክም፤›› ሲል የትምህርት ሚኒስቴርን ወቀሰ፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር በሰጠው ምላሽ፣ የኢትዮጵያን የትምህርት ችግር በአንድ ወር አስጠንቶ ማጠናቀቅ እንደማይቻል ጠቁሞ፣ ‹‹ፓርላማው ያግዘኝና ከገለልተኛ አካል ጋር በጋራ ሆነን በተሻለ መንገድ እናስጠና›› ብሏል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በተያዘው ዓመት ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር የሩብ ዓመት አፈጻጸሙንና የዓመቱን ዕቅድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት፣ ከምክር ቤቱ ተነስተው ከነበሩት ጥያቄዎችና ከመሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ጋር ውዝግብ ፈጥረው ከነበሩት ጉዳዮች አንደኛው፣ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኞች በከፍተኛ ቁጥር የሚወድቁበት ጉዳይ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

በዚህም የምክር ቤቱ የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሚኒስቴሩ ተማሪዎቹ በብዛት የሚወድቁበትን ምክንያት በሰፊው አስጠንቶ ለምክር ቤቱ እንዲያቀርብ ሐሳብ አመንጭቶና አዞት እንደነበርም የሚታወስ ነው፡፡

ይህንን ጥናት ነው ሚኒስቴሩ ባለፈው ሐሙስ የካቲት 7 ቀን 2016 ዓ.ም. የስድስት ወራት አፈጻጸሙን ባቀረበበት ወቅት፣ አላዘጋጀህም በሚል በተወካዮች ምክር ቤት አባላት የተወቀሰው፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ ተቋማቸው ባለፉት ስድስት ወራት ስላከናወናቸው ተግባራትና ዕቅዶች በስፋት ለምክር ቤቱ ካቀረቡ በኋላ፣ የቋሚ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ጥናቱ እንዲቀርብ ባዘዙበት ወቅት፣ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) ወደ መድረክ ወጥተው ማቅረብ ጀመሩ፡፡

ሆኖም እሸቱ (ዶ/ር) እያቀረቡ የነበረው ጥናት፣ የፈተና ጥያቄዎቹ አስተማማኝነትና ተገቢነት ጥናትና ግኝቶችን ስለነበረ፣ በቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ገለጻቸውን እንዲያቋርጡና ጥናቱ እንደ ከዚህ በፊቶቹ ዓይነት ጥናት፣ ከፈተና በኋላ ጊዜውን ጠብቆ የሚካሄድ ስለሆነ እንዲያቆሙ ነናግረዋቸዋል፡፡

የኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ ነገሪ (ዶ/ር) ኮሚቴያቸው ጠይቆት የነበረውን ጥያቄ በማስታወስ፣ ከ12ኛ ክፍል ጋር በተያያዘ ሰፋ ያለ ማዕቀፍ ያለው ጥናት እንዲቀርብና እሸቱ (ዶ/ር) ሲያቀርቡ የነበረው ጥናት ጥያቄያቸውን የሚመልስ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና ቋሚ ኮሚቴው በምክር ቤቱ ጥቅምት 7 ቀን 2016 ዓ.ም. የነበራቸው ቆይታ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ቋሚ ኮሚቴው ጥቅምት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ያዘዘው ጥናት በስፋት እንዲጠናና እስከ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ለምክር ቤቱ እንዲቀርብ ለሚኒስቴሩ ደብዳቤ ጽፈው እንደነበር ነገሪ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

የደብዳቤውን ዋና ጭብጥም ሲያስረዱ፣ በሁለት ዓመታት (በ2014 ዓ.ም. እና በ2015 ዓ.ም.) የታየውን ዝቅተኛ ውጤት በሚመለከት (ከ96 በመቶ በላይ ተማሪዎች ከ50 በመቶ በታች ውጤት ማምጣታቸውን በሚመለከት) የዘርፉ ባለሙያዎች የተካተቱበት አጥኚ ቡድን በማቋቋም፣ የችግሩን ዋነኛ መንስዔና መፍትሔዎችን ሊያመለክት የሚችል ጥናት እንዲቀርብ የሚያዝ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

‹‹የመጀመሪያው ጊዜ የ2014 ዓ.ም. ውጤት ይፋ ሲሆን አልጠየቅንም ነበር፡፡ የሁለተኛው ተመሳሳይ ሲሆን ነው የጠየቅነው፤›› ሲሉ የተደመጡት ዋና ሰብሳቢው፣ ትምህርት ሚኒስትሩ በ2015 ዓ.ም. ውጤት ቢያንስ እስከ 15 በመቶ ተማሪዎች ሊያልፉ እንደሚችሉ መገመታቸውንና ተማሪዎቹን የ2014 ዓ.ም. ውጤት አስደንግጧቸው እንደነበር አንስተዋል፡፡

‹‹እኛም እነሱም የጠበቅነው ለምንድነው ያልሆነው? የተማሪዎች ውጤት በዚህ ደረጃ ያሽቆለቆለው ለምንድነው?” ሲሉ ነገሪ (ዶ/ር) ጠይቀዋል፡፡ “የተፈለገው ጥናት ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አሁንም እንዲቀርብልን እንፈልጋለን፤›› ያሉት ዋና ሰብሳቢው፣ ጥያቄያቸው እስካሁን ምላሽ እንዳላገኘ ተናግረዋል፡፡  

የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ጥናቱን በሚመለከት ለተነሳላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ፣ ባለፈው ይጠና በሚባልበት ጊዜ አንዱ ተነስቶ የነበረው የፈተና አሰጣጡና የፈተናው ምንነት ተቀይሮ እንደሆነ መጠየቃቸውንና እነሱም ያደረጉት ፈተናው በእርግጥ ተቀይሮ ከሆነ በገለልተኛ ይጠና ብለው እንዳከናወኑት ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ በአንድ ወር ተጠናቆ ይቅረብ ብለው ለጠየቁት ምላሽ የሰጡት ሚኒስትሩ፣ የኢትዮጵያን የትምህርት ችግርና እዚህ ደረጃ የደረሰበትን ምክንያት አሁን በተሰጠ አንድ ወር በገለልተኛ አካል አጥንቶ ማቅረብ እንደማይቻል፣ ይህ ይሁን ከተባለም የችኮላ ችኮላ ሥራ እንደሚሆን ተናግረዋል። 

ትምህርት ሚኒስቴር በራሱ ይህ ውጤት ለምን እየመጣ እንደሆነና ለምንድን 1,328 ትምህርት ቤቶች ፈተና እንዳላሳለፉ በተወሰነ ደረጃ በራሳቸው ለማጥናት እየሞከሩ እንደሆነ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ግን ምክር ቤቱ አሁንም ከዚህ ሰፋ ያለ በገለልተኛ አካል ይጠና የሚል ከሆነ፣ ፓርላማው እንዲያግዛቸው ገለልተኛ በሆነ አካል የተሻለ ጥናት ቢያስጠኑ እነሱም እንደሚመርጡ ገልጸዋል፡፡  

‹‹በጋራ ብናደርገው ጊዜውንም ለመወሰን ይጠቅማል፡፡ እንዲህ ዓይነት ጥናት ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል›› የሚለውን ለማወቅ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

የሚኒስትሩ ምላሽ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት ዋና ሰብሳቢው ነገሪ (ዶ/ር)፣ ምክር ቤቱ ፈተናው ችግር አለበትና ፈተናው ይገምገም እንዳላላ፣ እንዲሁም እስከ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ጊዜ ተሰጥቷቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡  

“ይህንን አዳምጠው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ ሊቀርብ ይችል ነበር [ጥናቱ]፡፡ ዛሬ ላይ ባይደርስ ግዴታ አይደለም፣ እየተሠራ ነው ሲጠናቀቅ እናቀርባለን ማለት ይቻል ነበር፤›› በማለት ነገሪ (ዶ/ር) መልሰዋል፡፡  

ዋና ሰብሳቢው አክለውም፣ ‹‹የተከበረው ምክር ቤት ሕዝብን ወክሎ ነው ጥያቄ የሚያነሳው፡፡ አስፈጻሚው ደግሞ ሕዝብን የማክበር ግዴታ አለበት፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...