Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበአጭር የተቀጨው የማራቶን ተስፈኛ

በአጭር የተቀጨው የማራቶን ተስፈኛ

ቀን:

‹‹የሆነ ሰው መጥቶ ቤት ለምንሠራው ቤት ይረዳናል፡፡ አሁን ጥሩ ብቃት ላይ ስለምገኝ ከወራት በኋላ በማደርገው ውድድር 1፡59፡00 ለመግባት እየተዘጋጀሁ ነው በማለት የዓለም የማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤቱ ኬልቪን ኪፕተም ከአባቱ ጋር ያደረገው የመጨረሻ የስልክ ንግግር ነበር፡፡

ሰኞ የካቲት 4 ቀን 2016 ዓ.ም. በርካታ የአትሌቲክስ ወዳጆችን ያስደነገጠ የዓለም ሚዲያ የተቀባበለው አስደንጋጭ መርዶ ተሰማ፡፡ ይህ በአብዛኛው አትሌቲክስ ወዳጆች ዘንድ ሊታመን ያልቻለው ዜና የዓለም የማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤት በመኪና አደጋ ሕይወቱ ማጣቱን ተከትሎ ነበር፡፡

ኪልቪን ኪፕተም እ.ኤ.አ. በ1999 በኬንያ ፔፕሳም መንደር ተወለደ፡፡ ሥፍራው በኬንያ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ በኤልጊዮ ማራኪት ካውንቲ የሚገኘው ከፍተኛ ሥፍራ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በኬንያ የአትሌቶች መፍለቂያ በሆነችው ከኤልዩሬት ከተማ በስተምሥራቅ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት በደቡብ ምሥራቅ ካፕታጋታ ደን ድንበር አቅራቢያ በመሆኑ ለኬልቪን የአትሌቲክስ ሕይወት ጉዞ ምቹ ሁኔታን ፈጠረ፡፡

ሥፍራው በርካታ አትሌቶች የፈለቁበት በመሆኑ በባዶ እግራቸው በጫካ ውስጥና በጎዳና የሚሮጡ አትሌቶቸ ነበሩ፡፡ በአካባቢው ገና በልጅነቱ የቤተሰቡን ከብቶች የሚጠብቀው ኬልቪን አትሌቶቹን ለመከተል ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ ኬልቨን እ.ኤ.አ. በ2013 የ13 ዓመት ልጅ እያለ ወደ አትሌቲክስ ገባ፡፡

ኬልቨን በ13 ዓመት ዕድሜው በኤሌዶሬት ከተማ በተከናወነው በግማሽ ማራቶን 10ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቀቀ፡፡ በቀጣይ ዓመት በተደረገው የግማሽ ማራቶን ውድድርም ወጥቷል፡፡

በሁለቱ ውድድሮች በመጣው ውጤት ተስፋ ያልቆረጠው ኬልቨን፣ ለሦስተኛ ጊዜ በተሳተፈበት ግማሽ ማራቶን 62፡01 በመግባት ማሸነፍ ቻለ፡፡

በ2018 በተከናወነው የኤልዶሬት ግማሽ ማራቶን ሲያሸንፍ አሠልጣኝ አልነበረውም፡፡ እ.ኤ.አ. በ2019 በፖርቱጋል ሊዝበን ከተማ በተከናወነው ግማሽ ማራቶን የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ተሳትፎውን በማድረግ አምስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ የቻለ ሲሆን፣ 59፡54 በመግባት የግሉን ምርጥ ሰዓት ማስመዝገብ ቻለ፡፡

ኬልቨን በዚያው ዓመት በሰሜንና በምዕራብ አውሮፓ ከተሞች በመዘዋወር በስድስት ውድድሮች ላይ መካፈል ችሏል፡፡ የአውሮፓ ጉዞውን ካጠናቀቀ በኋላም በኬንያ በሚሰናዳው ፈታኙ ዓመታዊ ካስ ግማሽ ማራቶን ማሸነፍ ችሎ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ. በ2020 ሩዋንዳዊውን የ3000 ሜትር መሰናክል ክብረ ወሰን ባለቤት ጌርቫይስ ሃኪዚማናን ዋና አሠልጣኝ አድርጎ መቅጠሩ ተነገረ፡፡

በዚህም መሠረት አትሌቱ ከ2020 ጀምሮ የማራቶን ዝግጅቱን አጠንክሮ መቀጠሉ ተነግሯል፡፡ በዚያው ዓመት በታኅሣሥ ወር በስፔን ቫሌንሺያ በተከናወነ ግማሽ ማራቶን 58፡42 በመግባት ስድስተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ ዕድሜው 21 ዓመት ሲሆን፣ የግል ምርጥ ሰዓቱንም ማስመዝገብ ችሎ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ. 2021 በፈረንሣይ ሌንስ በተከናወነ ግማሽ ማራቶን 59፡35 አንደኛ፣ እንዲሁም በዚሁ በተከናወነ ሌላ ግማሽ ማራቶን 59፡02 በሆነ ሰዓት ስምንተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡

በግማሽ ማራቶን ውድድሮች ራሱን እያዳበረ የመጣው ኬልቨን፣ በ2022 የቫሌንሺያ ማራቶን በመካፈል አስደናቂ ውጤት ማሳካት ቻለ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈበት በዚሁ ማራቶን 2፡01፡53 በመግባት አራተኛውን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ በታሪክ ሦስተኛው የማራቶን ፈጣን ሰዓት ባለቤት መሆን ችሏል፡፡

አትሌቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ በረዥም ርቀት የራሳቸውን አሻራ ማኖር ከቻሉትና በማራቶን ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ ከቻሉት ኢትዮጵያዊው ቀነኒሳ በቀለና ኬንያዊው ኢሎድ ኪፕቾጌ ጋር ተርታ መሠለፍ ቻለ፡፡

በ2023 በታላቅ (ሜጀር) የዓለም ማራቶን ተሳትፎ ያደረገው ኬልቨን በለንደን ማራቶን በመካፈል 2፡01፡25 በማጠናቀቅ ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ ቻለ፡፡ በዝናብ በታጀበው ውድድር የቦታውን ክብረ ወሰን ለመስበር 16 ሴኮንዶች ብቻ ነበር የቀሩት፡፡

ኬልቨን በ23 ዓመቱ ሁለተኛውን ታላቅ የማራቶን ውድድር ባለፈው መስከረም በቺካጎ በማከናወን ዓለምን ጉድ ያሰኘውን በድንቅ ብቃት በ2፡00፡35 በማጠናቀቅ የዓለምን ሚዲያ ተቆጣጠረ፡፡ በአገሩ ልጅ ኢሎድ ኪፕቾጌ በ2022 በርሊን ማራቶን ተይዞ የነበረውን 2፡01፡09 በ34 ሴኮንዶች በማሻሻል ክብረ ወሰኑን በእጁ ማስገባት ቻለ፡፡

ውጤቱን ተከትሎ በርካታ መላምቶች ሲሰጡ ቢከርሙም፣ የዓለም አትሌቲክስ አስፈላጊውን ጊዜ ወስዶ ውድድሩን ከገመገመ በኋላ፣ ማክሰኞ ጥር 28 ቀን 2016 ዓ.ም.  የአትሌቱን ክብረ ወሰን ማፅደቅ ቻለ፡፡

የዓለም አትሌቲክስ የኬልቨን ክብረ ወሰንን ባፀደቀ በሳምንት ውስጥ አትሌቱ ከአሠልጣኙ ጋር ሆነው ባጋጠማቸው የመኪና አደጋ ሕይወቱ ተቀጥፏል፡፡ አትሌቱ የሚያሽከረክረውን መኪና መቆጣጠር ተስኖት ከመንገድ 60 ሜትሮች ርቆ ከዛፍ ጋር መጋጨቱ ተነግሯል፡፡

ኪልቨን ወዲያው ሕይወቱ ያለፈ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፣ አሠልጣኙ ለተወሰኑ ሰዓታት ቢቆይም ሕክምና ቦታ ሳይደርስ ሕይወቱ አልፏል፡፡

ኬልቨን በሚያዝያ ወር በሚደረገው የሮተርዳም ማራቶን ለመሳተፍ ዝግጅት ሲያደርግ ነበር፡፡ በዚህም ውድድር ከሁለት ሰዓት በታች ለመግባት መዘጋጀቱን ሲነገር ቆይቷል፡፡ ከዚህም በላይ በፓሪስ ኦሊምፒክ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ ዝግጅት ላይ ነበር፡፡

ከመኪና አደጋው ጋር በተያያዘ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ሲሆን፣ የኬንያ ፖሊስ እያጣራ መሆኑን ገልጿል፡፡ ሆኖም ተሽከርካሪው የቴክኒክ ችግር ሳያጋጥመው እንዳልቀረ ፍንጭ ሰጥቷል፡፡

አትሌቱ ከጥር 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከቻይናው የስፖርት ሰዓት አምራች አማዝፊት ጋር ስምምነት ፈጽሞ ነበር፡፡ በዚህም አትሌቱ ዘመናዊውን የእጅ ሰዓት ሃማዝፊት አጥልቆ በሮተርዳም ማራቶን ለመካፈል ዝግጅት ላይ ነበር፡፡

የሁለት ልጆች አባት የነበረው ኬልቨን ኪፕተም ብልጭ ብላ ወዲያው እንደጠፋች ፀሐይ በ24 ዓመቱ እስከመጨረሻው አሸልቧል፡፡

በዓለም ላይ ያሉ ዕውቅ አትሌቶች በአትሌቱ ሕይወት መጥፋት የተሰማቸውን ሐዘን አሰምተዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...