Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሦስት ማኅበራት የተደራጁ የላዳ ታክሲ ባለንብረቶች ከሰባት ዓመታት በኋላ 69 ዘመናዊ ታክሲዎች አገኙ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በአዲስ ይተካሉ የተባሉ ከአሥር ሺሕ የሚበልጡ ላዳ ታክሲዎች መኖራቸው ይታወቃል

በሦስት ማኅበራት የተደራጁ 69 የላዳ ታክሲ ባለንብረቶች ከሰባት ዓመታት ውጣ ውረድ በኋላ የዘመናዊ ታክሲ ባለንብረት መሆናቸውን አስታወቁ፡፡

የአገሬ ሜትር ታክሲ፣ የአዲስ ሜትር ታክሲና የገጽታ ሜትር ታክሲ ባለንብረቶች ማኅበር ሰብሳቢ አቶ ሔኖክ በለጠ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ማኅበራቸውን ካቋቋሙበት ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ የዘመናዊ ታክሲ ባለቤት ለመሆን በርካታ ቢሮክራሲዎችን አልፈዋል፡፡

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉ ሰማያዊ ላዳ ታክሲዎች በአዲስ መተካት አለባቸው ካለ ወዲህ፣ በርካታ ማኅበራት ይህንኑ ለማሳካት ላይ ታች ቢሉም ዛሬም እንዳልተሳካላቸውም ገልጸዋል፡፡

የቤት ካርታ አስይዘው፣ የገቢ ምንጭ የነበረውን ላዳ ሸጠው፣ ከዘመድ አዝማድ ተበድረው የዘመናዊ ታክሲ ባለቤት ለመሆን ለድርጅቶች ቅድመ ክፍያ በመክፈል ዓመታትን እየጠበቁ የሚገኙ ባለንብረቶች አሁንም እየተቸገሩ መሆኑን የገለጹት አቶ ሔኖክ፣ መንግሥት በብድርና በመኪና ገጣጣሚዎች በኩል ያሉ ችግሮችን እንዲፈታ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የቀድሞ የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ ከላዳ ታክሲ ባለንብረቶች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን፣ በኋላም በከንቲባ አዳነች አቤቤ ጥረት መደረጉን ያስታወሱት አቶ ሔኖክ፣ ትልቁ ችግራቸው የነበረው ብድር ማግኘት እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮና የተለያዩ አካላት ከሦስት ዓመታት በፊት አወያይተዋቸው ታክሲዎቹን በአገር ውስጥ ገጣጥመው የሚያቀርቡ ስምንት አማራጭ ድርጅቶችን እንዳቀረቡላቸው፣ በ2013 ዓ.ም. ታኅሳስ ደግሞ ከንግድ ባንክ የስድስት ቢሊዮን ብር ብድር መገኘቱ ተነግሯቸው ታክሲዎቹን ኤላአውት ኢንጂነሪንግ ቢዝነስ ግሩፕ ገጣጥሞ ለ10,500 ባለንብረቶች እንደሚያስረክብ ስምምነት መድረሱን ያስታወሱት አቶ ሔኖክ፣ ቃል የተገባው ባለመሳካቱ እሳቸው የሚያስተባብሯቸው ሦስት ታክሲ ማኅበራት ከኦክሎክ ጄኔራል ትሬዲንግ ጋር ስምምነት መፈጸማቸውን አክለዋል፡፡

ታክሲዎቹን እዚሁ ከሚገጣጥመው ድርጅት ጋር ከሁለት ዓመታት በፊት በገቡት ስምምነት መሠረት ለባለ ሰባት መቀመጫ ታክሲ፣ በነፍስ ወከፍ 215 ሺሕ ብር ቅድመ ክፍያ መክፈላቸውን፣ ታክሲውንም ከቀረጥ ነፃ 690 ሺሕ ብር ሊገዙ እንደነበር፣ በኋላ የዋጋ ግሽበት አለ ተብሎ 100 ሺሕ ብር በነፍስ ወከፍ መጨመራቸውንና የመኪናው ዋጋ 1,450,000 ብር ከቀረጥ ነፃ መድረሱን ተናግረዋል፡፡

ቀሪ ገንዘቡን ከፍሎ ታክሲዎቹን ለመረከብ ብድር ለማግኘት የግልና የመንግሥት ባንኮችን ከሁለት ዓመታት በላይ ቢጠይቁም አለመሳካቱን፣ ሆኖም በአሚጎስ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበር አባል ሆነው በመቆጠብ እያንዳንዳቸው 1,135,000 ብር ባገኙት ብድር 69 የማኅበሩ አባላት በኢትዮጵያ የተገጣጠሙትን ታክሲዎች መረከባቸውን አስረድተዋል፡፡

የታክሲዎቹ ርክክብ መደረጉን አስመልክቶ ማኅበራቱና አበዳሪው ማኅበር የካቲት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ ብድሩ ከ15 በመቶ ወለድ ጋር እንደሚከፈል ገልጸዋል፡፡

የአሚጎስ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበር የኮርፖሬት ሴልስ ዲፓርትመንት ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው በኃይሉ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ማኅበራቸው ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ለሦስቱ ማኅበራት ያበደረ ሲሆን፣ ክፍያውም ከስድስት ወራት እስከ አሥር ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአዲስ አበባ ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት የሰጡ ሰማያዊ በነጭ ታክሲዎች ወይም በተለምዶ የላዳ ታክሲዎችን በአንድ ዓመት ውስጥ በአዲስ ለመተካት ለተያዘው ፕሮጀክት ስድስት ቢሊዮን ብር ብድር ማመቻቸቱን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ በታኅሳስ 2013 ዓ.ም. አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ባንኩ የፈቀደው ብድር ያገለገሉ የላዳ  ታክሲዎችን በአዲስ ለመተካት የአዲስ አበባ የላዳ ታክሲ ባለንብረቶች ማኅበር ከኤላአውቶ ኢንጂነሪንግ ቢዝነስ ግሩፕ ጋር በጋራ በመሆን ለሚሠሩት ፕሮጀክት መሆኑን፣ ቢሮው በወቅቱ በሸራተን ሆቴል በነበረው የፕሮጀክቱ የፊርማ ሥነ ሥርዓት መግለጹ ይታወሳል፡፡

እስካሁን ባለው ሒደት በ2013 ከተገባው ስምምነት 200 ያህል ባለንብረቶች አዲስ ታክሲ የተረከቡ ሲሆን፣ ለ540 ባለንብረቶች በቅርቡ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አቶ ሔኖክ ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ የሚገኙ ሰማያዊ ላዳ ታክሲዎችን ሙሉ ለሙሉ በአንድ ዓመት ውስጥ በአዲስ እንደሚተኩ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ በታኅሳስ 2013 ዓ.ም. ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች