Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ይህንን ግፈኛ ዓለም ምን ብሎ ይፈርደው ይሆን?

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ይህንን ግፈኛ ዓለም ምን ብሎ ይፈርደው ይሆን?

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ጥር ወር መጨረሻ ሳምንት ላይ በቀሩት የወሩ ጥቂት ቀናት ውስጥ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ኢቲቪ፣ በየካቲት ወር እያለ የካቲት ወር ውስጥ ተደግሶ የሚቀርብልንን የዝግጅት/የፕሮግራም ሜኑ (የገበታ ዝርዝር) በሚያስተዋውቅበት የገዛ ራሱ የውስጥ ማስታወቂያው፣ የአፍሪካ ኅብረትን ጉባዔ ግንባር ቀደም ጉዳዩ አድርጎ ሲነግረን ሰማሁ፡፡ ‹‹የፊታችን የካቲት ወር ላይ የሚካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ በአኅጉሪቱ የሰላምና የፀጥታ፣ እንዲሁም ሌሎች ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የኅብረቱ መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ ጉባዔውን በተሳካ መንገድ ለማስተናገድ ዝግጅቷን እያጠናቀቀች ትገኛለች›› በማለት፣ ኢቲቪም ይህንን ስብሰባ ዓይንና ጆሯችን ሆኖ እየተከታተለ እንደሚነግረን/እንደሚያደርስልን ነገረን፡፡ እንዲህ ያለ የሕዝብ ዓይንና ጆሮነት በአጠቃላይ ስለመኖሩ ወይም እንዲህ ያለ የዕድገት ደረጃ ላይ ስለመድረሳችን፣ በራሱ በሚዲያው/በኢቲቪ የተለመደ ቋንቋ ወደፊት ‹‹…የምናየው ይሆናል››፡፡ ለማንኛውም በዛሬው ርዕሰ ጉዳይ ላይ እንድጽፍ ያነሳሳኝ/ኢቲቪ ነውና አመሠግናለሁ፡፡

እውነት ነው ፌብሩዋሪ (ጥር የመጨረሻ ሳምንት ጀምሮ የካቲት ውስጥ ዘልቆ የሚገባው የአውሮፓውያኑ ሁለተኛ ወር) የአፍሪካ ኅብረት የስብሰባ ወር ነው፡፡ በራሱ በአኅጉራዊው ተቋም አሠራርና ሕግ መሠረት ከጥር 6 ቀን እስከ 17 ድረስ የተካሄደው የኅብረቱ ቋሚ መልዕክተኞች ማለትም የአምባሳደሮች ኮሚቴ አስቀድሞ ‹‹የባረከው›› (ዝግጅት ያደረገበት) አርባ ሰባተኛው መደበኛ ስብሰባ፣ ከዚያ ቀጥሎ ለሚሰበሰበውና ለሚመክረው አርባ አራተኛው የሚኒስትሮች ስብሰባ መሰናዶና መዳረሻ ይሆናል፡፡ ይህም ከየካቲት 6 ጀምሮ የካቲት 7 ድረስ የሚካሄደው የሁለት ቀናት ስብሰባ ነው፡፡ የምንነጋገርበት ዋናው የአገርና የመንግሥት መሪዎች 37ኛው መደበኛ ጉባዔ የሚካሄደው የካቲት 9 እና 10 ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት አባልና መሥራች አገር ብቻ አይደለችም፡፡ መፀነሻውም፣ መቀመጫውም ጭምር ነች፡፡ አሥራ ሦስተኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ የሰጠው (የ2009) ውሳኔና ትዕዛዝ እንደመዘገበውና እንደሚያረጋግጠው ደግሞ ዛሬ አገራችንም ውስጥ ብዙ ቦታ ሲውለበለብ/ሲሰቀል የምናየው፣ የተጠቀሰው የኅብረቱ ጉባዔ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረትም፣ በዓለም የአዕምሯዊ ንብረት ድርጅት (WIPO) የተመዘገበው፣ እንዲሁም በ2010 ዓ.ም. የኅብረቱ መደበኛ ጉባዔ ላይ የተመረቀው የኅብረቱ ሰንደቅ ዓላማ ኢትዮጵያዊው አቶ ያደሳ ዘውገ ቦጃ ተወዳድሮ ያሸነፈበት፣ የአሥር ሺሕ የአሜሪካ ዶላርም የተሸለመበት ባንዲራ ነው፡፡

በነገራችን ላይ የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ የዚህ አኅጉራዊ ድርጅት ከፍተኛውና ከሁሉም የበላይ የሆነው የሥልጣን አካል ነው፡፡ ይህ ከፍተኛና የድርጅቱ ሉዓላዊ የሥልጣን አካል በ13ኛው ስብሰባው በሰጠው ውሳኔ መሠረት፣ የኅብረቱ ሰንደቅ ዓላማ ላይ አፍሪካ ከእነ መላ ደሴቶቿ የሚታዩበት ነው፡፡ ይህንን ከሚያመላክተው፣ ደሴቶቿንም ከሚያካትተው ሰንደቅ ዓላማ ጋር ከዚህ ቀደም የአፍሪካ የነፃነት ቀን (African Freedom Day፣ እንዲሁም African Liberation Day›› እየተባለ ይጠራ የነበረውን ዛሬ የአፍሪካ ቀን የሚባለውን ማክበራችን ባይቀርም፣ አኅጉሪቱ ዛሬም ከቀጥተኛ (ከእጅ እዙር አይደለም) አገዛዝ ሙሉ በሙሉ ነፃ አይደለችም፡፡ የዚህ ማስረጃ የቻጎስ አርኪፒላጎ፣ በዚህ ስም የሚጠሩት ደሴቶች ስብሰብ ጉዳይ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በየካቲት 2019 የዓለም ፍርድ ቤት (ICJ) እነዚህን ደሴቶች ታላቋ ብሪታንያ ለሞሪሽየስ እንድትመልስ ውሳኔ ቢሰጥም፣ የመንግሥታቱ ድርጅት ጉባዔም በ2019 ግንቦት ላይ ደሴቶቹ የሞሪሺየስ የግዛት አንድነት አካል ናቸው ብሎ ቢወስንም፣ የአፍሪካ ኅብረትም ይህንኑ አቤቱታ እያስተጋባ ብሪታንያ ቅኝ ግዛታዊ አስተዳድርሽን አቁሚ ብሎ ቢጠይቅም፣ ዲያጎ ጋርሽያ ላይ ከሚገኝ በሊዝ የተከራየ የአሜሪካ የጦር ሠፈርና ጥቅም ጋር በተሸራረበ ተንኮል ጭምር፣ አፍሪካ ዛሬም ድረስ ለዚያውም ከዓለም ፍርድ ቤት የፍርድ ባለመብትነት ጋር አሁንም ነፃ አልወጣችም፡፡ የቻጎስ ደሴቶች ግን አፍሪካ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ይውለበለባሉ፡፡    

በዚህም ብቻ ሳይወሰን ኢትዮጵያ በአዋጅ እንደደነገገችው፣ ‹‹በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ የኅብረቱ ሰንደቅ ዓላማና መዝሙር በአባል አገሮች እንዲውለበለብና እንዲዘመር፣ እንዲሁም የአፍሪካ ቀን እንዲከበር ያስተላለፈውን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ የሕግ ማዕቀፍ…›› ያስፈልጋል ብላ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ያፀደቀውን ይህንን ‹‹ስምምነት›› መሠረት አድርጋ፣ የአፍሪካ ኅብረት ሰንደቅ ዓላማ፣ መዝሙርና የአፍሪካ ቀን አዋጅ ቁጥር 1209/2012 የሚባል ሕግ አውጥታ፣ የኅብረቱ ሰንደቅ ዓላማ በየቀኑ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ በየክልል ቢሮዎች፣ በየሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ በሌሎች አስፈጻሚ አካላት ጽሕፈት ቤቶች፣ በየፍርድ ቤቶች፣ በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጨምሮ በየትምህርት ቤቶች፣ በየአገር መከላከያ ተቋማት፣ በአውሮፕላን ማረፊዎች፣ በፖሊስና በጠረፍ ጥበቃ ተቋማት፣ በኢትዮጵያ ሚሲዮኖች፣ በየአምባሳደር መኖሪያ ቤት ሕንፃዎች፣ ወዘተ እንዲሰቀልና እንዲውለበለብ ደነገገች፡፡ ከላይ በተዘረዘረው ውስጥ ባልተመለከቱት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ደግሞ የኅብረቱ ሰንደቅ ዓላማ በአፍሪካ ቀን (ሜይ 25) ጨምሮ በሕዝብ በዓላት ቀን እንዲሰቀልና እንዲውለበለብ በሕግ አዘዘች፡፡ ይህንን ሕግ ራሱን እናውቀዋለን ወይ? አክብረን እናስከብረዋለን ወይ? ይህ አንድ ራሱን የቻለ ችግራችን ሆኖ ኢትዮጵያ ይህንን የምታደርገው፣ እንዲህ ያለ ሕግ የምታወጣውና የምታስከብረው ግን የኅብረቱ መቀመጫ ወይም ሆስት አገር በመሆኗ አይደለም፡፡ አባል አገር በመሆኗ ነው፡፡ ይህንን የተጠቀሰው ሕግ (አዋጅ ቁጥር 1209/2012) መግቢያ በደንብ ያሳያል፣ ያረጋግጣልም፡፡ ‹‹አገራችን ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን አጋርነት ለማሳደግ፣ ለፓን አፍሪካኒዝምና ለአፍሪካ የውህደት አጀንዳ ተግባራዊነት ያላትን ቁርጠኝነት ለማስቀጠል፣ እንዲሁም የኅብረቱ ኮሚሽን አዘጋጅ አገርነት ሚናዋን ለመወጣት ከምታከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ፣ የአፍሪካ ኅብረት ሰንደቅ ዓላማን ማውለብለብ፣ የአፍሪካ ኅብረት መዝሙርን ማዘመርና የአፍሪካ ኅብረት ቀን ታስቦ እንዲውል ማድረግ፣ አገራችን ለኅብረቱ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ በመሆኑ›› ነው ይህንን ግዴታ በሕግ ያቋቋመችው፡፡  

በአፍሪካ ኅብረትም ሆነ የሌላ ተመሳሳይ ልዩ ጥበቃና ማዕረግ ያለው ተቋም መቀመጫ መሆንም ብዙ አገሮች የሚጓጉለትን የሚንሰፈሰፉለትን፣ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ፉክክር የሚያደርጉበትን፣ የሚመቀኙበትንና የፖለቲካ መሣሪያም የሚያደርጉትን ክብር፣ ዝና፣ ጥቅም የሚያጎናፅፍ ብቻ አይደለም፡፡ በመቀመጫ አገሪቱ ላይም፣ በዓለም አቀፍም፣ በአገር ቤት ሕግም የተደነገገ አደራ፣ ግዴታና ግዳጅ ያቋቁማል፡፡ የሕግ ማስከበር እክል ሲያጋጥም ዝምታ መፍትሔ አይደለም በሚል ርዕስ (በ2478 ከሁለት ሳምንት በፊት) ባቀረብኩ ሙግት ውስጥ የዚህን ከተራ ግዴታ በላይ የከበደ ግዳጅ የሕግ ማዕቀፍ ጠቋቁሜያለሁ፡፡ ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ጋር የተፈራረምነው የአስተናጋጅ አገር (ሆስት ካንትሪ አግሪመንት) ስምምነት የዚህ ማዕቀፍ አካል ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ይህንን የዘወትር አደራ፣ ግዴታና ግዳጅ መወጣታችንን የማረጋገጥ ሥራ ስንሠራ፣ ‹‹አማረች አዲስ አማረች/የአፍሪካ ኅብረት መሠረት ሆነች›› ብለን ስንዘምር፣ እንደ ኢቲቪም ‹‹… የኅብረቱ መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባም ጉባዔውን በተሳካ መንገድ ለማስተናገድ ዝግጅቷን እያጠናቀቀች ትገኛለች›› ብለን ስናወራ፣ ይህንን ሁሉ የሚገዛ በሕግ አምላክ የሚል፣ የሕግ ማዕቀፍ፣ ተቋም፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል ብቃትና ዝግጁነት መኖሩንም ጭምር መፈተሽና መመርመር የዓመት አንድ ጊዜ፣ የአንድ ሰሞን የ‹‹ቸብቸብ አርጉለት›› ወግ ሳይሆን የዘወትር ለሕግ የመገዛት ሥራ መሆኑን እስኪሰለች፣ እስኪዋሀደንና ንቃታችንና ግንዛቤያችንን እስኪሆን ድረስ መወቀጥ ያለበት ሥራ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ማክሰኞ ጥር 28 ቀን 2016 ዓ.ም. በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ለጥቄዎች መልስ በሰጡበት ውቅት፣ በተለይም ‹‹ዲፕሎማሲ››ን በተመለከተው ማብራሪያቸው ውስጥ በአጋጣሚ ይህንን የምንኖርበትን ዓለም ‹‹… ፌር/fair የሆነ ዳኝነት ያለበት ዓለም ግን አይደለም፡፡ ጉልበት ያለው፣ የተደራጀ፣ የተሰባሰበ የሚያሸንፍበት ዓለም እንጂ፣ በፍትሕ የሚታይበት ዓለም አይደለም አሁን ያለው፡፡›› ብለውታል፡፡ እውነት ነው፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት የቆመው፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን፣ የአሁኑን የአፍሪካ ኅብረት የመሠረትነው ይህንን የጉልበተኞች አድራጊ ፈጣሪነትን ለመከላከል ነው፡፡

ኢቲቪ ‹‹… የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ በአኅሪቱ ሰላምና ፀጥታ፣ እንዲሁም ሌሎች ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ላይ ይመክራል…›› ብሎ በደፈናው የገለጸው ጉባዔ አጀንዳ (እስከ ጥር 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ማለትም 27 ጃንዋሪ 2024 ድረስ የሚታወቀውን ይዞ በተዘጋጀው ረቂቅ አጀንዳ መሠረት) በአምስት ገጽ የተዘጋጀ በ16 ተራ ቁጥር የተዘረዘሩ ጉዳዮች ዝርዝር ዓይቻለሁ፡፡ ከእነዚህ ብዙዎቹ መካከል አንዱ በተራ ቁጥር 7 (VII) የተመዘገበው ‹‹COMMISSION REPORT ON THE SITUATION IN PALESTINE›› የሚለው ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ማለትም የዚህ አኅጉራዊ ተቋም ጽሕፈት ቤት ወይም ዋና መምርያ ስለፍልስጤም የሚያቀርበው ሪፖርት ጉባዔው ከሚሰማቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ‹‹… ፌይር የሆነ ዳኝነት ያለበት ዓለም ግን አይደለም…››፣ ወዘተ. ባሉት በዚህ ዓለም ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመንግሥታቱ ድርጅትም ሆነ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት/አሁን በአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ ብቻ ሳይሆን፣ ሥነ ጽሑፍና ታሪክ ውስጥ የፍልስጤም ጥያቄ ወይም ‹‹The Question of Palestine›› ተብሎ የሚታወቀው ጉዳይ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ፣ ከመንግሥታቱ ድርጅት መፈጠር ጋር የጀመረ የዓለም ግፎች፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች፣ ወዘተ ሁሉ ፊታውራሪ የሆነ፣ ታሪኩ በፀጥታው ምክር ቤት ድምፅ አሰጣጥ ታሪክና ቃለ ጉባዔ ውስጥ የተመዘገበ የእንግሊዝ፣ የአሜሪካ ቀንደኛ ግብረ አበርነት ያለበት ታላቅ በደል ነው፡፡

አፍሪካ ኅብረት ከፍ ሲል በጠቀስኩት አጀንዳው ሪፖርት የሚሰማበት (ሲጠብቅም ሲላላም) ጉዳዩ ያደረገው፣ ግን ከዚህ አጠቃላይ እውነትና ታሪክ በመነሳትና የመብትና የነፃነት ተቆርቋሪነት ስሜቱና ህዋሱ ጉዳዩን የሚቃጥልና የሚያንገበግብ አጀንዳ ስላደረገው አይደለም፡፡ ወይም የዓለም ፍርድ ቤት (ኢንተርናሽናል ኮርት ኦፍ ጀስቲስ) ጥር 17 ቀን 2016 ዓ.ም. (26/1/2024) ደቡብ አፍሪካ ያቀረበችውን ክስና የዕግድ/የጊዜያዊ ትዕዛዝ ጥያቄ ሰምቶ የሰጠው ውሳኔ ቀስቅሶት አይደለም፡፡ ከዚህ ጋር የተያያዘ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ውስጥ ቢያንስ ቢያንስ ወግና ባህል የነበረ ነገር (ቀጥተኛና የእጅ አዙቅ ቅኝ አገዛዝን ዘረኝነትን፣ አፓርታይድንና ሌሎችንም የጭቆናና የግፍ አገዛዝ ገጽታዎችን በፅኑ የመታገል፣ ከብሔራዊ አርነት ንቅናቄዎች ግንኙነትን ማጠናከር የመሳሰሉ) መኖር አለመኖርን ጨርሰን የምንሰማው/የሚለይልን ጉባዔው ተጠናቅቆ፣ ለዚያውም ምን ምን ላይ እንደተነጋገረ/እንዳልተነጋገረ እውነትም የሕዝብ ዓይንና ጆሮ ሆኖ የሚዘግብልን ሚዲያ ካለ ብቻ ነው፡፡  

የደቡብ አፍሪካ ክስና ፍርድ ቤቱም የሰጠው ውሳኔ (እስራኤል ክሱ ውድቅ ተደርጎ መዝገቡ ተዘግቶ ልሰናበት ብላ ያቀረበችው መልስና መቃወሚያ ራሱ ውድቅ መደረጉ፣ በዚህም ላይ የዕግድ ትዕዛዝ መሰጠቱ) አልሰማሁም፣ አላየሁም የሚባል ተራ ጉዳይ ባይሆንም፣ ደቡብ አፍሪካን የመሰለ ግዙፍ ቁም ነገረኛና ባለጉዳይ የስብሰባው ተሳታፊ በሆነበት በዚህ ጉባዔ ዝም ብሎ ተሰባስቦ፣ የወጉን አድርሶ፣ ማነው ባለተራ ተባብሎ መበተን ብቻ የሚጠበቅበት ተራና የዘወትር የሠርክ ዓይነት ጉባዔ ባይሆንም፣ ‹‹Commission Report on the Situation in Palestine›› የሚለው አጀንዳ ግን (ረቂቅ አጀንዳ ተራ ቁጥር 7) ይህንን ደቡብ አፍሪካን መኩሪያችንና መታፈሪያችን ያደረገው ዋና ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን በደቡብ አፍሪካ መሪነትና ባለቤትነት ‹‹ይታያል ጉዱ የቤተ ዘመዱ›› የሚባልበት መድረክ እንደሚሆን መጠርጠር ይቻላል፡፡  

እናም በዚህ 37ኛው ጉባዔ በዚህ አጀንዳ መሠረት የሚቀርበው ሪፖርት ይዘት ምን እንደሆነ ባይታወቅም (እኔ በበኩሌ ባላውቅም)፣ አፍሪካ ኅብረት የፍልስጤምን ጥያቄ በሚመለከት ረገድ ግን በቀጠሮ ያሳደረው፣ ምናልባትም ለጥቂት ጊዜም ቢሆን እየሸሸውና እያንከባለለው ያቆየው ኅብረቱ ውስጥ ስንጥቃት የፈጠረ የቤት ሥራ አለበት፡፡ ጉዳዩ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሐምሌ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. (July 2021) በሥልጣኔ ሥር የሚወድቅ ተግባር ነው ብለው እስራኤልን የኅብረቱ ታዛቢ አገር ያደረጉበት ዕርምጃ ነው፡፡ ዕርምጃው ተቃውሞ ያስነሳው ወዲያውኑ ነው፡፡ ከተቃዋሚዎች መካከል አንዷ (ብቸኛው ግን አይደለችም) ደቡብ አፍሪካ ናት፡፡ አዲስ አበባ የተካሄደው 35ኛው ጉባዔ (2022) ጉዳዩን ለ36ኛው ጉባዔ (ለ2023) በቀጠሮ ቢያሳድረውም፣ 2015 የካቲት የተካሄደው የዓምናው ጉባዔ የእስራኤሉን መልዕክተኛ አላስተናግድም ያለበት፣ ይህም የዓለም ዜና የሆነበትና አቧራ ያስነሳበት ጉዳይ ቢሆንም፣ አገራችን ውስጥ ግን ይህ ብዙ ሲነሳ/ወሬ ሲሆን አይሰማም፡፡ ይህ ነገር አሁን እየተባባሰ ጋዛ ውስጥ የሚካሄደውን ጦርነት፣ የዓለም ፍርድ ቤት ጊዜያዊ ትዕዛዝ የሰጡበትን የመሆን ምናልባቱ ጠንካራ ከሆነው የዘር ማጥፋት ወንጀል አደጋ ጋር ተደማምሮና ተጋግዞ የአፍሪካ ኅበረትን ቢያንስ ቢያንስ የአንደበት ወግ አቋም መጠየቁ አይቀርም፡፡ የዚህ አቅጣጫና ይዘት ምንም ሆነ ምን ግን፣ ደቡብ አፍሪካን የመሰለ አባልና አገር ኅብረቱን ለቅቄ እወጣለሁ ማለት ድረስ ያስፈራራችበት የእስራኤል ጉዳይ የሚዲያዎቻችን የሕዝብ ጆሮና ዓይን የመሆን፣ የነፃነታቸውንና የነባራዊነታቸውን የውኃ ልክ የሚያስገምት መሆኑን፣ የአገራችን ሚዲያዎች ሁሉ ሊያጤኑት ሌላው ቢቀር መኖሩን ሊረዱት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ጉዳዩ በተለይም የፍርድ ቤቱ ውሳኔንና ትዕዛዝ ይዘትና ቁም ነገር በዓለም ላይ አለን የሚሉ፣ ያለ እኛ ማን አለ ብለው ራሳቸውን የሾሙና ሰየሙ፣ ዓለምም አዎ! አሜን! ይሁን! ብሎ አርዓያ ብቻ ሳይሆን የሚያመልክባቸውን ሚዲያዎች ውሸታምነት፣ አስመሳይነት፣ ችሎታና ብቃት ብቻ ሳይሆን ሸፍጥና ሴራ ዕርቃኑን አውጥቶ ያጋለጠ ነው፡፡ ሚዲያዎቻችንና ጋዜጠኞቻችን ሙያቸውና ኃላፊነታቸው ይህንን የምለውን ጉዳይ ሰው ነግሯቸው፣ አቅጣጫ ተቀምጦላቸው፣ መመርያ ወርዶላቸው ሳይሆን ራሳቸው ብዙና ሁሉንም በመስማት ዜና የሚሰሙበትን ምንጭ በማብዛት፣ ሊደርሱበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በማንምና የትም መከበርንና መታመንን ለመቀዳጀት የሚሻ ሚዲያ እዚህ ግብ ላይ መድረስ፣ ወደ እዚህ ግብ የሚወስደውን መንገድ መያዝ የሚችለው ወደ የትኛውም ወገን ሳያጋድልና ማድበስበስ ውስጥ ሳይገደብ፣ እውነትን በመበርበርና እውነታን በመፈልቀቅ መንገድ ነው፡፡

በአንድ ወቅት ለአጭር ጊዜም ቢሆን ኢትዮጵያ ትተዳደርበት የነበረ ሕገ መንግሥት በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ክፍል በአንዱ ድንጋጌ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ‹‹… ለሰው ልጅ ሰላም፣ ደኅንነትና ዕድገት በቆሙ ዓለም አቀፍና አኅጉራዊ ድርጅቶች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያደርጋል›› ይል ነበር፡፡ ይኼውም የ1980 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት በሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ምዕራፍ ደግሞ መንግሥት ‹‹…ለብሔራዊ አርነት፣ ለፀረ ዘረኝነት፣ ለሰላምና ለዴሞክራሲ በሚያደርጉት ትግል ምክንያት ጥቃት ለሚደርስባቸው የውጭ አገር ሰዎች ጥገኝነት ይሰጣል›› ይልም ነበር፡፡ የአገር ሕገ መንግሥት ውስጥ ሳይቀር መደንገግ የቻሉ ጉዳዮች ሐሳብና እምነት ከሞላ ጎደል የሁሉም፣ አለዚያም የብዙዎቹ የገጠርም የከተማም የንቅናቄ/የትግል ቡድኖች እምነት ነበሩ፡፡ በሮዴዥያ ነፃነት ጉዳይ፣ ሠፋሪ ቅኝ ገዥዎችን የመታገል ነገር፣ ‹‹ዚምባብዌ ድል ታደርጋለች›› ማለት የኢትዮጵያ ፖሊስ ሠራዊት ዘፈን/ሙዚቃ እስኪሠራለት ድረስ የአገር መኩሪያ ነበር፡፡ ሰውየው ማንም ይሁን ማን ‹‹ማንዴላን ማን አሠለጠነው? መንግሥት!›› እስከማለት ድረስ የሚያኮራ ቅርሳችን ሲሆን ዓይተናል፡፡  

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ ጽዮናዊነት ዘረኝነትና አድልኦ ነው የሚል ተመድ እ.ኤ.አ. በ1975 ያሳለፈው ውሳኔ ነበር፣ ሪዞሉዩሽን 3379 የሚባል፡፡ በ1991 መጨረሻ ላይ ነው የዓለም ሕግ መሆኑ የቀረው፡፡ የዚህም ምክንያት በአጭሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከላይ በተጠቀሰው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ፣ ‹‹…ጉልበት ያለው የሚያሸንፍበት ዓለም እንጂ በፍትሕ የሚታይበት ዓለም አይደለም…›› ያሉት ነው፡፡ ይህ የተጠቀሰው ጽዮናዊነትን ዘረኝነት አፓርታይድ ያለው፣ እንደ አፓርታይድና ዘረኝነት እዋጋዋለሁ ብሎ ትግል የተከፈተበትና ሕግ የወጣበት ጉዳይ በወቅቱ አሸናፊ በሆነበት ጊዜ አቅሙንና ጉልበቱን፣ ጥንካሬውን ያገኘው በመጨረሻም ‹‹Determines that Zionism is a form of racism and racial discrimination›› ያለው ከራሱ ከአፍሪካ ንቅናቄ፣ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ትግልና ከድርጅቱ ውሳኔ ነው፡፡ የውሳኔው የ3379 መግቢያ አራተኛው ፓራግራፍ እንዲህ ይላል፡፡

Taking note also of resolution 77 (XII) adopted by the Assembly of Heads of State and Government of the Organization of African Unity at its twelfth ordinary session, held at Kampala from 28 July to 1 August 1975, which considred “that the racist regime in occupied Palestine and the racist regime in Zimbabwe and South Arica have a common imperialist origin, forming a whole and having the same racist stucture and being organically linked in their policy aimed at repression of the dignity and integrity of the human being”.

በዚህ በተጠቀሰው የተመድ ውሳኔ ውስጥ መሠረተ የተደረገው አፍሪካ ውሳኔ የአፍረካ አንድነት ድርጅት አሥራ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ ጁላይ/ኦገስት 1975 ባደረገው ስብሰባ ያሳለፋቸው ውሳኔዎችና አቋሞች ናቸው፡፡                   

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተቋቋመበት ቃል ኪዳን መግቢያ እና በአንቀጽ 2 የተደነገገው የድርጅቱ ዓላማ፣ ይህ ድርጅት የሚቆምለትን የሰው ልጅ ሰላም፣ ደኅንነትና ዕድገት የመርህ ዝርዝሮች ይናገራሉ፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ማቋቋሚያ ሰነድም ይህንኑ በዘላቂነት የማረጋገጥ ተከታይና ቀጣይ ጉዞ አካል ነው፡፡ እዚህ አፍሪካ አንድነት ድርጅትና አፍሪካ ኅብረት ተከታታይ ትግል ውስጥ አኅጉሩ አንድ ሆኖና ተባብሮ ያስመዘገባቸውን ድልና ፍሬ ይበልጥ ጎልቶ የምናየው፣ ቅኝ ገዥነትን ከማስወገድ ቀጥሎ ያለው በዓለም አቀፍ የሰው ልጆች መብቶች ሕግጋት ዝርዝር ውስጥ የተካተተው አድልኦን/መድልኦን ወይም ዲስክሪሚኔሽንን የሚከለክለው የኢትዮጵም የሕግ አካል የሆነው ስምምነት ነው፡፡ ዓለም አድልኦን የሚዋጋበት፣ ቢያንስ ቢያንስ ሕገወጥ የሚያደርግበት ይህ የዓለም አቀፍ የፀረ አድልኦ ስምምነቶች ዝርዝር አፓርታይድን፣ ስፖርት ውስጥ ያለ አፓርታይድንም ጭምር ያካትታል፡፡ ፓስፖርታችን ላይ ይመታ የነበረውን ‹‹ከደቡብ አፍሪካ በስተቀር›› የሚለውን ማኅተም ታሪክ/ወሬ፣ የይድነቃቸው ተሰማን የስፖርት መሪነትና ተጋድሎ የሚሰማ ሰው ኢትዮጵያ አነሰም በዛም እዚህ አጠቃላይ ለሰላም፣ ለደኅንነትና ለዕድገት የመቆም ተጋድሎ ውስጥ ያሳየችውን ጥረት አንድ፣ ሁለት ብሎ መቁጠር አይቸግረውም፡፡

እዚህ ሁሉ በተለይም የተመድ ውሳኔ ቁጥር 3379 የጠቀሰው/ለጥቅስ የበቃው ዓይነት ተጋድሎ፣ በአጠቃላይ አፍሪካ አንድነት ድርጅት ግዳጅና ድል ውስጥ ደግሞ፣ ከገዛ ራሷ የነፃነትና የኢትዮጵያ አድን ተጋድሎ ውስጥ የመነጨውን በአፍሪካውያን፣ በካሪቢያን በጥቁር ሕዝቦች መሃል፣ ከዚያም አልፎ በፀረ ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴ ኃይሎች ውስጥ የሰረፀውንና የተስፋፋውን፣ በአጠቃላይ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለሞችን የትግል ምልክትና የነፃነት ዓርማ ያደረገውን የኢትዮጵያን ሚናና አስተዋጽኦ እናያለን፡፡ ይህንን ከተገቢው ኩራት ጋር ስንናገር ያንኑ ያህል ደግሞ ኢትዮጵያና ነፃነቷ እነዚህ ሁሉ የለፉባት የእኛ ብቻ ያልሆነችው መሆኗን በክብር ከመግለጽ ጋር ነው፡፡

ኢቲቪ በየካቲት ወር የሚካሄደውን የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ የሚመከርባቸውን ጉዳዮች ገልጾ፣ የአኅጉራዊው ድርጅት መቀመጫም (አዲስ አበባ) ዝግጅቷን ማጠናቀቋን ገልጾ፣ የኢቲቪ የራሱም የየካቲት ወር ዋና ዝግጀት/ድግስ መሰናዶ ይኼው መሆኑን መነሻ ሆኖን ያነሳሁት ጉዳይ ሁለት ዋና ዋና ነገሮችን ልብ እንድትሉልኝ አደራ የሚል፣ የሚያመለክት ወይም አቤት የሚል ነው፡፡ አንደኛው ይህ አኅጉራዊ ተቋማችን ይህንን ‹‹fair የሆነ ዳኝነት ያለበት ዓለም ግን አይደለም››፣  ‹‹ጉልበት ያለው … የሚያሸንፍበት ዓለም እንጂ በፍትሕ የሚታይበት ዓለም አይደለም…›› ያልነውን፣ እውነቱን ለመናገር ደግሞ ጥቂት ጉልበተኞች አድራጊ ፈጣሪ ሆነው የሚፈነጩበት ዓለም ሁኔታ እንዴት አድርጎ ይመለከተዋል? ምን ብሎ ይገመግመዋል? እንዴት ያለ ‹‹ሪፖርት››ስ ያቀርብበታል? ይህ እስራኤልን፣ ፍልስጤምን፣ እዚህም ውስጥ የደቡብ አፍሪካን ክስና አቋሟን፣ የፍርድ ቤቱንም ውሳኔ የሚያመለከተው ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ጠቅላላ መጥፊያችን፣ የውድመታችን ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን ሁሉ – ጦርቶችንና የጦር መሣሪያዎችን፣ የአየር ንብረትን መለወጥን፣ የዴሞክራሲ መሸርሸርንና መቦርቦርን፣ ወዘተ የመሳሰሉትን ሁሉ ይጠቅሳል፡፡ እዚህ ውስጥ መሪዎቻችን እንዴት አድርገው ይወክሉናል? ምን ዓይነት ድምፅ ያሰሙናል? ብለን፣ ሥራችንም ጉዳያችንም አድርገን እንከታተለዋለን፡፡

ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ ዕውን መከታተል እንችላለን ወይ? የሚለውን ጥያቄ የሚመለከተው ነገር ነው፡፡ መቼም ሁላችንም፣ ሁላችንም ብቻ ሳይሆን የሚፈልግ ሁሉ ቦታው መገኘት አይችልም፡፡ የሚዲያ ሚና የሚመጣው እዚህ ላይ ነው፡፡ ዓይንና ጆሯችን ሆነው የሚወክሉንና የሆነውንም የሚነግሩን፣ ይህንንም የሚውቁበት ሚዲያና ጋዜጠኛ አለን ወይ? ነፃነቱ ኖረም አልኖረም ነፃነቱም፣ ሙያውም የሚያሸክመው ኃላፊነት ከነፃነቱ እኩል አያያዝና ዕውቀት ይጠይቃል፡፡ ኃላፊነትን የማክበር ጨዋነት የገዛ ራስን/የአሠሪ፣ ወገኔ/ጎጤ የሚሉትን ወገን የፖለቲካ አቋም ወይም አዝማሚያ በልጦ/ጥሶ ካልፀና በስተቀር፣ እንዲህም የሚያደርግ የተቋምና የባህል ግንባታ ካላደረግን በቀር ዓይንና ጆሮ የሌለውን ያህል መሆናችን የታወቀ ነው፡፡

እናም ጉባዔው አገሮቻችንን፣ መንግሥቶቻችንን፣ ባለሥልጣኖቻችን፣ ግፍንና ፀረ ዴሞክራሲን፣ ዘረኝነትንና ልዩ ልዩ መልኮቻቸውን በደፈናው፣ በጅምላ፣ ዝም ብሎ በውልና በጥቅል ስያሜያቸው ሳይሆን፣ በልዩ መታወቂያ ስማቸው ጠርተው ሲያወግዙት ሲታገሉት ለዚህም ሲሠሩ ማየት እንፈልጋለን፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ እንደ ዘረኝነት፣ አፓርታይድ ያለ፣ በደልን ግፍን ጥቅሜ ብሎ የያዘ ፖለቲካን ማውገዝና መታገል አለባቸው፡፡ ለሰብዓዊ መብት ለሰው ልጅ መብት የመቆምና የመቆርቆ ጉዳይ፣ ኢትዮጵያ በናሚቢያ ጉዳይ ደቡብ አፍሪካን (በእነ አቶ ሐዲስ ዓለማየሁና በዶ/ር ተስፋዬ ገብረ እዝጊ ፊርማ) በ1960ዎች፣ አሁን በ2023 ደግሞ ደቡብ አፍሪካ እስራኤልን የከሰሰችበት ሳይጠየቁ መቅረት የለም ብለው ግፍና በደል እንዲቆም፣ ፍትሕ እንዲሰፍን፣ ሰላም የጠየቁበት ‹‹አንተ ምን ቤት ነህ›› ማለትን የመሰለ ጥያቄ የሌለበት የሁሉም የሰው ልጅ ያገባኛል ብሎ ባለጉዳይ፣ ባለቤት የሚሆኑበት ጉዳይ መሆኑን ግንዛቤያቸውና ንቃታቸው ሲያደርጉ ማየት እንፈልጋለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...