Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የመሠረተ ልማት ተደራሽነት የሚፈልገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን የማሳደግ ዓላማ ይዞ የተመሠረተ ነው፡፡ ተቋሙ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥናቶችን ማካሄድ፣ አዳዲስና የተሻሻሉ የግብዓት ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቅ፣ የግብርናውን ክፍለ-ኢኮኖሚ የሚደግፉ ተቋማትን አቅም የመገንባትና አርሶ አደሩን በገበያ የማስተሳሰር ሥራ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ፣ በምግብ ሥርዓቱ ላይ ለውጥ እንዲመጣና እንዲያድግ አርሶ አደሮችን ከማደራጀት እስከ ገበያ ትስስር ድረስ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ ተቋሙ እያከናወናቸው ስላሉት ተግባራት የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም ዳይሬክተር የሆኑትን ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) የማነ ብርሃኑ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋማችሁ እንዲመሠረት ምክንያት የሆነው ምንድን ነው?

ማንደፍሮ (ዶ/ር)፡- ተቋማችን እንደ ስሙ የትራንስፎርሜሽን ተቋም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት አራት የሚተገብራቸው ዓላማዎች ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ የመጀመሪያው የግብርና ዘርፉን ሊያዘምኑ የሚችሉ ጥናቶችን ማካሄድና ምክረ-ሐሳብ ማቅረብ ነው፡፡  በሁለተኛ ደረጃ የተለያዩ ተቋማትን አቅም የመገንባትና የማጠናከር ሥራ ነው፡፡ ሦስተኛው የኢኖቬሽን ሥራዎችን ማከናወን ሲሆን፣ አራተኛው ደግሞ የማስተባበርና የማስተሳሰር ሥራ ነው፡፡ ይህ ማለት ከግብዓት ጀምሮ የአርሶ አደሩን ምርት እስከሚረከቡ ያሉ አካላትን የማገናኘትና በገበያ ሰንሰለት የማስተሳሰር ሒደትን ያጠቃልላል፡፡

ሪፖርተር፡- የማስተባበርና የማስተሳሰር ሥራዎቻችሁን በምን መልኩ ታከናውናላችሁ?

ማንደፍሮ (ዶ/ር)፡- በቅድሚያ አርሶ አደሮች በክላስተር እንዲደራጁ እናደርጋለን፡፡ እነዚህ በክላስተር የተደራጁ አርሶ አደሮች ያመረቱትን ምርት ኩባንያዎች እንዲቀበሏቸው ኔትወርክ እንዘረጋለን፡፡ ለምሳሌ የቢራ ገብስ የሚያመርቱ አርሶ አደሮች፣ በክላስተር ላደራጀናቸውና በፋብሪካ ደረጃ ብቅልን ለሚያበቅሉ ምርታቸውን ያስረክባሉ፡፡ ብቅልን የሚያበቅሉ ደግሞ ለቢራ ፋብሪካዎች ያቀርባሉ፡፡ አቡካዶ በሚመረትባቸው አካባቢዎችም የምናደርገው እንዲሁ ተመሳሳይ ነው፡፡ በክላስተር ተደራጅተው አቡካዶ የሚያመርቱ አርሶ አደሮች፣ ተደራጅተው አቡካዶን ወደ ዘይት ወይም ወደ ቅባትነት ከሚቀይሩ ፋብሪካዎች ጋር እናገናኛቸዋለን፡፡ በክላስተር ተደራጅተው አኩሪ አተርና ሱፍ የሚያመርቱ አርሶ አደሮችም፣ ያመረቱትን ምርት ዘይት ለሚጨምቁ ኩባንያዎች ወይም ፋብሪካዎች እንዲያቀርቡ እናደርጋለን፡፡ በዚህ መልኩ ነው የገበያ ትስስርና ግንኙነት እየፈጠርን ያለነው፡፡

ሪፖርተር፡- አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት እንዲገበያይ በማድረግ በኩል የምትጫወቱት ሚና ምንድን ነው?

ማንደፍሮ (ዶ/ር)፡- አርሶ አደሮች ያመረቱትን ምርት ወደ ውጭ ለሚልኩ ነጋዴዎች እንዲያስረክቡ የማስተባበሩን ሥራ ተቋማችን ይሠራል፡፡ በዚህ የማስተሳሰር ሥራም አርሶ አደሩንና ነጋዴውን በአካል በማገናኘት እንዲወያዩ፣ እንዲነጋገሩና ውል ይዘው እንዲገበያዩ እናደርጋለን፡፡ በዲጂታል አገር አቀፍ ገበያ በኩል የትኛው ምርት፣ የት ቦታ በምን ያህል ዋጋ እንደሚቀርብ መረጃ እያቀረብን እንገኛለን፡፡ የእኛን ማዕከል ደውለው የገበያ መረጃ ለሚጠይቁ ሁሉ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነን፡፡ ይህ ማዕከል አርሶ አደሮች ምክር እንዲያገኙና ችግር ሲገጥማቸውም መፍትሔ በመስጠት በኩል ትልቅ ግልጋሎት እየሰጠም ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- አርሶ አደሮችን በክላስተር ማደራጀቱ ምን ለውጥ አምጥቷል?

ማንደፍሮ (ዶ/ር)፡- ቀደም ሲል አርሶ አደሮች በክላስተር ተደራጅተው አያርሱም ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን 6.5 ሚሊዮን የሚሆኑ አርሶ አደሮች 95,500 በሚሆኑ ክላስተሮች ተደራጅተው ይገኛሉ፡፡ ይህም ፋይዳው እጅግ የጎላ ነው፡፡ የምርምር ውጤቶችን እንዲጠቀሙ፣ ግብዓቶችን በቅድሚያ እንዲያገኙ፣ የገበያ ትስስር እንዲኖራቸው ከማድረግ ባሻገር ምርትና ምርታማነታቸውን በማሳደግ ገቢያቸው እንዲጨምር በሰፊው እያገዘ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋማችሁ በክላስተር የተደራጁ አርሶ አደሮችን አቅም በመገንባት የሚያከናውናቸው ተግባራት ምንድን ናቸው?

ማንደፍሮ (ዶ/ር)፡- በክላስተር የተደራጁ አርሶ አደሮችን በቀጣይ ወደ ኩባንያና ኢንተርፕራይዝ እንዲያድጉ ትኩረት አድርጎ አቅማቸውን የመገንባት ሥራ ይሠራል፡፡ ይህን ስናደርግም ክላስተሮችን እያሰባሰብን ዘር የሚያመርቱበትን፣ የዘር ፕሮሰሲንግ ፕላንት፣ ማበጠሪያ፣ ማሸጊያና የመሳሰሉ ማሽኖችን እንዲገዙ በማገዝና ያመረቱት ምርት ዕውቅና እንዲኖረው ድጋፍ በማድረግ ነው፡፡ ሌላው በክላስተር የተደራጁ አርሶ አደሮች በየወረዳቸው የዘርና የግብዓት አቅርቦት እንዲያገኙ በየወረዳው 300 የሚጠጉ የአንድ መስኮት አገልግሎት ማዕከል አቋቁሟል፡፡ የሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከልም እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ይህ ቀደም ሲል ትራክተር ተከራይተው ለሚያርሱ አርሶ አደሮች ትራክተሮችን፣ መለዋወጫ ዕቃዎችንና የእርሻ መገልገያ ማሽነሪዎችን እንዲያመርቱና እንዲያቀርቡ የሚያስችላቸውን ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የግብርና ዘርፍን ከማዘመንና ዲጂታል ከማድረግ አንፃር ተቋማችሁ ምን እየሠራ ነው?

ማንደፍሮ (ዶ/ር)፡- የኢትዮጵያ ግብርና ኢንስቲትዩት የአገራችንን ግብርና ከማዘመንና ከማሳደግ አኳያ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህ ዙሪያ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት፣ የዲጂታል አጠቃቀም፣ የምክር አገልግሎት፣ እንዲኖር በማድረግ ለአርሶ አደሩ የሚጠቅሙና በግብርናው ዘርፍ ለውጥ የሚያመጡ መተግበሪያዎችን (አፕልኬሽን) በማበልፀግ ላይ እንገኛለን፡፡ በተለይ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (IT) የተመረቁ ወጣቶችን በማደራጀት ግብርናችንን ዲጂታል ለማድረግና ለማዘመን ከፍ ያለ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን በምታደርጉት እንቅስቃሴ የገጠማችሁ ተግዳሮት ይኖር ይሆን?

ማንደፍሮ (ዶ/ር)፡- አርሶ አደሩን ከመደገፍና የኢትዮጵያን ግብርና ከማሳደግ አኳያ እንደተቋም አጋጥሞናል የምንለው ችግር የመሠረተ ልማት ተደራሽነት ነው፡፡ አርሶ አደሮች ተደራጅተው እንዲያመርቱ እናደርጋለን፣ በእነርሱ የተመረተውን ምርት ወደ ገበያ ለማውጣት መንገድ ችግር ሆኖ እየፈተነን ይገኛል፡፡ ምርቱ እንደምንም ተጓጉዞ ቢወጣ እንኳን የማከማቻና የመጋዘን እጥረት ሌላው የሚያጋጥመን ተግዳሮት ነው፡፡ እነዚህ ችግሮች ባሰብነውና በምንፈልገው ፍጥነት እንዳንሄድ እያገዱን ይገኛሉ፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍና ለማስተካከል የግል ባለሀብቶች መጋዘንና ሌሎች መሰል ለአርሶ አደሩ አገልግሎት የሚሰጡ ግንባታዎችን እንዲያካሂዱ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹በአሁኑ ወቅት ከ21 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ሰብዓዊ ዕርዳታ ይፈልጋል›› አቶ አበራ ሉሌሳ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ምክትል ጸሐፊ

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ላለፉት 89 ዓመታት በመላ አገሪቱ የሰብዓዊነት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በድርቅ፣ በበሽታና በግጭት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የምግብ፣ የመጠለያ፣ የመድኃኒትና የ24 ሰዓት...

ከቢሻን ጋሪ እስከ ዶባ ቢሻን እንክብል

ዶባ ኢንዱስትሪያል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሦስት ዓመታት በላይ ጥናትና ምርምር ያደረገበትንና ለገበያ ያበቃውን ዶባ-ቢሻን እንክብል የውኃ ማከሚያ...

ለሴቶች ድምፅ ለመሆን የተዘጋጀው ንቅናቄ

ፓሽኔት ፎር ኤቨር ኢትዮጵያ ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በፆታ እኩልነት፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤና እንዲሁም የሴቶችን ማኅበራዊ ችግር በማቃለል ዙሪያ በተለያዩ ክልሎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ...