Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየሥነ ሕዝብና የጤና ዳሰሳ ጥናት በበጀት እጥረትና በፀጥታ ሥጋት ውስጥ እንደሚካሄድ ተነገረ

የሥነ ሕዝብና የጤና ዳሰሳ ጥናት በበጀት እጥረትና በፀጥታ ሥጋት ውስጥ እንደሚካሄድ ተነገረ

ቀን:

ለሰባት ዓመታት የተራዘመው የሥነ ሕዝብና የጤና ዳሰሳ ጥናት የፀጥታ ሥጋትና ከ1.7 ሚሊዮን ዶላር በላይ የበጀት እጥረት እያለበት ከመጋቢት ወር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚካሄድና በአንድ ዓመት ውስጥ ተሠርቶ እንዲጠናቀቅ መታቀዱን፣ ሥራውን ለማስፈጸም የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ አስታወቀ። 

ይህ የተገለጸው ከፕላንና ልማት፣ ከጤና፣ ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ ከአማራና ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥታት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ፣ ከኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ)፣ እንዲሁም ከሌሎችም የሚመለከታቸው ተቋማትና አጋር ድርጅቶች የተውጣጡ ተወካዮች የዳሰሳ ጥናቱን ሒደት ለመከታተልና በአግባቡ ለማስፈጸም የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ፣ ሰኞ የካቲት 4 ቀን 2016 ዓ.ም. የመጀመሪያ ስብሰባውን በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ሲያካሂድ ነው። 

በስብሰባው የስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር) የዳሰሳ ጥናቱ የሚያካትታቸውን ዘርፎች፣ የሚያስፈልገውን የበጀት መጠን፣ በዋናነት ትኩረት የሚያደርግባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የሚዳስሳቸውን አካባቢዎችንና ተሳታፊ የሚሆነውን የሕዝብ (የአባወራ) ናሙና መጠን፣ እንዲሁም አሉ የተባሉ የፀጥታ ሥጋቶችን የተመለከተ ጠቋሚ የወቅታዊ ሁኔታ ማሳያና ዕቅድ ማስገንዘቢያ ሰነድ ኮሚቴው እንዲወያይበት አቅርበዋል። 

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በዚህ ሰነድ መሠረት ጥናቱ ትኩረት የሚያደርግባቸው ዘርፎች በኢትዮጵያ የሥነ ሕዝብና የጤና ሁኔታ ምን እንደሚመስሉ ለማየት ይረዳል በሚል የተመረጡ የእናቶችና ሕፃናት ጤና፣ የሴቶች ሥነ ተዋልዶ ጤንነትና የቤተሰብ ዕቅድ፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ ተደራሽነት፣ የውልደት መጠን ዕድገት፣ የኤችአይቪ ሥርጭት መጠን፣ የቤት ውስጥ ጥቃት የደረሰበት ደረጃ፣ የሕፃናት ክትባት ሽፋን፣ የትምህርት ሽፋን፣ እንዲሁም በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ ሙሉ ምሥል ሊሰጥ የሚችል የመንግሥት ፖሊሲ ቀረፃና የሚሰጡ አቅጣጫዎች ላይ ዋናውን ሚና የሚወስዱ ዋና ዋና ጠቋሚ ዘርፎች እንደሚካተቱበት ተነግሯል። 

እንደ ሰነዱ መግለጫ የዳሰሳ ጥናቱ በአጠቃላይ 11.15 ሚሊዮን ዶላር ያህል የሚፈጅ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ አብላጫው ገንዘብ 6.7 ሚሊዮን ዶላር በአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) የሚሸፈን መሆኑም ታውቋል። 

ከበጀቱ 2.74 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋው የጤና ሚኒስትር በዓለም አቀፉ ተቋም ግሎባል ፈንድ የኤችአይቪ ሥርጭትን ለመግታትና ለሌሎችም መድኃኒቶች ግዥና ሥርጭት ተመድቦ ከማስፈጸሚያ ፕሮጀክቶች ጥቅም ላይ ያልዋለ ገንዘብ ተሰባስቦ፣ ዓለም አቀፉ ተቋም በጀቱን ለኢትዮጵያ ከሰጠበት ምክንያቶች ጋር ለተያያዘው የዳሰሳ ጥናት እንዲውል ከተቋሙ ጋር በመነጋገር በተፈቀደ ተዘዋዋሪ ገንዘብ የሚሸፈን መሆኑን የጤና ሚኒስትር ደኤታ ደረጄ ድጉማ (ዶ/ር) ለሪፖርተር አስረድተዋል። 

ሚኒስቴር ደኤታው አክለውም ለጥናቱ መሳካት አስፈላጊ ከሆነው የበጀት መጠን እስካሁን ማሰባሰብ ያልተቻለውን 1.71 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ፣ ከተለያዩ አጋር ዓለም አቀፍ ተቋማት ለማግኘት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። 

የስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ለብሔራዊ ኮሚቴው ያቀረቡት የወቅታዊ ሁኔታዎች ጠቋሚና የዕቅድ ማሳያ ሰነድ እንደሚያሳየው፣ የሥነ ሕዝብና ጤና የዳሰሳ ጥናቱ በአገሪቱ 12 ክልሎችና ሁለት የመስተዳደር ከተሞች ውስጥ በሚገኙ 805 ለጥናቱ የተለዩ አካባቢዎች፣ ከ22,540 አባወራዎች ናሙናዎችን በመውሰድ እንደሚካሄድ ተገልጿል። ከዚህም ውስጥ 14,672 አባወራዎች በገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ ናቸው ተብሏል። 

በጥናቱ የሚካተቱ አባወራዎች መጠን ኦሮሚያ በ2,212 እና አማራ በ2,100 ተቀዳሚዎቹ ክልሎች ሲሆኑ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ1,700 በላይ፣ ሲዳማና ሶማሌ ክልሎች እያንዳንዳቸው ከ1,600 በላይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ትግራይና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች እያንዳንዳቸው ከ1,500 በላይ፣ አፋርና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በተናጠል ከ1,400 በላይ አባወራዎች በጥናቱ እንደሚካተቱ ሲገለጽ፣ ጋምቤላ ክልል በ1,260፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በ1,156፣ እንዲሁም የሐረሪ ክልል በ1,126 ተሳታፊ የሚደረጉ አባወራዎች ብዛት የመጨረሻዎቹን ሦስት ደረጃዎች በተከታታይ ይዘው እንደሚገኙ በዋና ዳይሬክተሩ የቀረበው ሰነድ ያሳያል። 

በበከር (ዶ/ር) የቀረበው ሰነድ ለጥናቱ ከተለዩ 805 አካባቢዎች (enumerated areas) 87.5 በመቶው ማለትም 704 ያህሉ የደኅንነት ሁኔታቸው አስተማማኝ የሆኑና ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር የሌለባቸው በሚል ተገልጸዋል። 34 አካባቢዎች አጠራጣሪ የፀጥታ ሁኔታ ያላቸው ተብለው ሲጠቀሱ፣ ከአጠቃላይ በጥናቱ ከሚካተቱት አካባቢዎች 8.3 በመቶው ወይም 67 አካባቢዎች ደግሞ ከወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ አንፃር ጥናቱን ለማካሄድ የደኅንነት ሥጋት ያለባቸው፣ ስለሰላም ሁኔታቸው እርግጠኛ መሆን ያልተቻለባቸው ሥፍራዎች እንደሆኑ ተብራርቷል። 

ጥናቱን ለማካሄድ የሚያስችል የፀጥታ ሁኔታ ውስጥ ሊገኙ መቻላቸው ላይ እርግጠኛ መሆን አይቻልም የተባሉት 67 የተለዩ አካባቢዎች የሚገኙት በአማራ፣ በኦሮሚያና በጋምቤላ ክልሎች ውስጥ፣ እንዲሁም በአማራና በትግራይ ክልሎች በይገባኛል የሚወዛገቡባቸው አዋሳኝ አካባቢዎች እንደሆኑ በዝርዝር በሰነዱ ላይ ቀርቧል። 

የአማራና የትግራይ ክልሎች በሚወዛገቡባቸው የወሰን አካባቢዎች የሚደረግ የዳሰሳ ጥናት ውጤት መሬት ላይ ካሉ የይገባኛል ውዝግቦች አንፃርና ጥናቱ በተለይም አባወራዎችን መሠረት ያደረገ እንደ መሆኑ የተዓማኒነት ችግር ሊገጥመው አይችልም ወይ ተብሎ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ፣ የብሔራዊ ኮሚቴው አባል የጤና ሚኒስትር ደኤታው ደረጄ (ዶ/ር) ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።

ሚኒስትር ደኤታው አስቀድመው የፀጥታ ሁኔታ አሥጊ ስለሆኑባቸው ሁኔታዎች በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹ጥናቱ ሁሉንም ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች የሚያጠቃልል እንደ መሆኑ ናሙና ወስደን፣ ሁሉንም አካባቢዎች በተቻለ መጠን ማካተት መቻል ወሳኝና ቅድመ ሁኔታም የሰጠነው ተግባር ነው። ካሉበት የፀጥታ ሁኔታ ችግር አንፃር እርግጠኛ ሆነን የማናያቸው አንዳንድ ቦታዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ከአጠቃላይ 805 አካባቢዎች 8.3 በመቶ ወይም 67 ለፀጥታ ችግሮች የተጋለጡ ስለሆኑ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ የምንይዘው ጉዳይ ነው። ጥናቱን ማድረግ አንችልም ሳይሆን የጥናቱ ጥራት ችግር ውስጥ እንዳይገባ ከወዲሁ ልንወያይባቸው የሚገቡንን መለየት አለብን። የትኛው ቀበሌ ምን ዓይነት ሁኔታ አለ የሚለው በደንብ መታየት ያለበት ነገር ስለሆነ፣ ለዕቅድም ስለሚጠቅመን የለየነው ነው፤›› ብለዋል። 

ደረጄ (ዶ/ር) በሁለቱ ጎረቤት ክልሎች አወዛጋቢ የወሰን አካባቢዎች የሚገኙ አባወራዎችን መሠረት ያደረገው ጥናት ውጤት ተዓማኒነት በተመለከተም፣ ‹‹በትግራይና በአማራ ክልሎች ያሉ የወሰን አካባቢ ወረዳዎች አባወራዎችን ለሥነ ሕዝብና ለጤና ፖሊሲዎች ቀረፃ ግብዓት የሚሆኑ ጥናቶችን ነው የምናካሂደው። ከዚህ ውጭ በየትኛው ክልል ሥር ነው መረጃው የሚወጣው የሚለውን በኋላ አቅጣጫ ሲቀመጥ የሚወሰን ይሆናል። ለጊዜው ግን መረጃዎችን ማምጣት መቻል ላይ ነው ትኩረታችን። ምክንያቱም ጥናቱ የሚደረገው በእያንዳንዱ ቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞንና ክልል ያለው ነባራዊ የሥነ ሕዝብና ጤና ሁኔታ ምንድነው? ምን ዓይነት ለውጦችን ማድረግ አለብን? የሚለውን ምላሽ ለማወቅ ስለሆነ፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። 

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በብሔራዊ ኮሚቴው ውይይት ወቅት ስለእነዚህ የፀጥታ ሥጋቶች ስላለባቸው አካባቢዎች አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ ‹‹ሁኔታው እርስ በርሱ የሚጣረስ (paradox) የሆነ አሳዛኝ ነገር ነው። ጥናቱ ከየትኛዎችም አካባቢዎች በላይ የሚያስፈልጋቸው ለእነዚህ የፀጥታ ሥጋት ያለባቸው ሥፍራዎች ለሚገኙ ሰዎች ነው። ነገር ግን በፀጥታና በደኅንነት ችግሮች ምክንያት ይህ ጥናት መራዘም ደግሞ የለበትም፤›› ብለዋል። 

የብሔራዊ ኮሚቴው አባል የሆኑት የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ ሁንዱማ፣ ‹‹የዳሰሳ ጥናቱ ውጤት በጤና ፖሊሲ ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ትልቅ በመሆኑ የተሳታፊ አባወራዎች ናሙና መጠኑ በቂ ነው ወይ?›› የሚል ጥያቄ አንስተዋል።

ሌሎችም የኮሚቴው አባላት ተመሳሳይ ጥያቄዎችን አቅርበዋል። የስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የጥናቱ ባህሪ የምንወስደውን የአባወራዎች ብዛት ናሙና መጠን ይወስነዋል፡፡ በሥሩም ዘርዝረን ልናካትታቸው የምንችላቸውን ጉዳዮች (variables) መጠንም እንዲሁ። ከዚህ ቀደም ከተደረገው የዳሰሳ ጥናት ናሙና መጠን ግን የአሁኑ ብዛቱ ከፍ እንዲል አድርገናል፤›› ብለዋል። 

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ከሰባት ዓመታት በፊት በጤና ሚኒስትር በኩል ከተደረገው አነስተኛ የሥነ ሕዝብና የጤና ዳሰሳ ጥናት ከተወሰደው የናሙና መጠን ቢያንስ በስምንት ሺሕ ያህል ማደጉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የሥነ ሕዝብና የጤና የዳሰሳ ጥናት በየአምስት ዓመቱ መካሄድ የነበረበት እንደሆነ ሚኒስትሯ የገለጹ ሲሆን፣ በኮሮና ወረርሽኝና በተለያዩ የሰላም ችግሮች ምክንያት ወቅቱን ጠብቆ ማካሄድ ሳይቻል መቅረቱንም ገልጸዋል።

በዩኤስኤአይዲና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕፃናት መብት ኤጀንሲ ዩኒሴፍን የመሳሰሉ የሚመለከታቸው ኤጀንሲዎች ድጋፍ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት የበጀትና የተቋማት አስተዋፅኦ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሒደቶችና አሠራሮች (procedures and protocols) ጥናቱ መከናወኑን ክትትል አድራጊ አማካሪ ድርጅት የበላይ ተቆጣጣሪነት የዳሰሳ ጥናቱ የተካሄደው ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በ2008 ዓ.ም. እንደነበረ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የጤና ሚኒስቴር የዳሰሳ ጥናቱ ለፖሊሲ ቀረፃ ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የጥናቱ አለመደረግ ሊፈጥር የሚችለውን ክፍተት ለመሙላት በሚል በራሱ አቅም ከሰባት ዓመታት በፊት በ2011 ዓ.ም. አነስተኛ የሥነ ሕዝብና ጤና የዳሰሳ ጥናት አድርጎ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...