Sunday, April 21, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

አፍሪካውያን እንዳይታዘቡን ጥንቃቄ ይደረግ!

የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው የመሪዎች ጉባዔ በኅብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ እየተካሄደ ባለበት በዚህ ጊዜ፣ ከዛሬ 61 ዓመት በፊት ከጥንስሱ እስከ ምሥረታው ወሳኝ ሚና የነበራት ኢትዮጵያ ስሟ በግንባር ቀደምትነት ይነሳል:: በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በአዲስ አበባ የተመሠረተው የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት፣ በንጉሠ ነገሥቱና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው (አቶ ከተማ ይፍሩ) እልህ አስጨራሽ ትግል ነበር ዕውን የሆነው (የሌሎች በርካታ ኢትዮጵያውያን አስተዋፅኦ ሳይዘነጋ):: በወቅቱ ነፃ የወጡ የአፍሪካ አገሮችን በሞንሮቪያና በካዛብላንካ ቡድኖች በመከፋፈል አንድ ላይ እንዳይቆሙ ያደረጋቸውን መሰናክል በማስወገድ፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት ምሥረታ የከፈለችው መስዋዕትነት ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል:: ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንድነት ምሥረታ በፊት ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መነሻ የሆነውን አንፀባራቂውን ፀረ ቅኝ አገዛዝ ታላቅ ድል በዓድዋ ኮረብቶች ከተቀዳጀች በኋላ፣ የአፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝቦችና ነፃነት ናፋቂዎች ዓይን ማረፊያ በመሆን ታሪክ መቼም ቢሆን ሊዘነጋው የማይችል ተምሳሌት ሆናለች::

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ከመሆን አልፋ እንደ ኒውዮርክና እንደ ጄኔቫ የተባበሩት መንግሥታትና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መናኸሪያ መሆን የቻለችው፣ ቀደምት ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት ለአገራቸው ክብር በከፈሉት መስዋዕትነት ነው:: ይህንን በታላቅ መስዋዕትነት የተገኘ ክብር ተንከባክቦ መጠበቅና ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት በዚህ ትውልድ ትከሻ ላይ የወደቀ ሲሆን፣ በዚህ ወቅትም ልክ እንደ ትናንቱ የአፍሪካዊነትን የጋራ ማንነት መቀበል የግድ ነው:: የእዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን በጠበበ የብሔርና የእምነት ማንነት ውስጥ አጥረው የጎሪጥ መተያየቱ ጠቃሚ እንዳልሆነ ይገንዘቡ:: ማንም ሰው የሚገለጽበት የራሱ የሆኑ ማንነቶች ሲኖሩት፣ ሰፊውን ዓለም መቀላቀል የሚችለው ግን አገራዊና አኅጉራዊ ማንነቱን ጭምር ሲያስከብር ነው:: በጠበበ ማንነት ውስጥ በመታጠር በአይረቤ ምክንያቶች መጋጨትም ሆነ መፋጀት፣ ሰፋ ያለ የማንነት ራዕይ በሰነቁ ዘንድ ከማስናቅ ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም:: ቀደምቶቹ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን በጋራ ሆነው ከወራሪዎችና ከተስፋፊዎች ተከላክለው ለዚህ ክብር ሲያበቁ፣ የዘመኑ ትውልድ ደግሞ የበለጠ ታሪክ ቢሠራ ይከበራል::

እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት ቁምነገር ቀደምት ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ለመጠበቅ የከፈሉት መስዋዕትነት በዓለም እንዳስከበራቸው፣ የአፍሪካ አንድነትን ለመመሥረት ያደረጉት ትግል የተሳካው ሌሎች አፍሪካውያን የነፃነታቸው አርዓያ ስላደረጓቸው፣ ተጋድሎና መስዋዕትነታቸው ከዚህ ቀደም በማንም ያልተሞከረ በመሆኑና ከፍተኛ ከበሬታ ስላገኙበት ነው:: በዚህ ዘመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከዚህ አንፀባራቂ የታሪክ ክብር በመማር አገራቸውን ማልማት፣ ማሳደግ፣ በዕውቀትና በቴክኖሎጂ ከፍ ማድረግ፣ የሰላምና መረጋጋት ተምሳሌት መሆን፣ ሌብነትን መፀየፍ፣ አድሎአዊነትን ማስወገድ፣ ለብልሹ አሠራሮች ምክንያት የሆኑ ፀረ ዴሞክራሲ ድርጊቶችን ከመሠረታቸው መንግሎ መጣል፣ ኢሰብዓዊ ጥቃቶችን በጋራ መከላከል፣ አገርን መውደድና ማናቸውንም አገራዊ ግዴታዎች ለመወጣት ዝግጁ መሆን ይጠበቅበታል:: በዚህ ስሜት ለመራመድ ግን ብሔራዊ መግባባት የሚፈጥሩ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መተማመን ያስፈልጋል:: የአገር ጉዳይ የጋራ እስከሆነ ድረስ አንዱ ባለቤት ሌላው ባዳነት እንዳይሰማው፣ በተቻለ መጠን በሆደ ሰፊነት የንግግር ባህል ማስረፅ የግድ ሊሆን ይገባል:: ልዩነትን ይዞ መነጋገርና የጋራ መግባቢያ መፍጠር አያቅትም:: በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አዕምሮ ውስጥ የአገር ፍቅር ስሜት ሲሰርፅ ከአፍሪካውያን ወንድምና እህቶች ጋር አብሮ መሥራትም ሆነ መኖር አይቸግርም:: አፍሪካውያን ኢትዮጵያ የጋራ ቤታችን ናት ብለው ከበርካታ ዓመታት በፊት ሲወስኑ፣ የቀደምት ኢትዮጵያውያን አፍሪካውያንን የማሰባሰብና በአንድነት የማቆም ትልምን ከልባቸው በመቀበል ነበር:: በዚህ ዘመን እንኳንስ ለአፍሪካውያን ለመቆርቆር እርስ በርስ በጠላትነት ስንፋጅ ሲያዩ፣ የጥንቱን ታሪካችንን እያሰቡ በሐዘን አንገታቸውን የሚደፉ በርካቶች ናቸው:: የአፍሪካ ኅብረትን ከዚህ ቀደም ከአዲስ አበባ ነቅሎ ለመውሰድ ከአንዴም ሁለቴ የተደረገው ጥረት የከሸፈው፣ በወቅቱ የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎች ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያደረገችውን ተጋድሎ በእማኝነት በማቅረብ ሽንጣቸውን ገትረው በመሟገታቸው እንደነበር አይዘነጋም:: አሁንም ቢሆን የአፍሪካ ኅብረት ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ገዝፎ ቢታይም፣ በእኛ እንዝህላልነት ምክንያት ወሳኝ የሚባሉ ጽሕፈት ቤቶቹና በርካታ ስብሰባዎቹ ወደ ሩዋንዳ ኪጋሊና ሌሎች ቦታዎች መወሰዳቸው ይታወቃል:: ኢትዮጵያውያን የቀደምት አባቶቻቸውንና እናቶቻቸውን ተጋድሎና መስዋዕትነት የሚመጥን ከባድ ሥራ እየጠበቃቸው መሆኑን ይገንዘቡ::

ኢትዮጵያ የዛሬ 61 ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጉባዔ አዘጋጅታ የመመሥረቻ ሰነዱ ሲፈረም፣ አማርኛ ቋንቋ አንደኛው እንደነበር የሚታወስ ነው:: እንግሊዝኛ፣ ፈረንሣይኛ፣ ዓረብኛና ፖርቱጊዝ፣ የዛሬ ሁለት ዓመት ደግሞ ስዋህሊ ተጨምሮበት ኅብረቱ ሲጠቀምባቸው አማርኛ ግን ተረስቶ ነበር:: የመመሥረቻ ሰነዱ ከተጻፈባቸው አራት ቋንቋዎች አንዱ የነበረው አማርኛ አሁን እንደ አዲስ የኅብረቱ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ታዬ አጽቀ ሥላሴ (አምባሳደር) አማካይነት ለኅብረቱ ሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ጥያቄ ሲቀርብ፣ ኢትዮጵያ አካሏ እንጂ ቀልቧ ከአፍሪካ ኅብረት በጣም ርቆ እንደነበረ ቀላል ማሳያ ነው:: ኢትዮጵያውያን ለረጅም ዓመታት በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ተዘፍቀው ሲፋጁ፣ ከበርካታ ዓመታት በፊት መቅረብ የነበረበት ጥያቄ ድንገት ዱብ ዕዳ ሆኖ ሲቀርብ ያስደነግጣል:: ይህ የሚያሳየው ውስጣዊ ችግርን በሰከነ መንገድ ፈር አስይዞ አገር ለማሳደግ የሚያስችል ጊዜ መባከኑን ሲሆን፣ በአፍሪካውያን ዘንድ ሳይቀር ትዝብት ላይ የሚጥል ነው::

ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ለመግለጽ እንደተሞከረው በተለይ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ፅኑ ደዌ አለ:: ይህ ከታከመ ሊድን የሚችል ዝም ከተባለ ደግሞ እንደ ካንሰር ገዝግዞ የሚገድል ደዌ ኢትዮጵያን አዳክሟል:: በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ያሉም ሆኑ የአገር ጉዳይ የሚመለከታቸው በሙሉ፣ ይህንን ገዳይ ደዌ በጋራ ለማከም የሚያስችል መግባባት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል:: ይህ ደዌ በጥላቻ፣ በቂም በቀል፣ በክፋት፣ በሐሜትና በአሉባልታ፣ በስንፍና፣ በደንታ ቢስነት፣ በአድርባይነትና በአስመሳይነት፣ በውሸት፣ በሌብነት፣ በአድሎአዊነት፣ በሕገወጥነት፣ በሴረኝነትና በጠላት ተላላኪነት የሚገለጽ ነው:: በአንድ ወቅት ኢትዮጵያውያን ከያሉበት ተጠራርተው አገራቸውን ከወራሪና ከተስፋፊ ለመከላከል ሊታመን የማይችል ጀግንነት ፈጽመው ዓለምን እንዳላስደመሙ፣ አፍሪካውያን ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ከየጎራው አሰባስበው የጋራ መሰባሰቢያ እንዳልፈጠሩ የዚህ ዘመን ትውልድ እርስ በርሱ ሲፋጅ ያሳቅቃል:: አፍሪካውያን የነፃነታችን እናት የሚሏትን የጀግኖች አገር ኢትዮጵያን ማዋረድ ያሳፍራል:: የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ሲካሄድ አፍሪካውያን እንዳይታዘቡን ጥንቃቄ ይደረግ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አስማማው ቀለሙ (ዶ/ር) ሲታወሱ (ከ1932 እስከ 2016 ዓ.ም.)

በፋና ገብረሰንበትና ዮናስ ታሪኩ  ቅዳሜ ሚያዝያ 5 ቀን 2016 ዓ.ም....

የሐረር ድምቀት

ሐረሪዎች ዓመታዊ ባህላዊ በዓላቸውን ሸዋሊድን ከሚያዝያ 8 ቀን ጀምሮ...

ኦቲዝም በደሃዎች ጓዳ

ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆችን እንደ ባህሪያቸው ተንከባክቦ ማሳደጉ እንኳን...

ኢትዮጵያ በአበረታች ቅመሞች በግለሰብ ደረጃ ካልሆነ እንደ አገር ሥጋት የለባትም ተባለ

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የፀረ አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ (ዋዳ) የተቀመጠውን...

ምንድነው ሰውነት?

"ሰው መኾን እንዴት ነው?" ወፊቷ ጠየቀች። እኔስ መች ዐውቄው፤ የገዛ ቆዳሽ ሥር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

እንደገና ያገረሸው ግጭት መፍትሔ ይፈለግለት!

ሰሞኑን በራያና አካባቢው እንደገና ያገረሸው ግጭት አስቸኳይ መፍትሔ ካልተሰጠው፣ አድማሱ ሰፍቶ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚደርስ አያጠራጥርም፡፡ በራያ በኩል የተጀመረው ትንኮሳ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተዛምቶ ተጨማሪ...

ስልታዊ መፍትሔን የሚሻው የኪነ ጥበቡ ዘርፍ

የኪነ ጥበቡ ዘርፍ በተለይም ፊልምና ሙዚቃ በውስብስብ ችግሮች ውስጥ እያለፈ ይገኛል፡፡ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ሲስተም በአግባቡ አልተበጁለትም፡፡ ስለሆነም ይህ ችግር ከመሠረቱ እየተፈታና እየተቀረፈ ካልሄደ ከዓመት...

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...