Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ ሚዲያዎች ከሥርዓት አገልጋይነት እንዲላቀቁ ጥያቄ ቀረበ

በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ ሚዲያዎች ከሥርዓት አገልጋይነት እንዲላቀቁ ጥያቄ ቀረበ

ቀን:

በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚገኙ መገናኛ ብዙኃን (Public Media) ከኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር አኳያ በጣም አነስተኛ ቢሆኑም፣ ከሥርዓት አገልጋይነትና ከሕዝብ ግንኙነት ሥራ ተላቀው ነፃነታቸውን እንዲያስጠብቁ ጥያቄ ቀረበ፡፡

በኢትዮጵያ ለዘመናት ሚዲያዎቹ እያዳበሩት የመጡትና ባህል ያደረጉት የገዥ ሥርዓት መሣሪያ በመሆን ጋዜጠኝነትንና የሕዝብ ግንኙነት ሥራን እያምታቱ መቆየታቸውን፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህሩ ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህሩ ይህን የተናገሩት በአዲስ አበባ የሚገኘው የመልካም አስተዳደር ለአፍሪካ ምሥራቃዊ አፍሪካ ቅርንጫፍ ‹‹ተቋማዊ ልማት አደረጃጀቶችና አስተዳደር በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ በተከታታይ እያካሄደ የሚገኘውን ሕዝባዊ ውይይት 5ኛ ዙር መድረክ፣ የካቲት 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ‹‹የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን አደረጃጀትና የመረጃ ተደራሽነት በኢትዮጵያ›› በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ ባቀረቡት የመነሻ ጽሑፍ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ጌታቸው (ዶ/ር) ‹‹የሕዝብ›› የሚባለው ሚዲያና አስፈጻሚው የመንግሥት አካል አንድ መሆናቸውንና መደበላለቃቸውን እንደ ማሳያ አቅርበዋል፡፡ በቅርቡ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ምርቃት ላይ ጋዜጠኞች በአጋፋሪነታቸው የጋዜጠኝነቱን መስመር መለየት እስከሚከብድ ድረስ ጠልቀው ገብተው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ከዓመታት በፊት የመንግሥት ለውጥ በተደረገበት ወቅት ሚዲያውን ከመንግሥት ጫና ለማላቀቅ የተደረገው ጥረት መልካም የነበረ ቢሆንም እየቆየ ሲሄድ ግን የሚዲያ ሕጉ ተጥሶ ጣልቃ ገብነቱ ጨምሮ፣ የመገናኛ ብዙኃንና የሕዝብ ሚዲያ ተቋማት ቦርድ አሿሿም ሕጉ ከሚለው ውጪ የፓርቲ አባላት እየተሰየሙ በአጠቃላይ የሚዲያው እንቅስቃሴ ከትናንት ወዲያ ከነበረው ተለይቶ የማይታይበት ደረጃ ደርሷል ብለዋል፡፡

‹‹የሕዝብ›› የሚባሉት ሚዲያዎች የፓርቲ ሚዲያ ለመሆን እየመረጡ ነው ያሉት ጌታቸው (ዶ/ር)፣ የመንግሥት መሆንን ቢመርጡ እንኳ ቢያንስ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያወጣው ሕግ ሲጣስ የመጠየቅ አዝማሚያ ያሳዩ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

የሚዲያ ተቋማት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ሲያብራሩ ያቀረቧቸው አመላካች ጉዳዮች፣ የሚዲያዎች በሕዝብ ግንኙነት ሥራ ውስጥ መግባት፣ የኤዲቶሪያል ነፃነታቸውን ለመንግሥትና ለቢዝነስ ተቋማት መሸጥ፣ ሙስና ስለተንሰራፋበት ምክንያት የምርመራ ዘገባ ላይ አለመሳተፍ፣ ሕዝብ መረጃ ማግኘት ቅንጦት እንደሆነበት፣ ሕዝብ ደኅንነት ሥጋት ወድቆ ወጥቶ መግባት ተስኖት ከአደጋ የሚታደጉት መረጃዎች በማጣቱ ምክንያት፣ በመረጃ ፆም ከማደር ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መመርኮዙን አስረድተዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ የሚዲያ ነፃነት በመንግሥት መቀያየር በሚኖርበት ጊዜ ሁሉ የምታጓጓ የክረምት ፀሐይ ብቅ ትልና ልሞቃት ነው ብሎ ሰው ሁሉ ሲጓጓ፣ ወዲያው እንደምትጠፋው በሚዲያውም ዘርፍ ደጋግመን ብዙ ተስፋ አድርገን ነበር፤›› ብለዋል፡፡

የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህሩ አክለውም ‹‹የሕዝብ›› በሚባሉት ሚዲያዎች ላይ የነገሠው ችግር ራሳቸውን ሳንሱር ለማድረግ የሚዳዱት ነፃነታቸውን በማጣታቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ ጋዜጠኞችም በቁጥጥር ውስጥ ሆነው ከህሊናቸው ጋር ብዙ ሙግት ያለባቸው ናቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ሚዲያዎችን ሕዝቡ ሊደግፋቸው እንደሚገባ፣ ነገር ግን ሚዲያዎችም ሕዝቡ የእኛ እንዲላቸው ተጠያቂነት ያለው አሠራር ኖሯቸው ለሕዝብ የቀረቡ ዘገባዎችን ሊያቀርቡ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በውይይት ከተገኙ በርካታ ተሳታፊዎች ለችግሩ ምን እናድርግ፣ እንዲሁም ችግሩ የፓርቲ ተፅዕኖ በመሆኑ በውይይት ሊመጣ የሚችል ለውጥ ይኖራል ወይ የሚሉ በርከት ያሉ ሐሳቦች ተነስተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህር አብዲሳ ዘርዓይ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥትን አግዝፎና ሰፊውን የማኅበረሰብ ክፍል አኩስሶ የማየት ችግር አለው ብለው፣ ‹‹መንግሥትን የምንመለከትበት መነጽር በደንብ ሊፈተሽ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

የፓርላማ አባላት የፓርቲ ተወካይ እንጂ የሕዝብ ተወካዮች አይደሉም ያሉት አብዲሳ (ዶ/ር)፣ እስኪ በእውነቱ ሕዝብን የወከለ ፓርላማ አለ ወይ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ከመጣው ሥርዓት ጋር ጃኬቱን እየቀያየረ ምንዳ የሚለቅም አድርባይ የበዛበት ጊዜ መሆኑን ገልጸው፣ ሥልጣን የያዘ ፓርቲ መንግሥት ሲመሠርት ሚዲያዎችን እንደፈለገ አድርጎ የራሱን ተክለ ሰውነት የሚገልጽበት ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ሚዲያውን እንደ አፈ ቀላጤ በማድረግ አሁን ስለአገር ተጨባጭ ሁኔታ መግለጽ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ በመሆኑም ሚዲያዎች ራሳቸውን ሆነው መቆም እንዲችሉና የሕዝብ አገልጋይ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ሁሉም አካል ኃላፊነት አለበት፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር አብዱላዚዝ ዲኖ (ዶ/ር)በዘርፉ ሕዝብ ላይ ያተኮረ የአስተሳሰብ ለውጥ አስፈላጊነትን ገልጸው፣ ሕዝቡ የባለቤትነት ስሜት ኖሮት ጠያቂ ማድረግ የግድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከተሳታፊዎች መካከል መንግሥት በበጀት እየደገፋቸው ያሉ ሚዲያዎች ገለልተኛና ራሳቸውን ችለው ይቁሙ ማለት የማይታሰብ መሆኑን የገለጹ ነበሩ፡፡ የሚዲያ አመራሩ ለእንጀራ የሚሠራ ከሆነ ሥራውን ሊተውና ሊያቆም ይገባል የሚል አስተያየት ተሰንዝሯል፡፡

ይሁን እንጂ ጌታቸው (ዶ/ር)መንግሥት ‹‹የሕዝብ›› በሚባሉት ሚዲያዎች ላይ ጭራሽ ጣልቃ አይግባ እንደማይባል፣ በተወሰነ ደረጃ ሊገባ እንደሚችል፣ ነገር ግን ሁልጊዜም እኔ ብቻ ልናገር የሚል መሆን የለበትም ብለዋል፡፡

‹‹መንግሥት ማለት እኛ መርጠን ያስቀመጥነው እስከማይመስል ድረስ ከሚገባው በላይ አድርገን ስለምናስበው ልናወርደውና ልንቀይረው እንደማንችል፣ መንግሥት ኃይለኛ ሁሉን ነገር ማድረግ የሚችል ጉልበተኛና ጠያቂ የሌለው አድርጎ ማሰብ መቆም አለበት›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹የሚዲያ ሥራ ኢትዮጵያ ውስጥ የእንጀራ ጉዳይም ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ጋዜጠኝነት ከእንጀራ በላይ በመሆኑ ለእንጀራ ተብሎ የሚገባበት ሥራ አይደለም፡፡ ለእንጀራ ከሆነ የተሻለና የማያዋጣ ዘርፍ ላይ መሰማራት ይሻላል፤›› ብለዋል፡፡ ጋዜጠኛ ሆነው ለመሥራት የሚፈልጉ ሁሉ ሊከፈል የሚገባ ዋጋና ለኅብረተሰቡ አስተዋጽኦ መደረግ ያለበት በመሆኑ፣ ይህንን ግምት ውስጥ አስገብቶ ሙያው ውስጥ መሰማራት ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...