Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹የፕሪቶሪያው ስምምነት ሳይፈጸም ሠራዊታችን ትጥቅ ፈትቶ እንደማይበተን ለመንግሥት አሳውቀናል›› አቶ ጌታቸው ረዳ፣...

‹‹የፕሪቶሪያው ስምምነት ሳይፈጸም ሠራዊታችን ትጥቅ ፈትቶ እንደማይበተን ለመንግሥት አሳውቀናል›› አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት

ቀን:

የፕሪቶሪያው ስምምነት ተሟልቶ ሳይፈጸም ‹‹የትግራይ ሠራዊት›› ትጥቅ ፈትቶ እንደማይበተን ለፌዴራል መንግሥት ማሳወቃቸውን፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ። 

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የፌዴራል መንግሥትና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸምን በአዲስ አበባ ተገናኝተው የገመገሙ ሲሆን፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ሰኞ የካቲት 4 ቀን 2016 ዓ.ም. በመቀሌ ከተማ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በግምገማው ወቅት ከሁለቱም አካላት የተነሱ ጉዳዮችን አብራርተዋል።

በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት የፌዴራሉ መንግሥት ሊፈጽማቸው ይገቡ የነበሩ በርካታ ጉዳዮችን አለመተግበሩን፣ ይህንንም በውይይቱ ወቅቱ ማስረዳታቸውን አቶ ጌታቸው በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹የፕሪቶሪያው ስምምነት አልተፈጸመም፣ ሕወሓት ሕጋዊ ሰውነቱን መልሶ አላገኘም፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው አልተመለሱም፣ የአማራና የኤርትራይ ኃይሎች ከትግራይ ክልል ለቀው እንዲወጡ አልተደረገም፤›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ይህንንም ለፌዴራል መንግሥት በዝርዝር ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

የፌዴራል መንግሥት በበኩሉ በሕወሓትና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ላይ ካነሳቸው ቅሬታዎች መካከል፣ ‹የፕሪቶሪያውን ስምምነት ለጊዜ መግዣ እየተጠቀማችሁበት ነው፣ ትጥቃችሁን ለመፍታት ፍላጎት የላችሁም፣ ሠራዊታችሁን ማጠናከር ነው የምትፈልጉት፣ ከኤርትራና ከሌሎች የውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበር መንግሥትን ለመጣል እየሠራችሁ ነው› የሚሉት እንደሚገኙበት፣ አቶ ጌታቸው በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

ሕወሓትም ሆነ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የትግራይ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት ፍላጎት የላቸውም ተብሎ የቀረበባቸውን ክስ በተመለከተ ምላሽ መሰጠቱን የተናገሩት አቶ ጌታቸው፣ የትግራይ ተዋጊዎችን ትጥቅ በማስፈታትና መልሶ በማቋቋም ረገድ ትልቁ ኃላፊነት የፌዴራል መንግሥት ቢሆንም፣ ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ሊፈጸም እንዳልቻለ ገልጸዋል፡፡

‹‹የፕሪቶሪያው ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሳይሆን ይህንን ሠራዊት ተበተን የምንልበት ምክንያት የለም። ይህ ሠራዊት መስዋዕትነት የከፈለ፣ ለትግራይ ህልውና የቆመ ሠራዊት ነው፤›› ብለዋል።

አክለውም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ብዙ ችግሮች ያሉበት ቢሆንም፣ ለክልሉ የመንግሥት ሠራተኞች ሊከፈል የሚገባውን ደመወዝ በመቀነስ ለሠራዊቱ ወጪ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። ‹‹ይህንንም መተሳሰብ አለብን፤›› ሲሉም ተደምጠዋል።

የትግራይ ክልል ከ270 ሺሕ በላይ ሠራዊት እንዳለው የጠቀሱት አቶ ጌታቸው፣ ይህ ሠራዊት ወደ ቤቱ የሚመለስ ከሆነ ለዚህ የሚመጥን በጀት ሊመደብ እንደሚገባ፣ ለዚህም የፌዴራል መንግሥት ከውጭ አጋሮቹ ጭምር ገንዘብ ሰብስቦ በማምጣት ሠራዊቱ መልሶ የሚቋቋምበትን ሁኔታ ማቻቸት እንዳለበት ተናግረዋል።

ይህንን ማድረግ ረዥም ጊዜ የሚወስድ እንደመሆኑ መጠን፣ የፌዴራል መንግሥት በካምፕ ውስጥ ለሚገኘው የትግራይ ሠራዊት ስንቅ የማቅረብ ኃላፊነት እንደነበረበት፣ ነገር ግን ይህንን ኃላፊነት እንዳልተወጣ ገልጸዋል።

‹ከኤርትራና ከሌሎች ኃይሎች ጋር በመተባበር መንግሥትን ለመጣል እየሠራችሁ ነው› ተብሎ በፌዴራል መንግሥት የቀረበባቸው ወቀሳን በተመለከተ አቶ ጌታቸው በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹እኛ ፍላጎታችን ሰላም ብቻ ነው ብለን አብራርተን ምላሽ ሰጥተናል፣ እናም የተግባባን ይመስለኛል፤›› ብለዋል።

የትግራይ ሕዝብን በሰላም የመኖር ፍላጎት ከማረጋገጥ ባለፈ አገር የመበጥበጥም ሆነ አካባቢውን የማመስ፣ እንዲሁም የማዕከላዊ መንግሥትን ሥልጣን የመያዝ ፍላጎት በትግራይ በኩል እንደሌለ ማስረዳታቸውን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነበራቸው ቆይታ የአማራና የትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ አንስተው የሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች ጉዳይ በሕዝበ ውሳኔ እንዲፈታ የመፍትሔ ሐሳብ እንዳቀረቡ መናገራቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት ወቅትም አጀንዳ ነበር። 

አቶ ጌታቸው በዚህ ጉዳይ ላይ የተደረገውን ውይይት አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕዝበ ውሳኔ ቢደረግ ይሻላል ያሉት በሐሳብ ደረጃ እንደሆነ፣ ነገር ግን የግድ ሕዝበ ውሳኔ መደረግ አለበት የሚል አቋም እንደሌላቸው ገልጸውልናል፤›› ብለዋል።

በሕወሓትና በፌዴራል መንግሥት መካከል አሁንም መተማመን እንደሌለ የተናገሩት አቶ ጌታቸው፣ የሕወሓት ሕጋዊ ሰውነትን እንዲመለስ ማድረግን በተመለከተ ግን መግባባታቸውን ተናግረዋል። በዚህም መሠረት የሕወሓት ሕጋዊ ሰውነት እንዳይመለስ እንቅፋት የሆኑ የሕግ ጉዳዮችን በፍጥነት በመቅረፍ፣ ሕወሓት በምርጫ ቦርድ እንዲመዘገብና ዕውቅና እንዲያገኝ መስማማታቸውን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ ውይይቱ አለመተማመን የጎላበት እንደነበረ የገለጹት አቶ ጌታቸው በቅርቡ የአሜሪካ መንግሥት፣ የአፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካዮች የሚሳተፉበት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አተገባበር ግምገማ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...