Tuesday, April 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሜትር ታክሲና የሃይገር ባስ ባለንብረቶች ላይ አስገዳጅ የንግድ ትርፍ ግብር ተጣለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሜትር ታክሲና የሃይገር ባስ ባለንብረቶች 30 በመቶ የንግድ ትርፍ ግብር የመክፈል ግዴታ እንዳለባቸው የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር ሰኞ የካቲት 4 ቀን 2016 ዓ.ም. በድረ ገጹ ላይ ባወጣው ማስታወቂያ መሠረት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ባለንብረቶች የሚከፍሉት ግብር እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የታክሲ ሥርዓት ውስጥ የገቡ የሜትር ታክሲዎችና የሃይገር ባስ ባለንብረቶች 30 በመቶ ዓመታዊ ግብር የመክፈል ግዴታ አለባቸው ተብሏል፡፡

የግብር ክፍያው አስገዳጅ የሆነበት ምክንያት ሰኔ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ከገንዘብ ሚኒስቴር በተጻፈ ደብዳቤ መሠረት፣ ከ2016 ዓ.ም. ጀምሮ በንግድና በታክስ ሕጉ መሠረት ተፈጻሚ መደረግ ያለበት ውሳኔ መሰጠቱን ተከትሎ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በውሳኔው መሠረትም የሜትር ታክሲዎችና የሃይገር ባሶች በትራንስፖርት ቁርጥ ግብር ሥርዓት መሠረት ዓመታዊ የገቢ መረጃ እየተወሰደ፣ እንደ ድርጅት በተሽከርካሪዎች ዓይነትና ምርት ዘመን ግብር በሚከፈልበት ገቢ ላይ 30 በመቶ የመክፈል ግዴታ አለባቸው ተብሏል፡፡

በመሆኑም የታክሲ ማኅበራት በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 17 መሠረት የሒሳብ መዝገብ መያዝ የሚጠበቅባቸው የደረጃ ‹‹ሀ›› ታክስ ከፋዮች በመሆናቸው፣ የሒሳብ መዝገብ ይዘው የሚጠበቅባቸውን ግብር አስታውቀው እንዲከፍሉ የገቢዎች ሚኒስቴር አሳስቧል፡፡

ባለንብረቶቹ የሚከፍሉት እንደ ማንኛውም የንግድ ድርጅት መሆኑን፣ የዓመት ገቢያቸው 7,200 ብር እና ከዚያ በታች ከሆኑ ታክስ የማይከፈሉ፣ ከ7,201 እስከ 19,800 ብር ገቢ ያላቸው አሥር በመቶ፣ ከ19,801 እስከ 38,400 ብር ገቢ ያላቸው 15 በመቶ፣ ከ38,401 እስከ 63 ሺሕ ብር ገቢ ያላቸው 20 በመቶ፣ ከ63 ሺሕ እስከ 93,600 ብር ገቢ ያላቸው 25 በመቶ፣ ከ93,601 እስከ 130,800 ብር ገቢ ያላቸው 30 በመቶ፣ እንዲሁም ከ130,800 ብር በላይ ከሆነ 35 በመቶ ግብር መክፈል እንደሚጠበቅባቸው ሪፖርተር ያገኘው የንግድ ገቢ ግብር ምጣኔ ያሳያል፡፡

ዓመታዊ ግብራቸውን በሒሳብ መዝገብ ካላቀረቡ፣ የ30 በመቶ የንግድ ትርፍ ግብር በግምት እንዲሰላ፣ መዝገብ ያልያዙ ግለሰቦች በገቢ ግብር ደንብ ቁጥር 410/2009 እና በመመሪያ ቁጥር 138/2010 መሠረት አስተዳደራዊ ቅጣት በመቅጣት ከእነ ወለዱ እንዲከፍሉ እንደሚደረጉ፣ የገቢዎች ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ከገንዘብ ሚኒስቴር ወደ ገቢዎች ሚኒስቴር የተላለፈው ውሳኔ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ስድስት ወራት ያስቆጠረ በመሆኑ፣ በዚህም የታዩ ክፍተቶችን ለማሟላትና የግብር መክፈያ ወቅት ሳይደርስ ቅድመ ማሳሰቢያ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ምንጩ አስረድተዋል፡፡

ውሳኔው በአንዳንድ ባለንብረቶች ላይ በ2015 ዓ.ም. የተጀመረ ቢሆንም፣ ሌሎች ባለንብረቶች ደግሞ በነበረው የቀድሞ አሠራር መስተናገዳቸውን በመግለጽ ዘንድሮ ግን ሙሉ በሙሉ በአዲሱ ውሳኔ እንደሚስተናገዱ ምንጩ ገልጿል፡፡  

የአክሲዮን ማኅበራት በንግድ ሕጉ መሠረት ለአባላት የሚከፋፈለው የትርፍ ድርሻ (dividend) ግብር የሚከፈልገበት ስለሆነ የሒሳብ መዝገብ ካልያዙ ዓመታዊ የተጣራ ትርፍ ላይ ወይም በቁርጥ ግብር የገቢ መጠን ተመሥርቶ የንግድ ትርፍ ግብር ከተከፈለ፣ ግብር ከሚከፈልበት ገቢ ላይ የተከፈለው ተቀንሶ በቀሪው መጠን ላይ ሕጉን ተከትለው ካፒታላቸውን እስካላሳደጉ ድረስ የትርፍ ድርሻ ግብር አሥር በመቶ እንዲከፍሉ እንዲደረግ የተወሰነ መሆኑን፣ ለቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ግብር ከፋይ ለሆኑ የሃይገር ባስና የሜትር ታክሲ ባለንብረቶች ጥሪ ተደርጓል፡፡

የሜትር ታክሲ ባለንብረቶች እስከ 2015 ዓ.ም. ድረስ ዓመታዊ የቁርጥ ግብር ስምንት ሺሕ ብር ሲከፍሉ እንደነበር ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች