Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

 አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር መረጠ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስፈጻሚነት በተካሄደው የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የቦርድ ዳይሬክተሮች ምርጫ የተመረጡት 12ቱ አዲስ የቦርድ አባላት፣ የባንኩን የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር መረጡ፡፡ 

አዲሶቹ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የቦርድ አባላት ረቡዕ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄዱት ምርጫ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ሆነው እንዲያገለግሉ አቶ ሺሰማ ሸዋነካ ፈንቅርን መርጠዋል። በምክትል ሊቀመንበርነት እንዲያገለግሉ የተመረጡት ደግሞ ወንድሙ ተክሌ (ዶ/ር) መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ሺሰማ በአሁኑ ወቅት በናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ (ኖክ) ቺፍ ኦፕሬቲንግ ኦፊሰር በመሆን እያገለገሉ ናቸው፡፡ 

የትምህርት ዝግጅታቸውን በተመለከተ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ ቢኤ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን፣ ቻርተርድ ሰርቲፋይድ አካውንታትም ናቸው፡፡  

የአቶ ሺሰማን የሥራ ልምድ በተመለከተ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው በሥራው ዓለም ከ40 ዓመታት በላይ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ አገልግለዋል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚታወቁት ትልልቅ የነዳጅ ኩባንያዎች ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ላይ ሠርተዋል፡፡ 

ከእነዚህ መካከል በአጂፕ ኢትዮጵያ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ለ12 ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፣ የዚሁ ኩባንያ ፋይናንስ ማናጀር በመሆን ሲሠሩ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ 

በተመሳሳይ በሼል ኢትዮጵያ የፕላኒግ ማናጀር፣ የኖክ ኢትዮጵያ የፋይናንስ ማናጀር እንዲሁም ለሦስት ዓመታትም የውጭ ኦዲተር በመሆን ማገልገላቸው ተጠቅሷል፡፡ በሠሩባቸው ኩባንያዎች ውስጥ በዋናነት ከፋይናንስ ጋር በተያያዙ የኃላፊነት መደቦች ላይ ሲሠሩ እንደነበር የሚያመለክተው መረጃ፣ በአሁኑ ወቅት በኖክ ኢትዮጵያ እየሠሩበት ባለው የኃላፊነት ቦታ ላይ ከ13 ዓመታት በላይ ቆይተዋል፡፡ 

ከዚህ የሥራ ልምዳቸው ባሻገር ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በተገናኘ ሥራ ለስድስት ዓመታት የዳሸን ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ አባል በመሆን መሥራታቸው ይጠቀሳል፡፡ የቤተ ጉራጌ ባህል ማዕከል የቦርድ አባል በመሆን ሲያገለግሉ ነበር ተብሏል፡፡ 

በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ20 ዓመታት በላይ የቆየው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በምሥረታው ጊዜ ጀምሮ በአራት የቦርድ ሊቀመንበሮች የተመራ ሲሆን፣ አቶ ሺሰማ አምስተኛው ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ባንኩን ቦርድ ሊቀመንበርነት ከመሩት ውስጥ አቶ ደንበል ባልቻ (ዶ/ር)፣ አቶ ታፈሰ ቦጋለና አቶ ወልደተንሳይ ወልደ ጊዮርጊስ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ 

አዲሱ ምክትል የቦርድ ሊቀመንበር ወንድሙ (ዶ/ር)ም ዶክትሬት ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ ያገኙ ሲሆን፣ በሃይድሮሊክ ኢንጂነሪንግ የማስተርስ ዲግሪ፣ በዋተር ሪሶርስ ኢንጂነሪነግ የቢኤስሲ ዲግሪ ወስደዋል፡፡ በተለያዩ የክልልና የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ላይ የሠሩት ወንድሙ (ዶ/ር)፣ ከእነዚህም መካከል የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ የውኃ ሥራዎችና ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ መስኖ ልማት ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ፣ ሆነው መሥራታቸውን ይጠቅሳል፡፡ 

በፌዴራል ደረጃም በውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ውስጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃዎች ያገለገሉ ሲሆን፣ የዚሁ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሚኒስቴር ደኤታም ነበሩ፡፡ 

ከቦርድ ሊቀመንበሩና ከምክትል ሊቀመንበሩ ሌላ ባንኩን እንዲያገለግሉ ሹመታቸው የፀደቀላቸው አዲሶቹ የቦርድ አባላት መሐሪ መኮንን (ዶ/ር)፣ አቶ ፀጋዬ ደገፉ፣ አቶ አሰፋ ሽሬ፣ አቶ ሳላዲን ኢብራሒም፣ አቶ ሰይፉ አዋሽ፣ ወ/ሮ ገነት ወልዴ፣ አቶ በንቲ ሲራኒ፣ አቶ ዘውዴ ሲርባሮ አቶ ታፈሰ ይርጋና አቶ ማሙሸት አፈወርቅ መሆናቸውን መግለጹ ይታወሳል፡፡  

አዲስ የተመረጡት እነዚህ ቦርድ አባላት የምርጫ ዘመን ሦስት ዓመት ነው፡፡ ይህ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ አዲሱ ቦርድ ኃላፊነት የተረከቡበት ወቅት፣ ባንኩ የተለያዩ ተግዳሮቶች በገጠመው ሰዓት በመሆኑ ይህንን ተግዳሮት ለመቅረፍና ከፍተኛ ሥራ የሚጠብቀው እንደሚሆን እየተገለጸ ነው፡፡ አዲሱ ቦርድ ባንኩ አጋጥሞታል የተባሉ የአሠራር ግድፈቶችን ለማረምና የባንኩን ቀጣይ ጉዞ በተመለከተ የተለያዩ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ 

የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ወቅታዊ ሁኔታ በቅርብ እየተከታተሉ ያሉ ወገኖች እየገለጹ እንደሚገኙት፣ አዲሱ ቦርድ በባንኩ ውስጥ ተከሰተ የተባለውን ችግር ከመነሻው ጀምሮ በማጣራት አፋጣኝ ማስተካከያ ዕርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡ 

ብሔራዊ ባንክ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ አጋጥሞታል ያላቸውን ችግሮች መንስዔ ናቸው የተባሉ አስፈጻሚዎችንም በመለየት ዕርምጃ መውሰድ የአዲሱ ቦርድ ቀዳሚው ሥራ ይሆናልም እየተባለ ነው፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ እምነት አዲሱ ቦርድ ሊወስዳቸው ከሚችላቸው ዕርምጃዎች ሌለ ብሔራዊ ባንክም በተናጠል ሊወስዳቸው የሚችሉ ተጨማሪ ዕርምጃዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ 

ብሔራዊ ባንክ በንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ውስጥ የተባለውን ችግር ለወራት ሲመረምር ቆይቶ አጋጠሙ ለተባሉ ችግሮች ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን የባንኩን የቀድሞ የቦርድ አባላት በጋራና በተናጠል ተጠያቂ ናቸው በማለት ለስድስት ዓመታት በማንኛውም የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ እንዳይሠሩ ባለፈው ሳምንት እንዳገዳቸው መዘገባችን ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች