Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልአገራዊው ዕደ ጥበብ ወዴት እያመራ ነው?

አገራዊው ዕደ ጥበብ ወዴት እያመራ ነው?

ቀን:

በየማነ ብርሃኑ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ‹‹ባህሎቻችንን ማወቅ፣ ስብራቶቻችንን መጠገን!›› በሚል መሪ ቃል 15ኛውን ከተማ አቀፍ የባህል ፌስቲቫል ከጥር 24 እስከ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲያከብር ቆይቷል፡፡ 

ከፌስቲቫሉ ኩነቶች አንዱ የሆነው የቶክሾው መድረክም ‹‹የዕደ ጥበብ ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ›› /ከቱሪዝም፣ ከአገር ገጽታ ግንባታና ከሥራ ዕድል ፈጠራ መሳክነት /በሚል ርዕስ በፌስቲቫሉ መዝጊያ ቀን  ተካሂዷል፡፡ 

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም መምህር የሆኑት ኤፍሬም አሰፋ (ዶ/ር) በመድረኩ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ሲያቀርቡ እንደተናገሩት፣ ዕደ ጥበብ የሰው ልጅ የእጅ ሥራ ውጤት ሲሆን ባህሉን፣ ወጉን፣ እሴቱንና በአጠቃላይ ማንነቱን የሚገልጽበት ነው፡፡ 

አልባሳት፣ መዋቢያዎች፣ ጌጣጌጦች፣ የሸክላ፣ የብረት፣ የእንጨት፣ የቆዳ ሥራዎች፣ የሙዚቃ መሣሪያዎችና ሌሎችም ከዕደ ጥበብ ውጤቶች የሚመደቡ መሆናቸውን የሚናገሩት ጥናት አቅራቢው፣ በአብዛኛው የዕደ ጥበብ ውጤቶች አገር በቀል ግብዓቶችን የሚጠቀሙና ከሚዳሰሱ ቅርሶች መካከል የሚመደቡ ናቸው፡፡ 

እስያና አውሮፓ በዘርፉ ተጠቃሚ ከሆኑ አኅጉሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ህንድ እ.ኤ.አ. በ2006 የዕደ ጥበብ ውጤቶችን በማምረትና በመሸጥ 1.9 ቢሊዮን የውጭ ምንዛሪ እንዳገኘች የሚገልጹት ጥናት አቅራቢው፣ ዘርፉ በበርካታ አገሮች የሥራ ዕድል በመፍጠር የሚገኝና በታዳጊ አገሮች እስከ አሥር በመቶ የሥራ ዕድል ለዜጎች በመፍጠር በድህነት ቅነሳው ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛልም ብለዋል፡፡ 

ዕደ ጥበብ ከቱሪዝም ጋር እጅግ የተቆራኘ ነው፡፡ ቱሪስቶች ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር ሲዘዋወሩ፣ በቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎች ለዕደ ጥበብ ውጤቶች ወጪ ያወጣሉ፡፡ በዚህም ምርቱን ለሚያመርቱ ባለሙያዎች ገቢ በማስገኘት የአገር ኢኮኖሚን ይደግፋል፡፡ 

እ.ኤ.አ. በ2009 በአክሱም፣ ላሊበላና አዲስ አበባ በሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎች በተጠና ጥናት ቱሪስቶች ከምግብና ከመጠጥ፣ ከመዝናኛና ለተለያዩ አገልግሎቶች ከሚያወጧቸው ወጪዎች 54 በመቶ የሚሆነውን ወጪ የሚያወጡት የዕደ ጥበባት ውጤቶችን በመግዛት ነው የሚሉት ጥናት አቅራቢው፣ ይህም የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች በሥራዎቻቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያበረታታ ነው፡፡ 

በአገሪቱ የዕደ ጥበብ ዘርፍ እየሰጠ የሚገኘው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አበርክቶ እንዳለ ሁሉ፣ በተለያየ ተግዳሮቶች ውስጥ እያለፈ ይገኛል፡፡ የኢንዱስትሪ መስፋፋት፣ ሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን)፣ የሥልጠናና የፕሮሞሽን ችግር፣ ማኅበረሰቡ ለዕደ ጥበብ ባለሙያዎች ያለው አመለካከት፣ አነስተኛ የገንዘብ አቅርቦት፣ ያልዘመነ የዕሴት ሰንሰለት፣ የባለቤትነት መብት አለመጠበቅና የመሳሰሉት በዘርፉ የሚታዩ ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው ብለዋል፡፡ 

በአገራችን የዕደ ጥበብ ዘርፉን ለማሳደግና ባለሙያዎችንም በገቢ ተጠቃሚ ለማድረግ የዕደ ጥበባት ማዕከላትን ማቋቋም፣ ማስፋፋትና ማጠናከር፣ ዘርፉን በዕውቀት መምራት፣ ለዕደ ጥበብ ውጤቶች ወጥ የሆነ ደረጃ እንዲወጣና እንዲተገበር ማድረግ፣ ዘመናዊ የገበያ ትስስር መፍጠርና ለባለሙያዎች ዕውቅና መስጠት እንደሚገባም ጥናት አቅራቢው ተናግረዋል፡፡ 

በአዲስ አበባ ከተማ የባህል እሴቶች ዕደ ጥበብ ሀብቶችና ቋንቋዎች ልማት ዳይሬክተር ወ/ሮ አዳነች ካሳ እንደተናገሩት፣ የዕደ ጥበብ ፈጠራ ምርቶች የአገራችንን ማኅበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ጥበባዊ እሴት የተሸከሙ ሀብቶች ናቸው፡፡ 

በአካባቢያዊ ዕውቀትና ጥሬ ሀብቶች የሚሠሩ፣ ዝቅተኛውን የማኅበረሰብ ክፍል በአብዛኛው ሴቶችን ያቀፈ ዘርፍ ከመሆኑም በላይ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የምርቱ ተጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡ 

እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፣ ዘርፉ ከሥራ ዕድል ፈጠራነቱ ባሻገር ከአስተሳሰብ እስከ ገበያ ትስስር በሚዘልቁ ችግሮች የሚያልፍ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራበት ይገባል፡፡ ወደ ዘመናዊ አተያይ፣ ወደ ዓለም አቀፋዊ ገበያ እንዲያድግ በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ሊካተትና የተግባር ዕውቀቱም ሊያድግ ይገባል ብለዋል፡፡ 

ተቋማቸው የዕደ ጥበብ ዘርፉን ለማዘመንና ለማሳደግ ከእንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ጋር በጥምረት እየሠራ እንደሚገኝና አምራች ባለሙያዎችንም ከገበያ ጋር ለማስተሳሰር ዓውደ ርዕይ በማዘጋጀት ላይ ይገኛል፡፡ ከጥሬ ዕቃ አቅርቦት፣ ከብድር አቅርቦት፣ ከፈጠራ ባለቤት መብት ጋር ያሉ ችግሮችንም ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ 

የመድረኩ ተሳታፊዎች እንደተናገሩት፣ በአገራችን የዕደ ጥበቡ ዘርፍ የሚገባውን ትኩረት አላገኘም፡፡ በልቶ ለማደር ካልሆነ በገቢ ደረጃ ቤተሰብ የሚያስተዳድሩበት እንዳልሆነ፣ ዕውቀት ያልታከለበትና በልምድ ብቻ እየተሠራ እንደሚገኝ፣ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች የማምረቻ ቦታ እንደሌላቸው፣ ወጣቱ ትውልድም ሙያው ለቤተሰቡ እንዳልጠቀመ በመረዳት ጥበቡን ለመቅሰም እንደማይሻ፣ ከውጭ የሚገቡ የባህል አልባሳትም ገበያውን እየተቆጣጠሩትና ባህላዊ ልብስ አምራች ዜጎችን ከገበያ እያስወጡ እንደሚገኙ በመጥቀስ፣ መንግሥት የዕደ ጥበብ ዘርፉ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የጎላ ሚና እንዲጫወት መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚጠበቅበት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ 

የዕደ ጥበብ ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ /ከቱሪዝም፣ ከአገር ግንባታና ከሥራ ዕድል ፈጠራ መስክነት/ በሚል ርዕስ በተዘጋጀው መድረክ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሸማግሌዎች፣ የሙያ ማኅበራት፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...