Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢሰመኮ በአማራ ክልል ከሕግ ውጪ የሚፈጸሙ ግድያዎች አሳስበውኛል አለ

ኢሰመኮ በአማራ ክልል ከሕግ ውጪ የሚፈጸሙ ግድያዎች አሳስበውኛል አለ

ቀን:

  • ንፁኃን በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ገልጿል

በአማራ ክልል በፌዴራል መንግሥትና በክልሉ በሚገኙ ታጣቂዎች መካከል በቀጠለው ግጭት፣ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከሕግ ውጪ የሚፈጸሙ ግድያዎች (Extra-judicial killings) እንዳሳሰበው፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ትናንት ማክሰኞ የካቲት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና በታጣቂዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከሕግ ውጪ የሚፈጸሙ ጥቃቶችና ግድያዎች፣ አሁንም እጅግ አሳሳቢና ዕልባት ያላገኙ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡  

በሰሜን ጎጃም ዞን በመርአዊ ከተማ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና በፋኖ ኃይሎች መካከል ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ውጊያ መካሄዱን አስታውሶ፣ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ስለደረሰ ጉዳት ምርመራ እያከናወነ መሆኑን ኢሰመኮ አስታውቋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ኮሚሽኑ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ለጠየቀው መረጃ ምላሽ ስላልደረሰውና በፀጥታው ችግሩ ሳቢያም ልዩ ልዩ ተዛማጅ ምክንያቶች ሙሉ መረጃዎች በተሟላ ሁኔታ ማሰባሰብ ባለመቻሉ፣ የምርመራ ሥራው ተሟልቶ አለመጠናቀቁን ገልጿል፡፡

የተሟላ ምርመራ ውጤት እንደተጠበቀ ሆኖ እስካሁን ድረስ በተደረገ ክትትል ኮሚሽኑ ማንነታቸውን ለማረጋገጥ ከቻለው ቢያንስ 45 ሰላማዊ ሰዎችን የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች፣ ‹‹ለፋኖ ድጋፍ አድርጋችኋል›› በሚል ምክንያት ከሕግ ውጪ መግደላቸውን መረጋገጡን ጠቁሟል፡፡

ኮሚሽኑ ደረሱኝ ባላቸው ጥቆማዎችና ልዩ ልዩ የመረጃ ምንጮች ከተሰበሰቡ የሰላማዊ ሰዎች ስም ዝርዝር ውስጥ እስካሁን ድረስ ማንነታቸውን በመለየት ለማረጋገጥ የተቻለው 45 ሰላማዊ ሰዎችን ብቻ ቢሆንም፣ የጉዳቱ መጠን ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ምክንያታዊ ግምት ስለመኖሩ አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም ‹‹የፋኖ አባላት ናቸው›› በሚል ተጠርጥረው የተያዙና ለጊዜው ብዛታቸውን ለማረጋገጥ ያልተቻለ ሰዎች፣ በተመሳሳይ ሁኔታ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጪ መገደላቸውን አውቄያለሁ ብሏል፡፡

በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከተገደሉት መካከል ለቀን ሥራ ማለዳ ከቤታቸው ወጥተው ድንገት ተኩስ ሲከፈት በአንድ ቦታ ተጠልለው የነበሩ 18 ሰላማዊ ሰዎች እንደተገደሉ፣ ምስክሮች በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ለኢሰመኮ መግለጻቸውን አስታውቋል፡፡

ሚሊኒየም ተብሎ በሚጠራ ሠፈር አንድ የጠፋ አባልን ሲያፈላልጉ የነበሩ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ‹‹በፍለጋው አልተባበሩም›› ያሏቸውን ስምንት ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸውን፣ 12 ባጃጆች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መቃጠላቸውን ኮሚሽኑ አክሎ ገልጿል፡፡

በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሸበል በረንታ ወረዳ የዕድ ውኃ ከተማ ጥር 10 ቀን 2016 ዓ.ም. በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተኩስ ልውውጥ እንደነበር፣ ታጣቂዎች ከተማዋን ለቀው ከወጡ በኋላ ቤት ለቤት በተደረገ ፍተሻና መንገድ ላይ ቢያንስ 15 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል፡፡ ግድያው በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጪ የተከናወነ መሆኑን፣ በሌሎች ሁለት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን በመግለጫው አትቷል፡፡

በተመሳሳይ በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ ወይበይኝ ቀበሌ አብስራ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ጥር 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ለወታደራዊ ቅኝት በአካባቢው የተሰማሩ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ቤት ለቤት ባደረጉት አሰሳ፣ ስድስት ሰላማዊ ሰዎችን ከየቤታቸው አውጥተው ከሕግ ውጪ እንደገደሏቸው ከምስክሮች መስማቱን ኢሰመኮ ገልጿል፡፡

በየአካባቢው በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው ሥቃይ እጅግ እየጨመረ በመምጣቱ፣ ሁሉም ወገኖች ብቸኛው ዘላቂ መፍትሔ ሰላማዊ ውይይት መሆኑን ተቀብለው በቁርጠኝነት እንዲተገብሩ፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) አሳስበዋል፡፡ አክለውም፣ ‹‹የተሟላ ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥና የተበደሉም እንዲካሱ አሁንም በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን ፤ ›› ብለዋል፡፡

ከሕግ ውጪ የሚፈጸም ግድያ ሙሉ በሙሉ እንዲቆምና ተጠያቂነት ተረጋግጦ ሁሉም ወገኖች ሰላማዊ ውይይትን ለዘላቂ መፍትሔ በቁርጠኝነት እንዲቀበሉ ኮሚሽኑ በመግለጫው አሳስቧል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...