Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሚጥል ሕመም ላይ ያለው መገለል እስከ መቼ?

የሚጥል ሕመም ላይ ያለው መገለል እስከ መቼ?

ቀን:

የሚጥል ሕመምን (ኤፒሊፕሲ) አስመልክቶ በማኅበረሰቡ ዘንድ የተሳሳተ አመለካከትና የግንዛቤ ክፍተት እንዳለ ይስተዋላል፡፡ የሕመሙ ባህሪ ከመንፈሳዊ ሕይወት ጋር በማቆራኘትና እንደ እርግማን በመቁጠር በርካቶች የጉዳቱ ሰለባ ሆነዋል፡፡ በሕመሙ ዙሪያ ያሉ ጎጂ ልማዳዊ አመለካከቶችና ድርጊቶችም ሕመሙ ያለባቸው ሰዎች ወደ ሕክምና እንዳይሄዱ አድርጓቸዋል፡፡ መገለልና አድልዎ እንዲደርሰባቸውና ላልተገባ ሥነ ልቦና ጫና እንዲጋለጡ እያደረገ ይገኛል፡፡

ሕመሙ በተሳሳተ መልኩ እንደሚነገረው የፈጣሪ ቁጣ ወይም በእርግማን ምክንያት የሚከሰት ሳይሆን፣ በድንገተኛና ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የአዕምሮ ተግባርን የሚያውክ ክስተት ተከስቶ በአንጎል ነርቭ ውስጥ የኤሌክትሪካዊ ንዝረት ጊዜያዊ መረበሽ ምክንያት የሚከሰት መሆኑን ሐኪሞች ይናገራሉ፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው፣ በዓለም 50 ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ ከሚጥል ሕመም ጋር እንደሚኖር የሚገመት ሲሆን፣ አምስት ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ በየዓመቱ በዚህ በሽታ ይያዛሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከነዚህም ውስጥ ሁለት ሦስተኛው ያህሉ የሚገኙት ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ውስጥ እንደሚገኙ፣ ከነሱም 70 በመቶ የሚሆኑት የሚጥል ሕመም ያለባቸው ሕክምናቸውን በአግባቡ ከተከታተሉ ከሚጥል ሕመም ነፃ ሆነው ሊኖሩ ይችላሉ ተብሎ ይገመታል፡፡

የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በቅርቡ ባካሄደው ጥናት መሠረት በአገሪቱ የሚጥል ሕመም ካለባቸው መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት በአዲስ አበባ፣ በአማራና በቀድሞ የደቡብ ክልሎች የሚገኙት ናቸው፡፡

በየማኅበረሰቡ ያለውን የተዛባና የተሳሳተ አመለካከት ለማረቅ፣ የሚጥል ሕመም የፈጣሪ ቁጣ ወይም መርገምት አለመሆኑንን፣ ይልቁንም በድንገተኛና ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የአዕምሮ ተግባርን የሚያውክ ክስተት የሚታይ መሆኑን ለማስገንዘብ፣ ብሎም መገለልና አድልዎ መቆም እንዳለበት ለማስመር፣ የዓለም የሚጥል ሕመም ሳምንትን ከየካቲት 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ሳምንታት እየተከበረ ይገኛል፡፡

‹‹በሚጥል ሕመም ላይ ያለውን መገለል እንዲቆም ድምፅ እንሁን›› በሚል መሪ ቃል ዘጠነኛው ብሔራዊ የሚጥል ሕመም ሳምንት፣ በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሲከፈት የተገኙት የኢትዮጵያ ነርቭ ሐኪሞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ህሊና ዳኛቸው (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ የሚጥል ሕመም ሕክምና የታማሚዎችን ቤተሰብና የማኅበረሰብን ድጋፍ ይጠይቃል፡፡ ይህ ድጋፍ በተገቢው ሁኔታ ሊተገበር የሚችለው የሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች ለሕመሙ ያላቸውን የተሳሳተ አመለካከትና ግንዛቤ በአዎንታዊ መልኩ ሲለወጥ ነው፡፡

መውደቅ ወይም መንቀጥቀጥ የሚመጣው በአዕምሮ ላይ በሚፈጠር የኤሌክትሪክ ፍሰት መዛባት ሲሆን፣ ይህ በተደጋጋሚ ሲከሰት ነው የሚጥል ሕመም የሚባለው፡፡ ታማሚዎች በወቅቱ ወደ ጤና ተቋም ሄደው ምርመራና ሕክምና ሲያገኙ የሚከሰተውን የአካል ጉዳትና ሕመም መቀነስ ይቻላል፡፡

እንደ ፕሬዚዳንቷ አባባል፣ በዓለም ውስጥ የትም ቦታ ቢኬድ አንድ ሰው የሚጥል ሕመም አለበት የሚባለው ሁለት የተለያዩ መንቀጥቀጦች በ24 ሰዓት ልዩነት ውስጥ ከተፈጠሩ ነው፡፡ ወይም አንድ ሰው አንድ ጊዜ ከወደቀ በኋላ በድጋሚ የመውደቅ ዕድሉ ከ60 በመቶ በላይ ነው ከተባለ የሚጥል በሽታ አለበት ለማለት ይቻላል፡፡

በዓለም ውስጥ የሚጥል ሕመም ያለባቸው ሰዎች በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ነገር ግን ሁሉም የሚጥል ሕመም ያለበት ሰው ተመሳሳይ የሆነ መገለጫ ወይም ባህሪ የለውም፡፡ አንድ ሰው ሙሉ ሰውነቱ ወድቆ ሊያንቀጠቅጠው ይችላል፡፡ ሌላው ደግሞ የተወሰነ የሰውነት ክፍሉን ብቻ ለይቶ የሚያጠቃ ሕመም ሊኖር እንደሚችል ነው የተናገሩት፡፡

ከዚህም ሌላ መንገድ ላይ ወድቆ፣ ሰውነቱ ተግተርትሮና ተንቀጥቅጦ የሚታይ የሚጥል ሕመም እንዳለ ሁሉ፣ ለተወሰኑ ሰከንዶች/ደቂቃዎች ያለበትን ቦታ ባለማስታወስ ዝም ብሎ ቆይቶ ከዚያ ወደ ነበረበት የሚመለስ፣ በአንዳንድ ሰዎች ላይ ደግሞ እግራቸውን ወይም እጃቸውን ብቻ ማንቀጥቀጥ የሚጥል ሕመም መኖሩን የሚሳይ ነው፡፡

የሚጥል ሕመም ከሚታወቅበት ውስጥ የአንጎል የአፈጣጠርና የዘረመል ችግሮች፣ የአንጎል ኢንፌክሽኖች፣ የሆርሞኖች መዛባት፣ የነርቭ ሕዋሳትን የሚገድሉ በሽታዎች እንደ ኦቲዝምና አልዛይመር፣ በወሊድ ጊዜ ሕፃኑ በቂ አየር (ኦክስጅን) አለማግኘት (መታፈን) የመሳሰሉ ተጠቃሾች መሆናቸውን ከህሊና (ዶ/ር) ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

‹‹የሚጥል ሕመም ከሥራ፣ ከመኖር፣ ከመማር፣ ቤተሰብ ከመመሥረት፣ በሕይወት ከምንመኘው ነገር ሁሉ አያግደንም/አይከለክለንም፤›› ያሉት የኬር ኤፕሊፕሲ ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ የእናት የውነቱ ናቸው፡፡

የሚጥል ሕመም የተለያዩ ተፅዕኖዎች እንዳሉት፣ ከእነዚህም መካከል ሕመሙ ባለባቸው ልጆች ባህሪ፣ በትምህርት አቀባበላቸውና የማስተዋል ችሎታቸውን ቀነስ በማድረግ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

የሚጥል ሕመም ያለባቸው ልጆች የሚወስዷቸው መድኃኒቶች ሰውነታቸውን ትንሽ እንደሚያስወፍር፣ በዚህም የተነሳ የቀሩት ልጆች እንደሚቀልዱባቸውና እንደሚያፌዙባቸው፣ ይህ ዓይነቱም ሁኔታ የመገለል ባህሪ እንደሚያሳድርባቸው ወ/ሮ የእናት ገልጸው፣ ወላጆችም ልጄ ትምህርት ቤት ሄዶ ከሚሳቅበት ቤት አርፎ ቢቀመጥ የተሻለ ነው በሚል እምነት ትምህርቱን አቋርጦ ቤት እንዲውል እንደሚያደርጉና በዚህም የተነሳ ለራሱ ያለው ግምት ዝቅ ያለ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

ከፍ ብሎ የተዘረዘሩትን ተፅዕኖዎች ለመከላከል የሚችሉ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የሚረዳ ዕቅድ ድርጅቱ ከኢትዮጵያ የነርቭ ሐኪሞች ማኅበር ጋር በመተባበር ማዘጋጀቱንና  በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚሆንም አስታውቀዋል፡፡

ክብረ ቀኑን አስመልክቶ በዋዜማው በተሰጠው መግለጫ ላይ ወ/ሮ የእናት የውነቱ ሕመሙን ለመከላከል መደረግ ስላለበት የመጀመሪያ ዕርዳታ ማስገንዘቢያም ሰጥተዋል፡፡

ታማሚ በወደቀ ጊዜ ከጭንቅላት ሥር ለስላሳ ትራስ ነገር ማድረግ፣ ሲንፈራገጥ ራሱን እንዳይጎዳ ከእሳት፣ ከኤሌክትሪክና ከስለታማ ነገሮች ማራቅ፣ አንገት አካባቢ ያሉ የልብስ ቁልፎችን ማላላት፣ መንቀጥቀጡ ከቆመ በኋላ እስኪነቃ ድረስ በጎኑ ማስተኛት፣ ክብሪት አለማሽተት፣ ሕመምተኛው እስኪነቃ ድረስ አብሮ መቆየት፣ ከነቃ በኋላ ማረጋጋት ይገባል፡፡

ይሁን እንጂ መንቀጥቀጡ ከ5 ደቂቃ በላይ የሚረዝም ከሆነ ወይንም የታማሚው የቆዳ ቀለም ወደ ሰማያዊነት ከተለወጠ በአስቸኳይ ወደ ጤና ተቋም መውሰድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በዘጠነኛው ብሔራዊ የሚጥል ሕመም ሳምንት ውስጥ ከክልልና ከከተማ አስተዳደር ለተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች በአዳማ ከተማ ሥልጠና መስጠት፣ በተመረጡ የጤና ጣቢያዎች፣ እንዲሁም የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚጥል ሕመም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ይከናወናል፡፡ 

ከአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ለተወጣጡ መምህራን ሥልጠና እንደሚሰጥ፣ በመዝጊያው ዕለት የካቲት 17 ቀን  ከቴዎድሮስ አደባባይ እስከ ኢትዮ ኩባ ወዳድነት ፓርክ ድረስ የሚዘልቅ የእግር ጉዞ እንደሚካሄድ የወጣው መርሐ ግብር ያመለክታል፡፡

ብሔራዊ የሚጥል ሕመም ሳምንትን በጋራ ያዘጋጁት የጤና ሚኒስቴር፣ ኬር ኤፕሊፕሲ ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ የነርቭ ሐኪሞች ማኅበር ናቸው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...