Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በየወሩ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በማውጣት የሲሊንደር ጋዝ ለማስገባት ስምምነት ተደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በድሬዳዋ ከተማ ግዙፍ ዴፖ ይገነባል ተብሏል

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢዎች ድርጅት በየወሩ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ፣ እስከ ሁለት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሲሊንደር ጋዝ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ስምምነት ላይ መድረሱን አስታወቀ፡፡

ድርጅቱ ይህንን ያስታወቀው በኢትዮጵያ የሲሊንደር ጋዝ ለማስገባት ናይል ፔትሮሊየም ከተሰኘ ኩባንያ ጋር ሐሙስ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም. የመግባቢያ ስምምነት በተፈራረመበት ወቅት ነው፡፡

የነዳጅ አቅራቢዎች ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ እስመለዓለም ምሕረቱ እንደገለጹት፣ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ይገባ የነበረው የሲሊንደር ጋዝም ሆነ ነዳጅ በሱዳን በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ለሁለት ዓመታት ተቋርጦ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ናይል ፔትሮሊየም ከተሰኘው ኩባንያ ጋር በጋራ በመሥራት፣ የሲሊንደር ጋዝን ከሱዳን አገር ለማስገባት ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የደን ጭፍጨፋን ከመቀነስ አንፃር ያለውን አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ድርጅቱ በተሻለ ሁኔታ ሲሊንደር ጋዝ ለማስገባት ጥረት እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በፊት የናይል ፔትሮሊየም ድርጅት በገጠመው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የሲሊንደር ጋዝ ማቅረብ አቁሞ እንደነበር ያስታወሱት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በአሁኑ ወቅት ከኩባንያው ጋር በመቀናጀት ምርቱን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ስምምነት ላይ መደረሱን አስረድተዋል፡፡

ስምምነቱ ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል የሚለው አለመታወቁን ገልጸው፣ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የራሱን ፋሲሊቲ ማሟላት ሲችል አገር ውስጥ ማምረት ይጀምራል ብለዋል፡፡

የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ውስጥ መግባቱን የጠቆሙት አቶ እስመለዓለም፣ ድርጅቱም ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ውስጥ በመካተቱ ትርፍ የማስገኘት ኃላፊነት ስለሚኖርበት የራሱን አቅም ለማሳደግ ጥረት ያደርጋል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በድሬዳዋ ከተማ በ150 ሚሊዮን ዶላር ግዙፍ ዴፖ ለመገንባት በሒደት ላይ መሆናቸውን ገልጸው፣ ዴፖው ተገንብቶ ሲጠናቀቅ 300 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ እንደሚይዝ አክለው ገልጸዋል፡፡

በድሬዳዋ ከተማ የሚገነባው ዴፖ በ16 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ እንደሚያርፍ፣ ዴፖውን ለመገንባት ሁለት ዓመት ያህል ጊዜ እንደሚፈጅ ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ ድርጅቱ በዱከም ሊገነባ ያሰበውን ዴፖ ግንባታው ባለመጀመሩ ምክንያት፣ የከተማ አስተዳደሩ ቦታውን እንደወሰደባቸውና ክርክር ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የናይል ፔትሮሊየም ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መሐመድ ታይፎ እንደተናገሩት፣ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት የታቀደው የሲሊንደር ጋዝን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

በዚህ መሠረት በመጪው ወር ምርቱን ለማስገባት ዕቅድ መያዙን ገልጸው፣ ኩባንያው በኢትዮጵያ 32 ማደያዎች እንዳሉት ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት ምርቶችን ለማምጣት አማራጭ የምታደርገው ጂቡቲን ብቻ በመሆኑ፣ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ኩባንያው ከኢትዮጵያ ጋር ሰፊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው አብራርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች