Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልለትውልድ ያለማንበብ ድክመት ተጠያቂው ማን ነው?

ለትውልድ ያለማንበብ ድክመት ተጠያቂው ማን ነው?

ቀን:

‹‹አገራችን ላለችበት ጭንቅና ለገባችበት መከራ ትልቁ ምክንያት የሚያነብና ምናብ ያለው ትውልድ አለመፈጠሩ ነው፤›› ሲል ደራሲና ገጣሚ ታገል ሰይፉ አሁን ስላለው ደካማ  የማንበብ ባህል፣ ትውልዱ ከንባብ እንዴት እንደራቀና አለማንበብ በአገር ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ተናግሯል።

በንባብና በዕውቀት ባልተገነባ ትውልድ ላይ አገር ለመገንባት መሞከር ውጤቱ ኪሳራ ነው፡፡ ለአገር ግንባታ ያነበበ ትውልድ መፍጠር ላይ በቅድሚያ ሊሠራበት ይገባል የሚለው ታገል፣ በንባብ የታነፀ ትውልድ አገርን ከመፍረስ ይታደጋል፣ ያነበበ ትውልድ አሁን የሚታየውን ስህተት አይሠራም፣ ወንድሙን አይገልም ቤትም አያፈርስም በማለት ያስረዳል፡፡

ለትውልድ ያለማንበብ ድክመት ተጠያቂው ማን ነው? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በንባብ ለሕይወት መድረክ ከቀረቡት መጻሕፍት አንዱ

ገጣሚ ታገል በየአካባቢው በወጣቱ ለሚቃጠሉ፣ ሆቴሎች ለሚፈርሱ ድልድዮች፣  ለሚወድሙ ከተሞችና መሠረተ ልማቶች መንግሥትን፣ ባለ ሀብቶችንና ወላጆችን ዋነኛ ተጠያቂ ያደርጋል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ምክንያቱ ደግሞ እነዚህ አካላት “በዕንቁላሌ በቀጣሽኝ” እንዲሉ ሕፃናት ከጅምሩ  ማንነታቸውን ያከበሩ፣ የአገር ፍቅርን የተላበሱ እንዲሁም ታሪክና ማንነታቸውን ያወቁ ይሆኑ ዘንድ ኮትኩቶ ማሳደግ የመጀመሪያ ሥራ ሊሆን በተገባ ነበር ይላል፡፡

መንግሥት የትምህርት ሥርዓቱን ከማሻሻልና ከማስፋፋት ባሻገር ሕፃናትና ወጣቶች ላይ የሚሠሩ ደራሲዎችንና ሌሎች የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን መደገፍና ማበረታታት ይኖርበታል የሚለው ገጣሚ ታገል፣ ጣራ የነካውንና ብዙዎችን ከሙያው እንዲወጡ የሚያደርገውን የኅትመት ዋጋን ከመቀነስ ጀምሮ ዕገዛ ቢያደርግ ሲል ተናግሯል፡፡

 ባለሀብቶችም ቢሆኑ ሆቴል ከመገንባታቸው በፊት በአካባቢው ባሉ ወጣቶች ላይ ሊሠሩና ሊያስተምሩ ይገባል፣ በፈረሰ አስተሳሰብና ግንዛቤ ላይ ፋብሪካ ማቋቋምና ሆቴል መገንባትን “ከፈረሱ ጋሪው ቀድሞ” ይለዋል፡፡

ትናንት ስለአስተዳደጉ ያልተጨነቅንለት ወጣት ዛሬ የተሠራን ቢያፈርስ ጥፋቱ የእሱ ብቻ ሳይሆን የብዙዎች እጅ አለበት የሚለው ታገል፣ ባለሥልጣናትም ቢሆኑ ከልጆቻቸው ጀምረው የተሻለና ምክንያታዊ ትውልድ መፍጠር እንደሚገባቸው መክሯል፡፡ በሥራ ዘመናቸው ላጠፉት ይቅርታን የሚቀበሉ ለሠሩት መልካም ሥራ አክብሮትና ሽልማትን የሚያበረክቱላቸውን ትውልድ፣ ራዕያቸውንና ጅምራቸውን ዳር የሚያደርሱ አገር ተረካቢዎችን ለማፍራት የሚያነብና የሚያሰላስል ትውልድ ላይ መሥራት ተገቢ እንደመሆነም ያክላል፡፡ ባለሀብትም ሆነ ባለሥልጣን የሃይማኖት አባቶችም ቢሆኑ በየእምነታቸው የትውልድ መጽሐፍ ላይ ቢሠሩ ሲል ሐሳቡን ያክላል፡፡

አንዳንድ አስተዋይ ባለሀብቶች ፋብሪካ በሚከፍቱበት አካባቢ ትምህርት ቤት፣ ውኃ ሲሠሩ ይታያል፡፡ ይህ ጥሩ ሆኖ ሳለ ለሕፃናት የንባብ ሕይወታቸው ላይ ግን እየተሠራ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄን የሚያጭር ነው ያለው ገጣሚ ታገል፣ ብዙዎች ትኩረት ሊያደርጉበት እንደሚገባ ይናገራል።

በሌላ በኩል በብዙ ውጣውረድ የሚጻፉ መጻሕፍትን የሚያነብ ትውልድ አለወይ? የሚለው ያሳስበኛል የሚሉት ደግሞ ወ/ሮ የሺመቤት ካሳ ናቸው። ‹‹የትውልዱ ሁኔታ ያሳስበኛል፤›› ያሉት ወ/ሮ የሺመቤት ከዚህም በመነሳት  የተጫጫናቸው የእርጅና ዘመን ሳይበግራቸው ለሕፃናት ማስተማሪያ  የሚሆኑ በተረትና ምሳሌ የታጀቡ ግጥሞችንና መጽሐፍ ለንባብ አብቅተዋል።

‹‹አለላና ሌሎች ትምህርታዊ ተረቶች›› በሚል ለንባብ የበቃችው የተረት መጽሐፋቸውን የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. “ንባብ ለሕይወት” በሚል በሚሊኒየም አዳራሽ በተዘጋጀው የመጽሐፍ ዓውደ ርዕይ ለገበያ አቅርበው ነበር።

 ወላጆች ለልጆቻቸው መጽሐፍ ከመግዛት ይልቅ  ሌሎች ብልጭልጭ ነገሮችን ሲገዙ መታዘባቸውን ይናገራሉ። ቤት ሲሠራ መሠረቱን ጠብቆ ካልተሠራ ዕድሜ አይኖረውም ያሉት ወ/ሮ የሺመቤት፣ ልጆች ደግሞ የአገር ሥረ መሠረት በመሆናቸው ሁሉም መነሻውን ልጆች ላይ ማድረግ ይኖርበታል ባይ ናቸው፡፡

የግል ምልከታቸውን ሲናገሩ ወላጆች ለልጆቻቸው በቂ ትምህርት ሳይሰጡና አርዓያ ሳይሆኑ ትውልዱን ይወቅሳሉ ዘመንን ይራገማሉ ይላሉ፡፡

‹‹ዘመን ምን አደረገ? ይመሻል ይነጋል ሥራውን ይሠራል ስህተቱ ወላጆች ለልጆች ምን ማስረከብ አለብን? የሚለው ነጥብ ላይ ትኩረት አድርገው አለመሠራታቸው ነው፡፡ ለትውልዱ ድክመት የወላጆች እጅ አለበት በማለት ያስረዳሉ፡፡

በዚህ ወቅት ያለምንም ጦርነት ባህላችንና እሴቶቻችን በቴክኖሎጂ ታግዞ እየተወሰደብን ነው የሚሉት ወ/ሮ የሺመቤት፣ ቴክኖሎጂ ጠቃሚ እንደመሆኑ መጠን ጉዳቱም የከፋ እየሆነ ነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡

ክፉና ደጉን ላላዩ ሕፃናት ብዙ ጊዜአቸውን ስልክ ላይ እያዋልናቸው በመሆኑ ትልቅ አደጋ ደግኖብናል ይላሉ፡፡ አገራችን የብዙ ዕውቀትና ጥበብ ባለቤት ናት የሚሉት ወ/ሮ የሺመቤት፣ ካለን ዕውቀትና ታሪክ በመነሳት ታሪክን፣ ወግና ባህልን መሠረት ያደረጉ የተረትና ምሳሌ መጻሕፍት ቢጽፉ መልካም ይመክራሉ፡፡

ወላጆች ልጆችን የጠቀሙ እየመሰላቸው  ረዘም ላለ ጊዜ ስልክ ላይ እንዲጠመዱ በማድረግ ሱሰኛ እንዲሆኑ እያደረጓቸው መሆኑን ተናግረዋል። የወ/ሮ የሺመቤትን ሐሳብ የሚጋራው ገጣሚ ታገል፣ አንባቢ ትውልድ እንዳይፈጠር የጋረደውና ትውልዱ ከባህልና እሴቱ እንዲወጣ የሚያደርገው ገደብ የሌለው የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም እንደሆነ ያስረዳል።

ዘወትር ማኅበራዊ ሚዲያና ቴሌቪዥን ላይ የሚጣዱ ልጆች አስተሳሰባቸው፣ ንግግራቸውና ተግባቦታቸው ላይ ትልቅ ችግር ይፈጥራል የሚለው ገጣሚው፣ አንድ ሕፃን የተረት መጽሐፍ ሲያነብ ተራራውን፣ ገደሉንና በረዶማውን ሥፍራ በምናቡ እየሣለ፣ ገጸ ባህሪው በሚወጣበት እየወጣ በሚወርድበት እየወረደ ስለሚያነብ ምናቡ እያደገ ይመጣል፡፡ በፊልም ወይም በምሥል ሲታይ ግን ምናቡ እዚያው ያልቃል ይላል፡፡

ገጣሚው ማኅበራዊ ሚዲያ በተማሪዎች ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ተዘዋውሮ የገጠመውን ሲናገር ‹‹አንድ የግል ትምህርት ቤት የተማሪዎችን የማንበብ ልምድ ለማየት ሄጄ ነበር፡፡ ተማሪዎቹ የሰባተኛና የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው፡፡ ዳይሬክተሩን ስለተማሪዎች የንባብ ልምዳቸውና ከስልክ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ስጠይቀው በጣም እየተቸገሩ እንደሆነ አስረድቶኛል፡፡ ስልክ እንዳንከለክላቸው በቂ መጽሐፍ ባለመኖሩ  ልጆቹ የሚያጠኑት ስልክ ላይ  ነው፡፡  ምንም ማድረግ አልቻልንም ሲል አስረድቶኛል፤›› የሚለው ገጣሚ ታገል፣ በዚህም  የ7ተኛ እና የ8ተኛ ክፍል ተማሪዎች  የወሲብ ግሩፕ ፈጥረው መያዛቸውን ዳይሬክተሩ እንደነገሯቸው ጠቁሟል፡፡

 ትምህርት ቤቶቹ በራሳቸው ወጭ በሶፍት ኮፒ የተዘጋጀውን ጽሑፍ ፕሪንት በማድረግ ለተማሪዎች ለማቅረብ አስበው  መንግሥት እንደ ከለከላቸው መናገራቸውን ገጣሚ ታገል ያስረዳል፡፡

 ትምህርት ሚኒስቴር ባለሀብቶችን በማሰባሰብና በማስተባበር ለችግሩ መፍትሔ ማበጀትና ለሕፃናት መማሪያ መጻሕፍትን ማሳተም ቢችል፣ ትውልዱን ከጥፋት ማዳን ይቻላል፣ ይህ ካልሆነ ግን  መንግሥት ትምህርት ሚኒስቴርን ሊቆጣጠረው ይገባል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ለልጆቻቸው የማንበብ ልምድን ማስተማርና ወደ እምነት ተቋማት መውሰድ ልጆችን በባህላቸው ኮትኩቶ ማሳደግ ተገቢ ነው የሚሉት ወ/ሮ የሺመቤት፣ ሁሉም ተጋግዘው ካልሠሩ አዋቂና አንባቢ ትውልድን ማግኘት ቅንጦት ሊሆንብን ይችላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ስለልጆች መማሪያ መጻሕፍት አጻጻፍ ወ/ሮ የሺመቤት ሲያስረዱ፣ ልጆች ንፁህ፣ ያልቆሽሸና ያልተበረዘ፣ አዕምሮ ያላቸው በመሆናቸው፣ በእጅጉ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል ብለዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...