Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለአፍሪካ መሪዎች ‹‹ትምህርትን እንታደግ›› የሚል ጥሪ ቀረበ

ለአፍሪካ መሪዎች ‹‹ትምህርትን እንታደግ›› የሚል ጥሪ ቀረበ

ቀን:

ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገሮች የትምህርት ጥራት ላይ የሚሠራው ‹‹ሂዩማን ካፒታል አፍሪካ›› የተሰኘው የአገሮች ጥምረት፣ አደጋ ውስጥ ነው ያለውን አኅጉራዊ የትምህርት ጥራት ‹‹እንታደገው›› ሲል ለአኅጉሩ መሪዎች ጥሪ አቀረበ።

ትምህርት ላይ የሚሠራውና መንግሥታትን በጥናት በተደገፈ መረጃ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የሚሠራው ተቋሙ፣ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ከመጀመሩ አስቀድሞ ማክሰኞ የካቲት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ  ከአኅጉሩ የተወጣጡ የመንግሥታት ኃላፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ስብሰባ አካሂዷል።

የጥምረቱ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም የቀድሞ የዓለም ባንከ የአፍረካ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኦባይጌሊ አዜክዎስሊ፣ ከስብሰባው ጎን ለጎን ለሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ፣ በአፍሪካ ከአሥር ተማሪዎች ዘጠኙ በአሥር ዓመታቸው መጻፍ፣ ማንበብና መሠረታዊ የሒሳብ ሥሌቶችን አያውቁም ብለዋል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በአኅጉሩ ለትምህርት ዘርፉ የሚመደበውን ገንዘብ ባልተገባ የሕንፃ ግንባታና ለትምህርት ጥራት ፋይዳ በሌላቸው ጉዳዮች እንደሚያጠፉት፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ  ገልጸዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ሊካሄድ ቀናት በቀሩት 37ኛው የአፍረካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ለመሪዎች ባቀረቡት ጥሪ፣ መሪዎች ቅድሚያ ሊሰጠው በሚገባ የትምህርት ኢንቨስትመንት ላይ ተገቢውን ሀብት ያውሉ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአኅጉሩ የትምህርት ጥራት ከየትኛውም አኅጉር ጋር ሲወዳደር በጣም ዝቅተኛውን ደረጃ እንደሚይዝና ይህ ካልተስተካከለ አጀንዳ 2063 የተሰኘውን የአፍሪካ ኅብረት ትልም መሀል መንገድ ላይ እንደሚያስቀረው የገለጹት፣ ዴቨሎፕመንት ኦፍ ኤዱኬሽን በአፍሪካ የተሰኘ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አልበርት ኔሰንጅይሙቫ ናቸው።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም በአፍሪካ አኅጉር መፈንቅለ መንግሥት፣ ድርቅ፣ ጦርነት፣ የሰላም ዕጦት፣ የአየር ንብረት ለውጥና የመሳሰሉት ችግሮች  በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ከትምህርት ጥራት መውደቅ ጋር የተገናኙ መሆናቸውን አክለው ገልጸዋል።

የዩኒሴፍ የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ላይኬ ቫንዲዌል በበኩላቸው፣ ሕፃናት የተሻለ የትምህርት አቅርቦት ማግኘት እንዳለባቸው ገልጸው፣ ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ሀብት ለትምህርት በመመደብ እኩልና ጥራት ያለው የትምህርት አቅርቦት ማድረስ አለባቸው ብለዋል።

በመግለጫው በአፍሪካ አስፈሪ ለተባለው የትምህርት መውደቅ ከቀረቡት ምክንያቶች መካከል፣ አገሮች ለትምህርት ዘርፍ የሚሰጡት ትኩረት ማነስና ወጥ አለመሆን፣ የሚመደበውን ሀብት ተገቢው ቦታ ላይ አለማዋል፣ የተጠያቂነት አለመኖርና የፖሊሲ ማነቆዎች የሚሉት ይገኙበታል ተብሏል።

ዓለም ላይ ለትምህርት ዘርፍ ትኩረት የሰጡ አገሮች በዕድገት ጎዳና ላይ ቢሆኑም፣ በአፍሪካ ያለው የትምህርት ጥራት መውደቅ አሁን ለሚታየው ድህነት ዋነኛው ተጠቃሽ ምክንያት መሆኑ ታውቋል፡፡

መግለጫውን የሰጡት አካላት በትምህርት ላይ ትኩረቱን አድርጎ በሚካሄደው በመጭው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ፣ መሪዎች ችግሩን ዕውቅና እንዲሰጡትና ዕቅድ በማውጣት አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጠው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተጨማሪም የትምህርት ወጤት በየጊዜው እየተለካ ማስተካከያ እንዲደረግና ለዘርፉ ቅድሚያ ትኩረት እንዲደረግበት፣ ተገቢ የሆነውን ሀብት ለትምህርት ጥራት እንዲመደብና በመምህራን አቅም ግንባታና የመምህርና ተማሪዎች መጻሕፍት ላይ ትኩረት እንዲደረግ፣ የተጠያቂነት ሥርዓት እንዲዘረጋና ዘርፉን የሚቀይሩ መዋቅራዊ ለውጦች እንዲከናወኑ የሚሉና በርካታ ማሳሰቢያ በያዙት መልዕክቶች በአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ በትኩረት እንዲዳሰሱ ጥሪ ቀርቧል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...