Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለረመዳን የታሰበው ባዛር

ለረመዳን የታሰበው ባዛር

ቀን:

በየማነ ብርሃኑ

ቢላሉል ሐበሺ የልማትና መረዳጃ ዕድር ከሃይ ፕሮፋይል ጋር በመተባበር ከየካቲት 22 እስከ መጋቢት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. የሚቆይ የረመዳን ወር ባዛር በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ድርጅቱ የረመዳን ወርን ተከትሎ የሚያዘጋጀውን ባዛር በተመለከተ  የካቲት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጀማል መሐመድ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፣ ባዛሩ በዋናነት የተዘጋጀው ድርጅቱ እያከናወናቸው ላሉ ዘርፈ ብዙ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ገቢ ለማሰባሰብ ታቅዶ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ቢላሉል ሐበሺ ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ ከተቋቋመበት ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ ወላጆቻቸውን ላጡ፣ ለአረጋውያን፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለሴቶች፣ ለወጣቶችና ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች በርካታ የበጎ አድራጎት አገልግሎቶችን ሲሰጥ መቆየቱን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፣ ከ11,000 በላይ ለሚሆኑ ወላጅ አልባና ተንከባካቢ ለሌላቸው ሕፃናት የትምህርት ወጪዎችን በመሸፈን ትምህርታቸውን እንዲማሩ አድርጓል፡፡

በዓመት ከ350 በላይ ለሚሆኑ አረጋውያን በየወሩ በቋሚነት የገንዘብ ድጋፍ፣ ከ20,000 በላይ ለሚሆኑ አቅመ ደካሞች ወርኃዊ የአስቤዛ ድጋፍ፣ ከ3,500 በላይ ለሚሆኑ አቅም ለሌላቸው ወገኖች ነፃ የቀብር አገልግሎት መስጠቱን ገልጿል፡፡ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በአማራ፣ በአዲስ አበባና በሌሎች አካባቢዎች በሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖችም የአልባሳትና የአስቤዛ ድጋፍ ድርጅቱ ካከናወናቸው የበጎ አድራጎት ሥራዎች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

እንደ አቶ ጀማል ገለጻ፣ ትምህርታቸውን ጨርሰው ዩኒቨርሲቲ የመግባት ዕድል ላልገጠማቸው ወገኖች የሥልጠና ማዕከል በማቋቋም ከቴክኒክና ሙያ ዕውቅና ባገኘባቸው በቪዲዮ ግራፊክስ፣ ፎቶግራፍ፣ ጋርመንት፣ በቆዳና የቆዳ ውጤቶች ሥልጠና ከመስጠት ባሻገር፣ ሥልጠናዎችን አጠናቀው ለጨረሱ ሠልጣኞች የድጋፍ ፕሮጀክት በመቅረፅና ድጋፍ በማሰባሰብ በተለይም ሴቶችን ተጠቃሚ የማድረግና የማቋቋም ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡

የጤና ድጋፍ ለሚሹ ከ1,600 በላይ ለሚሆኑ ፅኑ ሕሙማን የጤና ድጋፍ ማድረግ፣ ከአለርት ሆስፒታል ጋር በመተባበር የሥነ አዕምሮ ጤናና ማገገሚያ ማዕከል በመክፈት አገልግሎት መስጠት፣ በሲልጤ ዞን፣ ሲልጤ ወረዳ ኩኖ ከተማ 2,500 ለሚሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የጉድጓድ ውኃ ቁፋሮ በማከናወን የንፁህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል፣ በኦሮሚያ ክልል ዳለቲ ከተማ ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ ስምንተኛ ክፍል ከ1,100 ለሚሆኑ ተማሪዎች ትምህርት በነፃና በአነስተኛ ክፍያ እንዲያገኙ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡  

ሥራ አስኪያጁ እንደሚገልጹት፣ እነዚህ ማኅበረሰብ አቀፍ የበጎ አድራጎት ሥራዎች የሚሠሩት 6,000 ከሚሆኑ ቋሚ የሰደቃ አባላት በወር ከ10 ብር ጀምሮ እንደ የአቅማቸው በሚሰበሰብ፣ ከዘካና ከአጭር የጽሑፍ መልዕክት 6833 ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ የተረጂ ወገኖች ቁጥር በመጨመሩ በሚፈለገው መጠንና ልክ ዕርዳታ ማድረስ ስላልተቻለ፣ በድርጅቱ የአምስት ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ መሠረት ሌሎች የገቢ ምንጮችን ለማሰባሰብ ታስቦ ኤግዚቢሽንና ባዛር ለማዘጋጀት ታቅዷል፡፡

ባዛሩ የሚካሄድበት ወቅት ረመዳን ከመድረሱ ቀደም ብለው ባሉት አሥር ቀናት ውስጥ በመሆኑ፣ ወሩ ወደ አላህ መቃረቢያችንና ያለንን ተካፍለን የምናሳልፍበት ትልቅ የራህማ ወር እንደመሆኑ፣ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በአንድ ቦታ እንዲሸምትና ነጋዴውና ሸማቹ በቀጥታ እንዲገናኝ የሚያደርግ እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡

ባዛሩ ለንግዱ ማኅበረሰብና ለሸማቾች ከሚያበረክተው ጉልህ አስተዋጽኦ ጎን ለጎን የእስላማዊ ባህሉን አጉልቶ በማሳየት በአገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሏል፡፡

ከየካቲት 22 ቀን ጀምሮ ለአሥር ቀናት በሚካሄደው ባዛር ላይ ከ300 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ አስመጪና ላኪዎች፣ አከፋፋዮች፣ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች፣ ባንኮችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በባዛሩ ለሕፃናትና ለአዋቂዎች የሚሆኑ መርሐ ግብሮች የተዘጋጁ ሲሆን፣ የሕፃናት መጫወቻዎች፣ የንባብ ቦታዎች፣ የመስገጃ ቦታዎችና ሌሎች የተለያዩ አዝናኝ ሁነቶችና ሽልማቶች መዘጋጀታቸውም ተገልጿል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...