Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርራሳችን የሰወርናትን ሰላም በመፈለግ ስንት ዓመት ባጀን?

ራሳችን የሰወርናትን ሰላም በመፈለግ ስንት ዓመት ባጀን?

ቀን:

በመኮንን ሻውል ወልደ ጊዮርጊስ

ሰላም ከራቀችን በርካታ ዓመታት ተቆጠሩ። ከደርግ ሶሻሊስታዊ ሥርዓት ጀምሮ ኢትዮጵያውያን ጎራ በመለየት እርስ በርስ እየተገዳደልን ሰላማችን እንድትሰወር በማድረግ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሰናል። ዛሬም መተላለቃችን ቀጥሏል። ሞት ቅርብና ጉያችን ያለ በተራ የሚወስደን መሆኑን ፍፁም ዘንግተን፣ በደመ ቀዝቃዛነት መገዳደላችን ለትውልድ ተሸጋግሯል።

ትናንት ግራና ቀኝ፣ አብዮተኛና ፀረ አብዮተኛ እየተባባልን እንገዳደል ነበር። ትናንት ትምክህተኛ፣ ጠባብ፣ የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ፣ ወዘተ እየተባባልን እንጠላላና እንተሳሰር ነበር። ዛሬ ደግሞ ሰው መሆናችንን ፍፁም ዘንግተን በጎሳ ተከፋፍለን ከፊል አገርን እያወደምን ነው (የትናንቱ የትግራይና የአማራ ክልሎች ጠባሳ ሳይሽር ዛሬ በኦሮሚያና በአማራ ክልል ሌላ ቁስል፣ ሌላ ጠባሳ ሌላ ቂምና ቁርሾ እያስተናገድን ነው። እናም የለውጥ ባቡሩ ከአምስት ዓመት በፊት ከተነሳንበት በቅንነት ላይ ከተገነባ ሐዲድ ያፈነገጠ ይመስላል)፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እናም እላለሁ ለሰላም መስፈን ገዥው የብልፅግና ፓርቲ እጁን ይዘርጋ። እርስ በርስ በመሰዳደብና በመገዳደል የሚገኝ አንዳችም አርኪ የሆነ ለውጥም ሆነ አመርቂ ድል የለም። የበለጠ ቁርሾና ቂም በቀልን ወልዶ የተራዘመ ግጭትና  አጠቃላይ ቀውስ ውስጥ አገርን ያሰጥማል እንጂ።

በእርግጥ ይህ እየታወቀ በተገኘው መድረክ ሁሉ በአንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች ስድቡና ለመተላለቅ የሚጋብዝ ፕሮፓጋንዳው በየዕለቱ ሲዥጎደጎድ ይሰማል። እጅግ አሳፋሪ በሆነ ሁኔታ ሳይቀር ሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳዎች ይረጫሉ። አንዱና ዋነኛ የኃፍረተ ቢስነት መገለጫ ለመከላከያ ሠራዊታችን እንደ አጠቃላይ የሚሰጠው ስም ነው። አሳፋሪ ስለሆነ ዝርዝር ውስጥ አልገባም። የአገር መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያ ዳር ድንበርን ጠባቂና አስከባሪ ነው፣ አለኝታችን ነው፣ መከታችን ነው። በአንፃሩ የሠራዊቱን ስም የሚያጠለሹ ግለሰቦች ኃፍረተ ቢሶች ናቸው። 

በኃፍረተ ቢስነት የሚያወሩትም ማረም አለባቸው። ከፋፋይ ሐሳብ በዕብደት ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ እንደ ሂትለርና ሞሶሎኒ ያበደ፣ በዘር ዛር የተያዘ ሰው ሐሳብ ነው። እሳቱን ማባባስና እሳቱ ላይ ነዳጅ መርጨትን እንደ ሙያ ይቆጥራልና፡፡ ስድብ ሙያ ሆኖ አያውቅም፡፡

ሙያ ማለት የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ ወንድማማችነቱን እንዲገነዘብና በአገሩ የትም ሥፍራ ሄዶ በነፃነት ሠርቶ የሚኖርበትን የፖለቲካ ዓውድ እንዲመጣ፣  ሰላማዊ ትግል የሚያደርግ የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋምና በሰላማዊ መንገድ መታገል ነው። ጥላቻን ፈፅሞ የሚጠላ አዲስ ትውልድ ለመፍጠር መትጋት ነው። ስድብ ሙያ አይሆንም። ዘረኝነትን እየተቃወሙና እያወገዙ በዘር ሙዚቃ አሸሼ ገዳሜ በማለት ‹‹እኛ›› እና ‹‹እነሱ›› ማለት ሙያ ሊሆን አይችልም።

አንዲሁም አንድ ወገንን ይጠቅማል ለሚል የፕሮፓጋንዳ ግብ ሲባል ብቻ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ‹‹እኛ›› እና ‹‹እነሱ›› በማለት በቋንቋና በጎሳ መከፋፈል ጥላቻን በማስፋፋት የእርስ በርስ ጦርነትን ሲያዋልድ እንጂ፣ ሰላምንና ፍቅርን ሲያነብር ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም።

  በዚህ ዘመን በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ያልተገባ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን የጥቂት ቡድኖች፣ ወይም የአንድ ፓርቲ ወይም ደግሞ የጎሳ ስብስብ አድርጎ መቁጠር የሰላም ዕጦትን ያባብሳል እንጂ የዜጎችን ወጥቶ መግባት አስተማማኝ ሊያደርግ አይችልም። አስተማማኝ ሰላም የሚመጣው በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ ከልብ በመወያየት ብቻ ነው።

 ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ በኦሮሚያም ሆነ በአማራ ክልል መንግሥታት የአስተዳደር ወሰኖች ውስጥ የውድ ዜጎቻችን ሕይወት በመከራ ውስጥ ያለውም ለተከሰቱት ግጭቶች፣ የሕዝብ ጥያቄዎችና የፖለቲካ ፍላጎቶች ወንበር ስቦ በጠረጴዛ ዙሪያ ከመወያየትና መፍትሔ ከማምጣት ይልቅ፣ በስድብና በጥይት ሰላምን ማስገኘት ይቻላል ብለው የሚያምኑ የግለሰብ ስብስቦች በቀኝም ሆነ በግራ በመኖራቸው ነው።

በጥይት፣ በስድብ፣ ስም በማጠልሸት በመጠፋፋት ዘላቂ ሰላምን በአገራችን ለማምጣት አይቻልም። በመገዳደልና በጥላቻ ብዛት የሚመጣው ከሆድ የማይጠፋ ቂምና ቁርሾ ነው። ይህ ቂምና ቁርሾም በቀልን ያረግዝና የትም ሥፍራ የሚወለድ ሞትን ያስከትላል።

እየሆነ ያለው ይኸው ነው። በማሰር፣ በመግደል፣ በማስፈራራት ሰላም አይመጣም። መንግሥትን በመሳደብም፣ የግለሰቦችን ስም በማጥፋትም፣ ስም በማጠልሸትና ገጽታን ጥላሸት በመቀባት የሚመጣ ድልም የለም።

ማንኛውም የፖለቲካ ቡድን በሕዝብ ቅቡልነት ያለውን የፖለቲካ ዓላማ በፍቅር ይዞ ከተነሳና ያንንም በእውነት ተሰባስቦ አብሮ የመኖርና የማደግ ፍላጎት በተግባር ካሳየ፣ ይዋል ይደር እንጂ ሕዝባዊ ድል መጎናፀፉ አይቀርም። ሕዝብን በመዝረፍ፣ በመግደል፣ በማፈናቀልና በማንጓጠጥ ግን ዘላቂነት ያለው ሰላምም ሆነ ድል አይገኝም።

በአሁኑ ወቅት እኮ በመሸ ቁጥር ‹‹ደሞ መሸ›› በማለት የሚሳቀቁ፣ ሲነጋ ደግሞ “ይኸው ነጋ ተመስገን” በማለት የሚያመሠግኑ ዜጎች ቁትራቸው ጥቂት አይደለም።

በአማራና በኦሮሚያ ክልል በገጠር ቀበሌዎች ያሉ ገበሬዎች፣ ነጋዴዎች፣ ወዛደሮች፣ አርብቶ አደሮች የዘወትር ኑሮ በሥጋት የተሞላ ሆኗል። በገጠር ያሉ ዜጎች በሙሉ ሕይወታቸው በምሽት በአደጋ የተሞላ በመሆኑ የጨለማውን ጊዜ ፈጣሪ ቢረሳውና ጀንበር ባትጠልቅ ደስ ይላቸዋል።

መቼም ተፈጥሮ ሒደቱን አይቀይርምና በየአንዳንዱ ቀንና በሚኖረው ጨለማ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የሞት ዜና በበነጋው ይሰማል። በየቀኑ የፖለቲካ  ዓላማ ይዘን፣ ነፍጥ አንግበን “በምርጫ” ሥልጣን ይዞ አገር እያስተዳደረ ያለውን መንግሥት በትጥቅ ትግል ለመቀየር ተሠልፈናል በሚሉ ቡድኖችና የእነሱን ጥቃት እከላከላለሁ በሚለው መንግሥት መካከል በሚካሄደው ጦርነት እንደ ዋዛ ቀላል ቁጥር የሌለው ሰው ሕይወት ያልፋል።

በየጊዜው ከየቤቱና ከየአውራ ጎዳናው ላይ ግለሰቦችን አግተው የሚወስዱ የታጠቁ ‹‹ኃይሎችም›› አልፎ አልፎ የወሰዷቸውን ሰዎች ሕይወት ይቀጥፋሉ። ያገቱትን ሰው ያላንዳች አስገዳጅ ሁኔታ መግደል የዕገታ ገንዘብ ጠያቂዎች አስቀያሚ ድርጊት ነው።

እንደሚታወቀው 98.6 በመቶ ሕዝብ ሃይማኖተኛ በሆነባት ኢትዮጵያችን ውስጥ፣ በዚህች የምድር ገነት በሆነች አገራችን ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት እየተደጋገመ መከሰቱና ጭካኔ መብዛት በራሱ እጅግ የሚያስደነግጥ ነው።

በዚህ ጊዜ በራሳችን ካልደረሰ በስተቀር የሌሎች ሰዎች ሞት የማያስደነግጣቸውና የማያሳስባቸው ‹‹የቁም በድኖች›› በአገራችን እየበዙ መምጣታቸው በራሱ መጪውን ጊዜ እጅግ አሳሳቢ ያደርገዋል።

መጪውን ጊዜ እጅግ አስፈሪ ሆኖ እንዲታየን የሚያደርገው ደግሞ ልበ ደንዳናው የትም ተገድሎ የወደቀን አምሳያውን ክቡሩን ሰው ‹‹እንኳን ሞተ፣ ሲያንሰው ነው፣ ይኼ ምንትስ፣ ወዘተ.›› ከማለት አልፎ  ለሌሎች ንፁኃን እህት ወንድሞቹ ሳይቀር ሞትን የሚመኝ ሁኖ ስናገኘው ነው። ሆኖም ወለፈንድ የሆነ ሁላችንም እንደ እምነታችን በየዕለቱ ወይም በየሳምንቱ የአምልኮ ሥነ ሥርዓት የምንፈጽምና ፈጣሪን እንፈራለን የምንል መሆናችንን አስተውልና በነባራዊው ሁኔታ ግን በእጅጉ አዝናለሁ።

የሞተው የገዛ ጎሳችን ሆኖ ሳለ እንኳ ጎሳውን ሰርዘን ሟችን ማንጓጠጣችን እንዴት አያሳዝንም? እኛ ብቻ ለዘለዓለም የምንኖር ይመስል። እንዴ ከሞት እኮ ማንም አያመልጥም። ዛሬ ወይም ነገ ሁላችንም እንሞታለን። ሁሉም ሰው ሞትን በጉያው ሸሽጎ ነው የሚኖረው። ዞሮ ዞሮ ሞት ላይቀርልን ለምን ይሆን እንዲህ የተካረረ ጥላቻ በመሀላችን በሐሰት ትርክት ተዘርቶና ለፍሬ በቅቶ እርስ በርስ  የምንጨራረሰው?

በእውነቱ ሊገባኝና የማይገባኝ ነገር ቢኖር በሐሰት ትርክት ተዘርቶ የጎመራውን ፍሬ ሁሉም በየጎሳው ሳያስተውል እየቀጠፈ በልቶ በጥላቻ አምረው መቆዘሩና በጥጋብ የተነሳ ሰማይን በእርግጫ ለማለት መቃጣቱ ነው።

የሠለጠነው አገር ሰው እኮ በልፅጎ እየኖረ ያለው ሰው መሆኑን ብቻ አምኖ ጥቁር፣ ቢጫና ነጩ በትብብር፣ በፍቅርና በአንድነት ተከባብሮና ተፈቃቅዶ በመኖር ነው። በጋራ እየሠራና የጋራ ጠላቱን በኅብረት እየተከላከለ በአንድነት በመበልፀጉ ድህነትን ታሪክ ማድረግ ችሏል። የሰው ልጅ በጎሳና በነገድ ተቧድኖና ተደራጅቶ የፈጠረው ታላቅ አገር የለም። የኃያሎቹን አገሮች አገር ምሥረታ በቅጡ መመልከት ብቻ ያነሳሁት ሐሳብ እውነትን ያረጋግጣል።

የዓለማችን ኃያላን አገሮች የተመሠረቱት በዜግነት ክብር ላይ ነው። መንግሥታቱ  ከተቋቋሙበት ጊዜ ጀምሮ በዜግነት ክብር ያምናሉ። ለዜግነት ክብርም የላቀ መስዋዕትነት ይከፍላሉ። በዚህ የተነሳም ዜጎች በአገራቸው ኮርተውና ተከብረው እንዲኖሩና የመቃብር ወግ እንዲያገኙ አድርገዋል። መቼስ ሁሉም ሰው ሟች ነውና።

የኃያላኑ መንግሥታት ቁንጮ ሰዎች አገራቸውን ለማበልፀግ ሕገ መንግሥታቸው  የሚሰጣቸውን ሥራና ሥልጣን በሚገባ በመጠቀም፣ የዜጎችን መብትና ግዴታ በእኩል ያስከብራሉ፣ ያስፈጽማሉ። ያልባነነው ኢትዮጵያዊ ግን በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባስቦ፣ በጨዋ ደንብ ከመነጋገርና በወጉ ተደማምጦ ለዜጎች የተሻለ ሰላምና ብልፅግና ከማዋለድ ይልቅ ጎራ ፈጥሮ ይጫረሳል። የከንቱ ከንቱ በሆነ የእርስ በርስ ጦርነት ወንድም ወንድሙን በመግደል ኢትዮጵያን ያደክማል።

ይህ ኢትዮጵያን የማዳከም እንቅስቃሴ በኃያላኖቹና በታሪካዊ ጠላቶቻችን ሥውር እጅ የታገዘ እንደሆነ ታሪክና ድርጊት ቢመሰክርም፣ እኛ ግን ይህንን ተገንዝበን ከእርስ በርስ መገዳደል ዛሬም አልታቀብንም፣ እንደ ትላንትና ሁሉ።

መገዳደል ብቻም አይደለም፣ እርስ በርስም እንሰዳደባለን። እርስ በርስ ዘውግ ለይቶ በመሰዳደብና በመገዳደል የሚገኝ በዜጎች ቅቡልነት ያለው ለውጥና ጮቤ የሚያስረግጥ ድል የለም፣ አይኖርምም።

በበኩሌ ኢትዮጵያውያን ሳንዘገይ ወደ ሰላም ጠረጴዛው መመለስ የሚያዋጣን ይመስለኛል። በሰላም ጠረጴዛው ላይ የተቀመጡ በሕዝብ ቅቡልነት ያላቸው ቅን አጀንዳዎች አሉና እነዚህን ቅን አጀንዳዎች ፖለቲከኞቻችን ግለሰባዊ አያድርጓቸው። ወደ ሒሳብ ማወራረድም አናመዝን። በግለሰባዊ ቁርሾ፣ ቂምና በቀል አገር ተረካቢውን ትውልድ አንጉዳው፡፡ አገሪቱ በሌላት አቅም ያሠለጠነቻቸውን ድንቅና ጀግና ወታደሮቻችንንም ትልቅ ስምና ደማቅ ታሪክ ለማይኖረው የእርስ በርስ ጦርነት ሰለባ አናድርጋቸው።

ጎበዝ በሰላምና በደስታ ኖሮ መሞትን እኮ ሁሉም ሰው ይመኘዋል። ማንም በወጣትነት መሞትን አይሻም፣ ፍላጎቱ ወደ ሞት አንደርድሮ ካልወሰደው በስተቀር። እንዲህ ስል በፖለቲካ ሰበብ ጎራ ለይተው የሚገዳደሉ በግራና በቀኝ ያሉ ወጣት ወንድምና እህቶቼ የፖለቲካ ዓላማ የላቸውም ማለቴ አይደለም። ይነስም ይብዛም የሚዋጉበት ዓላማ አላቸው። ሆኖም ቆም ብለው ካስተዋሉት ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ኑሮ መደላድል ሲባል ልዩነትን ይዞ ከመንግሥት ጋር በመደራደር፣ ተጨባጭ ሰላማዊ ውጤት ማምጣት እኮ ይቻላል። አሁን ለአገራችን ሕዝብ  የሚያስፈልገው አስተማማኝ ሰላም ነው።

ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለውን አምሳያውን እየገደለ፣ በነገድና በማኅበረሰብ እየጠራ ፉከራና ሽለላ የሚያሰማበት፣ ‹‹የፍየል ወጠጤ…›› የተባለ ቀረርቶ የሚዥጎደጎድበት  ዘመንና ወቅት ላይ አይደለንም።

ዓለም በቴክኖሎጂ በእጅጉ ተራቃለች። አንድ ወሬ በሰከንድ የዓለም ጫፍ ይደርሳል። የኢትዮጵያውያን ረሃብ፣ እርዛት፣ ጎዳና አዳሪነት ብቻ ሳይሆን የጥቂቶች ጥጋብና አስረሽ ምቺው ድርጊትም ከዓለም ሕዝብ የተሰወረ አይደለም። ክቡሩ ሰው እንዴት ተጨባጩን እውነት ክዶ ዘወትር አሸሼ ገዳሜ እያለ ስንት ሥራ ተሠርቶበት የሚያልፍ ሕይወቱን በከንቱ ያባክናል?

ኧረ ጎበዝ ሜዳ ላይ እየተንቀለቀለ ያለው እሳት እኮ ወደ ተራራው መገስገሱ አይቀርም። ሰውነትን የካደው አውዳሚው እሳት ተራራው ላይ ሲደርስ አገርን ሁሉ እንደሚያወድም ለምን አንገነዘብም? ይህንን እውነት ፖለቲከኞች በቅጡ ተገንዝበን ለምን ከወዲሁ መፍትሔ ለማምጣት ከልባችን አንንቀሳቀስም? ከአዲስ አበባ ጥቂት  ኪሎ ሜትሮች ዙሪያ ያለው ከፍተኛ ፍርኃት በተለይም በከተሞች ዳርቻ  ከመንግሥት የተሰወረ ነውን?

በከተሞች ጫፍ የሚኖሩ ዜጎችና የፋብሪካ ሠራተኞች በመሸ ቁጥር ምሽቱን በሰቀቀንና በሥጋት እስከ መቼ ያሳልፋሉ? እንዲህ ዓይነት የፍርኃት ኑሮ እኮ በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ አልነበረም። ጠመንጃ ያነሱ ኃይሎች ጥያቄ ምንድነው? ጥያቄያቸው በመነጋገር ሊፈታ አይችልም ወይ? አንዳንዱ መንግሥት ሞቶ ካልተቀበረና እሱ የሠራው በጎ ነገር ሁሉ ፈርሶና ወድሞ በሌላ ባለነፍጥ ካልተተካ በስተቀር በአገር ሰላም አይመጣም ወይ? ወይስ ሰላም በሽብር፣ በቅጥፈት፣ በመሰዳደብ፣ በመገዳደል፣ የዕለት እንጀራውን ለማግኘት ጎንበስ ቀና የሚል ዜጋን እያፈኑ የጠየቅንህን ገንዘብ ካላመጣህ ብሎ በመግደል ከጠመንጃ አፈሙዝ ነው እንዴ ሰላም የሚመጣው?

ሰላም የሚመጣው ሰውን ሁሉ እንደ ራስ ዓይቶ በመውደድ፣ ሞት ይዘገይ ይሆናል እንጂ ወደ ራስም መምጣቱን በማስተዋል፣ በሆደ ሰፊነት፣ ይቅር በፈጣሪ በማለት፣ አንደበትን ከስድብና ከአሉባልታ በማራቅና እንደገና ጥፋት ላለመሥራት ንሰሐ በመግባት ብቻ ነው።

በማኅበራዊ ኑሯችን እንኳ ሰላምን የምናሰፍነው በዕርቅና ይቅር ለፈጣሪ በመባባል ነው። ለመንግሥትና ለፖለቲከኞች ሰላምን በይቅርታ ማስፈን ከባድ  ቢሆንም እንወክለዋለን፣ ካለበት ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግር እናላቅቀዋለን ብለው በየትኛውም መንገድ ሠልፍ የያዙ ፖለቲከኞች ማየት ያለባቸው የሰላም ያለህ የሚለውን ሕዝብ ነው። የሰላም ያለህ የሚለውን ሕዝቤ የሚሉትን የሰዎች ስብስብ ሥቃይ በመገንዘብ ችግሩን ወደ መድረክ በማምጣት በጠረጴዛ ዙሪያ በመደማመጥ ተወያይተው ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት ይችላሉ።

ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣትም ሁሉም የፖለቲካ ቡድኖች የውይይት፣ የዕርቅና የሰላም ‹‹ጠረጴዛ›› ላይ አጀንዳቸውን በማስቀመጥ በሆደ ሰፊነት ለድርድር ቢቀመጡ መልካም ነው። ገዥው የብልፅግና ፓርቲም ዝነኛ ደራሲያችን በዓሉ ግርማ ነፍሱን ይማረውና በኦሮማይ መጽሐፉ፣ ‹‹እኔ ውብ የምለው የሰውን ልብ ነው›› በሚለው ግጥሙ ያለ ሰው አገርን መውደድም ሆነ ማሳመር ከንቱ እንደሆነ እንደገለጸው፣ ይህንኑ መልዕክት በቅጡ በመገንዘብ ለዜጎች ደኅንነትና ሰላም፣ እንዲሁም ለነገው አገር ተረካቢ ትውልድ በማሰብ የሰላም አጀንዳውን የውይይት ጠረጴዛው ላይ ያቅርብ፡፡

ቅን በሆነ ይቅር ባይነት ለሕዝብ ሰላምና ብልፅግና የሚበጅ አርኪ የፖለቲካ  ውሳኔ ላይ በመድረስ፣ በድርድር ዜጎችን በሙሉ ከጫፍ እስከ ጫፍ የሚያስደስት የሰላም መፍትሔ ለማዋለድ ሆደ ሰፊና አስተዋይ እንዲሆን ሰላማቸው የተናጋና በመሸ ቁጥር በሰቆቃና በሥጋት የሚኖሩ ዜጎች ሁሉ ምኞት ነው።

ሰላም  ለኢትዮጵያ!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው mekonnenshawelsun@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...